በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ወልመራ ወረዳ አንደኛ በርፈታ(በርፈታ ቶኮፋ) ቀበሌ ውስጥ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ጎረቤታሞች በሀገር ባሕል ልብስ ደምቀዋል። ምክንያታቸው ደግሞ ቀኑ ለእነርሱ የተለየ ስለነበር፤ ደስታቸውን ለመግለፅ አስበው ነው፡፡ ቀኑ ለማገዶ የሚሆን የከብት እዳሪ በመጠፍጠፍ ልስላሴውን አጥቶ የነበረውን እጃቸውን ከጉዳት የሚመልስላቸው ቴክኖሎጂን ማግኘት የቻሉበት ነው፡፡
ቀደም ሲል የሚጠቀሙት የማገዶ ቴክኖሎጂ ጭስ የሰውነትና የልብሳቸውን ጠረን የሚቀየር ብቻ ሳይሆን፤ ለዓይን ሕመምና ለሌላም የጤና ችግር በማጋለጥ ያስከትልባቸው የነበረው ችግር ቀላል አልነበረም፡፡ አዲሱ ቴክኖሎጂ እነዚህን ችግሮች የሚያስወግድላቸው እና በአጠቃላይ የማጀታቸውን ሥራ የሚያቀልላቸው በመሆኑ የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮላቸዋል፡፡
በዕለተ ዓርብ በቀበሌው ተገኝተን የአካባቢውን ሴቶች ደስታ ስንጋራ እንደገለፁልን፤ የመንደሩ ሴቶች የባዮጋዝ ተጠቃሚ ከሆኑ ገና አንድና ሁለት ወራቸው ነው፡፡ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ እፎይታ ማግኘታቸውን ይናገራሉ፡፡ ለማገዶ የሚሆን ኩበት ለማግኘት የከብት እዳሪን አጠራቅሞ መጠፍጠፍና የእንጨት ማገዶ ለቅሞ ማዘጋጀት የዘወትር ሥራቸው ነበር፡፡ ከአባወራውና ከልጆች በፊት ከእንቅልፍ ማልዶ በመነሳት እሳት አያይዞ ምግብ ማዘጋጀት የሴቷ ኃላፊነት በመሆኑ በዚህ መልኩ ሴቶቹ በየቀኑ ይደክማሉ። አሁን ግን ባዮጋዝ ተጠቃሚ መሆናቸው ድካማቸውን አቅልሎላቸዋል፡፡
እኛም በስፍራው በተገኘንበት ወቅት በባዮጋዝ የተዘጋጀ ምግብ፣ ቡናውም እንዲሁ ከፊታችን በባዮጋዝ ኃይል ፈልቶ ቀረበልን፡፡ በባዮጋዝ ኃይል አማካኝነት ሙዚቃም ከፍተው ነበር፡፡ በባዮጋዝ ተጠቃሚ የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች ለቤታቸው የመብራት አገልግሎት ከማግኘታቸው ባለፈ ለከብቶች መኖ የሚውለው የመቆራረጫ መሣሪያም በባዮጋዝ ኃይል ታግዞ ጥቅም እየሰጠ ነበር፡፡
በበርፈታ ቶኮፋ አካባቢ የባዮጋዝ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ እመቤት አዱኛ አንዷ ናቸው። እርሳቸው እንዳሉት በባዮጋዝ መጠቀም ከጀመሩ ሁለት ወራቸው ነው፡፡ እንደቀድሞ ማገዶ ለማዘጋጀት አይጨነቁም፡፡ ምግብ ለማዘጋጀትም በማለዳ መነሳት አይጠበቅባቸውም። ልጆቻቸውም ቁርስ በመጠበቅ ትምህርት ቤት አይረፍድባቸውም፡፡
ልጆች ሻይ የማይጠጡበት ጊዜም ነበር፡፡ ባዮጋዝ መጠቀም ከጀመሩ በኋላ ግን በፍጥነት የሚፈልጉትን ነገር ለመሥራትና ድካም በመቀነስ እፎይታ ሰጥቷቸዋል። ልጆቻቸው መብራት ባለመኖሩ ማታ ለማጥናት ትልቅ ችግር እንደነበረባቸው ያስታወሱት ወይዘሮ እመቤት፤ የሚሰጣቸውን የቤት ሥራ ለመሥራትም ሆነ ለማጥናት የነበረባቸው ችግር ተቃልሎላቸዋል፡፡ ባዮጋዝ እንደ ኤሌክትሪክ መብራት ይጠፋል፡፡ ይቆራረጣል ብለው አያስቡም፡፡ በፈለጉት ሰዓት ለኩሰው መጠቀም መቻላቸው ሌላው ትልቁ ጥቅማቸው እንደሆነም ገልጸውልናል፡፡
ወይዘሮ እመቤት ከአካባቢው የመጀመሪያዋ ተጠቃሚ እንደመሆናቸው፤ የነበረውንም ሂደት እንዲህ ነግረውናል፤ ፈቃደኝነታቸውን ሲጠየቁ የተቀበሉት በደስታ ነበር፡፡ ወቅቱ ክረምት ስለነበር ጭቃ በመሆኑ የተከላ ሥራ መሥራት ባለመቻሉ የሚሠሩት ሰዎች ትተው በመሄዳቸው ተናድደው ነበር፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ግን ተጠቃሚ መሆን በመቻላቸው ደስታ ተሰምቷቸዋል።
ቦታ ከማዘጋጀት ውጭ ምንም አይነት ወጪም እንዳላወጡ የተናገሩት ወይዘሮ እመቤት፤ የባዮጋዝ ተጠቃሚ ለመሆን ፍቃደኝነትና ዝግጁ መሆን፤ በቅድሚያም ሥልጠና መውሰድ እንደሚጠበቅና ሥልጠናውን የወሰዱትም ባለቤታቸው እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ እርሳቸውም በሂደት ስለአጠቃቀሙ ለማወቅ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ በበጋ ወቅት የመኖ እጥረት በመኖሩ እበት በሚፈለገው መጠን ማግኘት ግን ችግር እንደሆነ ነው ወይዘሮ እመቤት የገለጹልን፡፡
‹‹ጥቅሙን የሚያውቀው ያየ ነው፡፡›› በማለት፤ ሀሳባቸውን ያካፈሉን ሌላዋ የመንደሩ ነዋሪ ወይዘሮ የሺእመቤት ሰለሞን ናቸው፡፡ በርፈታ ቶኮፋ ተወልደው ያደጉበት፤ ተኩለው የተዳሩበትና የቤተሰብ ኃላፊ የሆኑት በእዚሁ አካባቢ ነው። እዚህ እስኪደርሱ ድረስ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን አላዩም፡፡ ተድረው ከቤት እስኪወጡ ድረስ ቤተሰባቸውን ለማገዶ የሚሆን እበት በመጠፍጠፍ፣ ማገዶ ለቅመው በማዘጋጀት፣ በአጠቃላይ የማጀቱን ሥራ ሲያግዙ እንደነበርና ትዳር ከያዙም በኋላ በተመሳሳይ እርሳቸውም በድካም ውስጥ እንዳለፉ አጫወቱን፡፡
ከቤተሰባቸው ጀምሮ ድካሙን ስለሚያውቁት የባዮጋዝ ተጠቃሚ መሆናቸው አስደሰቷቸዋል፡፡ ‹‹ድካም ቀርቶልኝ፣ ልጆቼም በሰዓቱ ምግብ አግኝተው፣ ልብሴም አይቆሽሽም፣ እሳት አይለበልበኝም፤ የተጠቀምኩት እረ ብዙ ነው፡፡›› ሲሉ በደስታ ይናገራሉ፡፡ የባዮጋዝ ተጠቃሚ መሆናቸው ጊዜ እንዲያገኙ እንዳደረጋቸውና ያተረፉትንም ጊዜ ቤት በማጽዳትና የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮቻቸውን እንደሚያከናውኑበት ገልጸውልናል፡፡
ስለአጠቃቀሙም ወይዘሮ የሺእመቤት እንደነገሩን፤ አራት ጀሪካን እበት በስምንት ጀሪካን ውሃ በመበጥበጥ ለተወሰነ ደቂቃ ካስቀመጡ በኋላ የሚጣራ ቆሻሻ ካለ አጣርተው ለኃይል ማስተላለፊያ ወደ ተዘጋጀው ይገለብጣሉ። ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም ኩበት እንደመጠፍጠፍና ማገዶ እንደመልቀም፣ በጭስ ከመጎዳት ጋር ለንጽጽር እንደማይቀርብ ነው ያስረዱት፡፡
የማገዶ ማብሰያ ለመጠቀም እሳት ለማያያዝ በትንፋሽ መጠቀም ግድ እንደሆነና ይህም ከመተንፈሻ አካል ጋር በተያያዘ ለጤና ችግር እንደሚያጋልጥ ከተሞክሯቸው የነገሩን ወይዘሮ አስካለ ደጉ፤ እንዲህ ካለው የጤና ችግር የሚታደጋቸው የባዮጋዝ አገልግሎት ማግኘታቸው እንደሌሎች ጎረቤቶቻቸው ሁሉ እርሳቸውም ተደስተዋል። ‹‹እንግዳ ቢመጣብኝ፣ ወደ መንገድም ፈጥኜ ለመሄድ ባስብ ገና እሳት አያይዤ የሚል ጭንቀት የለም፡፡ ምድጃዬን ለኩሼ የሚያስፈልገኝን ሁሉ ተጠቅሜ ጉዳዬን መፈጸም እችላለሁ፡፡ እንግዳዬንም አስተናግዳለሁ፡፡›› ይላሉ፡፡
እንዲህ ጊዜያቸውን የሚቆጥብና ድካማቸውን የሚያቃልላቸው ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንሆናለን ብለው አስበው እንደማያውቁ የሚናገሩት ወይዘሮ አስካለ፤ ረጅሙን ጊዜ በችግር ቢያሳልፉም አሁን ማግኘታቸውም አልረፈደም ይላሉ፡፡ ሌሎች ተጠቃሚ ያልሆኑ የአካባቢያቸው ሰዎች እንደርሳቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተመኝተውላቸዋል፡፡
በባዮጋዝ እየተጠቀሙ ያሉት ወጥ ለመሥራትና ቡና ለማፍላት ብቻ እንደሆነ የገለጹልን ወይዘሮ አስካለ፤ እንጀራ መጋገር አለመቻላቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ እንዳላወቁት ይናገራሉ፡፡ ባዮጋዝ መጠቀም ከጀመሩ ገና አጭር ጊዜ በመሆኑ ወደፊት እንደሚጠቀሙ ተስፋ አድርገዋል፤ ‹‹አካባቢው ላይ እንግዶች በዝተው ሲያዩና የተጠቀሙ ሴቶችም ደስታቸውን ሲገልጹ በማየታቸው ደስ ብሏቸው መገኘታቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹ምን ተባለ? የሚለውን ከሌሎች ከምሰማ በአካል ተገኝቼ እራሴው ባረጋግጥ ይሻላል ብዬ የመጣሁት ማንም ሳይጠራኝ ነው›› በማለት በስፍራው መገኘታቸውን የነገሩን የ65 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ወይዘሮ ጅሩ በዳዳም የዚሁ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ወይዘሮ ጅሩ ስለባዮጋዝ ጥቅም ገና ማወቃቸውን ነው የነገሩን፡፡ በተለይ እንደርሳቸው አቅመ ደካማ ለሆኑ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘባቸውንም ነው የገለጹልን። ‹‹የገጠሯን ሴት ድካምና ጫና ለመቀነስ አስበው እንዲህ ያለውን ጥሩ ሥራ የሠሩ ሰዎች ሊመሰገኑ ይገባል›› ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ጅሩ እንዳጫወቱን፤ ባለፈው ሥርዓት የሴቶች ሊቀመንበር ሆነው ለ17 ዓመታት በሦስት ቀበሌ ውስጥ ተዘዋውረው ሲሠሩ እንዲህ ያለ ቴክኖሎጂ አላጋጠማቸውም። ያኔ ኖሮ ቢሆን ከራሳቸው አልፈው ብዙዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ያኔ በኃላፊነታቸው ዘመን በአካባቢው ላይ የመፀዳጃ ቤት እንዲሠራ፣ የመጠጥ ውሃ እንዲገባ፣ የደን ልማት ሥራ ላይ በስፋት ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡
እንዲህ እንደ ወይዘሮ ጅሩ ያሉ ለመጠቀም ማንንም አንጠይቅም ብለው ከመንደራቸው የመጡ ሁሉ በታደሙበት የበርፈታ ቶኮፋ መንደር ነዋሪዎች የባዮጋዝ ተጠቃሚ መሆናቸው በይፋ ተበሰረ፡፡ በአውሮፓ ኅብረት የገንዘብ ድጋፍ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየሠራ የሚገኘው ኤስ ኤን ቪ ኢትዮጵያ (SNV) የተባለ ድርጅት የበርፈታ ቶኮፋ መንደር ነዋሪዎችን የባዮጋዝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስቻለ።
በኤስ ኤን ቪ ኢትዮጵያ በባዮጋዝ ፕሮግራም የፕሮዳክት ዲቨሎፕመንት ኳሊቲ ማኔጅመንት ቲም ሊደር አቶ ተስፋዬ ዓለማየሁ ስለአጠቃላይ ፕሮግራሙ እንደነገሩን፤ ባዮጋዝ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው እ.ኤ.አ 2008 ነው፡፡ በዚህም ቴክኖሎጂውን ኢትዮጵያ ውስጥ በማምጣት ኤስ ኤን ቪ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል። ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊትም ፕሮግራም አተገባበር ሰነድ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በአፍሪካ ደረጃ የአፍሪካ ባዮጋዝ ተብሎ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ዩጋንዳ፣ታንዛኒያና ቡርኪናፋሶ ሀገሮችን ያካተተ ፕሮግራም ነበር፡፡
እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2017 ድረስ የተካሄደው ፕሮግራም በኔዘርላንድ መንግሥት እና በተለያዩ ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ የታገዘ ነበር፡፡ ከ2017 ጀምሮ ደግሞ እስካሁን ድረስ ላለው ለሁለተኛው ምዕራፍ የአውሮፓ ኅብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የሁለትዮሽ ፈንድ በማድረግ በጋራ ፕሮግራሙን ሲያስኬዱ ቆይተዋል፡፡
በእነዚህ ጊዜያቶች የተለያዩ የተሻሻሉ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂዎች በመተግበር አሁን ላይ ስድስተኛውን የባዮጋዝ ዲዛይን ወደ ሀገር ውስጥ በማምጣት የተከናወነ ሲሆን፣ እስካሁንም ከ180ሺ በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደረገ ወደ 25ሺ ባዮጋዝ ተሠርቷል። የገጠሯ ሴት ለማብሰያ በምትጠቀመው ማገዶ ለሳንባ በሽታ፣ ለዓይን ትራኮማና ለተለያየ የጤና ችግር ተጋላጭ የምትሆንበትን ሁኔታ በማስቀረት፣ የአካባቢ ብክለትንም በመቀነስ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለመጨመርም ባዮጋዝ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አቶ ተስፋዬ ያስረዳሉ፡፡
ባዮጋዝ ለመብራት አገልግሎት ከመዋሉ በተጨማሪ ተረፈ ምርቱ ለተለያየ የሰብል ልማት በማዋል አርሶአደሩ ለማዳበሪያ ግዥ የሚያወጣውን ወጪ ለመቀነስ እንደሚያግዘውም አስረድተዋል፡፡ ይህ የሁለተኛው ምዕራፍ እ.ኤ.አ 2024 ላይ እንደሚያበቃ የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ ፕሮግራሙ ለገጠሩ ማኅበረሰብ ጠቃሚ በመሆኑ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል፡፡ እስካሁን በተሠሩት ሥራዎች በሀገር ውስጥ ሙያተኞችን ማፍራት በመቻሉ መንግሥት ሥራውን በማስቀጠል እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂ ነፃ እንዳልሆነና የማኅበረሰብ ተሳትፎም እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። እስካሁንም የተሠሩት ሥራዎች በለጋሾች፣ በመንግሥትና በማኅበረሰብ ተሳትፎ የተሳኩ መሆናቸውንና ይኸው ሊጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ አካባቢው ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ማኅበረሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀምበት እየተሠራ ስላለው ሥራም በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሸዋ ዞን የውሃና ኢነርጂ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ታፈሰ ገልፀውልናል፡፡ በምዕራብ ሸዋ ዞን ወልመራ ወረዳ ባዮጋዝ በመጠቀም ሞዴል ወረዳ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ከወረዳው አንዱ የሆነው በርፈታ ቶኮፋ ቀበሌ በሞዴልነት የተመረጠው ሌሎች ቀበሌዎችም ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት ተጠቃሚ በመሆኑ ነው ብለዋል። ቀበሌው ሞዴል የሆነው ፕሪፋብሪኬትድ የሚባለው አዲስ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ መግባቱንም ጨምር መሆኑን አስታውሰው፤ ቀደም ሲል በሲሚንቶ፣ አሸዋ ግብዓቶች ይሠራ የነበረው ቴክኖሎጂ በፕላስቲክ መተካቱ ቴክኖሎጂውን ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
ግብረሠናይ ድርጅቶች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በምዕራብ ሸዋ ዞን በሚገኙ 23 ወረዳዎች ቴክኖሎጂውን ተደራሽ ለማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገዛኸኝ፤ ከዚህ ቀደም በመንግሥት በጀት የማይያዝለት እንደነበርና በ2016ዓ.ም ግን ትኩረት ተሰጥቶ በዞኑ ለባዮጋዝ ግንባታ የሚውል ከ16ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መመደቡን ገልጸዋል፡፡
በተለይም የኤሌክትሪክ መብራት አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው የዞኑ አካባቢዎች የባዮጋዝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቅድሚያ በመስጠት እየተሠራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ወደ 160 ባዮጋዝ እንዲሠራ በእቅድ ቢያዝም ከእቅድ በላይ ለመሥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና እስካሁን ከእቅድ በላይ መሥራት የሚያስችል ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።
የሥራ ተነሳሽነቱ ቢኖርም ለባዮጋዙ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ገበያ ላይ ማግኘት ተግዳሮት መኖሩን አቶ ገዛኸኝ አንስተዋል፡፡ የባዮጋዝ ግንባታው የትምህርት ቤቶችንና ሌሎችም ተቋማት ተጠቃሚ እንዲያደርግ የሚሠራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ቴክኖሎጂዎች ሥራ ላይ ሲውሉ ለመቀበል ፍቃደኛ አለመሆን፣ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ደግሞ በአግባቡ ያለመጠቀም ሁኔታ መኖሩን ያነሳንላቸው አቶ ገዛኸኝ፤ ያለመቀበሉ ሁኔታ ቀደም ሲል የነበረ ቢሆንም አሁን መቀረፉን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ባለቤቶቻቸው ፍቃደኛ ባይሆኑ እንኳን ሴቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ተጠቃሚ በመሆን ሞዴሎችን ማፍራት መቻሉንም አመልክተዋል፡፡ አዳዲስ የቴክሎጂ ሽግግር ሲደረግ ባለሙያዎችም አብረው እንዲሠለጥኑ ባለመደረጉ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ለሚያጋጥም ችግር መፍትሔ ለመስጠት ተግዳሮት መኖሩን አቶ ገዛኸኝ አልሸሸጉም፡፡ በተቻለ መጠን ግን በክትትል ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡
ተረፈ ምርቱ ለግብርና ግብዓት መዋሉ፤ የኬሚካል ማዳበሪያን የዋጋ ውድነት ከመቀነሱ በተጨማሪ በተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም ለጤና ተስማሚ የሆነ ምርት ማግኘት ማስቻሉን ጠቅሰው፤ በዚህ መልኩ ከቀጠለ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የአፈር ለምነትን መመለስ እንደሚቻል አስረድተዋል። አርሶአደሩም ግብዓቱን ገበያ ላይ በማዋል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እንደቻለም አቶ ገዛኸኝ ነግረውናል፡፡
ከኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ርቆ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል በገጠር ኢነርጂ አማራጭ ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት ፖሊሲና አቅጣጫ ቀርጾ እየሠራ መሆኑንም በውሃና ኢኒርጂ ሚኒስቴር የገጠር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ልማትና ሽግግር መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብርሃኑ ወልዱ ነግረውናል። ላለፉት አስር ዓመታት ከ48ሺ በላይ የባዮጋዝ ማመንጫዎች ተገንብተው ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ገልጸውልናል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም