ለወደብ ጥያቄያችን ትክክለኛ አረዳድ ለመፍጠር!

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያሳዩት፤ ከ1983 ዓ.ም በፊት ኢትዮጵያ የባህር በር የነበራት ሀገር ናት። ይሁን እንጂ በጊዜ ሂደት ፖለቲካዊ ምክንያቶች በወለዷቸው ውስብስብ ችግርች የወደብ ባለቤትነቷን ተነጥቃ የሌሎች ሀገራትን ወደቦች ተጠቃሚ ለመሆን ተገዳለች፡፡ በዚህም የኢኮኖሚ እድገቷ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል። በዚህም ሀገሪቱ ለወደብ አገልግሎት ከ300 እስከ 500 መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ለማድረግ እየተገደደች ነው ፡፡

ወደብ አልባነት የአንድ ሀገር ልማትና እድገት እንቅፋት ነው፡፡ የባህር በር ያለው ሀገር ከሌለው፣ ዓመታዊ እድገቱ ላይ ቢያንስ 25 በመቶ ተጨማሪ እድገት እንደሚኖረው ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህ ማለት አንድ ሀገር 10 በመቶ ዓመታዊ እድገት ቢያስመዘግብ የባህር በር ያለው ከሆነ የባህር በር ከሌለው ከ3 ከመቶ በላይ ተጨማሪ እድገት ይኖረዋል፡፡

ሀገራችን ከ120 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ይዛ የባህር በር ባለቤት አለመሆኗ ከኢኮኖሚያዊ ተጎጅነቷ ባለፈ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት፤ ፖለቲካዊ አንድምታ ትልቅ አቅም ሊፈጥርለት እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ ይህም በራሱ ካላት ጂኦ – ፖለቲካዊ አቀማመጥ አንጻር ብሄራዊ ጥቅሞቹዋን በተሻለ መንገድ ለማስጠበቅ ይረዳት እንደነበር ይናገራሉ።

ትናንት አክሱምን ፈልፍላ ሮሃን ያነፀች ሀገር፤ መርከብ አበጅታ ቀይ ባህርን የቀዘፈች ዛሬ የባህር በር ከሌላቸው 17 የአፍሪካ ሀገራት አንዷ ለመሆን ተገዳለች፡፡ አንዳች መፍትሄ ካላገኘች በቀጣይ አስርት ዓመታት የህዝብ ብዛቷ 150 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ የምትገመተው ኢትዮጵያ ይህን ያህል ህዝብ ካላቸው የዓለም ሀገራት ብቸኛዋ ወደብ አልባ ሀገር ሆና መቀጠሏዋ የማይቀር ነው።

በርግጥ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ሕግና ከታሪክና ከሞራል አንጻር የባህር በር የማግኘት መብት አላት ። ይህ መብቷ በሰላማዊ መንገድ አካባቢው ካሉ የወደብ ባለቤት ከሆኑ ሀገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መንገድ ተጨባጭ ለማድረግ የጀመረችው የእንነጋገር ጥረት በብዙዎች ዘንድ ይበል የሚባል ሆኖ ተገኝቷል። የአካባቢው ሀገራትን በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ውህደትን ለማፋጠንም በራሱ አንድ አቅም እንደሚሆን እየተነገረም ነው።

ይህንን የአካባቢው ሀገራትና ህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት ያደረገ የእንነጋገር ጥሪ በማጣመም እና ጉዳዩን ባልተገባ መንገድ በመተርጎም በሀገራት መካከል አለመተማመን እንዲሰፍን የሚንቀሳቀሱ ሀይላት አሁንም እውነታውን ባልተገባ መንገድ /በአፍራሽ መንገድ በእጃቸው ባሉ በመገናኛ ብዙኃኖች ማራገባቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡

እነህ አካላት በቀጣናው ለሚገኙ ህዝቦች ብሩህ ነገዎች በጎ እይታ የሌላቸው መሆናቸውን በተደጋጋሚ በሚሰሩት ዘገባዎቻቸው አስመስክረዋል፡፡ የኢትዮጵያን የባህር በር ይገባኛል ጥያቄ ማንሳት ጦርነት ፍለጋ አድርገው በማናፈስ፣ ከአውዱ ውጪ የሆነ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት፤ ለሀገሪቱ እድገት በጎ አስተሳሰብ የሌላቸው አካላት /ሀገራት ጭምር ሴራ አስፈፃሚዎች በመሆን እየተንቀሳቀሱ ነው ፡፡

ኢትዮጵያ ጦሯን ለጦርነት እያሰናዳች ነው፣ በሀገሪቱ ያልተገባ ጉዳይ ጎረቤት ሀገራት ቁጣቸውን እየገለጡ ነው ..ወዘተ የሚሉና ሌሎች የተዛቡ መረጃዎችን በመልቀቅ የቀጣናውን ሀገራት ሰላም ለማናጋት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የጀመረችው ልማት ለጎረቤት ሀገራት ይዞት የመጣውን ትሩፋት ዓይናቸውን ገልጠው እንዲያዩ የጽልመት መጋረጃዎችን በመስፋት ላይ ናቸው።

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት እጣ ፈንታቸውን በጋራ ሊወስኑ የሚችሉባቸውን እድሎችን፤ባልተገባ መንገድ በመተርጎም ሀገራቱ ከነበሩባቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ወጥተው ለህዝቦቻቸው ዘላቂ እና ሁለንተናዊ እድገት ሊሰሩ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች የአደጋ ምንጭ አድርጎ በማቅረብ በመካከላቸው አለመተማመን እንዲሰፍን እንቅልፍ እንዳጡ ነው፡፡

የኢትዮጵያ በባህር ጥያቄዋ ዙሪያ እንነጋገር የሚለው ሀሳቧ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተና የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን የንግድ ትብብር የሚያጠናክር ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ፣ለቀጣናው ህዝቦች ብሩህ ነገዎች ተስፋ ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ይህን ግልጽ የሆነ እውነታ የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ አስመስሎ ማቅረብ ከጀርባው ሌላ የሴራ ጥንስስ ለመኖሩ አመላካች ነው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ጦርነትን የሚያራግቡ ዘገባዎች ተሰራጭተው መመልከት የሆነ አካል ቀጣናውን ወደ አለመረጋጋት እንዲያመራ ቀን ከሌሊት እየሰራ እንደሆነ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። በተለይም በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለውን ለውጥና ለውጡ እያመጣ ያለው ስኬት ያሳሰባቸው ኃይሎች ሴራ አካል እንደሚሆን ለመገመት የሚከብድ አይሆንም።

የወደብ /የባህር በር ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት የህልውና ጉዳይ እየሆነ እንደሚሄድ ለማንም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በአግባቡ መገንዘብ ለሚችል ባለ አእምሮ የተሰወረ አይደለም። ጉዳዩ በዚህ ሰዓት መነሳቱም ፀብ አጫሪ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ መንግሥትም የጉዳዩን አሳሳቢነት ለአካባቢው ሀገራት ወንድም ህዝቦች ለማሳየት መሞከሩ ጠብ አጫሪ የሚያሰኘው አይደለም። ይህን ማድረግ እንደ መንግሥት የሚጠበቅበት ነው።

ጉዳዩን ሲያነሳው በጉልበት/በኃይል እፈጽመዋለሁ አላለም፡፡ ለጦርነት ነጋሪት አስጎሽሞ ተነስ፣ ታጠቅ አላለም። እንነጋገር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መንገድ ጉዳዩን እንመልከተው ነው ያለው፡፡ ይህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት መንገድ ነው። ሊበረታታ እና እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው።

የኢትዮጵያን የባህር በር መሻት “ቀጣናውን ወደ ጦርነት የሚወስድ ነው” የሚሉ ዘገባዎች በሰላም እና በመግባባት የተፈታውን የኢትዮጵያና የጎረቤት ሀገራት ግንኙነት ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ለመውሰድ መፈለጋቸውን ሁነኛ አመላካች ነው። ይሁን እንጂ ጉዳዩን ከምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ጋር ብንመለከተው የምሥራቅ አፍሪካ ማቅ ሳይሆን ወርቅ የሚያለብስ ስለመሆኑ ቅንጣት ያህል አጠራጣሪ አይደለም፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ አንዳንዶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት በበጎ እየተመለከቱት አይደለም። አስርና ሃያ ዓመታትን ተሻግረው የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት እድገትን ከቀጣናው ጋር አስተሳስረው ለመመልከት ፍቃደኛም አይደሉም። እርግጥ ነው በአካባቢው ሀገራት ትናንት ላይ የነበሩ የታሪክ ስብራቶች አሁን ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ የትብብር ሃሳቦች ላይ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ ፡፡ ይህ ግን በራሱ አሁን ላይ /ዛሬ ላይ የሚቀርቡ የትብብር ጥያቄዎችን ሊያዳፍኑ አይችሉም፡፡

የህዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የምትገኘው ኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግዷን በማሳለጥ የጀመረችውን ድህነትን ታሪክ የማድረግ የታሪክ ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ የባህር በር ጉዳይ ወሳኝ ነው። ለዚህም በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ያነሳችው ጥያቄ ወቅቱን የጠበቀና ተገቢ ነው። የመንግሥት የፖለቲካ ጥያቄ ሳይሆን የመላ ህዝቦቿም የህልውና ጥያቄ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የባህር ህግ አንቀፅ 69 ንዑስ 1 እስከ 5 የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በአካባቢያቸው ካለው ባህር የተፈጥሮ ሀብት እኩል የመጠቀም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ይህ የህግ ድንጋጌ ሀገሪቱ እያቀረበች ያለውን ጥያቄ ህጋዊ መሰረት የሚያላብስ ነው። በዓለም አቀፍ መድረክ ሳይቀር ይሁንታ እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው።

ይህንን ከህግ፣ ከታሪክና ከሞራል አኳያ ተገቢ የሆነን የሀገር ጥያቄ፣ የመንግሥት የጦርነት መሻት ማሳያ አድርገው በማቅረብ የተጠመዱ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሆኑ በተለያዩ ምክንያቶች ከመንግሥት ጋር ባለመግባባት ውስጥ ያሉ አካላት ዘገባዎቻቸው የቱን ያህል ሚዛን የሳቱና የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥት ፍላጎት የማይወክሉ ስለመሆናቸው ቆመው በአግባቡ ሊያስቡ ይገባል ።

ይህን መሰል የሀገራችንንና ህዝባችን ፍላጎት የሚያዛባ ትርክት፣ የኢትዮጵያን ህዝብና መንግሥት የማይወክል፤ ከዛ ይልቅ ፍላጎታቸውን በማዛባት፣ ያልተገባ ትርጓሜ እንዲያገኝ የሚያደርግ የጥፋት መንገድ ነው። ይህን ለመከላከል በተለይም የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በስፋት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ትክክለኛውን እውነታ በተለያዩ ቋንቋዎች በማሰራጨት ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ተገቢና ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ መስራት፤ ለዚህ የሚሆን ዝግጁነትም መፍጠር ይኖርባቸዋል።

መንግሥትም ቢሆን አሁን እያደረገ ያለው እንዳለ ሆኖ ያሉ የዲፕሎማሲ አማራጮችን በመጠቀም እውነታው ትክክለኛ መልኩን/ቀለሙን ይዞ እንዲሄድ ማድረግ፤በጉዳዩ ዙሪያ ያሉ ዓለም አቀፍ አረዳዶች የተዛቡ እንዳይሆኑ በስፋት ሊንቀሳቀስ ይገባል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም በተለይም በውጪ ያለው የዲያስፖራ ማህበረሰብ ራሱን ከተዛቡ መረጃዎች በማቀብ እና የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ለሀገሩና ለመላው ህዝብ ተጠቃሚነት ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ለሀገሩ ዘብ መሆን ይጠበቅበታል።

ከዚህም ባለፈ በጉዳዩ ዙሪያ የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ግልፅና መግባባት ላይ የሚደረስባቸው እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰፊ ሥራ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ምሁራን እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጉዳዩ ዙሪያ ጥናቶችንና የፓናል ውይይቶችን በማዘጋጀት ጉዳዩ የበለጠ ግልጽ እንዲሆን በስፋት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። እነዚህን ማድረግ ከቻልን በእርግጠኝነት ጉዳዩን ከጥፋት አሉባልታ መታደግ እንችላለን።

በታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You