ላለመስማማት መደራደር – የግብጽ አሁናዊ አካሄድ

በተደጋጋሚ የተደረጉ የሶስትዮሽ ድርድሮች ያለስምምነት መፈታትን ለታዘበ ግብጽ ላለመስማማት የምትደራደር ይመስላል። ይሄን ወለፈንዲያዊ / ፓራዶክሲካል/ አካሄድ የመረጠችው ደግሞ ወቅታዊ ጂኦፖለቲካዊ ስፍራዋንና ሚዛኗን በመተማመን፤ የናይልን ጉዳይ ዘላለማዊ አጀንዳ በማድረግ የሕዝብን ድጋፍ ላለማጣት እና ሀገራችንን ከዲፕሎማሲያዊ ጫና ብዛት ሉዓላዊነቷን ሸብረክ በማድረግ አስገዳጅ ውል በመፈራረም ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ነው። እነዚህን አመክኒዎችን አንድ በአንድ እንመል ከት።

ከመስከረም 26ቱ የሀማስ የእስራኤል ጥቃት በኋላ ግብጽ በቀጣናው ያላት ጂኦፖለቲካዊ ዋጋ በፊት ከነበረው ጨምሯል። የሀማስና የእስራኤል አደራዳሪና አሸማጋይ ኃይል ሆና ከመውጣቷ ባሻገር ወደ ጋዛ የሚገባው የዕለት ደራሽ ርዳታ የሚመጣው በግብጽ በኩል ስለሆነ፤ ሶስተኛ ወሩን በያዘው የእስራኤል የጋዛ የአየር ድብደባ የተጎዱ ንጹኃንና ህጻናት ለህክምና ወደ ግብጽ ስለሚላኩ በቀጣናው ያላት ሁለንተናዊ ተጽዕኖ ከፍ ብሏል ።

በዲፕሎማሲው መተላለፊያ ወይም ኮሪዶር ሰጥቶ መቀበል እንጂ ነጻ ምሳ የሚባል ነገር ስለሌለ ግብጽ ለዋለችው ውለታ በአሜሪካ የሚመራው ዓለምአቀፍ ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ፣ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንዲያደርግላት ትፈልጋለች። በኢትዮጵያ ላይ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያሳድርላት ትሻለች። እንደ ሀገር ለዚህ ጫና አበክረን መዘጋጀት አለብን። እርስ በርስ መጠላለፉን፣ ሸፍጡንና መጠፋፋቱን ትተን የቤት ሥራዎቻችንን ለይተን መሥራት ይጠበቅብናል። የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ሀስ ፣ “የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሀገር ውስጥ ይጀመራል።” እንዳለው።

ደጋግሜ እንዳልሁት የአንድነታችን ጉዳይ ወቅታዊ የአኬሊስ ተረከዛችን ወይም ስስ ብልታችን መሆኑ እንዳለ ሆኖ ቢያንስ ወቅታዊና ግልጽ መረጃ በመስጠት ረገድ ክፍተት መኖር የለበትም። አዎ ! ብዙኃን መገናኛዎችም ሆኑ የሚመለከታቸው አካላት እንደገና ያለ ውጤት ስለተፈታው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ፣ የሱዳንና የግብጽ የሶስትዮሽ የድርድር ሒደት እግር በእግር እየተከታተሉ በማያሻማ ሁኔታ ለሕዝብ መተርጎም ፣ መግለጽ፣ ማብራራትና ማሳወቅ ሕዝብ እንዳይደናገር ያደርጋል።

አራተኛው ዙር የውሃ ሙሊት ባለፉት ሶስት ዓመታት በሦስት ዙር ከተካሄደው የግድቡ የውሃ ሙሌት እኩል ሊሆን 2 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው የሚቀረው። በእነዚህ ዓመታት የተያዘው አጠቃላይ የውሃ መጠን 22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ሲሆን ፣ በዘንድሮ አራተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በአንድ ጊዜ የተያዘው የውሃ መጠን ግን 20 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው። ይህ ትልቅ እምርታ ነው። የሀገራችን ጂኦፖለቲካዊ ስፍራ ከፍ ያደረገ ስለሆነ ማስጠበቅ ፣ ማጽናትና ማዝለቅ ይጠይቃል።

በቅኝ ግዛት ውል ላይ ተመስርቶ አስገዳጅ ስምምነት መፈረም ማለት ይሄን በስንት ርብርብና ዋጋ የተገኘን ጂኦፖለቲካው ድል የሚያሳጣና በጀግኖች አባቶቻችን መስዋዕትነት ያስከበርነውን ሉዓላዊነታችንን ለድርድር እንደማቅረብ ስለሆነ መንግሥት በቅኝ ግዛት ውሎች አልደራደርም ማለቱ ትክክል ነው።

ሰሞነኛው ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአዲስ አበባ ሲያደርጉት የነበረው የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ኢትዮጵያ እና ግብፅ አስታውቀዋል። ሦስቱ ሀገራት በሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እንዲሁም ዓመታዊ የሥራ ሂደትን የተመለከተ መመሪያ ላይ ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ በአራት ዙር ሲካሄድ የቆየው ድርድር በሀገራቱ መካከል ባሉ መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በድርድሩ ወቅት ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አስተሳሰቧን በመያዟ ስምምነት እንዳይደረስ እክል ሆናለች ብሏል። አራተኛው ዙር የመጨረሻው ድርድርም በአዲስ አበባ ባለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውሶ፣ በድርድሮቹ ላይ ኢትዮጵያ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር በግድቡ ግንባታ፣ ውሃ አሞላል እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ያሏትን መሠረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ጥረት አድርጋለች። ይሁን እንጂ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር አሞላል እና ዓመታዊ የሥራ ሂደትን የተመለከተ መመሪያ እና ደንቦች ላይ ሲደረግ የነበረው ድርድር ግብፅ የቅኝ ግዛት ዘመን አቋሟን በመያዟ ስምምነት እንዳይደረስ እንቅፋት ሆኗ ል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መርህ ላይ በመመሥረት የዜጎችን ፍላጎት ለማሟላት የምታደርገውን ጥረት እንደምትቀጥል ማሳወቅ ትፈልጋለች” ብሏል። ግብፅ በበኩሏ “የግድቡን አሞላል እና ኦፕሬሽን በቅርበት በመከታተል መብቴን አስከብራለሁ”። የግብፅ የውሃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በግድቡ ምክንያት “ግብፅ የትኛውም አይነት ጉዳት ቢደርስባት በዓለም አቀፍ ቻርተሮች እና ስምምነቶች መሠረት የውሃ

ድርሻዋን እና ብሔራዊ ደህንነቷን የመጠበቅ መብቷ የተጠበቀ ነው” ብሏል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ይህ ግብፅ ከድርድሩ መጠናቀቅ በኋላ ያወጣችው መግለጫ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር እና የአፍሪካ ኅብረት ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌን የሚጻረር ነው በማለት መግለጫውን እንደማትቀበለው አስታውቃለች። ኢትዮጵያም የቅኝ ግዛቱን ውል እንደማትቀበለው ደጋግማ አሳውቃለች። ሀገራችን ይሄን አስገዳጅ ስምምነት አደረገች ማለት እኤአ ዘመን አቆጣጠር በ1929 እና በ1959 ዓ.ም ግብጽና ሱዳን የተፈራረሙትን የቅኝ ግዛት ሕግ ተቀበለች ማለት ነው።

የመጀመሪያው ስምምነት የታላቁ የአባይ ወንዝ መነሻ የሆነችውንና 77.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ወይም 86 በመቶውን የምታበረክተውን ሀገራችንና ሌሎች ስምንት የግርጌ ተፋሰስ ሀገራትን ያገለለ ነው። በዚህ ኢፍትሐዊ ስምምነት ግብጽ 48.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ለመጠቀም ፤ ሱዳን ደግሞ 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ለመጋራት ተስማምተዋል። ሀገራችንን ጨምሮ ለራስጌ ሀገራት የተውት ጠብታ ውሃ የለም። ጉድ እኮ ነው።

ሁለተኛውና የፈርኦን እብሪት ግዘፍ ነስቶ የተገለጠበት ስምምነት ደግሞ ፣ “ከግብፅ መንግሥት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ሥራዎችን በአባይ ገባሮችና ሀይቆች ላይ መገንባት አይቻልም::” የሚል ነው። እነዚህን የቅኝ ግዛት ውሎችን ሀገራችን እንዴት ትቀበላለች ተብሎ ይጠበቃል። በነገራችን ላይ ይሄን አስገዳጅ ስምምነት ተፈራረሚ ማለት ግብፅ የህዳሴው ግድብ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሃ በየዓመቱ ይልቀቅ በሚል ያቀረበችውን ግዴታ መንግሥት ከመቀበሉ ባሻገር ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ በኋላ በዓባይ ወንዝ ላይም ሆነ በገባሮቹ ምንም ዓይነት ልማት እንደማታካሂድ በመስማማት ሉዓላዊነቷን አሳልፋ ልትሰጥ ነው ማለት ነው።

በእጅ አዙር የውሃ ክፍፍል ስምምነቱን ተቀበለች፤ ለሚቀጥሉት ዓመታት ከህዳሴ ግድቡ በየዓመቱ የሚለቀቀው የውሃ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን ተስማሚ ማለት ነው። መንግሥት ይሄን አስገዳጅ ስምምነት ይቀበል ማለት የዓባይ ውሃ ምንጭና ተፈጥሯዊ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን ያግልል በተጨማሪ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የውሃ ድርሻ የላትም ማለት ነው። ግድቡን በጋራ እናስተዳድረው የሚለው ሌላው የግብጽ ደባና ጥያቄ በዚህ አሳሪ ስምምነት ይካተት አይካተት ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።

ለናይል ወንዝ 86 በመቶ ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ፍትሐዊ በሆነ አግባብ ውሃውን የመጠቀም መብቷ ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም:: ሀገራችን አስገዳጅ ስምምነቱን ፈረመች ማለት ፤ በተዘዋዋሪ መንገድ ግጭትንና አለመግባባትን ለመፍታት ሰባቱ የራስጌ የተፋሰስ ሀገራት የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አዳዲስ ውሎች ሊተኩ እንደሚገባ የሚጠይቀውና በ2002 ዓ.ም የተፈረመውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት Co­operation Framework Agreement (CFA) አፈረሰች ማለት ነው።

ስምምነቱን የተፈራረሙ ሀገራትን ብሩንዲ፣ ኬንያ ፣ ኡጋንዳ ፣ ኢትዮጵያ ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ ካጂ ፤ የትብብር ማዕቀፉ የናይልን ወንዝ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መጠቀምን የሚያረጋግጥና ዋስትና የሚሰጥ ቋሚ ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚጠይቀውን ስምምነት ተቃረኒ ማለት ስለሆነ ሀገራችንን እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ አቋሟን አሳውቃለች::

ዳሩ ግን ሱዳንና ግብፅ ይህን የትብብር ማዕቀፍ ለመፈረም ፈቃደኛ ባይሆኑም በ2007 ዓ.ም በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ (Declaration of Principles) ፈርመዋል:: በዚህ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን የተቀበሉ ሲሆን ኢትዮጵያም ግድቡ በግርጌ ተፋሰስ ሀገራት ማለትም በግብፅና በሱዳን ሊያሳድረው የሚችል ተፅዕኖ ወይም ጉዳት ካለ ጥናት እንዲደረግ ተስማምታለች:: በዚህ ስምምነት ላይ ተከታታይ ውይይቶች የተካሄዱ ሲሆን ተስፋም ተጥሎባቸው ነበር::

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለቀጣናዊ ትብብር አብነት የሚሆንና የራስጌ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ስለሆነ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ሊደረግለት ሲገባ ግንባታን መም የራስጌ ተፋሰስ ሀገራትን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነው :: ይልቁን ግብፅም በግድቡ ውሃ አሞላል ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ጀምራ ወደነበረው ድርድር ብትመለስ ሀገራቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል መግባባት መድረስ ይችላል ::

ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ ሀገራትን በተለይ ሀገራችንን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር ስምምነቶቹ የመንግሥታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የወንዞች የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ :: ሆኖም የራስጌ የፋሰሱ ሀገራት የጋራ የሆነውን የዓባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም:: ሱዳንና ግብፅ ዓባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው::

ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን ዓለምአቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብድር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው:: የተፋሰሱ ሀገራት የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የውሃ፣ የምግብና የኃይል ፍላጎታቸው በእጅጉ እያሻቀበ ነው::

የሚያሳዝነው እነዚህ ፍትሐዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለግብፅ ሲሆን እጃቸው ይፈታል:: በዚህም ጭው ባለ በረሃ ግዙፍ መስኖዎችን ፣ ሀገሪቱን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረጉ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል:: በስተሰሜን የሱዳንና ግብፅ ድንበር ላይ ግብፅ በዓለማችን ረጅሙን የዓባይ ወንዝ በመገደብ በግዙፍነቱ ከዓለም 3ተኛ የሆነውን የአስዋን ግድብ ገንብተዋል::

የአስዋን ግድብ 10 ዓመት ከፈጀ ግንባታ በኋላ እአአ በ1970 ተጠናቋል:: በ1954 ግብፅ ከዓለም ባንክ ብድር ፣ ከአሜሪካ ደግሞ ርዳታ ለማግኘት ጠይቃ ተስፋ ተሰጧት የነበር ቢሆንም ከእስራኤል ጋር በገባችበት ውዝግብ የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል:: በዚህ የተከፋችው ግብፅ ወዲያው ፊቷን ወደ ሶቪየት ሕብረት በማዞር ባገኘችው ብድር ግንባታውን ማካሄድ ችላለች::

ግድቡ 90ሺህ ሱዳናውያን ከማፈናቀሉ ባሻገር በቅርስነት ተከልለው የነበሩ ቦታዎችም በውሃ ተውጠዋል:: እነዚህ ተፈናቃዮች ከቀዬአቸው 600 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ ፤ በግድቡ የተነሳ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ግብጻውያን ግን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀው እንዲሰፍሩ ተደርጓል:: ግብፅ ይህን ግዙፍ ግድብ ስተገነባ ከሱዳን ውጭ ሌሎች ሀገራትን ማማከር አይደለም እወቁልኝ እንኳ አላለችም:: ሱዳንንም ያማከረቻት አስባላት ሳይሆን በዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታውቀው ይመስላል::

የአስዋን ግድብ 2ሺህ 100 ሜጋ ዋት በማመንጨት ማለትም ግማሹን የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያሟላ ሲሆን ለከፍተኛ መስኖ ልማትም ውሏል:: ግብፅ እምቅ የኃይል አማራጭ ቢኖራትም ከውሃ የኃይል ማመንጫዎች ውጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም:: አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በርሚል የነዳጅ ድፍድፍ ክምችት በምድሯ ቢኖርም በቀን እያመረተች ያለው ከ 640ሺህ በርሚል በታች ነው ::

የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ወደ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮን የሚጠጋ ኩም የሚጠጋ ሲሆን እያመረተች ያለው ግን ወደ 60 ቢሊዮን ኩም የሚጠጋ ብቻ ነው:: እንዲሁም 547ሺህ 500 በርሚል በቀን የተጣራ ነዳጅ ታመርታለች :: ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ:: ይህ ሁሉ አማራጭ የኃይልም ሆነ የመስኖ ሀብት እያላት መላው ስስቷና ቀልቧ ዓባይ ላይ ነው ::

ግንባር ያድርገው ብላ በየአደባባዩ እየማለች ፣ እየተገዘተችና እየካደች ፤ ኢትዮጵያ ዝናብን ጨምሮ በርካታ አማራጭ የውሃ ሀብት እያላት ጥቁር አባይ ላይ ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለማንበርከክና ጂኦ ፖለቲካዊ ሚዛኗን ለመጨመር ነው ስትል በየመድረኩ የአዞ እንባዋን እየረ ጨች ነው::

ሻሎም ! አ ሜን ።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 18 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You