የአርሶ አደሮች ቀን መከበር ሀገራዊ ፋይዳ!

በቅርቡ በአርሶ አደሮች ቀን መከበር አስፈላጊነት ላይ እንድ መድረክ ተካሂዶ ነበር። በመድረኩ ላይ የግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ የቀድሞ የአለማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ማኅበር እንዲሁም አሊያንስ ፎር ሳይንስ የተሰኘ ግብር ሠናይ ድርጅት አባላት እንዲሁም አርሶ አደሮች ተገኝተዋል። የአርሶ አደሮች ቀን መከበርን አስመልክቶ የተካሄደውን መድረክ ዋቢ ያደረገ መረጃ በዚህ ጋዜጣ የግብርና ዓምድ ላይ ወጥቷል።

በመድረኩም ከ1988 እስከ 2006 ለተከታታይ ዘጠኝ ዓመታት የልማት አርበኛ አርሶ አደሮች ይሸለሙ የነበረበት መድረክ ለመታወስ በቅቷል። በዚያ መድረክ ላይ የልማት ጀግና የተባሉ አርሶ አደሮች እውቅና እንዲያገኙ ይደረግ እንደነበር ይታወቃል። በርካታ የልማት አርበኛ አርሶ አደሮች ወደ ባለሀብትነት መሸጋገራቸው እየተገለጸ ይሸለሙ የነበረበት ሁኔታ እንደነበርም ይታወሳል። ያ ለአርሶ አደሮች እውቅና የሚሰጥበት ሁኔታ ሌሎች አርሶ አደሮች እንዲበረታቱ መነሳሳት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል የሚል እምነትም በወቅቱ ነበር።

ያ መድረክ ክፍተቶች እንደነበሩበትም የአርሶ አደሮች ቀን መከበር አስፈላጊነት ላይ የተወያየው መድረክ ለዓመታት ተካሂዶ የተቋረጠውና ብርቱ የተባሉ አርሶ አደሮች ይሸለሙበት ደካማ ጎኖች እንደነበሩበትም ተጠቁሟል። አሁን እንዲከበር የታሰበው የአርሶ አደሮች ቀን በዓል በቀደመው መድረክ አግባብ እንዲከበር የሚፈልጉ እንዳሉም በመድረኩ ታይቷል። ጠንካራውን ይዞ ደካማውን ጥሎ መድረኩን ማስቀጠል እንደሚቻል ሀሳብ ተሰጥቶበታል።

በእርግጥም የአርሶ አደሮች ቀን ቀደም ሲል የልማት ጀግኖች በሚል ይካሄድ በነበረበት መንገድም ይሁን በሌላ መከበር ይኖርበታል። ይህ ቀን ሲከበር አብረው የሚከናወኑ በርካታ ተግባሮች ስለሚኖሩ እነዚህ ተግባሮች የአርሶ አደሩን ልማት ወደፊት ሊያራምዱ፣ ችግሮቹን አውጥቶ እንዲናገር ሊያደርጉ፣ ልምድ እንዲለዋወጥ ምቹ ሁኔታ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ የመድረኩ ወሳኝነት ጥያቄም ጥርጣሬም ውስጥ አይገባም ባይ ነኝ። ብርቱዎች የሚበረታቱበት፣ ወደኋላ የቀሩ ልምድ የሚቀስሙበት መድረክ ሊሆን ስለሚችል የቀኑ መከበር አጠያያቂ አይደለም፤፤

የቀኑ ይከበር መድረክ ተሳታፊዎችም በእዚህ ላይ ተማምነው እንዴትና መቼ ይከበር በሚለው ላይ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ግብረ ኃይል ሰይመዋል። በዚህ ጊዜ ሊባል ባይችልም፣ የአርሶ አደሮች ቀን አርሶ አደሩን፣ ሀገሪቱ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እያደረገች ያለችውን ርበርብና እሱን ተከትሎ እየመጣ ያለውን ለውጥ በሚመጥን መልኩ ይህ እንደሚከበር እንጠብቃለን።

በዓለም አቀፍ ደረጃም፣ በሀገር ደረጃም ‹‹…. ቀን›› የሚል መጠሪያ እየተሰጣቸው የተለያዩ ጉዳዮች ይከበራሉ፤ ከቅርብ ጊዜ ደግሞ ስሙ …. ሳምንት፣ …. ወር በሚል ለሳምንት፣ ለወር የዘለቁ የተለያዩ ዘርፎች መድረኮች ሲካሄዱ ይታያል። መድረኮቹ በጉዳዩ ላይ አንዳች ግንዛቤ ሊያስጨብጡ ስለሚችሉ እኔ መኖራቸውን እደግፋለሁ ።

ከእነዚህ ጋር ተያይዞም እንደ ዓውደ ርዕይ፣ ሲምፖዚየም፣ ጉብኝትና የመሳሰሉት ልዩ ልዩ መድረኮች ይፈጠራሉ። መድረኮች ቀኑ በሚከበርለት ዘርፍ ምን ምቹ ሁኔታ እንዳለ፣ ይህን በመጠቀም በኩል ምን ያህል ርቀት መሄድ እንደተቻለ፤ ተግዳሮቶቹ ምን እንደሆኑ፣ መፍትሔዎቹ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ይመላከትባቸዋል። ባለድርሻዎች ይገናኛሉ፤ ልምድ ይለዋወጣሉ፤ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ይካሄዳል።

መከበር ፋይዳው ከዚህም ያለፈ ሊሆን ይችላል። በእዚህ አይነቱ መድረክ አጀንዳው ደብዝዞ የነበረ ጉዳይን ማነቃቃት፣ አዲስ የተቀረጸ አጀንዳ መነጋገሪያ ማድረግ ይቻላል፤ የተረሳውን ማስታወስ፣ በቀጣይ ለሚሠራው ሥራ አቅም ማግኛ መንገድ ይፈጠራል። ከዚህ የተነሳ አርሶ አደሩ ቀን ያስፈልገዋል የሚል እምነት አለኝ። የአርሶ አደሮች ቀን እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ ።

በዚህ መድረክ ላይ ጠቆም የተደረገው የአርሶ አደሮች ማኅበር አስፈላጊነት ነው። ጉዳዩ የበለጠ ትኩረቴን ስቦታል። ጉዳዩ በመድረኩ መነሳቱን ስሰማ በወታደራዊው መንግሥት ዘመን /በደርግ ዘመን/ የነበረው የመላ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር / መኢገማ/ አስታወሰኝ። ቦሌ መንገድ ወደ ፍላሚንጎ አካባቢ ማኅበሩ ያሠራው በዘመኑ ግዙፍ የተባለ ሕንጻም ነበረው።

ካስታወስኩ አልቀረ አንዳንድ ነገሮችንም ላስታውስ። በዚያ ዘመን መኢገማ ብቻ ሳይሆን ሌሎች በርካታ ማኅበራትም ነበሩ። የመላ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር /መኢሠማ/፣ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበር /አኢወማ/፣ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር /አኢሴማ/ ፣ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር /ኢመማ/ የሚሉና ሌሎች በርካታ ማኅበራትም ነበሩ።

ከእነዚህ ማኅበራት አንዳንዶቹ በኢሕአዴግ ዘመንም የሆነ ለውጥ እየተደረገባቸው ቀጥለዋል፤ የያኔው መኢሠማ የዛሬው ኢሠማኮ ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። አሁንም ድረስ ከእነስማቸው የሚሠሩም አሉ። ኢሕአዴግ እንደ ዘጋቸው የቀሩ በርካታ ማኅበራት እንዳሉም ይታወቃል። ከእነዚህ ማኅበራት አንዱ ኢሕአዴግ እንደዘጋው ሳይከፍተው ያሸለበበት የመላ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር /መኢገማ/ ነው።

በማኅበሩ መዘጋት ሳቢያ ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ አንስቶ አርሶ አደሩ ድምፁን የሚያሰማለት፣ ስለመብቱ የሚከራከርለት አልነበረውም፤ የለውም። ከሠላሳ ዓመት በላይ ማለት ነው። የአርሶ አደሩን ጉዳይ ግብርና ሚኒስቴርና መሰል ተቋማት ናቸው ሲያነሱ የኖሩት፤ መንግሥት ነው ሲያነሳ የኖረው።

የአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከግብዓት አቅርቦት ከምርት ለገበያ በማቅረብ ጋር በተያያዘ ስለ አርሶ አደሩ የሆነ የሆነ ነገር ሲሉ ቆይተዋል። እነሱም በኢሕአዴግ መምጣት ተበትነው ነበርና ይህን ለብዙ ጊዜ ሠርተውታል ሊባሉ አይችሉም። ቆይቶ ቆይቶ ነው እንደገና የተቋቋሙት።

የኢሕአዴግ መንግሥት የደርግ ዘመን ስሪት ያለውን በሙሉ በመዝጋት የሚታወቅ መንግሥት ነበር፤ የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት አደባባይ የተባለውን ስፍራ ስንት ዓመት ዘግቶበት እንደነበር የምታስታውሱ ታስታውሳላችሁ። እኔ እስረኛው ሐውልት እለው ነበር። ለመከላከያ ሠራዊት በነበረው ጥላቻ ሐውልቱን ዳዋ እንዲበላው፣ ለድምቀቱ የተሠሩ መብራቶች እንዲወድሙ አድርጓል፤ የቆሻሻ መጠያ ሲሆን ዝም ብሎ ነው የተመለከተው። በኋላ ላይ የኢትዮ ኩባ ወዳጅነት አደባባይ ተባለና ለሕዝብ ክፍት ተደረገ እንጂ ቢያፈርሰው ደስታውን አይችለውም ነበር።

ወደ ጉዳዬ ልመለስ፤ ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው አካላት/መንግሥት ወይም ግብርና ሚኒስቴር፣ የአርሶ አደሮች ኅብረት ሥራ ማኅበራት/ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በሚያደርጉት ርብርብ አርሶ አደሩን ደግፈውታል። ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ በሚልም ገበያ የመፍጠር ሥራዎችን ሠርተዋል። ከቴክኖሎጂ እንዲተዋወቅ፣ ልምድ እንዲጋራ ሠርተዋል። ለእዚህ ተግባራቸው ባለውለታ ናቸው።

አርሶ አደሩ ማኅበር ቢኖረው ደግሞ በዚህ ላይ ሊጨመረው የሚችለው እንደሚኖር መጠርጠር አይገባም። ችግሮቹን በሙሉ መፍታት ባይችልም፣ የተወሰኑትን መፍታት፣ ማስፈታት ይችላል። ከአንዳንድ ንቁ ማኅበራት መገንዘብ እንደሚቻለው ማኅበር የአባላት መብት ያስጠብቃል፤ የአምራች ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበር ከሆነ ደግሞ መብት ተጠብቆበታል፤ የአምራቾች ማኅበር ከሆነ ደግሞ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ የዘርፉ ደንቃራዎች እንዲወገዱ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ይሠራበታል።

በማኅበር መቋቋም ላይ ብዙ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። አንዳንዶች በአንዳንድ ማኅበራት ላይ የታዩ ክፍተቶችን በማሰብ ማኅበር ምን ያደርጋል ሊሉ ይተቻሉ። በገዛ እጅ በላተኛ ማብዛት አርገውም ይቆጥራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ቢከፋም ቢለማም ማኅበር እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። እነዚህ አካላት ማኅበር እንዲኖር ሲፈልጉ ክፍተቶች እንዳሉ አጥተውት አይደለም።

እርግጥ ነው ሁሉም ማኅበራትን ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ናቸው፤ አባሎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል ማለት አይቻልም። የማኅበራቱ መሪዎች ከማኅበራቸው ይልቅ ለአሠሪዎች ታማኝ የሆኑበት ሁኔታ ጥቂት አይደለም፤ ይህን ይህን የተመለከቱ ወገኖች ማኅበርን ቢጠሉ አያስገርምም።

አንዴ አመራሩ ላይ ከወጡ በኋላ የማይወርዱ ጥቂት የማይበሉ የማኅበራት መሪዎች ያሉበት ሁኔታም ሰዎች ማኅበርን እንዲጠራጠሩ ቢያደርግ አያስገርምም። የማኅበራቱ መሪዎች የሥልጣን ቆይታ በጣት ከሚቆጠሩ ዓመታት የማይዘልቅ መሆኑ በሕጋቸውም ሰፍሮ እያለ እነሱ ግን የምንጊዜም፣ የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት፣ ጸሐፊ ወዘተ ሆነው የሚቆዩበት ሁኔታ ጥቂት አይደለም። ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ የማኅበር መሪ የሆኑ አሉ።

እነዚህ መሰል ማኅበራት አሉ ተብሎ ግን ማኅበር ከመመሥረት መቆጠብ አያስፈልግም፤ ለአባሎቻቸው መብት ሲሉ የተሰደዱ፣ በእስር የማቀቁ፣ ተረጋግተው ሥራቸውን እንዳይሠሩ የተደረጉ ጥቂት እንዳልሆኑም ማሰብ ያስፈልጋል። በእነሱ መስዋዕትነት ይነስም ይብዛ የአባላት መብት የተከበረበትን ሁኔታ መዘንጋት አይገባም።

አንዳንዶች ደግሞ ማኅበር ተብዬው ሊያደርግ የሚችለውን አሠሪው ወይም መንግሥት እያደረገ ስለሆነ ማኅበር አያስፈልግም ሊሉ ይችላሉ። መንግሥት ለዘርፉ እድገት ሲል የዘርፉን ተዋናይ ሊደግፍ ይችላል፤ ከእዚያ በዘለለ ግን የማኅበሩን ሚና ሊጫወት አይችልም።

በሀገራችን በርካታ የሙያ ማኅበራት እንዳሉ ይታወቃል። የሠራተኞች ማኅበራትና ኮንፌዴሬሽናቸው፣ የመምህራን ማኅበር፣ የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበራት፣ የአሽከርካሪዎች ማኅበር፣ የጋዜጠኞች ማኅበር፣ የወጣቶች ማኅበር፣ የሴቶች ማኅበር…. ተዘርዝረው አያልቁም።

እነዚህ የሙያና የመሳሰሉት ማኅበራት የሠራተኞችን መብቶች ለማስጠበቅ፣ ሙያዊ ነፃነት እንዲኖራቸው ለማድረግ፣ ከቀጣሪዎች ወይም ከመንግሥት ጋር ሊደረጉ በሚችሉ ውይይቶች ላይ አባላትን በመወከል ይወያዩባቸዋል። በኢንዱስትሪዎች የሠራተኛ ማኅበራት ሚና ጥያቄ የለውም።

ለኢንዱስትሪ ሠላም መጠበቅ፣ ለምርትና ምርታማነት የበለጠ ማደግ የሠራተኛው ሚና ወሳኝ እንደመሆኑ ማኅበራቱም የበኩላቸውን ያደርጋሉ። ማኅበራት ለአባሎቻቸው እንደ ሥልጠና፣ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን የመሳሰሉትን የሚያደርጉበት ሁኔታም ይታያል።

በሠራተኛውና በአሠሪው መካከል የሚደረጉ ውይይቶች በሠለጠነ አግባብ እንዲፈጸሙ የሠራተኛ ማኅበር ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የሁሉም ድምር ውጤት ሠራተኛው መብቱ ተጠብቆ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እንዲሁም ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረግም ነው።

የሠራተኛው መብት ተጠበቀ ማለት፣ ሠራተኛው በነፃነት የሚሠራበት ሁኔታ ተፈጠረ ማለት ሥልጠናና የመሳሰሉትን በማኅበሩ በኩል አገኘ ማለት ምርታማነቱ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ያርፋል ማለት ነው።

ወደ አርሶ አደሩ ማኅበር እንምጣ። ኢትዮጵያ የአርሶ አደሮች ሀገር ናት፤ የቅርብ ጊዜ መረጃ ባይኖርም ከሀገሪቱ ሕዝብ 85 በመቶው አርሶ አደር ነው ይባላል። ይህን አኃዝ ኢንዱስትሪና የአገልግሎት ዘርፉ እየቀነሰው ሊመጣ ቢችልም፣ አኃዙ ብዙም የሚነቃነቅ አይሆንም።

አርሶ አደሩን ያቀፈው የግብርናው ዘርፍ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ከፍተኛውን እጅ የሚይዝ ነው፤ በአገልግሎቱና ኢንዱስትሪው ላይ በተከናወነ ተግባር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እነዚህ ዘርፎች በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያላቸው ድርሻ እየጨመረ ቢመጣም ግብርናው ከፍተኛውን ድርሻ እንደያዘ ነው ።

የዚህ ምጣኔ ሀብት ዋና ተዋናይ አርሶ አደር የእኔ የሚለው ማኅበር ቢኖረው ዘርፉ ይበልጥ ያድጋል፤ ከሌሎች ዘርፎች ጋር የሚኖረው ትስስርም የበለጠ ይጠናከራል እንጂ አይጎዳም። መንግሥት እንደ መንግሥት የሚያደርገው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ አርሶ አደሩ በማኅበር ተደራጅቶ በመንቀሳቀሱ በግብርናው ላይ የሚያመጣው ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ጥርጥር የለውም።

ይህን አጋርነት ፈጥኖ ማምጣት ግብርና የበለጠ እንዲመነደግ ማድረግ ሊሆን ይችላል። የማኅበር ጥያቄው ፈጥኖ እንዲመለስ ማድረግ ይገባል፤ ይህን ማጓተት መጅ እንደመደበቅ ይቆጠራል። ይህን ዘርፍ የሚያንቀሳቅሰው አርሶ አደር ከሦስት አስርተ ዓመታት በፊት አረረም መረረ ስለራሱ የሚናገርበት የራሱ የሆነ መድረክ ነበረው። የመላ ኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኅበር የተሰኘ። ከላይ ጠቅሼዋለሁ።

ኢሕአዴግ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ይህ ማኅበር ሕልውናውን እንዲያጣ አደረገው እንጂ ትልቅ ማኅበር ነበር። ‹‹ረጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈ ራሩበት›› እንደሚባለው ማኅበር መመሥረት ፋይዳ አለው። መኖሩ የአርሶ አደሩን መብት ለመግፈፍ የሚንቀሳቀሱ ካሉ እንዲታቀቡ ማድረግ ያስችላል። በማዳበሪያ በምርጥ ዘር በቴክኖሎጂ አቅርቦት በኩል ያሉትን ጥያቄዎች ሊያነሳበት ይችላል። አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ አጋርነት ቢመሰረትበትስ።

እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ የአህያ ባል ከጅብ አያስጥልም ከሚሉት አይደለሁም። በሌሎች ማኅበራት ላይ የሚታየው ጉድለት አዲስ በሚቋቋም ማኅበር ላይ ሊከሰት ይችላል ብዬ ማኅበሩ አለመቋቋሙን አልደግፍም። የሆነ ችግር ሊፈታ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።

ይህን መሥራት ማለት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ መሥራት ነው፤ አርሶ አደሩ ለምርቱ ተገቢውን ገበያ እንዲያገኝ መሥራት ነው። የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መሥራት ነው። አርሶ አደሩ በማኅበር ተደራጅቶ መብቱን እንዲያስከብር አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው ።

በራሱ ብርቱዎችን ለመሸለም፣ ደካሞችን ለማጠንከር የሚችልበት እድል እንዲኖረው ማስቻል ነው። የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ መጋራት፣ ከአቻ ማኅበራት ጋር በመሥራት የግብርናውን ዘርፍ ይበልጥ ማሳደግ፣ ሕይወቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችለውን ሁኔታ መፍጠር ነው ።

”ረጅም ጦር ባይወጉበት ያስፈራሩት” እንደሚባለው የማኅበሩ መኖር አፍጠው፤ አግጠው ሊመጡ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ ለመቋቋም ይጠቅማል። የማኅበሩ መኖር በራሱ አንዳንድ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ያስችላል። አርሶ አደሩ ማኅበሩን በመመሥረቱ ብቻ ሊፈጠር የሚችል ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ /ተጠቃሚ የሚያደርገው ሊኖር እንደሚችል ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል። የማኅበሩ መኖር በራሱ ትልቅ ፋይዳ አለውና ማኅበሩን እውን ለማድረግ ሀሳቡን ያነሳችሁ ጥረታችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ።

ለአርሶ አደሩ የቅርብ ድጋፍ የሚያደርጉ መንግሥታዊ አካላት፣ ሌሎች የዘርፉ አካላት ለእዚህ ማኅበር እውነትነት ሊተጉ ይገባል። የአርሶ አደሮች ቀን እንዲከበር የአርሶ አደር ማኅበር እንዲመሠረት ሀሳቡን ያነሳችሁ ያዳበራችሁ በቀጣይም በዚህ ላይ ለመሥራት ኃላፊነቱን የወሰዳችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል። እደገመዋለሁ፤ ማኅበሩ እውን እንዲሆን ሀሳቡን ያነሳችሁ አካላት ርብርባችሁን አጠናክራችሁ በመቀጠል ታሪክ ሥሩ እላለሁ።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 17 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You