ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለጋራ ጥቅም ከጎረቤቶቿ ጋር ለመሥራት ያላትን ፍላጎት በተጨባጭ ያሳየ ነው

የአፍሪካ ቀንድ ከመልከዓ ምድራዊ፣ ጂኦ-ፖለቲካዊ፣ ስትራቴጂካዊ ፋይዳው አንፃር ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ፣ ዲፕሎማሲና የጸጥታ ተለዋዋጭነት ያስተናግዳል፡፡ የኃያላን ሀገራት ጣልቃ ገብነት ጎልቶ ይታይበታል፡፡ የኢትዮጵያ መገኛም በዚሁ የተጨነቀ ቀጠና መሃል /nucleus / ውስጥ ነው፡፡

የዚህ የፖለቲካ ድባብና ሁኔታም ሀገሪቱም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ይነካካታል፡፡ ቀጠናው ላይ የተለኮሰ እሳት ኢትዮጵያንም ይጠብሳታል፡፡ ከጥንት እስከ ዘመናዊ የዲፕሎማሲ መስተጋብር የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማዕከላዊ መሠረቶች ወይንም /determinant/ ዋነኛው ይህ ቀጠና ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ውጥረት ለአፍታም በማይለየው ቀጠና ውስጥ ጥበብ በተሞላበት መልኩ ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቃ ዘመናትን አሳልፋለች፡፡ ይህ ስኬታማነቷ በአንዳንድ ተመራማሪዎች ዘንድ ዋነኛ ጥያቄ ሆኖ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም ቀጥሏል፡፡

ኤድሞንድ ኬለር የተባሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ‹‹The Politics of State Survival: Change and continuity of Ethiopian Foreign Policy›› በሚለው ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንዳመላከቱት፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ የሀገሪቱን ህልውና ለማስጠበቅ ትልቁ መሳሪያና ጥበብ ነው፡፡

በርግጥም በዚህ ቀጠና በተለያዩ ጊዜያት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፈትኑ ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊ ክስተቶች ቢስተዋሉም ፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በሳል የዲፕሎማሲ ክንውኖችን ስታደርግ ቆይታለች።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በመልካም ጉርብትና፣ ሰጥቶ መቀበል፣ በጋራ ተጠቃሚነት፣ በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፣ የጋራ ደህንነት እና ሌሎች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ወርቃማ መርሆች የሚመራ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ቀጠናውን አስመልክቶ የምታራምደው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በጋራ ልማት፣ ተጠቃሚነትና ትብብር ላይ የተመሠረተ መሆኑን በግልፅ የሚታይ ነው። የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲ ብልህ የሆነ ሀገራዊ፣ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ነባሬዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው።

ከጋራ ተጠቃሚነት ማዕከሉን ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ጎረቤቶቿን ጭምር የሚጠቅምና የቀጠናውን ሁኔታ መቀየር በሚችል መልኩ የተቃኘ ነው፡፡ የተለያዩ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ ባልተረጋጋና ውጥንቅጡ በወጣ ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ሀገራት ሁለንተናዊ ማለትም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ደህንነታቸውን ለማረጋገጥ (maximizing its security) መሥራት ግድ ይላቸዋል፡፡ ራሳቸውን በማጠናከር፣ የውስጥ አቅማቸው ከውጫዊ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም በማድረግ ለውጫዊ ሁኔታው ምላሽ የሚሰጡበት አቅጣጫ ሁሌም ማማተርን መዘንጋት የለባቸውም፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ሕዝቦች ጋር የሚያስተሳስሯት ጠንካራ የባህል፣ የንግድ፣ የተፈጥሮ ሀብት፣ በመልከዓ ምድር፣ በሃይማኖት፣ የቋንቋ እና የታሪክ ሰንሰለት አላት፡፡ ይህን ከግምት ባስገባ መልኩ ሀገሪቱ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማዳበር በተለይም የሕዝብ ለሕዝብ ጨምሮ የተለያዩ የትስስር ዲፕሎማሲ መንገዶችን እያራመደችም ትገኛለች፡፡

የጎረቤት ሀገራት ዜጎች በኢትዮጵያ የትምህርት፣ ስልጠናና ሌሎች ድጋፎች እንዲያገኙ ማድረግም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራ፣ የሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን ተማሪዎች በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አስፈላጊው ትብብር ተደርጎላቸዋል። ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጎረቤት ሀገር ስደተኞችን በመቀበል ስመ ገናና ናት፡፡

ከቀጠናው ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በሰላምና ደህንነት፣ በንግድ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ መስኮች ይበልጥ በማጥበቅ ላይ ትገኛለች። በኢኮኖሚ ትስስር ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና በመተግበር አፍሪካን በተለይም ምስራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር እየተጋች ትገኛለች፡፡

በዚህም መሠረት ከጅቡቲ የሚያገናኛት የባቡር ሃዲድ ገንብታለች፡፡ ከሱዳንን ጋር ለመገናኘት የየብስ ትራስፖርት ሥራ ጀምሯል። ኢትዮጵያን ኬንያን የሚያገናኝ የየብስ ትራንስፖርት ሌላኛው የትስስር ገመድ ነው። በእርስ በእርስ መስተጋብር በኢኮኖሚ ትስስር በተለይ ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ከጅቡቲ፣ ኬንያና ሱዳን ጋር እየሰራች ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ ከጅቡቲ የወደብ አገልግሎቶችን ስታገኝ፣ ከሱዳን ጋር ደግሞ በነዳጅ ዘይት ግዢ ትገናኛለች፡፡ ይህ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር (interdependence) በማስፈን አንዱ ከሌላው ጋር ተደጋግፎ ነገዎቹን ብሩህ የሚያደርግበት፣ የጋራ ተጠቃሚነት ዋነኛው የዲፕሎማሲያ መርህ ያደረገ ስለመሆኑ በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በሁሉም መስፈርት ትልቅ ሀገር ነች፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከዓለም የባህር በር/ ወደብ ከሌላቸው ሀገሮች በሕዝብ ብዛት አንደኛ ነች፡፡ ሀገሪቱን ከቀይ ባህርና ከወደብ ባለቤትነት ለመግፋት ከውስጥም ከውጭም የተሰራው ደባና ሴራ ሁሌም ቢሆንም ትውልድን የሚያስቆጭ ነው፡፡

ወደብ ለአንድ ሀገር ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው እድገት ወሳኝ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለከፍተኛ ኢኮኖሚ ባለቤት የሆኑ ሀገራት በሙሉ የወደብ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት መተንፈሻን ማስፋት የግድ ነው። ኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት መሆን ባለመቻሏ ኢኮኖሚው ክፉኛ ታፍኖ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ ከወራት በፊት ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድና በጋራ የመልማት መርህን በተከተለ መልኩ በወደብ የመተሳሰር ጥያቄን ማቅረቧም የሚታወስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል የሚለውን ጉዳይ በተለያዩ መድረኮች ሲያነሱ ያላመኑ፤ ከንቱ ቅዠት የመሰላቸውና ይልቁንም ሀገሪቱን ወደ ጦርነት ሊወስዷት እንደሆነ ስጋት ያደረባቸው ብዙዎች እንደነበሩ የሚታወስ ነው፡፡

ይሁንና በርካቶች መረዳት ያልቻሉት፤ አሊያም ተረድተው መቀበል ያልፈለጉት የዲፕሎማሲ አማራጭ ከቀናት በፊት አሸናፊ ሆኖ ታይቷል፡፡ ከቀናት በፊት ኢትዮጵያን ሶማሊያ-ላንድ ታሪካዊ የተባለ ትስስርን ፈጥረዋል፡፡ ሁለቱ ሀገራትም በወደብ ልማት በጋራ ለመሥራትና በጋራ ለማደግ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ታሪካዊ ነው የተባለውን የመግባቢያ ሠነድ ተፈራርመዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበትን የመግባቢያ ስምምነት የሀገሪቱንን መጻኢ ዕድል የሚያሳምር ከመሆኑም በላይ፤ ለዓመታት ወደብ አልባ ለሆነው ሕዝብ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው። የተገኘው የባሕር በር የኢትዮጵያን ስብራት የጠገነና የትውልድን የዘመን ቁጭት የመለሰ ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ለማግኘት ያደረገችው የትብብርና አጋርነት ስምምነት ሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ጡንቻ መፈርጠም ያለው አስተዋጽኦ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም። የኢትዮጵያን በሳል የዲፕሎማሲ ውጤት ምስክር ነው፡፡ ይህ ስምምነት ኢትዮጵያ መንግሥት በሰጥቶ መቀበል መርህ እና ለጋራ ጥቅም ከጎረቤቶች ጋር የመሥራት ፍላጎትና አቋምን መልሶ የሚያፀና ነው።

አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ ቢኖር ኢትዮጵያ የባሕር በር ብታገኝ የሚጎዳው አካል የለም፡፡ የኢትዮጵያ ፍላጎትም በጋራ ማደግ፣ በጋራ መበልፀግ፣ በጋራ ደህንነትን ማስጠበቅ መሆኑን መረዳት የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝን በተለይም ግድቡም በሚመለከት የምታራምደው አቋም ከዚህ በተለየ መነፅር የሚታይ አይደለም።

ምንም እንኳን ወንዙ ከኢትዮጵያ የሚመነጭ ቢሆንም ሀገሪቱ ሀብቱን በብቸኝነት ልጠቀም የሚል አቋም አሳይታም አታውቅም፡፡ ወደፊትም አታሳይም፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የጋራ መሆናቸውንና ታሳቢ ባደረገ መልኩ አጠቃቀሙም በተለይም ጎረቤት ሀገራትን በሚጠቅምና የጋራ ተጠቃሚነትን እውን በሚያደርግ መልኩ መሆን እንዳለበት በማመን በፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ ዲፕሎማሲዋን እየመራች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፍላጎትና የዲፕሎማሲ አቋም የማንንም ብሔራዊ ጥቅም የማይጎዳ ይልቁንም የጋራ ተጠቃሚነት ያስቀደመ መሆኑን ሁሉም ሊረዳ ይገባል፡፡ እንደ ወደቡ ሁሉ የግድቡን ጉዳይም ከጋራና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም የአብሮነት ብልጽግና አንፃር መመልከት ተገቢ ይሆናል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You