የማንነት መሠረትን የማወቅና የማሳወቅ ሀገራዊ ጥሪ

በኢትዮጵያ በርካታ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት የሚከበሩባት ሀገር ነች። ከዓውደ ትዕይንቶች ባሻገር የሀገሪቱ ሕዝቦችን ቀደምት ሥልጣኔ የሚያሳዩ፣ የታሪክ መሠረትን የሚያንፀባርቁ ሀብቶች በስፋት ይገኙበታል። ሀገሪቱ በተፈጥሮ፣ በባህል፣ በሥነ-ፅሁፍና የጥበብ ውጤቶች፣ በቅርስ፣ በአርኪዮሎጂ ታድላለች። የብዝሀ የቱሪዝም መስህብ መገኛ ሀገርም እንደሆነች የሚያሳዩ አያሌ መረጃዎች አሉ። ሶስት ሺህ ዘመናትን የተሻገረ ታሪክና የመስህብ ሀብት ዛሬም ህያው በሆኑ ማስረጃዎች ቁልጭ ብለው ይታያል።

ይህን ሀብት ወደ ቱሪዝም መስህብነት መቀየር እና ከዚያም ተጠቃሚ ከመሆን አኳያ ገና ብዙ መሥራት ይኖርበታል። ሀገሪቱ ይህንን ሀብት ለዓለም ሕዝብ ከማስተዋወቋ አስቀድሞ ዜጎቿ በተለይም አዲሱ ትውልድ ይህን ሀብት በቅጡ እንዲያውቀውና የማንነቱን መሠረት እንዲገነዘበው ማድረግ ላይ መሥራት ይገባል።

‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ አበዳሪ አይቀበለውም›› እንደሚባለው ሀገርኛ ብሂል የማንነት መሠረት የሆነንን፣ ኢትዮጵያዊ ያሰኘንን የኩራታችን ምንጭ የሆነውን ታሪክ፣ ባህል፣ መልከዓ-ምድር እንዲሁም የመስህብ ሀብት ሁላችንም ጠንቅቀን ማወቅ ይጠበቅብናል። ይህ ሲሆን ነው አንገታችንን ቀና አድርገን፤ በድፍረትና በእውቀት ቀሪው ዓለምን ‹‹ተጋበዙልን ›› ማለት የምንችለው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ትኩረቱን በማድረግ እየሠራ ይገኛል። በተለይ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ እያበረታታ ነው። የባህል የታሪክና የተፈጥሮ መስህቦችን በማስተዋወቅና ዜጎች እነዚህን ሀብቶች እንዲጎበኙ፣ ጥብቅ ቁርኝት እንዲኖራቸው ግፊት እያደረገ ነው። ለዚህም በቱሪዝም ሚኒስቴር አማካኝነት ‹‹ልወቅሽ ኢትዮጵያ›› የሚል ንቅናቄ ቀርፆ ኢትዮጵያውያንና፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲያውቁ ቅስቀሳ እየተደረገ ይገኛል።

በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲገቡና ከባህልና ታሪካቸው ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ጥሪ በማድረግ ከዚህ ቀደም የነበረውን የተዳከመ የጉብኝትና የግንኙነት መስመር ለመስበር ጥረት እያደረገ ነው።

ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ሀገሮች የሚኖሩት ‹‹ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን›› ወደ ሀገራቸው እንዲመጡና ከታሪክ፣ ባህልና ማንነታቸው ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ጥሪ አቅርበዋል። የቱሪዝም ሚኒስቴርም ይህንን አስመልክቶ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ የተያዘውን መርሀ-ግብር አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥቷል።

በውጭ ሀገሮች ለሚኖረው ለእዚህ ሁለተኛው ትውልድ በተደረገው ጥሪ መሠረት የተቋቋመውን ብሔራዊ ምክር ቤት በሰብሳቢነት የሚመራው የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ‹‹ወደ ትውልድ ሥፍራችሁ ተመለሱ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጥሪ በሶስት ዙሮች የሚካሄድ ነው።

በዚህ መሠረትም የመጀመሪያው መርሀ ግብር ‹‹ከብዝኃ-ባህል መሠረትዎ ጋር ይገናኙ›› በሚል መሪ ሃሳብ ከታህሳስ 20 እስከ ጥር 30 ይካሄዳል። ይህ ወቅት ደግሞ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የገናና የጥምቀት በዓላት የሚከበሩበት መሆኑ ይታወቃል። በዓላቱ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ በልዩ ሁኔታ በድምቀት የሚከበሩ መሆኑ ለመርሃ-ግብሩ ተግባራዊነት ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል።

በሁለተኛው ዙር የሚካሄደው የትውልደ ኢትዮጵያውያን መርሀ ግብር ደግሞ ‹‹ታሪካዊ መሰረትዎን ይወቁ›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ይሆናል፤ ይህም መርሀ ግብር ከየካቲት 20 እስከ ሚያዝያ 30 ድረስ እንደሚካሄድ ሚኒስትሯ አመልክተው፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸው ተገኝተው የኢትዮጵያን ታሪክ በሚገባ የሚያውቁበት፣ ከማንነታቸው ጋር ትስስር የሚፈጥሩበት ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሶስተኛው ዙር ‹‹ዐሻራዎን ያኑሩ፣ የእረፍት ጊዜዎን ያጣጥሙ›› በሚል ከሰኔ 10 ቀን 2016 ዓ.ም እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ሚኒስትሯ አብራርተዋል። በሂደቱም በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው ትውልድ የዲያስፖራው የማህበረሰብ ክፍል የሀገሪቱን የመስህብ ሀብቶች በመጎብኘት፣ በመዝናኛ ሥፍራዎችና ሌሎች የእረፍት ቦታዎች ጊዜያቸውን በማሳለፍ ቆይታ እንደሚያደርጉበት አስታውቀዋል።

ሚኒስትሯ በውጭ ሀገሮች ለሚኖሩት ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሀገሪቱ ጥሪ የመደረጉ ምክንያት የሀገር ፍቅር ስሜታቸው እንዲዳብር እና ከሀገራቸው ጋር ያላቸው ትስስር እንዲጠናከር ለማስቻል መሆኑን አስታውቀዋል።

ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው ለሚመጡ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ትኬት ቅናሽ እንደሚደረግላቸውም ገልፀዋል። ሆቴሎች፣ አስጎብኚ ድርጅቶች የትራስፖርት አገልግሎት አቅራቢዎች ልዩ የዋጋ ቅናሽ አድርገው ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውን ነው የተናገሩት። በተለይ ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡበት ወቅት መጉላላትና አላስፈላጊ ጉዳዮች እንዳይገጥማቸው የተቀላጠፈ የጉምሩክና ኢሚግሬሽን አገልግሎቶች ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውንም ገልጸዋል።

‹‹በውጭ ሀገሮች የሚገኙት እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ጋር እንዲቀራረቡ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል›› የሚሉት አምባሳደሯ፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጥሪ ቀርቦላቸው ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንም አስታውሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተለያዩ ጊዜያት በውጭ ሀገራት ተገኝተው እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች በማግኘት እንዳወያዩና በዚህም የተነሳ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እና መነሳሳት ተፈጥሮ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሀገራቸው መምጣትና ትስስር መፍጠር ችለዋል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፤ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ማድረግ ተችሏል። ነገር ግን የትውልድ ቅብብሎሽ አስፈላጊ በመሆኑ ምክንያት ሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ላይ ትኩረት ማድረግ አስፈልጓል። በዚህም እነርሱ ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ መጋበዝና ከወላጆቻቸው ሀገር፣ ባህል ታሪክ ጋር ትውውቅና ጥብቅ ትስስር እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈልጓል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ በትውልድ መሃል ቅብብሎሽ እንዳይኖር እና ክፍተት እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል።

ይህ ሀገራዊ ጥሪ ዝርዝር ዓላማዎች ያሉት መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ በትውልድ መካከል ድልድይ መገንባት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን ነው ያመለከቱት። በትውልደ ኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ከኢትዮጵያ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ልዩ ልዩ እሴቶች ጋር እንዳይራራቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድም በተለያዩ ሀገራትም ተመሳሳይ ልምድ እንዳለም ጠቅሰው፣ በተለይ እንደ እስራኤልና ቻይና የመሳሰሉት ሀገራት መሰል ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ትውልዶች ከሀገራቸው ጋር ጥብቅ ትስስር እንዲኖራቸው መሥራታቸው ተጠቃሚ ያደረጋቸው መሆኑን አመልክተዋል።

ከዝርዝር ዓላማዎቹ መካከል አምባሳደሯ በሁለተኝነት ያስቀመጡት ሁለተኛው ትውልድ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ክፍሎች ሀገራቸውን ካወቁ በኋላ ለሌላው የዓለም ክፍል እንዲያስተዋውቁና የአምባሳደርነት ሚና እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ይህም የቱሪዝም ዘርፉ ለማስፋት ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ከልዩ ልዩ ዘርፎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን ከማስፋት አኳያ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ይህንን ጥሪ እየመራ የሚገኘው ለሀገር ውስጥም ሆነ ለቀሪው ዓለም ማስተዋወቅ የሚችላቸው በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች በመኖራቸው እንደሆነ የሚገልፁት አምባሳደሯ፤ ይህንን ኢትዮጵያውያን እራሳቸው እንዲያውቁት እንዲሁም ለሌሎች የዓለም ክፍሎች በአምባሳደርነት እንዲያስተዋውቁ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ይህ ጥረት በውጭ ያሉት ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን እነዚህን በርካታ የቱሪዝም ሀብቶች እንዲያውቁ በሀገራቸውም ኩራት ተሰምቷቸው እንዲያስተዋውቁና ለቱሪስት ፍሰቱ መጨመር አስተዋፆ እንዲያደርጉ ያስችላል ሲሉም አብራርተዋል።

‹‹እዚህ ያሉ ኢትዮጵያውያን የሁለተኛው ትውልድ የዲያስፖራ ወጣቶች ለነገ የሀገሪቱ እጣ ፈንታ ወሳኝ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል›› ያሉት አምባሳደር ናሲሴ፤ ምክንያቱን ሲያብራሩ ሀገር የምትገነባው በውስጥም በውጭም በሚኖሩ ዜጎቿ እንደሆነ ገልፀዋል። በመሆኑም እነዚህ ዜጎች የተለየ ስሜት እንዳይሰማቸውና የኢትዮጵያ አካል እንደሆኑ እንዲያውቁ በሀገር ውስጥ የሚኖሩ የሁሉም ዜጎች ሃላፊነት እንደሆነ አብራርተዋል። በመሆኑም ይህንን ሃላፊነት ኢትዮጵያውያን ተቀብለው ጥሪ የተደረገላቸውን የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያንን ተቀብለው እንዲያስተናግዱም ጥሪ አቅርበዋል።

እንደ መውጫ

አምባሳደር ናሲሴ ቀደም ሲልም በመግለጫቸው እንዳብራሩት ኢትዮጵያ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ይፋዊ ጥሪ ስታደርግ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከዚህ ቀደም የኮቪድ ወረርሽኝና ግጭት በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የፈጠረውን መፋዘዝ ለመቀልበስና ዘርፉን ለማነቃቃት እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ከሀገራቸው ጋር የጠበቀ ትስስር እንዲኖራቸው ለማስቻል በማለም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ ተደርጎ ነበር።

በዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከበሩ ዓመታዊ ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ባህላዊ ፌስቲቫሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ወቅቶችን ተጠቅመው ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲመጡ ተደርጎ ነበር ። በዚህም አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ገብተው በታቀደው መሠረት አጋርነታቸውን አሳይተዋል። በወቅቱም በርካታ ከዚህ ቀደም ወደማያውቋቸው የሀገሪቱ ክፍሎች ተጉዘው ባህልን፣ ታሪክን፣ ተፈጥሮን መመልከትና ስለሀገራቸው በቂ እውቀት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል። የእረፍት ጊዜያቸውንም በመዝናናትና ከወገኖቻቸው ጋር በመሆን አሳልፈዋል። ወደ መጡበት ሲመለሱም ለቀሪው ዓለም ኢትዮጵያን በአምባሳደርነት ወክለው አስተዋውቀዋል ።

በዚህ ሥራ ለብዙዎች የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር የተቀዛቀዘው ቱሪዝም ዳግም እንዲያንሰራራ ትልቅ ሥራ መሠራቱንም ነበራቸው። ለዚህም ነው የትውልድ ቅብብሎሹ እንዲቀጥልና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሩቅነት ስሜት እንዳይሰማቸው በቀጣይነት ይህንን ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት የሀገረ-መንግሥት ታሪክ፣ ውብ ባህልና ማንነት ያላቸው ብሔረሰቦች በጋራ ተዋደውና በአንድነት ተጋምደው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗ በገሃድ የሚታይ ሃቅ ነው። ይህንን በውጭ ተወልደው ያደጉ (የሁለተኛው ትውልድ) ኢትዮጵያውያን ማወቅ ይገባቸዋል። ሕዝቦቿ ለአይን ማራኪ፣ ጆሮ ገብና ተወዳጅ የሆኑ እሴቶች ባለቤት ፤ ባህልና ወጋቸው ለባዳው የሚያስቀና ለወዳጅ ሃሴትን የሚፈጥር መሆኑን በአካል መጥተው ማወቅና የዚያ እሴት ተጋሪ የመሆን መብትም አላቸው።

ኢትዮጵያውያን ጠላትን በአንድነት መክተው ድባቅ የሚመቱ ለሉዓላዊነታቸው መከበር በጋራ ዘብ የሚቆሙም መሆናቸውን እዚሁ ሀገራቸው ድረስ መጥተው ከዓድዋ ድል ታሪክና ከሌሎችም ታሪካዊ ሀብቶች መገንዘብ አለባቸው የሚል እምነት አለን። ሁሉም ዜጎች ኢትዮጵያዊነትን ሳይለቁና የመጡበትን ማህበረሰብ ባህልና ማንነት ሳይሸራርፉ አብረው የመኖር የሺህ ዓመታት ታሪክ ባለቤትም መሆናቸውንም ከፈረሱ አፍ መስማት ይገባቸዋል። እነርሱም የዚህ ታሪክ፣ ባህል ውብ ሀገር ባለቤት እንደሆኑ ለማወቅ ይህ ሀገራዊ ጥሪ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን የዝግጅት ክፍላችንም እምነት ነው።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You