አዲስ አበባ፡– በተያዘው በጀት ዓመት በመጀመርያው ሦስት ወራት ውስጥ በመዲናዋ በቱሪዝም ዘርፍ 17 ቢሊዮን 250 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ መንቀሳቀሱንና ወደኢኮኖሚው ፈሰስ መደረጉን የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሓፍታይ ገብረእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ በሩብ ዓመቱ 268 ሺህ 80 የሚሆኑ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ከተማዋን ጎብኝተዋል።
በበጀት ዓመቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የከተማው ቱሪዝም የተሻለ መነቃቃት ታይቷል ያሉት አቶ ሓፍታይ፤ የተገኘው ውጤት በገቢና በቱሪስት ፍሰት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል። በከተማው የቱሪስቶች ቆይታ ለማድረግ ትኩረት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በከተማዋ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ሀብት ወደ ኢኮኖሚ ቀይሮ ለመጠቀም በዘርፉ ያሉ ችግሮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
የቱሪዝም ዘርፉ ለከተማው ኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ አስተዋጾ እያበረከተ እንደሚገኝም ኃላፊው ተናግረዋል።
በከተማው እየተገነቡ የሚገኙ ሰፋፊ መሠረተ ልማቶች ለከተማው ቱሪዝም ዘርፍ ያላቸው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው ያት አቶ ሓፍታይ፤ በተለይ የዓድዋ ሙዚዬምና የአፍሪካ ኮንቬንሽን ሴንተር ለዘርፉ ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በከተማው የተገነቡ ፓርኮችና የመዝናኛ ሥፍራዎች ዋነኛ የቱሪስት መስህብ እየሆኑ እንደሆነ ጠቁመው፤ የቱሪዝምን ኢኮኖሚ እያሳደጉ እንደሚገኙም አመላክተዋል።
እንደ አቶ ሓፍታይ ገለጻ፤ ቱሪዝምን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከማስተዋወቅ አንጻር ውስንነቶች አሉ። ይህንን ችግር ለመቀነስ በቀጣይም በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ቱሪዝምን ለማስተዋወቅ በከንቲባዋ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ የቱሪዝም ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
ልጅዓለም ፍቅሬ አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም