መልካም የገና በዓል!

 የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ ከሚያከብሯቸው በዓላት አንዱ ገና ነው:: የገና በዓል በየዓመቱ ታህሳስ 29 እንደ ዘንድሮ ደግሞ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ታህሳስ 28 ይከበራል:: የገና በዓል መለያየት የጠፋበት፣ መከፋፈል የተወገደበት፣ የአንድነት እና የሰላም በዓል ነው።

የገና በዓል የአብሮነት በዓል ነው:: በልደት በዓል ሰውና አምላክ፣ እንስሳትና ሰው፣ እረኛና ንጉሥ፣ ሴቶችና ወንዶች፣ ሕጻንና አረጋዊ፣ በአንድ በረት ተገናኝተዋል። እነዚህ ሁሉ በበረት ውስጥ ሲገናኙ አብሮነትን ፈልገው ነው:: ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ሽተው ነው:: ለዛሬዋም ኢትዮጵያ የሚያስፈልገው ይኸው አብሮነት ነው::

የጾታ፣ የቀለም፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአስተሳሰብ፣ የአመለካከት፣ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ ናቸው:: ሆኖም እነዚህ ልዩነቶች የቅራኔና አለመግባባት ምንጮች ሊሆኑ አይገባም:: ኢትዮጵውያን በልዩነቶች ውስጥ በአንድነት ደምቀው የሚታዩባትና ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ጎልቶ የሚታይባት ሀገር ናት::

እነዚህን ልዩነቶች እንደጌጥ በመቁጠር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ መውሰድ ይገባል:: በገና ዕለት በበረቱ ውስጥ የተወለደውን ህጻን በመመልከት ዘርና ቋንቋ እንዲሁም ጾታ ሳይለያቸው የተለያዩ ሰዎች በአንድነት እንደተሰባሰቡ ሁሉ ዛሬም ኢትዮጵያውያን አንድታቸውን ማጽናት ይጠበቅባቸዋል::

የገና በዓል አንዱ መሠረት ሰላም ነው:: በጌታ ኢየሱስ ልደት ለዓለም ሁሉ የሚሆን ዘላለማዊ ሰላም ተገኝቷል። ይህም “ክብር እግዚአብሔር በሰማያት ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጐ ፈቃድ” እያሉ ቅዱሳን መላእክት በመዘመራቸው ተረጋግጧል። ሉቃ 2፥14። ስለዚህ በክርስቶስ ያገኘነው እውነተኛ ሰላም በእኛ ጸንቶ እንዲኖር ዘወትር በጾምና በጸሎት እየተጋን ስለሰላም የምንማፀን ሆነን ልንገኝ ይገባል። ሰላም የክርስትና መታወቂያ ዓርማ ነውና።

ስለዚህም እኛ ኢትዮጵያውያን ገናን ስናከብር ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሰላማችንን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል:: በሰላም እጦት የታመመችው ሀገራችን ወደ ቀድሞ ሰላሟ እንድትመለስና ሁሉም ያለስጋት ወጥቶ የሚገባባት ፤ ነግዶ የሚያተርፍባት እና ሮጦ የሚያሸንፍባት የሰላም ሀገር እንድትሆን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ልናበረክት ይገባል:: ይህ ሲሆን የገና በዓል ኃይማኖታዊ እሴቱን የተላበሰ ይሆናል፡፤

የገና በዓል የተስፋና የብርሃን በዓል ነው:: ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ የነበረው አዳም ወደሚደነቀው ብርሃን የተሸጋገረው በክርስቶስ ልደት ነው። እናም በልደቱ የተገኘነውን የጽድቅ ብርሃን ጠብቀን ለመኖር አንዳችን ለአንዳችን ተስፋና ብርሃን መሆን አለብን:: ወንድም ወንድሙን ከመግደልና ከማሳደድ ወጥቶ አለኝታው ሊሆን ይገባል:: እኛ ኢትዮጵያውያን የትኛውንም ሃይማኖት እንከተል፤ የየትኛውም ብሔር አባል እንሁን ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችን የሚያይል፤ ከችግራችን ይልቅ ጥንካሬያችን የሚልቅ፤ ከመከራችን ይልቅ ተስፋችን የሚበዛ እና እጣ ፋንታችን የተሳሰረ በመሆኑ አንዳችን ለሌላችን መከታ ፤አንዳችን ለሌላችን ተስፋ ልንሆን ይገባል:: ይህ ሲሆን የገና በዓልን ሙሉ በረከት የሚገኝ ይሆናል::

በክርስትና አማኞች የገና በዓል የይቅርታ በዓል ነው:: በአዳም በደል ምክንያት ከአብራኩ የተከፈሉ በሙሉ በደለኛ ሆነው የነበሩበትን ዘመን ለውጦ አዳምንና የልጅ ልጆቹን በደል ደምስሶ ፍቅርን ይመሰርት ዘንድ ጌታ ተወለደ። በምድርና በሰማይ ላሉት ፍቅርን መሠረተ። እርሱ የሰው ልጆችን በደል ሳይቆጥር ሁሉን ይቅር እንዳለ ክርስቲያንም የበደሉትን ሁሉ ይቅር ይል ዘንድ የፈጣሪው ትዕዛዝ ነውና ዘወትር ሊፈጸም የሚገባው ትዕዛዝ ነው:: የዛሬዋም ኢትዮጵያ ይህ መለኮታዊ ትእዛዝ ያስፈልጋታል::

ዛሬ ኢትዮጵያውያን በረባው ባልረባው የምንጋጭ፤ ጦር የምንማዘዝ እና ቂም ቁርሾ የምንቋጥር ሆነናል:: በዚህም በርካቶች ከቀያቸውና ከቤታቸው እንዲሰሰዱ፤ እንዲፈናቀሉና አልፎ ተርፎም አካላቸውን ህይወታቸውን እንዲያጡ ሆነዋል::ይህ ድርጊት እንዲያበቃ የገና በዓልን ምሳሌ በማድረግ ኢትዮጵያውያን ልባቸውን ለይቅርታ ሊያዘጋጁ ይገባል::

የገና በዓልን ስናከብርም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው የሚያሳልፉትን ሰዎች በማሰብ ሊሆን ይገባል:: የእነዚህ ሰዎች ስቃይ እንዲበቃና ዳግም በኢትዮጵያ ግጭት፤ ጦርነት፤ ስደትና መፈናቀል እንዲቆም ኢትዮጵያውያን ልባቸውንን ለይቅርታ ክፍት ሊያደርጉ ይገባል::

ዛሬ ላይ የገና በዓልን ስናከብር በልደቱ ያገኘነውን ሰላም፣ ነጻነት፣ ይቅርታ፣ ብርሃንና ፍቅር ዋጋ የተከፈለበት ጸጋ የወረስንበት መሆኑን በማመንና በዕለት ተዕለት ሕይወታችንም ለመተግበር በመጣጣር ሊሆን ይገባል:: መልካም የገና በአል!

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You