ያልተጠቀምንበት ሀገር በቀል ዕውቀት

አንድ ማኅበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ ተፈጥሮን መሠረት አድርጎ የረጅም ዓመታት ልምዱን ታሳቢ በማድረግ የሚያካብተው እውቀት ‹‹ሀገር በቀል ዕውቀት›› ይባላል። ሀገር በቀል እውቀት እንድ ማኅበረሰብ ከተፈጥሮና ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር ባለው ቁርኝት የሚያገኘውን፣ የሚያዳብረውንና የእለት ተእለት ሕይወቱን ወይም መስተጋብሩን የሚያሳልጥበት እውቀት ነው፡፡

እውቀቱ ለብዙ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደመፍትሔ ሆኖ የሚያገለግል፤ አንድ ማኅበረሰብ በዘመናት ሂደት ውስጥ እንደ ማኅበረሰብ ያጋጠሙትን/የሚያጋጥሙትን ግለሰባዊም ሆነ ማኅበራዊ ተግዳሮቶችን ተሻግሮ አሁን ላይ እንዲገኝ ትልቅ አበርክቶ ያለው ነው።

ይህ እውቀት መገለጫው ብዙ ነው፤ ለምሳሌ ዛሬ ድረስ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት አርሶ አደሩ የሚያርሠው መሬት ላይ ምን መዝራት እንዳለበት፣ እንዴት እንደሚዘራ፣ የመሬቱን ለምነት ለመጠበቅ የሚያደርጋቸው ተግባራት፣ የአካባቢው የአየር ንብረት ሁኔታ ምን እንደሚመስል እና ምን መደረግ እንዳለበት የሚያውቀው ከትውልድ ትውልድ ሲወራረድ በመጣ ሀገር በቀል እውቀቱ ነው፡፡

ሀገር በቀል ዕውቀት በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል ጃፓን፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ታይላንድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት ያሏቸውን ሀገር በቀል እውቀቶች ወደ ዘመናዊ መንገድ በመቀየር እንዲሁም በቀላሉ ሌሎች ሊጠቀሙባቸው በሚቻልበት መንገድ በመለወጥ ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መትረፍ የቻሉም ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር በቀል ዕውቀት ጠቀሜታ ላይ ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ መሻሻሎች እየታዩ ይገኛሉ፡፡ ሀገር በቀል እውቀትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ያልነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ላይ ግን በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ውስጥ ተካቶ ተማሪዎች እንዲያውቁት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃም ትኩረት ተሰጥቶት ጥናት እና ምርምሮችን ከማድረግ ባሻገር መረጃዎችን አሰባስቦ ለመሰነድ ጅምር ሥራዎች መኖራቸው እየተነገረ ነው። ሁኔታው የዘገየ ቢሆንም ዓለም ለሀገር በቀል እውቀቶች ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ባለበት በዚህ ጊዜ እንደ ሀገር በጉዳዩ ዙሪያ ከተኛንበት ነቅተን መገኘታችን የሚበረታታ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህም ባለፈ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት በትምህርት ደረጃ ለሁሉም ማኅበረሰብ ተደራሽ እንዲሆን ዓላማ ያደረገው ‹‹የኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ማዕከል›› መመሥረቱ እንደ ጅምር የሚታይና ብዙ አስቦ መሥራትን የሚጠይቅ የቤት ሥራ ቢሆንም ይበል እና ይጠንክር የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡

በተለይም ሀገር በቀል የባሕል መድኃኒቶችን በዘመናዊ መልክ ቀይሮ በሳይንሳዊ መንገድ በመታገዝ ለብዙኃኑ እንዲዳረስ ከማድረግ አኳያ ያለው ክፍተት በእጅጉ ከፍ ያለና ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው። በችግሩ ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያስረዱት፤ አንድም ለመድኃኒት የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ ከመቆጠብ፤ ሌላም የሐክምናውን ዘርፍ በሚገባ ከመደገፍ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ነው ፡፡

ሀገር በቀል የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ እውቀቶች ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ አጥንተን በዘርፉ ለሚያጋጥሙ ችግሮቻችን የመፍትሔ አካል አለማድረጋችን ሌላው ችግራችን እንደሆነ የሚስማሙ ጥቂት አይደሉም። እነዚህን ዕውቀቶች መርምሮና አዳብሮ ዘመኑን በዋጀ መልኩ ከመጠቀም አኳያ በርካታ ክፍተቶች እንዳሉም ይስማማሉ፡፡

አዲሱ ትውልድ የውጪውን ዓለም ይናፍቃል፤ ለሌላ ሀገር ባሕሎች ተገዢ ሆኗል፤ ተብሎም ይታማል፡፡ ነገር ግን የራሱን ሀገር በቀል እውቀትና ጥበብ የሚያስተምረውና የሚያሸጋግርለት አንድ ወጥ ሥርዓት አለመዘርጋቱ ለእንዲህ አይነት አመለካከት ዳርጎት እንደሆነስ፡፡ ያ ባይሆን ለሌላ ሀገር ባሕል እጁን ለመስጠት አይገደድም፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የታሪክ ምሑሩ ፍቅሬ ቶሎሳ(ፕ/ር) በአንድ ወቅት፤ ‹‹ሀገር በቀል ዕውቀቶቻችንን ባለመጠቀማችን፣ ባለማሳደጋችን ብሎም ለትውልድ እንዲተላለፉ ባለማድረጋችን የውጭ ተፅዕኖ ውስጥ እንድንወድቅና ውስጣዊ ማንነታችን እንዲወሰድብን በር ከፍቷል›› ብለዋል፡፡

እንደ ሀገርም ይሁን እንደ ግለሰብ ብዙ ነገሮችን በሰነድ መልክ ማዘጋጀት (ሰንዶ) ማስቀመጥ ላይ ብዙ ክፍተቶች መኖራቸው አይካድም፡፡ ሀገር በቀል ዕውቀቶቻችንን ለመጪው ትውልድ ተደራሽ ለማድረግ በሚገባ ሰንዶ የማስቀመጡ ጉዳይ ከወሬ በዘለለ በተግባር ብዙ ርቀት አልተሄደበትም፡፡

ከሀገር በቀል ዕውቀቶቻንን መካከል ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶቻችን ሌላው ያልተጠቀምንባቸው ሀብቶቻችን ናቸው፡፡ በሀገራችን እንደየአካባቢው ባሕልና ወግ የተለያዩ ስኬታማ የግጭት አፈታት ባሕላዊ ሥርዓቶች አሉ። እነዚህን አቅሞች በመጠቀም እዚህም፤ እዚያም የሚታየውን ግጭት ለመፍታት በሚገባው ልክ ትኩረት ሰጥተን አልሠራንም፡፡

እዚህ ላይ መርሳት የሌለብን ጉዳይ፤ ‹‹ሀገር በቀል እውቀት ጥቅም ላይ ይዋል›› ሲባል የሌላ ሀገር ዕውቀት ወደ ሀገር ቤት አይግባ ማለታችን አይደለም። ከሌሎች የምናገኛቸው ጠቃሚ እውቀቶችንም በአግባቡ ከራሳችን እውቀት ጋር አጣጥመንና አቀናጅተን ብንጠቀምባቸው ችግሮቻችንን ልንፈታባቸው እንችላለን፡፡

ያለንበት ወቅት በሰኮንዶች ውስጥ ዓለምን ለማማተር የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉበት ከመሆኑ አንጻር ብዙ አማራጮችን ተጠቅመን መረጃዎችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ ይሁንና ከውጭ የሚገኙ እውቀቶችን እንደ ወረዱ ማኅበረሰቡ ላይ ለመጫን መሞከር ኪሳራ ሊኖረውም ይችላል። በጤና፣ በማኅበራዊ መስተጋብር፣ በትውልዶች የስብዕና ግንባታ ላይም የሚፈጥረው ተጽዕኖ ሊኖር እንደሚችል መገንዘብም ተገቢ ነው። ስለሆነም ወደ ሀገራችን የምናስገባቸው የዓለም ተሞክሮዎችና እውቀቶች ከማኅበረሰቡ ባሕል፣ ሃይማኖትና ሞራል ጋር እንዳይጋጩ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ቀደም ስለ ግብረገብ፣ እፅዋት ጥበቃና እንክብካቤ፣ ጥንታዊ ስዕሎች አሳሳል፣ ቀለማት አቀማመም፣ ወዘተ ትምህርቶችን በመስጠት ትውልዱ አባቶቹ ለዘመናት ያቆዩትን እውቀት እንዲወርስ ሲሠራ ነበር፡፡ እውቀቶቹ ለሀገሪቱ የቀደሙ እድገቶች መሠረትም ነበሩ፡፡ ዛሬም አስፈላጊው ትኩረት ከተሰጣቸው ለእድገትና ለሥልጣኔ የመኖራቸው አበርክቶ ቀላል አይሆንም፡፡

ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሀገር በመሆኗ የብዙ ባሕል፣ ቋንቋ እና እሴቶች ባለቤት መሆን ችላለች፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን በብዙ ባሕሎች ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ ባለመቻሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን እንዳታገኝ ሆናለች፡፡

ሀገር በቀል ዕውቀቶች ከመጠበቅ፤ ከማስተዋወቅ እና አግባብ ባለው መልኩ ከመጠቀም አንጻር የሚመለከታቸው አካላት በተለይም የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በባሕል ላይ የሚሠሩ ተቋማትና ምሑራን እንዲሁም መገናኛ ብዙኃን በትኩረት ሊሠሩ ይገባል፤ በኪነ ሕንፃ፣ በፍትሕ ሥርዓት፣ በፊደል ቀረፃ እና በሌሎች ተግባራት ቀዳሚ የነበረች ሀገር ዛሬ እዚህ መድረሷ ቁጭት ውስጥ ሊከተን ይገባል፡፡ ይህ ቁጭት በሚፈጥረው መነቃቃት ሀገራችንን ከፍ ለሚያደርጉ ሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል፤ ይህን ለማድረግ አልረፈደም፡፡

በምስጋና ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You