የህዳሴ ግድብ ማንም የማይጎዳበት የሚዛናዊነት አሻራ

ኢትዮጵያውያን እንደዓይናችን ብሌን ስለምናየው፣ በህዳሴ ግድባችን ለዓለም ማኅበረሰብ ያንፀባረቅነው አንድ ገናና እውነት አለን:: እርሱም ማንም የማይጎዳበት፣ ይልቁንም የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ነው:: በዚህ አቃፊና አሳታፊ ሀሳብ እና እምነት ላለፉት ከአስር ለበለጡ ዓመታት ተጉዘን የህዳሴ ግድባችንን እያገባደድን እንገኛለን:: በዚህ የንቅናቄ ወቅት ከግብፅም ሆነ ከሱዳን ከፍ ሲልም ከጎናቸው ካሰለፏቸው ወዳጆቻቸው ከሆኑ ሀገራት የሚደርስብን ጫና ምን ያክል እንደሆነ በትውስታ ማኅደራችን ላይ የተከተበ እውነታ ነው::

በግብፅ መንግሥት በኩል እየተስተዋለ ያለው የአንድ ወገንን ተጠቃሚነት የሚያንፀባርቅ አካሄድ ከታሪክ አንጻር ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን እኤአ የ1929 እና የ1959 ስምምነትን እንደመነሻ ወስዶ የሚሞግት ነው:: ባለፉት ዓመታት የሦስትዮሽ ድርድሩ በሁለት እግሩ እንዳይቆም እንቅፋት ከፈጠሩ ሁነቶች ውስጥ ይሄን መሳይ ኢ-ፍትሐዊ የታሪክ ስምምነት ተጠቃሽ ነው::

ቅኝ ግዛት በተስፋፋበት የ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያና መገባደጃ ላይ አፍሪካውያን በብዙ የአውሮፓ ሀገራት ቅኝ ግዛት ስር ነበሩ:: በዚህም ታላቋ ብሪታንያ የግብፅ ገዢ ሆና ወደ ምድረ ርስቷ ስትገባ፣ ቀጥ ለጥ አድርጋ እንድትገዛ ያደረጋት ደካማ ጎኗን በማሰብ ጭምር ነበር:: በእንግሊዛውያን ልብ ውስጥ የግብፅ ደካማ ጎን የዓባይ ወንዝ መሆኑን ለማወቅ ብዙ አልተቸገሩም:: በዚህም መሠረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የተፋሰስ ሀገራት ያልተሳተፉበትን ሁለት ስምምነቶች ለማድረግ ተነሱ::

የመጀመሪያው ስምምነት እ.ኤ.አ ግንቦት 7 ቀን 1929 በግብፅና በቅኝ ገዢዋ በእንግሊዝ መካከል የተደረገ ነው:: በዚህ ስምምነት ውስጥ ዓባይ በሚለው ታሪክ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ሌሎች የተፋሰስ ሀገራትን ባላማከለ መልኩ የግብጽን የብቻ ተጠቃሚነት የሚያውጅ ነበር:: በዚህም ግብፅ 48 ቢሊዮን ኪዊቢክ ሜትር የሚሆነውን የውሀ መጠን ስትጠቀም የሱዳን የውሀ ድርሻ 4 ቢሊዮን ኪዩብክ ብቻ ነበር::

በኋላም በሱዳን ውትወታና የይገባኛል ጥያቄ ግብፅ ለሁለተኛ ጊዜ ስምምነት ማድረጓ ግድ ሆነ:: ከሠላሳ ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ ኅዳር 8 ቀን 1959 ሱዳንን ያማከለ ሌላ ስምምነት በቅኝ ገዢዋ በእንግሊዝ በኩል ለሁለተኛ ጊዜ ነፍስ ዘራ:: ይሄም ሲሆን በአባይ ወንዝ ላይ ከ85 ከመቶ በላይ ድርሻ ያላትን ኢትዮጵያ ያላሳተፈ ነበር::

በእኚህ ጥንድ አድሎአዊ ስምምነቶች በኩል ግብፅ ዓባይን የራሴ ብላ እንድታምን ከማድረጉም ባለፈ የዓባይን ታሪካዊ መነሻ ምንጭ እስከመቀየር በሚያደርስ የተዛባ ትርክት ስር ወድቃ ነበር:: በዚህ ሳያበቃ ሌሎች የተፋሰስ ሀገራትን ባላገናዘበ መልኩ ከ55 ቢሊዮን ኩዊቢክ ሜትር በላይ የውሀ ድርሻን የሰጠ ስምምነት ነበር::

ሱዳን የተሳተፈችበት የሁለተኛው ዙር ስምምነት የ18 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የውሀ መጠን የጋራ ነበር:: ሆኖም ሁሉን አቀፍና የተፋሰስ ሀገራትን ግምት ውስጥ ያላስገባ ስምምነት ስለሆነ ዛሬም ድረስ ጥያቄ በመፍጠር አለመግባባትን በመፍጠር ላይ ይገኛል::

እንግሊዝ ግብፅን ይዛ የመጀመሪያውን ዙር ስምምነት ስታደርግ የላይኛውን ተፋሰስ ሀገራት ማለትም ሱዳንን፣ ታንዛኒያን፣ ዑጋንዳን እና ኬንያን በመወከል ግን ደግሞ ሌሎች ሀገራትን ባላሳተፈ መልኩ ነበር:: የሁለተኛው ዙር ስምምነትም ተመሳሳይ አዝማሚያ የነበረው በግብፅ ጥቅም ውስጥ የቅኝ ግዛት ፍላጎትን የማስፈጸም አይነት ተልዕኮ የነበረው እንደሆነ ለመረዳት ቀላል ነው:: ይሄ ተልዕኮ ነው ዛሬም ድረስ ፍትሕንና የጋራ ተጠቃሚነትን ወዲያ ብሎ የሦስትዮሽ ስምምነቱን እያደናቀፈ ያለው::

በዓባይ ወንዝ ላይም ሆነ በቀጠናው ላይ የነበረው የኢትዮጵያ ኃያልነትና የተሰሚነት ሚና እንዴት ደበዘዘ ብለን ስንጠይቅ፣ የምናገኘው መልስ የቅኝ ግዛት መስፋፋት ተከትሎ የመጣው የአውሮፓውያን ጣልቃ ገብነትን ነው:: ግብፅና ሱዳንን ቅኝ ትገዛቸው ከነበረችው እንግሊዝ ጋር አብረው ነው በዓባይ ወንዝ ላይ ዛሬም ድረስ የሚያነታርከን ስምምነት ለመፈረም የተገደዱት::

በዓባይ ወንዝ ላይ የተደረጉትን ሁለት ኢ-ፍትሐዊ ስምምነቶች በአንድ ቃል ወይም ደግሞ በአንድ ሐረግ አሊያም በአንድ ዓረፍተ ነገርና በአንድ አንቀጽ እንግሊዝ ካልን የእንግሊዝ ቅኝ ግዛትን ከፊት አምጥተን ግብፅን ከኋላ የምናስተከትል ይሆናል:: ማብራራትካስፈለገው ደግሞ እንግሊዝ ግብፅን እንዴት በተደላደለ መንገድ መግዛት እንዳለባት ስታስብ የመጣ ራስን የመጥቀም መላ እንደሆነ እንደርስበታለን:: ይሄ የስምምነት ሸፍጥ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በገዢና በተገዢ ሃገራት መካከል ጥቅምን የማስከበር የሴራ ጥንስስ ነው::

የዚህ ስምምነት አካል ሆነው ከተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች መካከል የመጀመሪያው ከግብፅ መንግሥት ይሁንታ ውጪ የግብፅን ጥቅም የሚጎዳ ማንኛውም ተግባር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የሚደነግግ ሲሆን፤ ሌላኛው የስምምነት አካል ደግሞ ወንዙ ላይ የሚካሄድ የትኛውም የግድብ ግንባታ በግብፅ መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲሆን የሚያስገድድ ነው::

ሁለቱም የስምምነት መርሆች ብዙኃኑን በተለይም በወንዙ ላይ ሰፊ ድርሻ ያላትን ሀገራችንን ያላቀፈ፣ ያላሳተፈ እንዲሁም ያላግባባ ድርጊት ነው:: ከዚህም በላይ የወቅቱን የኢትዮጵያን ነፃና ሉዓላዊነት ምድር ያላገናዘበ፤ በራሳቸው በቅኝ ገዥዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ሀገራትን ብቻ ከግምት ያስገባ ነው::

የሦስትዮሽ ስምምነቱን አስመልክቶ ዛሬም ድረስ ላለው አለመግባባት በር ከፋች ሆነው ከፊት የሚመጡት እነዚያ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችባቸውና የማትቀበላቸው ስምምነቶች ናቸው:: ምክንያቱም ሂደቱ በግብፅ በኩል ድሮን እየጠቀሱ አልሸነፍባይነትን ማሳየት፤ በእኛ በኩል ደግሞ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያንፀባርቁ ሀሳቦችን እያነሱ አብሮነትን ማስቀጠል ነው:: በዚህም ስምምነቱን የሚያስታርቅ የጋራ መግባባት ላይ ግን አልተደረሰም:: አራተኛው ዙር የሦስትዮሽ ድርድርም በዚህ መልኩ ባለመግባባት የተቋጨ ነው::

ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት ስምምነት ለዚህ አዲስ ትውልድ እና ለዚህ አዲስ ዘመን መከራከሪያ ሆኖ መነሳቱ አስቂኝ ቢሆንም፤ ሁነቱ ግን ለዘመኑ በቀረበ አስታራቂ ሀሳቦች የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ ስምምነቶች እንደሚቋጭ እምነት አለን:: ምክንያቱም ማንም የማይጎዳበት አብሮነትን የሚያጠናክር መነሻና መድረሻ የሀሳብ ስምምነት ነው ወደፊት ሊያራምደን የሚችለው::

ይሄንንም ተደጋግፎ ከመልማት ውጪ ዓላማና ተልዕኮ እንደሌለን ፅኑ በሆነ የብዙኃነት ድምፅ በተደጋጋሚ ገልጸናል:: ሆኖም መጪው ገናናነታችን ያስፈራት ግብጽ ግን ከፍትሐዊነት እሳቤያችን ጋር ለመቧደን አሻፈረኝ ላይ ናት:: ይባስ ብሎ ከጉዳዩ ጋር ያን ያክል ንክኪ የሌላቸውን ሀገራት በማስነሳት በማይሆንና ማንንም ሩቅ በማይወስድ የእብለት ከንፈር ተደነቃቅፋ ስታደነቃቅፈን መሰንበቷ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው::

ከሰሞኑም እዚህ ግባ በማይባልና አካታችነት በሌለው ስምምነት ላይ አቋሟን በማንጸባረቅ በተደጋጋሚ ድርድሩን ፉርሽ አድርገዋለች:: የህዳሴ ጉዟችንን ማደናቀፍ የሚለውን ሀሳብ እንደትልቅ ትልም ወስዳም በማይሆን ሀሳብ እንድንከተላት አስገዳጅ ጫናዎችን ለማሳደር በመሞከር ላይ ትገኛለች:: መነሻውን ሀገር፣ መድረሻውን ሕዝብ ላደረገ ኢትዮጵያዊነት ታዲያ ከዓላማው የሚያዛንፈው እንደሌለ በተደጋጋሚ ብንነግራትም፣ ጆሮ ዳባ ልበስ ብላለች:: ሆኖም ከእኛ የሚጠበቀው በጀመርነው የአንድነትና የአብሮነት መንፈስ መቀጠል ነው::

ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የዓድዋ መልክ ነው:: ባሳለፍነው የአብሮነት ታሪክ ውስጥ አንድ ብለን ሁለት የምንለው ገድለ ታሪካችን ነው:: እንዴት ጀምረን እንዴት እየጨረስነው እንደሆነ እናውቃለን:: በደምና በአጥንታችን የተማገረ፣ በማጣትና በድህነት የጸና የትንሳኤ ደብራችን ነው:: ግብፅ ያለማንም ተቀናቃኝ ያለፉትን በርካታ ዓመታት ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ሁኔታ ዓባይን ለብቻዋ ስትጠቀም መኖሯ ይታወቃል:: አባቶቻችን ሞክረው አልሆን ያላቸውን እና በአደራ መልክ ለመጪው ትውልድ ያስተላለፉት ዓባይ፣ በዚህ ትውልድ ላይ ከቃል አልፎ ተግባር ሲጎበኘው ማነው ወንዱ ማለት በዚህ የሠለጠነ ዘመን ላይ ትዝብት ላይ የሚጥል ነው::

ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ስለህዳሴ ግድብ የተደረጉ የጋራ ድርድሮች በግብፅ በኩል የፈረሱ ናቸው:: ያለፈውን ትተን ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ተገናኝተው የጋራ መግለጫ መስጠታቸው ይታወሳል:: በዚህ የጋራ መግለጫ መሠረትም ላለፉት አራትና አምስት ወራት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሦስትዮሽ ድርድር ሲካሄድም የጋራ ተጠቃሚነት መርሕን በማታውቀው ግብፅ በኩል ውጤት ማምጣት አልተቻለም::

የዓባይ ግድብ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከሰሞኑ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሚዲያ አካላት በሰጡት ማብራሪያ፣ አራት ዙር የሦስትዮሽ ድርድሮች በአዲስ አበባና በካይሮ መደረጋቸውን ገልጸዋል:: የሀገራት ፍላጎትና አቋም በትክክል መገለጹ ድርድሩን በበጎ የሚያስነሳው ቢሆንም፤ በዛው ልክ ተግባቦትን ያላገኙ የአቋምና የፍላጎት ልዩነቶችም የተንፀባረቁበት ነበር:: ካለፈው የሦስትዮሽ ድርድሮች ጋር ሲነጸጻር ግን ብዙ መሻሻሎች የታዩበት እንደነበር በተደራዳሪው በኩል ለማወቅ ተችሏል::

የግብፅ ወቅታዊ አቋም ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት ስምምነት ላይ ተገዢ እንድትሆን የሚያግባባ ሲሆን፤ ይሄ ደግሞ ቅዠትና ፈጽሞ የማይሆን እንደሆነ በተደራዳሪዎች በኩል የተገለጸበት ሁኔታ ነው ያለው:: የኢትዮጵያ አቋም ትላንትናም ዛሬም ያው ነው:: ዓባይን ለብቻዬ ከሚል ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ወጥተን ማንም በማይጎዳበት የጋራ የተጠቃሚነት መርሕ ስር መተዳደር የሚል ነው::

በፈረንጆቹ 2015 የፀደቀው የጋራ መርሕ አብሮ መልማትን፣ አብሮ ማደግን፣ በፍትሕና በእኩልነት መራመድን የሚደነግግ ቢሆንም፣ ይሄ የጋራ መርሕ ግን ከኢትዮጵያ በቀር ግብፆች ሲጠቀሙበት አይታይም:: ለፈረሙበትና ላመኑበት መርሕ ተገዢ መሆን አቅቷቸው ኢትዮጵያ ያልነበረችበትን በተንኮልና ሸር የሆነውን የዛን ዘመን ስምምነት የሚያስታውሱ ናቸው::

ኢትዮጵያ ተደራዳሪዎቿ በኩል የሚነሱት፣ ልዩነትን በሚያጠብቡ ሰፋፊ ሀሳቦች ናቸው:: ግብፅ ደግሞ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን የቆየ ስምምነት አስታውሳ በዛ አቋም ስር የምትሰቃይ ናት:: እኚህ ሁለት የተለያዩ አመለካከቶች እንዴትም ይቃኙ በላጭና ፍትሐዊ ሆኖ የሚታየው የኢትዮጵያ አቋም ነው:: ምክንያቱም ሀሳቧ ጭፍን የሆነ አይደለም:: በዚህ ዘመን በዛ የድንጋይ ዘመን እንኳን ከአንድ ሀገርና መሪ የማይጠበቅ አስተሳሰብ ነው ግብፅ እየተከተለችው ያለው::

ከኢትዮጵያ ጀምሮ አስራ አንድ የሚሆኑ ሀገራትን ነካክቶ ሜዲቴራኒያን ባሕር የሚያበቃው ዓባይ፤ ዛሬ ዋሾነቱን ትቶ ኢትዮጵያውያንን ሊያኮራ ብርሃንን መለገስ ጀምሯል:: ሁሌም ዓባይ አፍ ቢኖረው ኖሮ ስል አስባለው..ለምን ላለኝ ይሄን እነግረዋለው:: በአቅምና በአበዳሪ ማጣት የማንም መጠቀሚያ ሲሆን በማዘን ቆሞ ላየው ለዛኛው ዘመን ትውልድና ለዚህኛው ዘመን ብርቱ ትውልድ ዓባይ እንዲህ የሚል ይመስለኛል፤

‹እናንተ ጥቋቁር ዮቶራውያን ከእናቴ በመፀነሴ ክብር ይሰማኛል:: ስሄድ ቆማችሁ ላያችሁኝና በእንጉርጉሮ ለሸኛችሁኝ ሁሉ መልካም የምሥራች አለኝ..የክህደቴን ያክል እስኪደክመኝ ላገለግላችሁ ናይልን ትቼ በእናቴ ስም ዓባይ ሆኜ መጥቻለሁ› የሚል ይመስለኛል::

በግብፅ ምድር ስለዓባይ ያልተደረገ ክንውን የለም:: ከ2500 በላይ አሞካሽና አወዳሽ ዘፈኖች ስለዓባይ ተጽፈዋል:: በየዓመቱ እጅግ ብዙ ለሆኑ ለሁለተኛ እና ለሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች የጥናት ጽሑፍ ምንጭ በመሆን ያገለግላል:: በሕገ መንግሥታቸው ሳይቀር ምዕራፍና አንቀጽ የተከተበለት አቅጣጫ አለው:: ከዚህ ባለፈ ከግብፃውያን አፍ የማይጠፋ ዓባይ የግብፅ ሕልውና ነው የሚል የቆየ አባባል አለ:: ሆኖም ይሄ ሁሉ ግድ አይሰጠንም፤ ግድ ሊሰጠን የሚችለው አብሮ በመልማት መርሕ ሲመጡ ብቻ ነው::

እንዲህ አይነት ተልካሻ ምክንያት ከተነሳ ደግሞ ከእኛ ዘንድ ሚዛን የሚደፋ እውነታ አለ:: የኤሌክትሪክ ብርሀን በማጣት በኩራዝ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሆኑ፣ ለዘመናት በሥራችን ሲያልፍ አንድ ማንኪያ ውሀ አለመጠቀማችን፣ በአቅም ማጣት ብቻ ‹የአፍሪካ የውሀ ገንቦ› ከሚል መጠሪያ ውጪ ምንም እንዳላተረፍን፣ የራሳችን በሆነ ተፈጥሮዓዊ ፀጋ ሳንጠቀም እልፍ ዘመን በድህነት መኖራችን ትልቅ ጥያቄ ሆኖ የሚነሳ ጉዳይ ነው::

በአምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) የተበሰረው ሌላው ብሥራት፣ ህዳሴ ግድቡ ያለበት አሁናዊ የአፈጻጸም ደረጃ ነው:: እንደሳቸው ገለጻ የህዳሴ ግድባችን ሊጠናቀቅና ትንሳኤውን ሊያይ ከአንድ እጅ ጣት ያልበለጠ የመቶኛ ስሌት እንደቀረው ነው የተነገረው:: ይሄ ማለት ሊጠናቀቅ 6 ከመቶ ብቻ እንደቀረውና በ94 ከመቶ ግስጋሴ ውስጥ ተስፋና ብሥራቱን ይዞ እንደሚገኝ ነው:: ይሄ የለውጥና የተሐድሶ ንቅናቄ በማንም ሳይሆን በጸኑና በበረቱ በተያያዙ እጆችም የመጣ ነው::

እንደ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጻ ከሆነ፣ የግድቡ የኮንክሪት ሥራ እስከመጪው ሰኔ ድረስ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል:: በያዝነው 2016 ዓ.ም አምስት ተርባይኖች የኃይል ማመንጨት ሥራ ይጀምራሉ:: ቀሪ የግድቡ ሥራዎችም በፍጥነት በመጠናቀቅ የኢትዮጵያውያንን የመልማት፣ የማደግ፣ የመበልጸግና የመለወጥ መሻት በእውን ለማድረግ ተቃርበዋል::

ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ ከዓላማቸው ፈቀቅ የሚያደርጋቸው ኃይል እንደሌለ በተግባር ያሳየንበት የአንድነትና የአብሮነት የእድልና የድል ታሪካችንም ነው:: ግብጽ ፍትሐዊነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ባላረጋገጠ ሀሳብ በተደጋጋሚ ጊዜ ድርድሩን ውድቅ ወይም ደግሞ ተስፋ ሰጪ እንዳይሆን ማድረጓ ከዚህ በኋላም ስላለመቀጠሉ ማረጋገጫ ባይኖርም እኛ ግን ከበረቱ የሕዝብ ክንዶች ጋር ወደፊት መሄዳችንን እንቀጥላለን::

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You