ለፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማነት፣ ምሕረት የለሽ ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል!

ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ጽሑፍ ሳነብ፣ ጽሑፉ ውስጥ እንዲህ የሚል ሃሳብ ተመለከትኩ። ‹‹… ሙስና በኢትዮጵያ የየዕለት ሕይወት አካል ሆኗል…›› … በእርግጥ ሃሳቡ ሙስና በሀገሪቱ ውስጥ የደረሰበትን ደረጃ ቀላልና ግልጽ በሆነ (አስደንጋጭ ቢሆንም) አገላለፅ ለማሳየት ጥሩ እድል ይፈጥራል፡፡ ይህ ሃሳብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሙስና ወንጀል ለመግለፅ ቢያንስ እንጂ አይበዛም፡፡

ኢትዮጵያን እግር ከወርች ይዘው ጉዞዋን የኋልዮሽ ካደረጉባት አስከፊ ችግሮች መካከል አንዱ ሙስና ነው፡፡ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹በሙስና ውስጥ አለመሳተፍ እና ሙስናን መዋጋት ወንጀል ነው›› የተባለ እስኪመስል ድረስ የወንጀሉ ተሳታፊ ለመሆን የሚደረገው እሽቅድድም እጅን በአፍ ላይ የሚያስጭን ነው፡፡ በጉቦ፣ በምዝበራ፣ በማጭበርበርና በሌሎች የሙስና መልኮች የሚፈፀመው የወንጀል ብዛትና ዓይነት ታይቶም ተቆጥሮም አያልቅም፡፡ ጉዳይ ለማስፈጸም ጉቦ መጠየቅና መስጠት ‹‹በሕግ ያልተፃፈ ግዴታ›› ሆኗል፡፡ የሚጠየቀውና የሚከፈለው የጉቦ መጠን ደግሞ ‹‹ጆሮ አይስማ›› ያሰኛል፡፡

ቀደም ሲል በረቀቀ መንገድ ሲፈፀም የነበረው ሙስና አሁን በማን አለብኝነትና በግላጭ ይደረጋል። ያለጉቦና ዝምድና አገልግሎት ማግኘት ፈፅሞ የማይታሰብ እየሆነ ነው፡፡ በአጠቃላይ ዜጎች ጉዳይ የማስፈጸምና አገልግሎት የማግኘት መብት እንዳላቸው እንዲሁም የመንግሥት ሹማምንትና ሠራተኞች ደግሞ የዜጎችን አገልግሎት የማግኘት መብት የመፈፀምና የማስፈፀም ግዴታ ያለባቸው መሆኑ ጨርሶ ተዘንግቷል፡፡ ‹‹ሌብነትን እየተለማመድነው ይሆን?›› ብሎ የመጠየቂያው ትክክለኛ ጊዜ ላይ ሳንሆን አንቀርም፡፡

በኢትዮጵያ ያለውን የሙስና ወንጀል የከፋና አስፈሪ የሚያደርገው ደግሞ ሙስና ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተጋምዶ ሲፈፀም መቆየቱና አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ ነው፡፡ የጎሳ መዛመድን መነሻ ያደረገ ጥልፍልፍ የሙስና ወንጀል በእጅጉ ተንሰራፍቷል። ይህም በአንድ በኩል ሙስናን ተፀይፈው የሚሠሩ ጥቂት ሐቀኛ ሠራተኞችን፣ በሌላ በኩል ወንጀሉ ያሰባሰባቸው ጎሳ አባል ያልሆኑትን ለማጥቃት ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ሙስና ከጉቦ፣ ከማጭበርበርና ከዝርፊያ የተሻገረ ትርጉምና ውጤት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ገንዘብ በማባከንና ጉቦ በመቀበል የሚቆም ሳይሆን እጅግ አስከፊ ወንጀሎች እንዲበራከቱ በማድረግ ሀገር እንዳትጠገን ሆና እንድትፈራርስ የሚያደርግ አደገኛ መመዘዝን ያስከትላል፡፡

እንዲህ የተንሰራፋውን የሙስና ተግባር ለመቀነስ በየጊዜው ልዩ ልዩ ጥረቶች ቢደረጉም፣ ሙስናን ትርጉም ባለው መጠን መቀነስ ያስቻለ ተጨባጭ ለውጥ ሊመዘገብ ግን አልቻለም፡፡ ከዓመት በፊት ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል። የመንግሥትን ሙሉ አቅም በመጠቀም በተቀናጀና በተናበበ ሁኔታ ሙስና የፈጠረውን ችግር ለመቀልበስ እንደተሰየመ የተነገረለት ኮሚቴው ሰባት አባላት ያሉት ሲሆን፣ መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የማስተባበር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የመለየትና ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለው ተገልፆ ነበር።

በፀረ-ሙስና ዘመቻው የአገሪቱ የጸጥታ እና የፍትሕ ዘርፍ እንዲሁም የመንግሥት የመሬት አስተዳደር ቅድሚያ እንደተሰጣቸው እንዲሁም የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር፣ የፋይናንስ፣ የመንግሥት ገቢ እና ጉምሩክ ሥርዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ አስተዳደር እና የመንግሥት ግዢን የመሳሰሉ ዘርፎች ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል ከተባሉት መካከል እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ በፍትሕ እና በፀጥታ ዘርፍ ሥልጣናቸውን ያለ አግባብ በመጠቀም የዜጎችን ሰላም እና የሀገርን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን ተገን አድርገው በተለያዩ ሕገ-ወጥ መንገዶች ከግለሰቦች እና ከንግድ ድርጅቶች ገንዘብ እና ሀብት ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል ተብሎ መነገሩም የሚታወስ ነው፡፡

ሙስናን ለመዋጋት ተብሎ ኮሚቴ ሲቋቋም ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደምም መሰል ኮሚቴዎች ተቋቁመው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ‹‹በሙስና ላይ ዘመቻ ተከፈተ›› ተብሎ ይወራና ሕዝቡም ‹‹ሙሰኛው ሁሉ ተጠራርጎ ለፍርድ ሊቀርብ ነው›› ብሎ በፀረ ሙስና ዘመቻው ላይ መጠነኛ ተስፋ ሲያደርግ ይስተዋል ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር ተደጋግሞ ተደርጎ የዘመቻው ውጤት ግን ከዜሮ ያልተሻለ ሆኖ ሲገኝ፣ ሕዝቡም ተሰላችቶ ዘመቻውን ‹‹ጉራ ብቻ›› ብሎ ሲገልፀው ነበር፡፡ ‹‹ቀደም ሲል የተቋቋሙ የፀረ ሙስና ኮሚቴዎችስ የት ደረሱ? ምን ተግባራትንስ አከናወኑ?›› ተብሎ ቢጠየቅ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡

በእርግጥ ብዙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በፀረ-ሙስና ዘመቻው በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ድረስ ሙስናን ለመከላከል በተሠራ የቅድመ መከላከል ሥራ፣ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ከምዝበራ ማዳን እንደተቻለ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ከ829 ሚሊዮን ብር በላይ በሙስና የተገኘ ገንዘብም ተመላሽ ሆኗል፤ ከአንድ ኪሎ ግራይ በላይ ወርቅ ወደ መንግሥት ካዝና እንዲገባ ተደርጓል፤ ከአራት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከምዝበራ ማዳን ተችሏል፡፡

‹‹ለመሆኑ የዘመቻ ተግባር ለሙስና ችግር ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል?›› ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የፀረ ሙስና ዘመቻ ሙስናን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስና ከስሩ ለመንቀል ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሔ አይሆንም! ‹‹የሀገር የደኅንነት ሥጋት ሆኗል›› የተባለ ችግር ሐቀኛና ዘላቂ በሆነ ስር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ እንጂ በአንድ ሰሞን ዘመቻ መፍትሔ አያገኝም። ሙስና መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ መገለጫም እየሆነ ነው፡፡ ‹‹ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል›› በሚል ብሂል የሚኖርና ሐቅንና መርሕን ተከትሎ ሥራን የሚሠራን ሰው ‹‹ሞኝ፣ ጅል›› ብሎ የሚያሸማቅቅ ኅብረተሰብም ሆነ በሥርዓትና በመዋቅር ታግዞ የሚዘርፍና የሚያጭበረብር ሹመኛና ሠራተኛ በዘመቻ አይደነግጥም፡፡

ዘመቻውን እያካሄድኩ ነው የሚለው መንግሥትም ሙስናን ለመዋጋት ከልቡ ቁርጠኛ ሊሆን ይገባል፡፡ ስር ለሰደደ ችግር የአንድ ሰሞን ዘመቻን መፍትሔ አድርጎ መመልከት፣ በሙስና ላይ የመዝመት ፅኑ ፍላጎትን አያሳይም፡፡ ስለሆነም ለሐቀኛና ዘላቂ መፍትሔ ዝግጁ በመሆን ዘመቻው ከአንጀት መሆኑን ማሳየት ይገባል፡፡ አለበለዚያ ግን ነገሩ ሁሉ ከአንጀት (የእውነት) ሳይሆን ከአንገት (የይምሰል) እንደሆነ ይቆጠራል፡፡

ሙስና በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለውና እየፈጠረ የሚገኘው ቀውስ በቃላት ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ችግሩ በአጭር ጊዜ ከሚታይ የአገልግሎት አሰጣጥ ብልሽት እስከ ትውልድ መምከንና ሀገር መፍረስ የሚደርስ አሰቃቂ ቀውስን የሚያስከትል አደጋ ሆኗል፡፡ ኅብረተሰቡ በተቋማት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር በማድረግ በመንግሥት ተስፋ ይቆርጣል። ከዚህ ባሻገርም ሙስና ሞራልንና ሥርዓትን በገንዘብና በዝምድና በመተካት ማኅበረሰባዊ መስተጋብርና መተማመን እንዲዳከም በማድረግ የሀገር መፍረስን ያስከትላል፡፡

ሀገራት ሙስናን ለመታገል የተለያዩ የአሠራር ሞዴሎችን ይተገብራሉ፡፡ አንዳንድ ሀገራት ሙስናን በመከላከል ላይ ብቻ የሚያተኩር ሥርዓት (Corrup­tion Prevention Model) ሲዘረጉ፣ ሌሎች ደግሞ የሕግ ማስከበር ትኩረት የሚሰጥ አሠራር (Law En­forcement Model) ይተገብራሉ፡፡ መከላከልን እና ሕግ ማስከበርን ያጣመረ ሥርዓትን (Multi-Purpose Anti-Corruption Model/The Universal Mod­el/) የሚተገብሩ ሀገራትም አሉ፡፡

የሙስናና ብልሹ አሠራር ችግሮችን ለመቅረፍ በየተቋማቱ ያሉ የሥነ-ምግባር መከታተያ ክፍሎች በተቋሞቻቸው ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት የሚስችል የአሠራር ሥርዓት ጥናት እንዲያካሂዱ የሚያስችላቸውን የሥራ ነፃነትና አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ የፌደራል የሥነ-ምግባር ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የጥናት ምክረ ሃሳቦች ይጠቁማሉ፡፡ መሰል የአሠራር ሥርዓት ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ተከስተው ከፍተኛ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ለችግሩ መንስኤ የሚሆኑ ሁኔታዎችን መርምሮ በማውጣት የመፍትሔ ሀሳቦችን በማቅረብ ችግሮች ከወዲሁ እንዳይከሰቱ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግልጽ የሆነ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የሚፈጠሩ የሙስናና ብልሹ አሠራር ችግሮች በቀላሉ እንዲጋለጡ ለማድረግ ያግዛል፤ የሥነ-ምግባር ትምህርትና ሌሎች የመከላከል ሥራዎች የሚያተኩሩባቸውን የሥራ አካባቢዎች ለመወሰን በማስቻልም ረገድ ዕገዛ ያደርጋል፡፡ ይህ የአሠራር ጥናት ለሙስናና ብልሹ አሠራር የሚዳርጉ የአሠራር ክፍተቶችን እንዲለይ እና የታዩ ክፍተቶችን ለመፍታት የሚያግዙ የማሻሻያ/የመፍትሔ ሃሳቦችን እንዲጠቁም ይጠበቃል፡፡

የመንግሥት ንብረትና ገንዘብ አላግባብ እንዲባክን፣ ተገልጋዮች እንዲጉላሉ፣ ለሥነምግባር ተቃራኒ የሆነ ድርጊትን ወይም ባሕርይን የሚያበረታታ ወይም እንዳይፈጸሙ የማይከላከል፣ ለብልሹ አሠራር የተጋለጠ፣ የአሠራር ሥርዓትን በፅናትና በሐቀኛነት መታገል ያስፈልጋል፡፡ ሁሉንም የሙስና ስጋቶች በአንድ ጊዜ ለመቅረፍ አዳጋች በመሆኑ የሙስና ተጋላጭነት ደረጃን እና ሙስና ቢፈፀም ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ቀዳሚ/ከፍተኛ ተብለው የሚገመቱትን በመለየት የፀረ-ሙስና ዘመቻውን ማካሄድ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ሙስናን ለመከላከል የተተገበሩ አሠራሮች በቂ ውጤት እንዳላስገኙ በመገንዘብ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ከመስጠት ጀምሮ ጠንካራ የሕግ ማስከበር እርምጃዎችን መውሰድ ይገባል፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ በትክክለኛ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጫ ከሚሆኑ መለኪያዎች መካከል አንዱ ጠንካራ፣ ነፃና በሕዝብ ተቀባይነት ያለው የፀረ ሙስና ተቋማት አደረጃጀት መፍጠር ነው፡፡ ስለሆነም የፀረ-ሙስና ትግሉ ከመንግሥትም ሆነ ከገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ በተላቀቀና ጠንካራ መሠረት ባለው ነፃና ገለልተኛ ተቋም ሊመራ ይገባል፤ ተቋሙ ለፀረ-ሙስና ዘመቻው ቁርጠኛ በሆኑ ሀገር ወዳድ ባለሙያዎች እንዲመራና እንዲዋቀር መደገፍም ያስፈልጋል። የሙስና መከላከልና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን በተለያዩ ተቋማት ማከናወን የፀረ ሙስና ትግሉ የተበታተነ እንዲሆን በማድረግ ትግሉ እንዲዳከም ስለሚያደርግ፣ የፀረ-ሙስና ተቋማት አደረጃጀቶች ለትግሉ ውጤታማነት አመቺ ሊሆኑ ይገባል፡፡

‹‹ሙስና ጠላታችን ነው›› ብሎ ከመናገር አልፎ ድርጊቱን በተግባር ለማሸነፍ የሚያበቃ ቁመና መላበስ ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን የነበረውንና አሁንም ያለውን የፀረ ሙስና ሥርዓትና አደረጃጀት ጉድለቶች በአግባቡ ፈተሾ የማስተካከያ ርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ የሙስና አስተሳሰብንና ድርጊትን የሚጠየፍ ኅብረተሰብና መንግሥት መፍጠር ካልተቻለ፤ ጠንካራና የተረጋጋ አገር፣ መንግሥትና ኅብረተሰብ ለመፍጠር ያለው ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡

የፀረ ሙስና ትግሉን በዋናነት እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት ጠንካራና ተከታታይነት ያለው የመረጃ ልውውጥ፣ የመደጋገፍ እንዲሁም በፀረ ሙስና ትግሉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመለየት የሚያስችል የተቀናጀ አካሄድ መከተል ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሙስናን የመዋጋት ትግሉ ለጥቂት ተቋማት ብቻ የሚተው ተግባር ባለመሆኑ ሁሉም ዜጋ የፀረ ሙስና ትግሉን በዋናነት እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት ለተሰጣቸው ተቋማት ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው የነበሩት የፀረ ሙስና ትግሎች የተኮላሹት መንግሥታት በሚፈለገው ልክ ድጋፍና እገዛ ባለማድረጋቸው ነው፡፡ ስለሆነም ለፀረ ሙስና ትግሉ ጠንካራ መንግሥታዊ የድጋፍ ሥርዓት በመፍጠር ምሕረት የለሽ ተጠያቂነትን ማስፈን ይገባል፡፡

የትምህርት ተቋማትን፣ መገናኛ ብዙኃንን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ መደበኛ ያልሆኑ የማስተማሪያ ዘዴዎችንና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ ኅብረተሰቡ ሠርቶ መበልፀግን ብቻ አማራጭና ባሕል እንዲያደርግ እንዲሁም የፀረ-ሙስና ትግሉ ባለቤትና ዋና ተዋናይ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ ቁርጠኛነት ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ፣ ሙስና የሀገር ሕልውና አደጋ እንደሆነ ሊታወቅና፣ ለፀረ- ሙስና ዘመቻው ሊሰጥ የሚገባው ትኩረት ይህን መራራ እውነት የሚመጥን ሊሆን ይገባል!

ፒያንኪ ዘኢትዮጵያ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You