አብሮነታችን ለጋራ ሠላምና ብልጽግናችን መሠረት ነው!

 አብሮነት መተዋወቅን፣ መቀራረብን፣ መተሳሰብና መደጋገፍን፣ በጥቅሉም እህትማማችነትንና ወንድማማችነትን የሚፈጥር የሰውነት እሴትና ባሕሪ ነው:: አብሮነት በዚህ መልኩ ማኅበራዊ መሠረት የሚያጎለብት ብቻ ሳይሆን፤ በወንድማማቾች መካከል መተዋወቅና መተሳሰብን በማጽናት ውስጥ፣ በብዝኃነት የሚገለጥ አንድነትን የሚጎለብት፤ ተግባብቶ በመተባበር ውስጥ የሚገለጥ ኃያልነትን የሚገነባ ታላቅ ዓውድ ነው::

አብሮነታቸው የበረታ ሕዝቦች እንደ ሕዝብ ጠንካራ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብሎም ሥነልቡናዊ ከፍታን ተጎናጽፈዋል:: በሕዝቦች በኅብር የደመቀ መተባበር፤ በአብሮነት የጸና አንድነት ላይ ተመስርተው የተገነቡ ሀገራትም ሁለንተናዊ ብልጽግናቸውን፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነታቸውን አጽንተዋል:: በአንጻሩ ከዚህ በተቃራኒው የተጓዙ ሕዝቦች እና ሀገራት በድህነት፣ በኋላ ቀርነት፣ በመከፋፈልና ጦርነት ውስጥ ሲዳክሩ፤ እንደ ሀገር ፈርሰው፣ እንደ ሕዝብም ተበትነው ተገልጠዋል::

ዛሬ ላይ በልጽገውና የኃያልነት መንበርን ተቆናጥጠው የሚታዩ ሀገራት በሕዝቦቻቸው አብሮነት ላይ ተመሥርተው የተገነቡ ናቸው:: እነዚህ ሀገራት ጠንካራ ማኅበራዊ መሠረትን የገነቡ ሕዝቦች የእውቀት፣ የባሕልና እሴት ፍሬዎች እንደመሆናቸው ማንም ሰው ደርሶ ሊንጣቸው፣ ሊንዳቸው አልያም ሊያፈርሳቸው አይችልም:: ይልቁንም የትናንት የሕዝቦች አብሮነት ማዕከልነታቸው ለሌሎች በአርዓያነቱ እየተገለጠ የሚሄድ ነው::

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያንም በዚህ ረገድ ከትናንት እስከ ዛሬ የዘለቀው ታሪክና እሴታቸው በዚሁ ልክ የሚገለጽ ነው:: ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን አብሮነታቸው ታላቅ ሀገርን ፈጥሮላቸዋል፤ አብሮነታቸው ታላቅ የታሪክ ድልና ገድልን አስገኝቶላቸዋል፤ አብሮነታቸው ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስጠብቁ፣ ባሕልና እሴታቸውን ከፍ አድርገው ሳይበረዝ አጽንተው እንዲይዙ አቅም ፈጥሮላቸዋል::

በባሕልና እሴት ከፍታቸው፤ በታሪክ ክታብ ገናነነታቸው፤ በነፃነትና በድል መንገዳቸው፤ በብዝኃነት ኅብር ድምቀታቸው ምክንያት የሆነው ይሄ አብሮነታቸው ታዲያ፤ ከትናንት እስከ ዛሬ በምቾት ላይ ምቾት ተላብሶ ያለ እንከን የዘለቀ አይደለም:: ይልቁንም ሲፈተን እና በፈተና ውስጥ የበለጠ እየጸናና እየጠበቀ በሄደ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ወንድማማችነት ላይ ሊመሠረት የቻለ እንጂ::

ለዚህም ነው ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊነት የወል መገለጫቸው ላይ ተቆናጥጠው ረዥሙን ጉዞ ድካም ተቋቁመው፤ የረዥሙን ታሪክ ስንክሳር ተሻግረው፤ የረዥሙን ጉዞ ውጣ ውረድ አልፈው እንደ ቀደመው ሁሉ በአብሮነት ጸንተው መገኘታቸው:: ለዚህም ነው ኢትዮጵያን በዘመን ጅረት ውስጥ ነፃነትና ሉዓላዊነቷን በገናና የታሪክ ድርሳን ላይ ተከትቦ እንዲዘልቅ ማድረጋቸው::

የኢትዮጵያውያን አብሮነት መገለጫው ታዲያ አንድ ፈርጅ ብቻ አይደለም:: ይልቁንም እንደ ጊዜና ሁኔታው እየተቃኘ የሚታይ፤ ሊንደው ለሚሻ ማናቸውም የክፋት ኃይል ልፋቱን ከንቱ በሚያደርግ መስተጋብር የሚገለጥ ነው:: ምክንያቱም የኢትዮጵያውያን አብሮነት በባሕል ውስጥ ጎልቶ የሚታይ የተዋረሰ ባሕላዊ እሴትን ፈጥሯል:: የኢትዮጵያውያን አብሮነት ከፍ ባለ ማኅበራዊ ጉድኝት ውስጥ የሚከሰት የኢትዮጵያውያንን በደስታና በኃዘን የመተጋገዝ ሰብዓዊ ልዕልናን ገንብቷል::

የኢትዮጵያውያን አብሮነት በውስጥም በባንዳነት የሚነሳን፤ ከውጪም በጠላትነት የሚነሳን ማናቸውም ፀረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ኃይል አንገት በሚያስደፋ የጀግንነት መሠረትን የገነባ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን አጽንቷል:: የኢትዮጵያውያን አብሮነት በየትኛውም ዓውድ ላይ ከፍ ብሎ የመገለጥን፤ የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ልዕልና ማስጠበቅን፤ ለችግር ያለመንበርከክና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በጋራ መሰለፍን በዓለም አደባባይ መግለጥ ችሏል::

ይሄ የኢትዮጵያውያን የአብሮነት ገጽ የፈጠረው ሁሉን አቀፍ መገለጫ ታዲያ በትናንት ታሪክ ብቻ የሚተረክ አይደለም:: ይልቁንም ዛሬም በሚደንቅ ሁኔታ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ ለማድረስ፤ ኢትዮጵያውያንንም ወደ ክብር ቦታቸው ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እየታየ ያለ ሐቅ ነው:: የኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ የተጀመረው ጉዞ እያሳየ ያለው ውጤት ደግሞ የዚህ እውነት ማጽኛ ዓውድ ነው::

ይሄ በትናንት ሁነት እና በዛሬ ኑረት ውስጥ የሚገለጠው የኢትዮጵያውያን አንድነት ታዲያ፤ ለነገው ትውልድ መሠረትን አኑሮ የመገለጥ ከፍ ያለ ግዴታ በዛሬው ባለ ሀገር ላይ የታለ መሆኑን መገንዘብ የተገባ ነው:: ምክንያቱም የትናንቶቹ ከችግሮቻቸው ልቀውና በአብሮነታቸው ዘልቀው ዛሬን ፈጥረዋል:: እናም የዛሬዎቹ የቀደምቶቻቸውን አደራ ጠብቀውና አልቀው ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል::

ይሄን የሚያደርጉት ታዲያ ከትናንቱ የአብሮነት ፈተናዎች መሻገሪያ አቅም ፈጥረው፤ ከመልካም ሁነቶቹ ተምረውና አዳዲስ እሴቶችን ገንብተው ሊሆን ይገባል:: በዚህ መልኩ የሚገነቡት አንድነት ደግሞ በኅብረ ብሔራዊነት ላይ የተመሠረተ፤ በሰላምና መተሳሰብ፣ በፍቅርና ይቅርታ ላይ የተመረኮዘ፤ ከራስ አልፎ ለነገው ትውልድ ታላቅ ሕልምን የሰነቀ ሊሆን ይገባል::

ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር፣ ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ የሚሹትን ሰላም እና ሁለንተናዊ ብልፅግና እውን ማድረግ የሚቻለው ይሄን መሰል አብሮነት መገንባት ሲቻል እንደመሆኑ፤ አብሮነታችን የሰላምና የሁለንተናዊ ብልጽግናችን አስኳል መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው!

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 25 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You