በሰላም ወጥተን በሰላም እንድንገባ!

መንግሥት ከሚሠራቸው ተግባራት መካከል ዋንኛውና ቀዳሚው ሕግና ሥርዓትን ማስፈን ነው። ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ ንግድ፣ ማህበራዊ ህይወትን ጨምሮ የእለት ተእለት ፍላጎቶቻቸውን ያለምንም ስጋት እንዲያስፈፅሙ ይህንን መርህ መሰረት በማድረግ ጥበቃ የማድረግ ሥልጣንና ኃላፊነት አለበት።

ዜጎች ይሆነኛልና ፍላጎቶቼን ያስፈፅምልኛል ብለው የወከሉትን አካል ሲመርጡ ቀዳሚ ከሚያደርጉት ፍላጎቶቻቸው ውስጥ አንዱ ደኅንነታቸውን እና በሕግ ጥላ ስር ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ማስተማመኛ ማግኘታቸውን እንደ መስፈርትነት አስቀምጠው ነው።

በዛሬው የአጀንዳ ሀተታዬ መግቢያ ላይም ‹‹ሕግና ሥርዓትን›› እንዲሁም ለዜጎች ‹‹የደህንነት ጥበቃና ዋስትናን›› በተመለከተ ሃሳብ ለመሰንዘር የፈለግኩት በስፋት ልመለከተው የወደድኩት አንድ ትዝብት በመኖሩ ምክንያት ነው።

ይህ ርእሰ ነገር በቀጥታ ከእነዚህ የፍትህ አንኳር ከሆኑ ፅንሰ ሃሳቦች ጋር በቀጥታ የሚገናኝ በመሆኑ በዝርዝር ማንሳት እንዲሁም ለመወያየት እንዲሆን ጥቂት ግላዊ ነጥቦችን ማንሸራሸር አስፈላጊ መስሎ ስለታየኝ ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ልታሳካቸው ያስቀመጠቻቸውን የልማት፣ እድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ አጀንዳዎች እንዳይሳኩ እንቅፋት ለመሆን የሚጥሩ ትናንሽ አጀንዳዎች እዚህም እዚያም መፈጠራቸው የማይቀር ነው።

ዜጎችም በሰላም ወጥተው እንዳይገቡና ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዳልሆነ (insecurity) እንዲሰማቸው የሚያደርጉ ጉዳያችን በሀገራችን በስፋት እየተመለከትን ነው። መንግሥትም ትልቁ የልማት አጀንዳ (big picture) ላይ እንዳያተኩር ይሉን የሚከፋፍሉ እንቅስቃሴዎች እዚህም እዚያም እንመለከታለን።

በዚህ ሰዓት ነው ዜጎች ሕግ አሊያም ፍትህ እየሰፈነ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው የሚሆነው/ለጸረ ልማት ኃይሎችም የሚፈጠረው። ለደህንነታቸው ማረጋገጫ ዋስትና እንደሌላቸው በማሰብም ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ የሚወድቁት። ይህ ጉዳይ በዝርዝርና በግልፅ እንድንገነዘበው የሚከተሉትን ምሳሌዎች ለማንሳት እንሞክር።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ (አንዳንዴም በዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ገፆች ላይ) ሲንሸራሸሩ የምንመለከታቸው ሕገወጥ ድርጊቶች እዚህ ጋር ማንሳት ተገቢ ነው። ለምሳሌ ያህል ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ሥርዓት አልበኛ በሆኑ ግለሰቦች የአደባባይ ፍትህ ተሰጥቶ በመዝናኛ ስፍራዎች ላይ ግድያና የግድያ ሙከራ ሲደረግ አስተውለናል። ዋና ዋና መንገዶችን በመዝጋት የግል ጥቅማቸውንና ፍላጎታቸውን የሚያስፈፅሙ ግለሰቦችን እንዲሁ።

እነዚህ ድርጊቶች አንድ መቶ 20 ሚሊዮን ሕዝብ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ውቂያኖስ ውስጥ እንደተጣለ ጠብታ ውሃ ሊከሰት የሚችል በጣም ትንሽ ያጋጠመ ወንጀሎች አድርገን ልንቆጥራቸው እንችል ይሆናል። ይሁን እንጂ መረጃ በፍጥነት በሚሰራጭበትና ሁሉም የራሱ ዘጋቢና ጋዜጠኛ በሆነበት ዘመን ላይ በመሆናችን ተፅእኖውና በዜጎች ላይ የሚፈጥረው ስነልቦናዊ ጫና እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ አይሆንም።

ወንጀሎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ መምጣታቸውና ተደራራቢ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ማስተዋላችን የችግሩን ምንጭ ለማድረቅ የሄድንበት ርቀት አመርቂ አለመሆኑን የሚያሳይና በሕግ ሥርዓቱ ጠንካራ ፈጣን ውሳኔ ላይ የላሉ ነገሮች ስለመኖራቸው የሚያመላክት ነው።

በአዲስ አበባ ውስጥ በመዝናኛ ስፍራ፣ እንዲሁም በጎዳና ላይ ሁለት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ግለሰቦች መገደላቸውና ዜናው በማህበራዊ ድረ ገፅ በስፋት መዘገቡ የምናስታውሰው ነው። እንዲሁም በተመሳሳይ አንድ ግለሰብ በመዝናኛ ስፍራ መሳሪያ ተኩሶ ሁለት ሰዎችን እንዳቆሰለና ይህም ዜና የተለያየ ትርጉም ተሰጥቶት ለበርካታ ቀናት የማህበራዊ ሚዲያ እንዲሁም የማህበረሰቡ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ መቆየቱ ይታወሳል።

እነዚህ በአጋጣሚ ግጭት የተፈጠሩ የሚመስሉ ነገር ግን ተራ ወንጀሎች ናቸው ብለን ልናልፋቸው የማንችላቸው ጉዳዮች ናቸው። መሰል ወንጀሎች ቀናት፣ ወራትና ዓመታት ባለፉ ቁጥር ሲፈፀሙ እናስተውላለን። ዜጎች ከጎዳና ላይ ታግተው ሲወሰዱ፣ ሀብትና ንብረታቸው በተለይ መኪኖች ልክ እንደ ቀላል ቁስ ከጎዳናዎች ላይ ሲዘረፉ፣ ግለሰቦች የራሳቸው የሆነ የመኪና ንብረት በተደራጁና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች ሰነዶች በረቀቀ ሁኔታ ተቀይረው ሊነጠቁ ግብ ግብ ሲገባ ተመልክተናል።

እነዚህ ከባድ ወንጀሎች በዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት እና ደህንነታቸው መጠበቅ ላይ ስጋት የሚያጭሩ ናቸው። ለዚህ ነው ፈጣንና የዜጎችን ደህንነት የሚያረጋግጥ የፍትህ ሥርዓት መዘርጋት የሚያስፈልገው።

ቀደም ሲል ለማንሳት እንደሞከርኩት በዲጂታል ሚዲያው (ማህበራዊ ድረ ገፅ) ላይ እያንዳንዱ ተጠቃሚ መረጃዎችን በራሱ መረዳት ለብዙ ሺህዎች ያጋራል። ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች ያለምንም ግምገማ በቅፅበት ተዳርሰውና መነጋገሪያ ሆነው እናያቸዋለን።

ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት እና የሕግ አካላት ለክስተቱ ማጣራት አድርገው መረጃውን ከመስጠታቸው አስቀድሞ ልክ የሆኑም፤ የተሳሳቱም መረጃዎች ለኅብረተሰቡ ደርሰው ውጥረት ሲፈጥሩ እንመለከታለን። በዚህ ጊዜ ነው ሕግና ሥርዓትን የሚያስከብረው አካል ዘመኑን የሚዋጅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የምንገነዘበው።

በማህበረሰቡ ውስጥ መከፋፈል የሚፈጥሩ፣ ሥርዓት አልበኝነትን የሚያጎሉ ድርጊቶች ሲፈጠሩ ሕግ አስከባሪ አካሉ በፍጥነት ምላሽ የማይሰጥባቸው ከሆነ ኅብረተሰቡ ቀድሞ የራሱን ትርጓሜ መስጠቱ የማይቀር ይሆናል። ጥቂት ፅንፈኞች አሊያም ሕግ አይገዛንም ብለው የሚያስቡ ግለሰቦች የአደባባይ ፍርድ ሲሰጡ ማህበረሰቡ ሲመለከትና ሕግ አስከባሪው የሚወስደው እርምጃ ሲዘገይ የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይሆንም።

በተለይ ዜጎች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዳልሆነና የሕግ ከለላ እንደሌላቸው ሊሰማቸው ይችላል። ሕግ አስከባሪ አካልም ይሁን ፍትህ እንዳይጓደል የሚሰሩት የመንግሥት አካላት ሥርዓት አልበኛ ግለሰቦች የሚፈፅሟቸው ወንጀሎች አንድን ማህበረሰብ የማይወክል መሆኑን ማሳየት አለባቸው። ከዚያ በዘለለ ፈጣን እርምጃ ወስዶ አስተማሪ ቅጣት መበየን ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ደህንነታቸው የተጠበቀ እንደሆነ እንዲሰማቸው የሚያደርግ ነው።

እዚህ ጋር በሀገረ አሜሪካ ተከስቶ የነበረውን የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ እና የቀሰቀሰውን ታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ማስታወስ ተገቢ ነው። ጆርጅ ፍሎይድን በእግሩ ተጭኖና አፍኖ የገደለው አንድ ነጭ ፖሊስ የአሜሪካ የሕግ ሥርዓት (ፍትህ) ምን ያክል ክፍተት እንዳለበት ከማሳየት ባለፈ ዓለም አቀፍ ሰፊ የጥቁሮች መብት ንቅናቄን ያስነሳ ነበር።

ይህ አንድ ተራ ግድያ ሳይሆን በማህበረሰቡ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነበር። መላው የሰው ዘርን ቆም ብሎ እንዲያስብ ያስቻለ ድርጊት ከመሆን ባለፈም ዜጎች ምን ያክል በሕግ ከለላና ጥላ ስር መሆን እንዳለባቸው ያመላከተ ነበር። በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፈው ወንጀለኛ በፍጥነት ፍርድ በማግኘቱ ምክንያት ቀጣይ ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዲቀንሱ በር ከፋች ሆኖ አልፏል።

በመሆኑም ትልቁ ሀገር የሚለውን ምስል ማየት እንድንችል እንደዚህ አይነት በየሰፈሩና በየመንደሩ የሚከሰቱ ወንጀሎችን ልንገታ ይገባል። ለዚህ ደግሞ ፈጣን ፍትህ፣ የሕግ ከለላ ወንጀልን አስቀድመን የመከላከል ሥራችን ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት ልዩ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል የሚል መልእክት አለኝ። ይህ ሲሆን ዜጎች ወጥቶ የመግባትና ደህንነታቸው የተረጋገጠ ስለመሆኑ ዋስትና ያገኛሉ። ሰላም!!

ሰው መሆን

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You