መንግሥት ለትግራይ ክልል የሰብዓዊ ርዳታ በበቂ መጠን እያቀረበ ነው

አዲስ አበባ፡- መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጥፎ አስፈላጊውን በጀት መድቦ የሰብዓዊ ዕርዳታን ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ብቻ ሳይሆን በበቂ መጠን ለትግራይ ክልል እያቀረበ እንደሚገኝ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትናንት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ከሰሞኑ በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅና ረሃብ ከ77 ጋር የሚስተካከል ቀውስ ሊፈጥር ወደሚችልበት ደረጃ እየተሸጋገረ ነው በሚል የተሰጠው መግለጫ ፈጽሞ የተሳሳተ ነው፡፡ አጋር አካላት የርዳታ አቅርቦት ቢያቆሙም መንግሥት

 ፕሮጀክቶቹን አጥፎ አስፈላጊውን በጀት መድቦ የሰብዓዊ ርዳታን ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ብቻ ሳይሆን በበቂ መጠን ለትግራይ ክልል እያቀረበ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

“የሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦትና ፖለቲካ መቀላቀል የለባቸውም” ያሉት ሚኒስትሩ፤ እንዲህ ያለ ቀውስ ሲኖር ማወጅ ያለበት የፌዴራል መንግሥቱ የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት መሆኑን እና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ ተገምግሞ የሚደርስበት እንጂ ፖለቲካና ሰብዓዊ ጉዳይን በማያያዝ የሚወሰን እንዳልሆነ ነው የገለጹት።

የአደጋ ስጋት አመራር ምክር ቤት በትግራይ ክልል በአራት ዞኖች ድርቅ መከሰቱን ቢያረጋግጥም ከ77 ድርቅና የረሃብ ቀውስ ጋር ሊስተካከል ይችላል የሚል ማረጋገጫ እስካሁን አለማውጣቱንም ጠቅሰዋል።

ሕዝብን ቀጣይነት ወዳለው የልማት ሥራ ከማስገባት ይልቅ በግምገማ ስም ለወራት ተሰባስቦ የሚቀመጥ አመራር፤ በመቶ ሺህ የሚቆጠር ባለሙያ በታጣቂ ስም በአንድ ቦታ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በተመደበ በጀት እየቀለበ በምን ሞራል ስለትግራይ ሕዝብ መናገር ይችላል ሲሉም ጠይቀዋል።

በሕዝብ ሽፋን የሚደረግ የትኛውም አይነት ፕሮፖጋንዳ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በአማራ ክልል ስምንት ዞኖች፣ በአፋር ክልል ሦስት ዞኖች እና በሌሎች ክልሎች በሚገኙ አካባቢዎች 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ወገኖች የድርቅ አደጋ እንዳጋጠማቸው ጠቅሰዋል።

መንግሥት ፕሮጀክቶቹን አጥፎ አስፈላጊውን በጀት መድቦ የሰብዓዊ ርዳታን ከሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ብቻ ሳይሆን በበቂ መጠን ለትግራይ ክልል እያቀረበ ነው ብለዋል።

መንግሥት ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ በሦስት ዙር አንድ ሚሊዮን 725 ሺህ ኩንታል የርዳታ እህል በድርቅና በጎርፍ ወደ ተጠቁ አካባቢዎች እያሰራጨ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የአጋር አካላትን ጨምሮ እየተደረገ ያለው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን 15 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል።

በመግለጫቸው፤ በአማራ ክልል የሠላም ጥሪ በማወጅ ሠላምን ለማስጠበቅ መንግሥት በሠራው ሥራ በርካታ መሣሪያ የታጠቁ ቡድኑ አባላት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ተሐድሶ ሥልጠና መግባታቸውን ጠቅሰው፤ “መንግሥት የሠላም በሮችን አሁንም ክፍት እንዳደረገ ይገኛል” ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በተዛባ የፕሮፖጋንዳ ቅስቀሳ ተደናግረው ወደ ሁከትና ብጥብጥ ገብተው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ወደ ተዘጋጀላቸው የተሐድሶ ማዕከላት እየገቡ ይገኛሉ። ወደ ተሐድሶ ማዕከላት ከገቡት መካከል ሁለት ሺህ 500 ያህሉ የቡድን መሣሪያ የታጠቁና አመራሮች ናቸው። ከሠላም ጥሪው በፊት ከአምስት ሺህ 500 በላይ ከጉዳዩ ጋር ንክኪ ያላቸው አካላት በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉና እጅ የሰጡ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉት የተሐድሶ ሥልጠና ወስደው ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።

ለሰው ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ተጠያቂ የሚሆኑ 360 ግለሰቦች ተለይተው ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ 288 የሚሆኑት ግለሰቦች ደግሞ ጉዳያቸው በደረቅ ወንጀል የሚታይ ይሆናል ብለዋል።

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ክልሎች በተደረጉ ውይይቶች ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ወደ ሠላም እንዲመጡ በመደረጉ በአካባቢዎቹ ከመቼውም ጊዜ ሠላም መስፈኑን ጠቁመው፣ በአንጻሩ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚያደርገውን የሰላም ጥሪ ወደ ጎን ብለው የሕዝብን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች በመጻረርና ሃብትና ንብረትን በማውደም ተግባር ላይ በተሰማሩ አካላት ላይ ርምጃ መውሰድ መቀጠሉን ገልጸዋል።

መንግሥት ከሸኔ ጋር የሠላም ንግግር ለማድረግ መሞከሩን ያወሱት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ጥረቱ ባለመሳካቱ ሠላምን ለማስጠበቅ ሲባል በሽበር ቡድኑ ላይ ርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ በቀጣይም መላው ሕዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ሠላምን ለመጠበቅ እና ለማጽናት የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ተስፋ ፈሩ

 አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You