የዓውደ ዓመት ገበያው በዓሉን እንዳያደበዝዝ

ኢትዮጵያውያንና ነባር ባሕላዊ እሴቶቻቸውን ነጣጥሎ ማየት አይሞከርም። ለዘመናት አብሯቸው የኖረው ማንነት ከሃይማኖት፣ ባሕልና ዕምነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ይህ እውነታ እነዚህን ሕዝቦች ከነደማቅ ቀለሞቻቸው ሳይፈዙ፣ ሳይበረዙ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል።

ከኢትዮጵያውያን የማንነት መገለጫዎች አንዱ ከሃይማኖትና ባሕል ጋር ተያይዞ የሚያከብሯቸው ዓውደ ዓመቶች ዋንኞቹ ናቸው። እነዚህ ጊዜና ወቅትን ጠብቀው በድምቀት የሚከበሩ በዓላት ከጥንት እስከ ዛሬ በየትውልዱ ዓውድ ሲሸጋገሩ ዘመናትን ቆጥረዋል።

ዓውደ ዓመት ማለት ለኢትዮጵያውያን ትርጉሙ ብዙ ነው። ጊዜያትን ጠብቀው ቢፈራረቁም ቀኑ ላይ በዋሉ አጋጣሚ ሁሉ እንደ አዲስ ሆነው ይከበራሉ። ዓውደ ዓመት ለአክባሪው ሁሌም ድንቅና ብርቅ ነው። ዕለቱን ተከትሎ የሚኖረው ማኅበራዊነት አብሮ የመኖር ስንቅ ሆኖ ይዘልቃል ።

ይህ ቀን ለአብዛኞች ውስጠት ደስታን ያጎናጽፋል። ይህ ጠንካራ የማንነት ገመድ በእያንዳንዱ ጎጆና ቤተሰብ አይቀሬ ውዴታ ነው። ከዚህ አለፍ ሲል ጎረቤትና ዘመድ አዝማድን በአንድ የማዋል፣ አብሮነትን በስፋት የማጠናከር ኃይል አለው።

ማንም እንደሚያውቀው ለዓውደ ዓመት የሚሰጠው ግምት ከፍ ያለ ነው። በዚህ ቀን ሁሉም እንደቤቱ ዕለቱን በድምቀት ያከብራል። የእጁን ከፍሎ የአቅሙን አጋርቶ ከሌሎች መስሎ ተመሳስሎ ይውላል። ይህ ይሆን ዘንድ ከጥንት እስከዛሬ ያልተሸረሸው ተለምዷዊ እሴት ውዴታዊ ግዴታን እንደጣለ ቀጥሏል።

ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የነዋሪውን አቅም እየፈተነው ይገኛል። ዛሬ ገንዘብ ይሉትን ይዞ ገበያ የወጣ ሸማች የልቡን ሳያደርስ፣ ያሰበውን ሳያሳካ ከቤቱ መመለሱ ብርቅ አልሆነም። በአሁኑ ጊዜ በእያንዳንዱ ሸቀጥ ላይ በየአፍታው የሚጨመረው ዋጋ የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም ከፈተና በላይ አድርጎታል።

ዛሬን እየናረ ላለው የኑሮ ውድነት በእሳት ላይ ጋዝ የሚጨምሩ፣ ከብዙኃኑ ጥቅም ለግል ዓላማቸው የሚሮጡ ራስ ወዳዶች ተበራክተዋል። ‹‹እንኳን ዘንቦልሽ›› እንዲሉ ሆኖም ምክንያትና አጋጣሚን የሚሹ አንዳንድ ነጋዴዎች የዓውደ ዓመትን የመሰሉ ሰበቦች ሁሌም ሠርግና ምላሻቸው ነው።

በእነዚህ ስግብግቦች ላይ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር ካልተደረገ ችግሮች መፍትሔ የላቸውም። ተደጋግሞ እንደሚስተዋለው አጋጣሚን የሚሹ አንዳንድ ነጋዴዎቹ እንደ ሁልግዜው ልምዳቸው መጋዘኖቻቸውን በሸቀጦች ሞልተው የራሳቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ። ቀድመው በአነስተኛ ዋጋ ያስገቧቸውን ዕቃዎችም ዓውደዓመቱ ሲቃረብ ከእጥፍ በላይ አትርፎ ለመሸጥ አይደራደሩም።

ይህ አይነቱ ተለምዷዊ አሠራር እስከዛሬ ብዙኃኑን ላልተገባ ወጪ ዳርጎ፣ የጥቂቶችን ኪስ ሲያዳጉስ ቆይቷል። ዛሬም ቢሆን ሽቅብ በናረው የኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ ችግር የሚያክሉ ራስ ወዳዶች ጥቂት አይደሉም። አሁንም መጋዘን የሚያሰፉ፣ ዛሬም ለትርፍ የሚሮጡ በርካቶች ናቸው።

ይህን ችግር ተከትሎ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ከመንግሥት በተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎች በከተማዋ በተመረጡ አካባቢዎች የዕሁድ ገበያዎች ተደራጅተዋል። እነዚህ የገበያ ስፍራዎች ለሸማቹ የሚያስፈልጉ የምግብ ሸቀጦችን ከመደበኛው የገበያ ዋጋ በተሻለ እንዲያቀርቡ ሲባል የተዘጋጁ ናቸው።

ከእነዚህ አቅራቢዎች አብዛኞቹ ሥራ በጀመሩ ሰሞን የተቋቋሙበትን ዓላማ በአግባቡ ሲተገብሩ ቆይተዋል። ይህን በማድረጋቸውም በተመጣጣኝ ዋጋ ፍላጎቱን ለሚሞላው ተጠቃሚ መድሕን መሆናቸው ይታወሳል። ዋል አደር ሲል ግን ጥቂት የማይባሉት ታማኝነታቸው ተሸርሽሮ፣ ለትርፍ ብቻ ሲሯሯጡ ተስተውለዋል ።

አንዳንዴ በነዚህ የገበያ ስፍራዎች ከሌሎች ነጋዴዎች ባልተሻለ መልኩ ግብይት ይካሄዳል። አንዳንዶች የተቀበሉትን አደራ ዘንግተው ሸቀጦችን በእጥፍ ዋጋ ይሸጣሉ። በነዚህ ስፍራዎች የሚገኙ አቅራቢዎችን እንዴትና ለምን ብሎ መጠየቅ ነውር እስኪመስልም መከራከር አይቻልም። በዚህ መሐል ኪሱ የሚራቆተው፣ ኢኮኖሚው የሚሳሳው ሸማች ጉዳቱ ቀላል አይሆንም።

ተደጋግሞ እንደሚስተዋለው የኑሮ ውድነት መልኩ ደምቆ የሚጎላው በበዓላት ግብይት ወቅት ነው። በአንድም ይሁን በሌላ ገበያውን መርገጥ ግድ የሚለው ሸማች በዚህ ወቅት አስተውሎ ካልገበየ በስግብግቦች እጅ የመውደቁ ዕድል ሰፊ ይሆናል።

ብዙ ግዜ ለኑሮ ውድነቱ መባባስ ምክንያት ሆነው የሚጠቀሱ ማሳያዎች ይኖራሉ። በጦርነት ሳቢያ በሀገር ላይ ሠላምና አለመረጋጋት መኖር፣ በምርት ላይ የሚያጋጥም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ አደጋዎች፣ በወቅቱ ምርት ያለመሰብሰብና መሰል ምክንያቶችን በዝርዝር ማስቀመጥ ይቻላል።

ምንግዜም በተጠና የገበያ ስልት ዓውደ ዓመቱን ተከልለው ትርፍ የሚያጋብሱ አንዳንዶች ግን የሸማቹን አቅም ለማዳከም ወደኋላ የሚሉ አይደሉም። ምርት ሳይጠፋ፣ ግብዓት ሳይጎድል በወቅቱ ላይ የሚንጠላጠሉ አትራፊዎች ከራሳቸው ጥቅም የዘለለ የሌላውን ችግርና ጎዶሎ የሚያዩበት ዓይን ኖሯቸው አያውቅም።

እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በሰፋ ጊዜ ግን ቀዳሚው የመፍትሔ ትግል ከራስ ሊጀምር ግድ ይላል። ዓውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ ከኑሮ አጉድሎ፣ ከራስ ቆርሶ ተበድሮ የሚደረግ ልማዳዊ ጉዞ ለማንም አይበጅም። ይህ አይነቱ ተሞክሮ የሚቀጥል ከሆነም በአጭር ሊቀጭና ሊቋጭ ያስፈልጋል። ለምን ከተባለ ሰው እንደቤቱ እንጂ እንደጎረቤቱ አይኖርምና ።

አቅምን አውቆና ለክቶ፣ ከራስ ጓዳ ተማክሮ የሚውሉበት ገበያ ቢጠቅም እንጂ አይጎዳም። ትናንት በነበረ የገበያ ዋጋ ዛሬን አስቦ መግዛት እንደማይቻልም ነጋሪ አያሻም። አስቀድሞ ስለነገ ሕይወቱ አርቆ የሚያስብ ቢኖር እርሱ ብልህና አዋቂ ነው። ምንግዜም ይህን ያደረገ ራሱን ከችግር ያተርፋል። ነገን ያለሀሳብ ይሻገራልና ።

ዓውደ ዓመቱን አሳበው ዋጋን በእጥፍ የሚያንሩ ነጋዴዎች በሕግ አግባብ ሊዳኙ እንደሚገባ አያጠያይቅም። ይህ እንዲሆን ግን የኅብረተሰቡ ተሳትፎና አጋርነት ሊኖር ግድ ነው። በገበያ ያልጠፋን ምርት አስቀድሞ አከማችቶ ጊዜን ጠብቆ በማውጣት ኑሮን የሚያከብዱ ስግበግቦች ጥቂት አይደሉም ።

ምንግዜም እንዲህ አይነቶቹ ድርጊቶች ከኅብረተሰቡ ዓይን አይሰወሩምና ለተገቢው አካል ተጨባጭ መረጃዎችን በማድረሰ ኃላፊነትን መወጣት ይገባል። ይህ አይነቱ ጥቆማ የሚደርሳቸው አካላትም ራሳቸውን ከሙስናና ካልተገባ ጥቅም አርቀው ለኅብረተሰቡ መወገን ይኖርባቸዋል። የተረባረቡ እጆች ለኑሩ ውድነቱም ሆነ ለሌሎች ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉና። ለክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ መልካም የገና በዓል ይሁን።

 መልካምሥራ አፈወርቅ

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You