ለወገኖቻችን ሰብአዊ እርዳታ በወቅቱ ለማድረስ የሁላችንም ርብርብ ወሳኝ ነው

የሰብአዊ እርዳታ የሚለው ቃል በተፈጥሮ አደጋዎች፣ ግጭቶች እና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ለተቸገሩ ሰዎች የሚሰጠውን እርዳታ ያመለክታል። በችግር ጊዜ ህይወትን ለማዳን፣ መከራን ለማቃለል እና የሰውን ልጅ ክቡር ህይወት ለመታደግ ያለመ የድጋፍ ዓይነት ነው።

በሰብአዊነት እና በገለልተኝነት መርሆች የሚተገበር፤ የመጨረሻ ግቡ ለሰው ሰራሽም ሆነ ለተፈጥሯዊ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን በሕይወት ለማትረፍ እና ከድንገተኛ አደጋዎች እንዲያገግሙ ለማስቻል አስፈላጊ የሆኑ ሀብቶችን፣ አገልግሎቶችን እና ጥበቃ እንዲያገኙ የማድረግ ሂደትም ነው።

በአደጋ ጊዜ፣ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ ወይም በግጭቶች ሳቢያ የሰብአዊ እርዳታ እንደ ምግብ፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ የጤና እና የንፅህና መጠበቅያ ያሉ አፋጣኝ ፍላጎቶችን በማስተናገድ ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በዚህም ተጨማሪ የህይወት መጥፋትን ለመከላከልም ይረዳል፡፡

አስቸኳይ የህክምና አገልግሎትም በዚሁ የሰብአዊ እርዳታ ውስጥ የሚካተትበት ሁኔታ ያለ ሲሆን ከአደጋዎች ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችለውን የበሽታ ወረርሽኝ ለመከላከለና ስርጭቱንም ለመግታት ወሳኛ አቅም እንደሚሆን ይታመናል ፡፡

ከዚህም ባለፈ በሰብአዊ ዕርዳታ ማእቀፍ ለአጭር ጊዜ እገዛን በማድረግ ለተጎጂዎች እፎይታ መስጠት ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ካሉበት እንዲያገግሙ እና እንዲቋቋሙ ማድረግ ይቻላል። የተጎዱትን ማህበረሰቦች ከጉዳታቸው አገግመው ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲጀምሩ፣ ወደ ነበሩበት የኑሮ ሁኔታ ለመመለስ እና ዘላቂ ልማትን ለማምጣትም የራሱ እገዛ ይኖረዋል፡፡

ከሰብአዊ ርዳታ ቁልፍ መርሆዎች ውስጥ አንዱ ገለልተኛነት ነው። ገለልተኝነት ሰብአዊ ድጋፍን ያለ አድልዎ መከወን ማለት ነው፡፡ ሰብአዊ እርዳታው የተጎጂዎችን ዘር፣ ዜግነት ፣ ሃይማኖት እና የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላማከለ፤ ሰው በመሆናቸው ብቻ የሚያገኙት ነው፡፡

የሰብአዊ እርዳታ አገልግሎት በአለም አቀፍ የሰብአዊነት ህግ እና መርሆዎች የሚመራ ፤ ሴቶችን፣ ህጻናትን፣ አረጋውያንን እና ሌሎች ተጋላጭ የማህበረሰብ ክፍሎችን ጨምሮ ለሲቪሎች ደህንነት ቅድሚያ የሚሰጥ ነው ፡፡ በዚህም የሰዎችን የሰብአዊ መብቶች መከበርን፣ ሰብአዊ ክብር መጠበቅንና ማንኛውንም አይነት አድልዎ፣ ጥቃት ወይም ብዝበዛ መከላከልን ያካትታል፡፡

በሀገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ ግዜያት በሚከሰቱ ግጭቶችና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በተለያዩ ወቅቶች የድርቅ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ በያዝነው አመትም በትግራይ ክልል 32 ወረዳዎች ላይ ድርቅና የምግብ እጥረት ማጋጠሙን የትግራይ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

ታኅሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም በታተመው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የትግራይ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ግብረ መልስ አስተባባሪ አቶ ልጅዓለም ካሕሣይ በክልሉ 32 ወረዳዎች የከፋ ድርቅና የምግብ እጥረት ማጋጠሙን ተናግረዋል። በትግራይ ክልል ደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅ፣ መካከለኛውና ሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች የድርቅ አደጋ ያጋጠማቸው መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በክልሉ የተከሰተው የድርቅ አደጋ በዋነኝነት ከጦርነቱ እና ከተፈጥሮ ጋር ተያይዞ መከሰቱን፤ በዚህም አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ እርዳታ ፈላጊ መሆኑንም አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡ ያጋጠመው የምግብ እጥረት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለመከላከል በጥቂቱ ለአንድ ዓመት የሚቆይ የእርዳታ አቅርቦት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በትግራይ ክልል ሁለት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅና በግጭት ምክንያት ለምግብ እጥረት መጋለጣቸውን ደግሞ በኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ አታለለ አቡሐይ አመልክተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ ዋግኽምራ፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ ሰሜን ሸዋ አካባቢ፣ በምሥራቅ ጎጃም እንዲሁም በአፋር ክልል ወደ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች በድርቅ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት በምግብ እጥረት አደጋ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ፤ ሰብአዊ እርዳታዎች በፌዴራል እና በክልል መንግሥታት ፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ጨምሮ በአካባቢያዊ ማህበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች እየተሰጠ ይገኛል። ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ግን ”የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ” እንዲሉ ሰብአዊ እርዳታው የመላውን ሕዝባችንን ተሳትፎና ርብርብ ይጠይቃል፡፡

የሰብአዊ እርዳታ ለአደጋ ወይም ለችግር ጊዜ የሚሰጥ በጎ ምላሽ ከመሆኑ አንጻር፣ አሁን ላይ በችግር ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን ሕይወት ለመታደግ ፣ እንደ አንድ ለብሔራዊ ክብሩ ከፍ ያለ ዋጋ እንደሚሰጥ ሕዝብ ብሔራዊ ንቅናቄ መፍጠር ይኖርብናል።

በኢትዮጵያዊ የመረዳዳትና የማካፈል ባህል ያለው ለሌለው ማካፈል ይኖርበታል፡፡ እርዳታውን በማፋጠን የወገኖቻችንን መከራ በማቃለል እና ለተቸገሩት ተስፋ በማምጣት ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወትም ይጠበቅብናል።

ከዓመታት በፊት የሰሜኑ የሀገራችን ጦርነትን ተከትሎ ኢትዮጵያ ላይ የተጋረጠውን አደጋ ለመቀልበስ መላው የሀገሪቱ ሕዝብ ርብርብ ማድረጉ አይዘነጋም። በወቅቱ ክልሎች፤ ባለሀብቶች፤ድርጅቶች፤ እና እያንዳንዱ ዜጋ የአቅሙን ያህል እያዋጣ ሕግ የማስከበር ተልእኮውን ደግፏል፡፡

አሁን ሌላ ርብርብና ድጋፍ የሚያሻ የወገናችን ችግር ከፊታችን አግጥጦ ቆሟል ።ችግሩን በስኬት ለመሻገር ለዚህም ከዚህ በፊት እንደታየው የመላው ሕዝባችን ርብርብና ትብብር ወሳኝ ነው፡፡

ከምግብ አቅርቦት በተጨማሪ ከችግሩ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የጤና ችግሮችን ጎን ለጎን በልዩነትም ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ማለትም ለጉዳት የተጋለጡ ሕፃናት፤ ለጉዳት ተጋላጭ ለሆኑ ሴቶችና አረጋውያን፤ ነፍሰጡር እናቶች ፤ አካል ጉዳተኞች እና ከባድ የጤና ችግር ያለባቸው፤ ልዩ የሕግ ጥበቃና ከለላ የሚያስፈልጋቸው ወገኖች በልዩነት ድጋፍ ሊደረግላቸውም ይገባል፡፡

ሰብአዊም፤ ቁሳዊም እርዳታ መስጠት ፤ እንደ ምግብ፣ መጠለያ እና ህክምና የመሳሰሉ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከማቅረብ በተጨማሪ የትምህርት፣ የኑሮ ድጋፍ እና የስነ-ልቦና አገልግሎቶችን መስጠት ያካትታል።

ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ እርዳታን በሰብአዊነት ለተቸገሩ ወገኖች የማድረስ ሂደት የረጅም ጊዜ እና የቆየ የመረዳዳት ባህላችንን በተለያዩ ጊዜያት በግልጽ የታየ ነው። በዚህም በባለፈው የኮቪድ ወረርሽኝ ጊዜ በመንግሥትና በግለሰቦች ሲደረግ የቆየው የመረዳዳት ባህላችን አሁንም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ድርቅና የምግብ እጥረት ሊደገም የሚገባው ተግባር ነው።

አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታን የማድረግና ያለማድረግ ጉዳይ ባለ ድርሻ አካላቱ እከሌ ከእከሌ ሳይባል የሁላችንም ነው። ለተከሰተው ችግር ምላሽ መስጠት የአንድ ወገን ተግባርና ኃላፊነት ሳይሆን የሁላችንም ነው። “ለወገን ደራሽ ወገን ነው፡፡ የሚለውን የኖረ አባባል በተግባር ማሳየት ያለብን እኛው ነን። በመሆኑም ሁላችንም የሰብአዊ ድጋፍና እርዳታው ተግባር ልንደግፍ ይገባል!!

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You