የአንዳችን ችግር፤የሁላችንም ችግር ነው

የሰው ልጅ መቼም በምድር ላይ እየኖረ የመጥፎ እና ጥሩ ዕድሎች መመላለሻ ሃዲድ ነው፡፡ መልካም ዕድሎች ሲመጡ ዝም ብለው የሚመጡ ሳይሆኑ ለዚህ የሚሆኑ መደላድሎች በመፈጠራቸው ነው። መጥፎ ዕድሎችም የሰው ልጅ የእሳቤ ውጤት ናቸው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ሀገርም የሚከሰቱ ጥሩ ይሁኑ መጥፎ ክንውኖች የዜጎችና የመንግሥታት የጋራ ውጤቶች ናቸው፡፡

እንደ ሀገር ችግር ሲመጣ ለጊዜው የተወሰነውን ቡድን ወይንም ማህበረሰብ ብቻ ለይቶ የሚጎዳ ይመስላል፡፡ ከዚህ የተነሳ አያገባኝም የሚል ብዙ ሊሆን ይችላል፤ ቆይቶ ግን ችግሩ ሁሉንም የሚያገባው ይሆናል፡፡ የአንዱ ችግር የሁሉም ችግር፤ የሁሉም ችግር ደግሞ የአንዱ ችግር ሆኖ መፍትሄውም ችግሩም የእሽክርክሪት ጨዋታ ይመስል እዚያው በዚያው ይሆናል፡፡

ይህን ሃሳብ የበለጠ ለማብራራት አንቂ መፅሃፍት ገፆች ከሚል የማህበራዊ ድረ ገጽ የወሰድኩትን ፅሁፍ ላጋራችሁ፡፡ ‹‹በአንድ ገበሬ ቤት የምትኖር አይጥ ነበረች። ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ይህችው አይጥ ገበሬው እና ባለቤቱ እቃ ሸምተው ወደ ቤታቸው ሲገቡ ትመለከትና ለእኔ የሚሆን ምን ገዝተው ይሆን? ብላ በቀዳዳ አጮልቃ ስታይ ፍፁም ያልጠበቀችው ነገር ትመለከታለች፡፡ የተገዛው ነገር የሚበላ ሳይሆን የአይጥ ወጥመድ ነበር፡፡

‹‹በድንጋጤ ውስጥ እንዳለች ከጉድጓዷ ወጥታ እየሮጠች በጊቢው ውስጥ ወዳሉት የቤት እንስሳት ሄደች፡፡ መጀመሪያ ያገኘችው ዶሮን ነበር፤ እየጫረች ጥራጥሬ ስትለቅም። ‹‹ማነሽ አንቺ ዶሮ፣ ኧረ! ጉድ አልሰማሽ፣ ቤት ውስጥ ወጥመድ ተገዝቷል።›› ብትላት ጊዜ ዶሮዋ እየተቆናጠረች ‹‹እና ምን ይጠበስ! አንቺ ተጨነቂበት እንጂ እኔን የሚያሳስበኝ ነገር አይደለም›› አለቻት፡፡

‹‹አይጧ እየተበሳጨች ወደ በግ ሄደችና ‹‹ስማኝማ! አቶ በግ፣ ቤት ውስጥ ወጥመድ ተገዝቷል፤ እባክህ አንድ ነገር እናድርግ›› ስትል በተማፅኖ ብጠይቀውም በጉ ካቀረቀረበት ሣር ላይ ቀና ሳይል ‹‹በጣም ያሳዝናል! ግን ልረዳሽ አልችልም፤ ራስሽ ተወጪው›› አላት፡፡

‹‹አሁንም አይጥ ቁና ቁና እየተነፈሰች፣ ወደ በሬ ዘንድ ሄደችና ቤት ውስጥ ስለተገዛው ወጥመድ ነገረችው፡፡ በሬውም ምንም ሳይመስለው እንዲህ ሲል መለሰላት፣ ‹‹እንዲያው ምን ይሻልሻል? ባይሆን በግ እና ዶሮ ይርዱሽና አንድ ነገር አድርጊ፤ እኔን እንኳን ተይኝ አላት፡፡

‹‹አይጧ ተበሳጭታ፤ ‹‹ኧረ ተው! ተው! አንድ ነገር ብናደርግ ይሻላል፤ ለጊዜው ቢመስላችሁም ችግሩ የጋራችን ነው›› ስትል ተናገረች፡፡ ሁሉም ተያይተው ተሳሳቁባት። ‹‹ቀልደኛ ነሽ!›› እየተባባሉ። አይጥም ተስፋ ቆርጣ ወደ ጉድጓዷ ገብታ ሌሊቱን ሙሉ እንቅልፍ ሳይወስዳት አደረች፡፡

‹‹ማታ ወጥመዱ ተጠምዶ እያለ ቀጭ የሚል ድምፅ ሲሰማ የገበሬው ሚስት ተስፈንጥራ ተነሳች፤ ወጥመዱ የያዛትን አይጥ ለማየት። ጨለማ ስለነበር በዳበሳ ወደ ወጥመዱ ሄዳ ወጥመዱን ስትነካው በአይጥ ፋንታ የተያዘው መርዘኛ እባብ ስለነበረ ነደፋት፡፡

‹‹በነጋታው የገበሬው ሚስት ከሐኪም ቤት ስትመለስ ራስ ምታት እንዳያስቸግራት ተብሎ ዶሮዋ ታረደችና ሾርባ ተዘጋጀላት፡ ፡ የገበሬው ሚስት ህመሙ እየጠናባት ሲሄድ በቶሎ እንድታገግም ተብሎ በግ ታረደላት፡ ፡ ሆኖም ግን ሴትዮዋ ማገገሟ ቀርቶ ሞተች፡፡ ይህንን ተከትሎ ዘመድ አዝማድ ለለቅሶ ሲመጣ ለተስካር በሚል በሬውም ታረደ። የሚገርመው አይጥም ቁጭ ብላ እያለቀሰች ሦስቱም ሲታረዱ አየች።

እንደ ሀገር የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ እንደመሆናችን፤ በብዙ ተግዳሮቶች እየተፈተንን ነው። ከነዚህ ውስጥ የሠላም ጉዳይ በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ዜጎች ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተንቀሳቅሰቀው ለመስራት ብዙም ነፃነት እየተሰማቸው አይደለም፡፡

አሁን አሁን ከኢትዮጵያዊ እሴትና ባህል በእጅጉ ያፈነገጡ ወንጀሎች እና ፀያፍ ድርጊቶች እየተፈፀሙ ስለመሆናቸው መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡ የሠዎች እገታ፣ መፈናቀልና ኢ-ሠብዓዊ የሆኑ ድርጊቶች፤ በእነዚህ ችግሮች ላይ ደግሞ የኑሮ ውድነት ዜጎችን ምሬት ውስጥ እየከተተ ነው፡፡

ዜጎችን በማገት ከፍተኛ ገንዘብ ከሚጠይቁት ኢ-መደበኛ ኃይሎች እና ፀረ ሠላም አካላት ጨምሮ እራሳቸውን በተለያየ መንገድ አደራጅተው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች እንደ ሀገር ተፈጥረው የነበሩ አጋጣሚዎችን በመጠቀም፤ የልብ ልብ እየተሰማቸው እውነታውም መከሰቱ የአደባባይ ሚስጥር ነው።

እርግጥ ነው፤ ‹‹ውፍረት እና ስህተት ለባለቤቱ አይታየውም›› የሚባል ብሂል አለ። እነዚህ አካላት አሁን ስህተቱ አይታያቸውም፤ በእነርሱ አተያይ ትክክል ናቸው፡፡ የበለጠ ትክክል ነን የሚያስብላቸውን ዕድል ደግሞ ሕዝቡ የሰጣቸው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ገና እነዚህ ልምምዶችን ሲጀምሩ እረፉ! አድቡ! የሚላቸው ማህበረሰብ መኖር ነበረበት። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ለእነዚህ አካላት ከለላ የመስጠት ዝንባሌ መኖሩ መንግሥትም ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ እንቅፋት ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡ ነገሩን ገና ከመነሻው መግታት ቢቻል፤ ከመሠረቱ ፈር ቢይዝ፤ ዛሬ የሚታዩ እኩይ ተግባራት ቦታ ባልነበራቸው ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን አልረፈደም፤ ችግሩ የጋራ ነው፤ መፍትሄውም መተመሳሳይ የጋራ ነው የሚል እሳቤ ያስፈልጋል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው የአይጥ እና የሌሎች እንስሳት ታሪክ ለአሁናዊ ችግሮቻችን ሆነ ለቀጣይ ብዙ ልንማርበት የሚገባ ነው። እንስሳቱ ገና ከጅምሩ ችግሩ ሁሉም ይመለከተናል ቢሉ ኖሮ ባላለቁ ነበር፡፡ ‹‹ያልጠረጠረ ተመነጠረ›› እንዲሉ አበው፤ ነገሮችን ከተለመደው መንገድም ወጣ ባለ ሁኔታ መቃኘት አሊያም መመልከት ይገባል፡፡

በሀገር ላይ የተደቀነ አደጋን በክብደቱ መጠን ልንመለከተው የሚገባ ነው። የሀገር ጉዳይ የሀገር ነው፤ የሁላችንም ነው፡፡ የሀገር ጉዳይን የሆነ አካል ወይም ቡድን ጉዳይ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። በዚያ መልኩ ማየት ከጀመርን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እንደሞኙ በግ፣ እንደ ቸልተኛው በሬ እና እንደ ሆድ አደሯ ዶሮ ከመበላት አናመልጥም፡፡ አይጧ እንዳለችው… ‹‹ለጊዜው ቢመስልም፤ ለኔ የመጣ ጢስ ላንቺ አይመለስም›› ነው ነገሩ፡፡

ከዚህ የተነሳ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የማህረሰብ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አውታሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ በአንድም ይሁን በሌላ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አካላት ሆነ ማንኛውም ዜጋ እዚህ ሀገር በሚከሰቱ ችግሮች ዙሪያ በኃላፊነት መንፈስ በጋራ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውጪ ሀገራዊ ችግሮችን ለተወሰነ አካል ሰጥቶ እጅን አጣምሮ መቀመጥ ሆነ ችግሮችን በማራገብ የሚመጣ ዘላቂ መፍትሄ አይኖርም፡፡

ክፍለዮሐንስ አንበርብር

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 24 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You