ሀገሪቱ ከቱሪስት ሀብቷ ተጠቃሚ እንድትሆን ለማድረግ

ኢትዮጵያ የጎብኚዎችን ቀልብ ለመሳብ የሚችሉ በርካታ ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ መስህቦች፤ ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ከሆኑ ጥቂት የዓለማችን ሀገሮች መካከል አንዷ ናት፡፡

ሀገሪቱ የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ፤የረጅም ዘመን የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ባለቤት የመሆኗ ፣የብዙ ብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መኖሪያ የመሆኗ እውነታ ፣ አሁን ላይ ደግሞ እንደ ሀገር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (UNESCO) የተመዘገቡ 16 የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ የቱሪስቶችን ቀልብ እንድትስብ ተጨማሪ አቅም ፈጥረውላታል።

የተለያየ ሃይማኖት ተከታይ ሕዝቦች በመተሳሰብ አብረው የሚኖሩ ፤የራሷ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያላት መሆኗ፤ የሃይማኖት በዓላት አከባበር እጅግ ደማቅ መሆን ጨምሮ የሕዝቦቿ እንግዳ ተቀባይ መሆን በርካታ ቱሪስቶች ሀገሪቱን ለመጎብኘት እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል፡፡

እንደ ሀገር የሰው ዘር መገኛ መሆኗ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕዝቦቿ የነፃነት ተምሳሌት መሆናቸው፤ ከዛም አልፎ በጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል ውስጥ ካበረከቱት ከፍያለ አስተዋጽኦ አንጻር፤ በተለይም በጥቁር አፍሪካውያንና አሜሪካውያን ዘንድ የመጎብኘት ተፈላጊነቷ ከፍ ያለ ነው።

ሀገሪቱ እንደ ሀገር የዚህ ሁሉ አቅም ባለቤት ብትሆንም፤ያላትን ይህንን ተጨባጭ አቅም በመጠቃም ሂደት ውስጥ እዚህ ግባ በሚባል ደረጃ ላይ አይደለችም። ከዘርፉ እያገኘች ያለው ጥቅም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር ከዝቅተኝነቱ የተነሳ ለውድድር የሚቀመጥ አይደለም፡፡

ይህንን አሁናዊ እውነታ ለመቀየር፤ ያሉንን ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ የቱሪስት መስህቦችን በስፋት ከማስተዋወቅ ጀምሮ በየክልሉ አዳዲስ መስህቦችን መፈተሽና ጥቅም ላይ ማዋል ተገቢ ነው፡፡

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ በርካታ የቱሪስት መስህብ ሀብቶች ያሏት ሀገር ነች፤ በሌላው ዓለም ብዙም ያልተለመዱትን ባህላዊ፤ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ መስህቦች ሀገሪቱን ከአፍሪካ የተለየች የቱሪስት መዳረሻ ሊያደርጓት የሚችሉ ናቸው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2019 ከአጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ቱሪዝም የነበረው ድርሻ 10 በመቶ ነበር፣ ለ334 ሚሊዮን ሰዎች ሥራ መፍጠር ችሏል።

ጭስ አልባው ኢንዱስትሪ በመባል የሚታወቀው ይህ ዘርፍ/ የቱሪዝም ዘርፍ የበርካታ ሀገራት ዋነኛ የኢኮኖሚ መሠረት እየሆነ ነው። ከአፍሪካ እንኳን ኬንያ ታንዛኒያ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ከዘርፉ በተሻለ ተጠቃሚነታቸው የሚጠቀሱ ናቸው።

ከነሱ ያልተናነሰ /እንዲያውም የተሻለ ጎብኚዎችን መሳብ የሚያስችሉ ታሪካዊና ተፈጥሮአዊ ሀብቶች ያሏት ሀገራችን ከዘረፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻለችም።

በየትኛው የዓለም ክፍል ወረርሽኝ፣ ድንገተኛ አደጋዎች እንዲሁም ጦርነት በሚኖርበት ወቅት ሰው ተኮር የሆነውን የቱሪዝም ዘርፍ እንደሚጎዳ ይታወቃል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቀጣይነት ባለው መልኩ ገቢ በማስገባት ወደር የማይገኝለት የቱሪዝም ዘርፍ በሚጠበቅበት መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዲችል በተለይም ከዘርፉ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለውን ሰላምና ፀጥታ ማስጠበቅ ጥልቁ የቤት ሥራ ነው።

በሀገራችን ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ ሆነ በውጭ ጎብኚ የሚጎበኙ ታሪካዊ ቅርሶች እንዳሉ ሆነው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በመላው ኢትዮጵያ እየተሠሩ ያሉ እንደ ወንጪ፣ ጎርጓረ፣ ሀለላ ኬለ ዓይነት የቱሪስት መስህብ ሥፍራዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ መጥራት የሚችሉ ናቸው። በዘርፉ እየተሠራ/እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች በውጤት የታጀቡ እንዲሆኑ የሰላም ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል።

ጎብኚዎች ወደ አንድ ሀገር እንዲጓዙና በዚያ እንዲቆዩ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። ያለንን አቅም ማየት ማልማትና መጠበቅን ይፈልጋል። ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብትን (የውሃ አካላት፣ ደን፣ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች፣ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ . . .ወዘተ.) በአግባቡ ማወቅን፤ የማኅበረሰቦችን ስብጥር፣ የእነርሱን ባህል፣ ወግ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ለይቶ ማወቅና ማስተዋወቅን የሚፈልግ ነው።

ጎብኚዎችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማርዘም፤ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችን፣ሎጆችን ፣ የመዝናኛ ተቋማትን፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ ሁለገብ አዳራሾችን… የመጓጓዣና የመገናኛ ፣ የጤና ወዘተ መሰረተ ልማቶችን በስፋት መገንባት ያስፈልጋል።

ሀገራችን የዳሎል ፣ የራስ ዳሸን፣ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ፣ የነጭ ሳር ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የአክሱም ሀውልቶች፤ የአፄ ፋሲለደስ ቤተ መንግሥት የጀጎል ግንብ ፣ የሶፍ ኡመር ዋሻ ባለቤት መሆኑዋ በራሱ የዘርፉ ተጠቃሚ አላደረጋትም ።

የተለያዩ ሃይማኖታዊ ፣ ባህላዊ በዓላት በድምቀት የሚከበሩባት ፣ ከ10 በላይ የሥነ ምህዳር ባለቤት መሆኗ ሞልቶ የተትረፈረፈች ታሪክ ባለቤት መሆኑዋ በራሱ ሀገሪቱን በሚጠበቀው መልኩ የሀብቱ ተጠቃሚ አላደረጋትም። ይህን እንቆቅልሽ ለማረም ይህ ትውልድ ከፍያለ ኃላፊነት አለበት።

ለዚህ ደግሞ ለቱሪዝም ዘርፍ መንግሥትም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል። ሀገራችን የቱሪስት አቅማችን ዓይን ከፍቶ ከማየት ጀምሮ አልምቶ እስከ መጠበቅ ድረስ ያለውን ሂደት ታሳቢ ያደረገ የልማት ስትራቴጂ ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋል።

በተለይም አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አነሳሽነት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ሀገራዊ መነቃቃቶች እያስመዘገቡት ካለው ስኬት አንጻር፤ ይህንን መልካም ጅማሮ በማስፋት ረገድ የግል ባለሀብቶችና የክልል መንግሥታት ጥልቅ ኃላፊነት አለባቸው።

ክብረአብ በላቸው

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You