ጥናት ወይስ አስተያየት…!?

በሀገራችን በጣት ከሚቆጠሩ ተጽዕኖ ፈጣሪ አንጋፋ የሙያ ማህበራት ወይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ግንባር ቀደም ተቋም ነው። ሀገራዊ ፋያዳ ያላቸውን በርካታ ጥናትና ምርምሮችን አካሂዷል። የፖሊሲ ሃሳብ አቅርቧል። ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል። የሙሉ ጊዜ ተመራማሪዎች ያሉት፤ የራሱ የሆነ ሕንጻ መገንባት የቻለ ተቋም ነው። የተቋም ሾተላይ በሆነች ሀገር ከአስርት ዓመታት በላይ መዝለቅ በራሱ ስኬት ሆኖ ሊወሰድም ይችላል። ማህበሩ በቅርብ ይፋ ካደረጋቸው ጥናቶች አንዱ በዋጋ ግሽበት ላይ የሠራው ይገኝበታል። ይህ ጥናት በመጽሐፍ ታትሞ ወጥቷል። ሰሞኑን ደግሞ ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ስለሚኖረው አንድምታ ያደረገውን ጥናት ይፋ ማድረጉን በአማርኛው “ሪፖርተር” ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ተመለከትሁ። በጥናቱ ሥነ ዘዴና ግኝት ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ወደድሁ።

ባለፈው ዓመት መጠናቀቂያ ነሐሴ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ብሪክስን በይፋ መቀላቀሏ ከተነገረ ጀምሮ ከ330 በላይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የተሳተፉበትና ኢትዮጵያ መቀላቀሏ ስላለው ጥቅምና ጉዳት የተደረገውን ጥናት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር ታኅሳስ 11 ቀን 2016 ዓም ይፋ አደረገ፡ ፡ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ህንድ፣ ቻይናና ደቡብ አፍሪካ የመሠረቱትን ብሪክስ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ላይ በይፋ የተቀላቀሉት ኢትዮጵያ፣ ግብፅ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ማኅበሩ “ኢትዮጵያ ብሪክስን በመቀላቀሏ ምን ትጠቀማለች? ምንስ ትጎዳለች?” የሚለውን ለመለየት ጥናት ማካሄዱን፣ በማኅበሩ የጥናትና ፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ በሠራው የባለሙያዎች ዳሰሳ ጥናት (Expert Survey)፣ ብሪክስን ወይም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትን ለማሳተፍ የሚያስችል ሁኔታ ስለመኖሩ ግምገማ መደረጉን፤ በተጨማሪም ማኅበሩ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዓላማዎቹን ማሳካት አለማሳካቱን በሚመለከት ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን በመጠቀም መገምገሙን፤ ብሪክስ ሰባት ዓላማዎች ያሉት ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ (New Development Bank) ያቋቋመ ሲሆን፣ ዓላማዎቹን የሚያሳካ ከሆነ፣ “ኢትዮጵያ ማሳካት ትችላለች ወይ?” የሚልና ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ አባል መሆኗ (መቀላቀሏ) ሲታወቅ የሚወሰድባት ርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ እንዲሁም ሌሎችንም መለኪያዎች ተጠቅሞ፣ ማኅበሩ ጥናቱን ማካሄዱን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

ይሁንና የዳሰሳ ጥናቱ የተለያየ ሙያ ያላቸው ማለትም ከኢኮኖሚክስ በተጨማሪ የዓለምአቀፍ ግንኙነት፣ የሕግ፣ የታሪክና የሌላ ተዛማች ባለሙያዎች ብሪክስን ያዩበትና የተረዱበት፣ እንዲሁም ያላቸው አመለካከት ቢገለጽበት፤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ማለትም የመንግሥት ሰዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንንና ሕዝብ ቢካተቱበት ኖሮ ስለብሪክስ ያለ አተያይን ይበልጥ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የሚታመን ጥናት ማውጣት ይቻል ነበር። ጥናቱ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎችን ብቻ ማካተቱ ምልኡ እንዳይሆን አድርጎታል ብየ አምናለሁ።

ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከብሔራዊ ጠቅላላ ምርት አኳያ (GDP Per Capita) ባደጉና በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች መካከል ያለው ልዩነት እየጠበበ ነው? ወይስ እየሰፋ ነው?፣ ወደ ውጭ የሚልኩት የንግድ ምጣኔያቸው (FDI) በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት መሻሻል አምጥቷል? የሚሉትን ዓለም አቀፍ መለኪያዎችን በመጠቀም በተደረገው ጥናት፣ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ሥርዓት የገንዘብ ተቋማትን ሪፎርም እንደሚያደርግ ማስታወቁን ጥናቱ ጠቁሞ፣ ነገር ግን የፋይናንስ ጥያቄ በታዳጊ ሀገሮች ቢቀርብም፣ እንደ አሜሪካ የመሳሰሉ ሀገሮች ድጋፍ ካላገኙ በስተቀር ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንደማይኖረው ጠቁሟል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በዓለም ባንክም ሆነ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ከፍተኛ ድምፅ (Voting Power) ያላቸው ሀገሮችን ይሁንታ ስለሚያስፈልግ መሆኑን ማኅበሩ በጥናቱ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

በእርግጥ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥናት ያስፈልግ ነበር? ወይስ በቀላሉ በደቂቃ ውስጥ በበይነ መረብ አስሶ ማወቅ? በበለጸጉ ሀገራትና በድሃ ሀገራት መካከል ልዩነት እያደገ መምጣት፤ የዓለም ባንክንም ሆነ ዓለምአቀፉን የገንዘብ ተቋም አሜሪካ መር ሥርዓቱ ርዕዮተ አለሙንና ፍላጎቱን በሀገራት ለመጫን የሚጠቀምባቸው ተቋማት መሆናቸው ዓለም ያወቀው፣ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ሆኖ ሳለ ለዚህ ጥናት ገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት መባከን ነበረበት ስል እጠይቃለሁ። ጥናቱ ፓፓው ካቶሊክ ናቸው? ብሎ ከመጠየቅ ጋር ተመሳስሎብኛል። ከዚህ ይልቅ ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች መቅደም አልነበረባቸውም። የጥናቱ ሥነ ዘዴስ የባለሙያዎች የዳሰሰ ጥናት ነበር መሆን ያለበት ስል እሞግታለሁ። ምክንያቱም ሙሉ ስዕሉን ማሳየት አይችልም።

የዳሰሳ ጥናቱ ግኝት ተደርጎ ከቀረበው መካከል፤ 37 በመቶ የሚሆነውን ካፒታል ስቶክ የተቆጣጠሩት አምስት ሀገሮች፣ 52 በመቶውን አሥር ሀገሮችና 70 በመቶውን 20 ሀገሮች ድምፅ ያላቸው ሲሆን፣ 162 ሀገሮች ያላቸው ድምፅ 30 በመቶ ብቻ መሆኑን ያትታል። ይሄን ለመውቅስ ጥናት ያስፈልግ ነበር። በተለያዩ የበይነ መረብ የመረጃ ቋት በቀላሉ ማግኘት እየተቻለ። በማስከተልም እነዚህ 30 በመቶ ድምፅ ያላቸው ሀገሮች ለእያንዳንዳቸው ቢካፈል ያላቸው ድምፅ ከአንድ በመቶ በታች ከመሆኑ አንፃር፣ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ የሚለው፣ ዓላማ የተዘነጋና ምንም ዓይነት መሻሻል ያልታየበት መሆኑ በጥናቱ ተመልክቷል።

የ2ኛው የዓለም ጦርነት አሸናፊ ኃይላት የዓለም ባንክንም ሆነ ዓለምአቀፉን የገንዘብ ተቋም ያቋቋሟቸው ጥቅማቸውን ለማስከበር እንጂ መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ አለመሆኑ እየታወቀ ጥናቱ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጣ። ከፍተኛ ገቢ ባላቸውና በድሀ ሀገራት መካከል ያለው ልዩነት ትናንትም ዛሬም ነገም የሚቀጥል መሆኑ እየታወቀ ሌላው ይቅርና የአፍሪካ ጥቅል አህጉራዊ ምርት ከጀርመን ያነሰ መሆኑን ለማወቅ በደቂቃዎች በበይነ መረብ ጎልጉሎ ማወቅ እየተቻለ አንጋፋው ማህበር ይሄን ያህል መድከም ለምን አስፈለገው። በጋዜጠኝነት በተሳሳተ ትንተናና ትርጉም ጊዜህንና ጉልበትህን ስታባክን ኤዲተርህ የእንግሊእኛውን ፈሊጣዊ አነጋገር ማለትም “Barking up the wrong tree” ተጠቅሞ በከንቱ ማሰንህ። ደከምህ ሊልህ ይችላል። ይህ ጥናትም ከታላቅ ይቅርታ ጋር በከንቱ የተደከመበት ላብ የፈሰሰበት ነው የሆነብኝ።

ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው ለምንድነው? የሚለውን ጥያቄ 233 የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ተጠይቀው፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማዕቀብ ጫና ስለበዛባት መሆኑን 49 በመቶ የሚሆኑ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲገልጹ፣47 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አዲስ የኢኮኖሚ ተቋም በመሆኑ እንደሆነ መግለጻቸው ተጠቅሷል፡፡ 41 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የተቀላቀለችው የውጭ ግንኙነቷ በጣም እየወረደ (እየወደቀ) ስለመጣ በመሆኑ እንደሆነ ሲገልጹ፣ 46 በመቶ የሚሆኑት ባለችበት የጂኦግራፊ አቀማመጥ ምክንያት መሆኑን እንደተናገሩ ደግዬ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ 41 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ የውጭ ጣልቃ ገብነት ስለበዛባት መሆኑን እንደገለጹና በአጠቃላይ 11 የሚደርሱ ምክያቶችን መስጠታቸውን አክለዋል፡፡

እነዚህ አስተያየት ሰጪ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ሙያ እያላቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ እንዴት እንዲህ አራንባና ቆቦ ወይም የተራራቀና የተለያየ መልስ ሊሰጡ ቻሉ። አሁንም የምለው እነዚህን አስተያየቶች ለመስጠት የግድ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ መሆን ይጠይቃል ወይ? ከሆነስ ባለሙያነታቸው ምኑ ላይ ነው የተገለጠው። አዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ወጥተን የሕዝብ አስተያየት ብንጠይቅ ከእነዚህን የተለዩ የአቦሰጥና የአፈተት መልሶችን እናጣለን ወይ የሚል ጥያቄ ያጭርብኛል።

የዚህ ጥናት ሌላው ውስንነት የብሪክስን ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ብቻ አድርጎ ማየቱ ነው። ብሪክስ ከኢኮኖሚ ይልቅ ጂኦፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። የድህረ 2ኛውን የዓለም ጦርነት አዲስ የዓለም አሰላላፍ the new world order የመገዳደር ውሳኔ መሆኑን ልብ ይሏል። በዚህ ጥናት 61 በመቶ የሚሆኑት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ዶላርን ማስወገድ እንደሚቻል፤ 23 በመቶ የሚሆኑት ባለሙያዎች ለማስወገድ አምስት ዓመታትን እንደሚወስድ፣ 53 በመቶ የሚሆኑት ግን አሥር ዓመታት፣ 67 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ 15 ዓመታትን እንደሚወስድና ከዚያም በላይ ዕድሜ እንደሚፈልግ 18 በመቶ የሚሆኑት መግለጻቸውን ደግዬ (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

ሲጀመር የዓለምን ኢኮኖሚ እንዳሻው ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ዶላር እንዲህ በቀላሉ የሚወገድ ምንዛሬ ነውን፤ መልሱን ለባለሙያዎች ልተወው። መልሳቸው አዎ ከሆነ እንዴት የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት እገደዳለሁ። በጥናቱ ሌሎች ግኝቶች ላይ ተመሳሳይ ሙግቶችን ማንሳት ቢቻልም በዚህ ልለፈውና የጥናቱን ምክረ ሀሳብ ላጋራ።ከዚህ በፊት ግን በጥናቱ ላይ ደርዘን ጥያቄዎች እየተነሱበትና የጥናቱ ሥነ ዘዴም በራሱ የሚያከራክር ሆኖ ሳለ ምክረ ሃሳቡስ እንዴት ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው ሊሆን ይችላል የሚለውን ያዙልኝ።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማህበር በሰጠው ምክረ ሃሳብ፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ መናገር የቻሉት፣ ኢትዮጵያ ብሪክስን የተቀላቀለችው መንግሥት እንደሚለው በሜሪት ወይም ተመራጭ ስለሆነች ሳይሆን ባጋጠማት የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ችግር መሆኑን፤ ብሪክስ ግን ለምን እንደተቀበላት ማንም የሚያውቅ እንደሌለ፣ መስፈርታቸው ህቡዕ መሆኑን፤ ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዓላማ ስላልተሳካ፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ ሥርዓቶችን መፍጠር አስፈላጊ ቢሆንም ጠቃሚነቱን በደንብ ተገምግሞ፣ የኢትዮጵያ መቀላቀልም ከጥቅሙና ከጉዳቱ አንፃር ተጠንቶ መረጋገጥ እንዳለበት፤ ለምሳሌ ያህል ማሌዥያ አመልክታ የነበረ ቢሆንም፣ የሀገሯ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጥናት አድርገውና ገምግመው ባገኙት ውጤት ‹‹መቀላቀሏ ጥቅም የለውም›› በማለታቸው፣ ሳትቀላቀል መቅረቷን በመጠቆም፣ ኢትዮጵያም ያንን ማድረግ እንዳለባት ምክረ ሃሳቡ ያትታል፡፡

ምርመራው (ግምገማው) ከአባል ሀገሮች ጋር ተነፃፃሪ መሆን ስላለበት፣ ልዩነቱና አንድነቱን መርምሮ፣ የጋራ አጀንዳ ተገምግሞ መሆን እንዳለበት፤ ፈርጀ ብዙ አደጋ ስላለው ኢትዮጵያ እስካሁን ከምዕራቡ ዓለም የምታገኘውን ጥቅም የሚያካክስ ጥቅም መገኘት አለመገኘቱ መረጋገጥ እንዳለበትም፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር የገባቻቸው ብዙ ስምምነቶች (Engagements) ስላሉ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከብሪክስ ጋር መሥራት የሚያስችላት አለመሆኑን፤ ዋናው የብሪክስ ዓላማና ኢትዮጵያም የተቀላቀለችበት ምክንያት በሀገር ውስጥ ገንዘብ ለመጠቀምና የዶላርን የበላይነት ለመጣል በመሆኑ፣ ይህንን ለማድረግ አዳዲስ አጋር የማግኘት ተግዳሮት ሊገጥማት እንደሚችል ያመላክታል።

ከብሪክስ ጋር በብር መሥራት ከተቻለ፣ ከምዕራባውያን ጋር መሥራት ስለማይቻል ከሁለቱም ተቋማት ጋር መሥራት ግድ ስለሚል፣ በሁለቱም አባል ሀገሮች ተቀባይነትን ማግኘት ግድ ይላል፤ እንደ ህንድ ሩፒ፣ እንደ ቻይና የንና እንደ ሩሲያ ሩብል የኢትዮጵያ ብር ተቀባይነት ያገኝ ይሆን? በሚል የሚጠይቁት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ፣ ይህ ሁሉ መፈተሽ ስላለበት ጥልቅ ግምገማና ጥናት አስፈላጊ መሆኑን ምክረ ሃሳቡ ይዘክራል።

እንደ መውጫ

ጥናቱ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ባህሪያትን፣ ጅኦፖለቲካን፣ ማህበራዊ ባህሪያትን ቢያካትት ኖሮ በተለይ የብሪክስ አባል ሀገራትን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ልማት፣ ጥቅል ሀገራዊ ምርት፤ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባላት ጋር ያላት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት፤ ጂኦፖለቲካዊ አንድምታዎች ማለትም ብሪክስ ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ጋር የሚኖረውን ጂኦፖለቲካዊ አንድምታ፣ ተጽዕኖ፣ ቀጣናዊ መረጋጋትንና ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶችን መገምገም፤ የብሪክስ አባል ሀገራት የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ ያላቸው ቁርጠኝነት፤ ሀገራችን ከአባላቱ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት፤ ወዘተረፈ በጥናቱ ቢዳሰሱ ኖሮ ጥናቱ ሙሉ ስዕልን የማሳየት ጉልበት ይኖረው ነበር። ማህበሩ ከዚህ አንጻር ጥናቱን መለስ ብሎ ይፈትሸዋል የሚል እምነት አለኝ።

ሻሎም !

አሜን።

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You