ሠላም ለኪ

ብዙዎች እንደሚመሰክሩት፣ እኛም (ሌላው እንኳን ቢቀር) ደመነፍሳችን እንደሚነግረን፣ የሠላም ትክክለኛ ትርጉሙ የሚታወቀው እራሱ ሠላም የጠፋ እለትና እኛንም ሠላም የራቀን ቀን ነው። በቃ፣ ከዚህ በላይ የሠላምን ምንነት፣ ስለሠላም ፋይዳና ትርጓሜ የሚናገር የለም። “አለ” ከተባለም ያው የአካዳሚክስ ጉዳይ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም።

ወደ ወቅታዊው የሀገራች የሰላም ሁኔታና ይዞታ በቀጥታ ከመሄዴ በፊት ስለ “ሠላም” ጥቂት ልበል። መቼም የሰላም ጉዳይ ምን ያህል አንገብጋቢ፤ ምን ያህል የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችንን እንደሚገዛው ለመገመት አይከብድም አይደለም ፤ የሰው ልጅ እጣ ፈንታም የቱን ያህል በሠላምና ሠላም ላይ እንደተደላደለ ለመረዳት ብዙም የሚቸግር አይደለም። በተጨባጭ አሁን ላይ እያየነውም ያለነውም ይሄንኑ ነው።

ከዛም ባለፈ እንደ ሀገር፣ የሠላም እጦትም እንበለው የሠላም መደፍረስ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲም ሆነ ሌሎች እንቅስቃሴዎቻችን ላይም ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ፣ የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በተጨባጭ የታየና ሀገርና ሕዝብን በብዙ መልኩ የተፈታተነ ነው። “ውሻ በቀደደው ∙ ∙ ∙” እንደሚባለው ክስተቱ ለታሪካዊ ጠላቶቻችን የጥፋት ሴራ እንደ አንድ እድል ሆኖ የታየበት ሁኔታም እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው ።

አሁን ላይስ፣ “ሀገራችን ምን ላይ ነች?” ከተባለ፣ ተደጋግሞ ሲነገር እንደምንሰማው “አንጻራዊ ሰላም” ላይ ነች። የሰላሙ ደረጃ ምንም ይሁን ምን፣ አሁን ላይ ሀገሪቱ እንደ ሀገር ከነበረችበት የህልውና ስጋት ነጻ ነች። ለዚህ ደግሞ የተከፈለው መስዋእትነት ትልቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ መስዋእትነቱ ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል።

በርግጥ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዛሬም የሰላም ጥያቄ ዋነኛ ጥያቄ ነው። ከሰላም ጋር በተያያዘ በሕዝባችን ውስጥ ያለው ስጋት ገና ብዙ መሥራትን የሚጠይቅ ነው። አሁንም ዜጎች ወጥቶ ለመግባት ብዙ ፈተና አለባቸው። በተለይም በአማራ ክልል ካለው የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ የክልሉ ሕዝብ የተደራረቡ ችግሮች ሰለባ እየሆነ ነው።

ይህ ጸሐፊ ሰሞኑን የዩኒቨርሲቲዎችን የተማሪዎች አቀባበል ለመመልከት ወደ ተወሰኑ ዩኒቨርሲቲዎች ጎራ በማለት፣ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ጦርነት ከተደረገባቸው አካባቢዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር ለመወያየት ሞክሯል። ጦርነቶች ባይኖሩ እነዚህ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ከዛሬ ሶስትና አራት ዓመት በፊት እንደ ነበር በቁጭት ሲናገሩ ታዝቧል።

ቀደም ባለው ጊዜ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ጀምረው ያቋረጡ ተማሪዎችም ያለ ትምህርት እቤታቸው ቁጭ ብለው ወራትን እያሳለፉ ነው፤ እነዚህ ተማሪዎች እንደ ብጤዎቻቸው ተምረው እንዳይመረቁ ያደረጋቸው የሠላም እጦቱ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች ራሳቸው ሲናገሩ እየተሰማ ይገኛል። ይህ ደግሞ ተማሪዎቹ እንዳይመረቁ ብቻም ሳይሆን፣ የተሻለ ነገን እንዳያስቡ እንደሚያደርጋቸው ለማሰብ የሚከብድ አይሆንም።

የሠላም እጦቱ ያደረሰው ጉዳት ይህ ከላይ የጠቀስነው በተማሪዎቹ ላይ ያደረሰው ማህበራዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ብቻ አይደለም፤ ኢኮኖሚውንም ሸንቁጦታል። የሰሞኑን፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የመጀመሪያውን ሩብ በጀት ዓመት የተመለከተ ሪፖርት ያየ (ወይም፣ ያነበበ) ሰው የሀገራችን ሰላም መደፍረስ ኢኮኖሚያችንን ምን ያህል ወደ ኋላ እንደ ጎተተው በግልፅ ይመለክታል።

ሪፖርቱ ከጦርነትና ከግጭቶች የተነሳ ማግኘት እየቻልን ማግኘት ያልቻለውን፤ ያጣነው፣ ከእጃችን ያመለጠውን ሀብት ይመለከታል። “ሠላም ቢሆን ኖሮ ∙∙∙” በማለትም ፀጉሩን ከመንጨትም አልፎ ከንፈሩን ሲነክስ ውሎ ከንፈሩን ሲነክስ ማደሩ የግድ ይሆናል። ችኩልና ስሜታዊ ከሆነም ራሱን ይዞ ሊጮህ ይችላል። እስከዚህ የሚደርስ ሀገራዊ ጉዳት አስተናግደናል።

በያዝነው ወር የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት “በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚታዩ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ምክንያት፣ ሀገራዊ ይዘት ያለው ጥናት ማካሄድ አለመቻሉን ዋና ዳይሬክተሩ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ አስታውቀዋል። ይህም ፣ ከጦርነት ይልቅ ሠላም መሻሉን፤ ሠላም ባለመኖሩ ምክንያት እየሆነ ያለውን፤ በተለይም ከላይ በጠቀስናቸው ወሳኝ ተቋማትና ሌሎችም ላይ እያደረሰ ያለውን ምስቅልቅሎሽ ያመላከተ ነው። አሁንም ምርጫችን ሠላም መሆን እንዳለበት፤ ባስቸኳይ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣት ያለብን መሆኑን የሚጠቁም ነው። እዚህ ላይ የሠላም እጦት በገቢ ላይ ያደረሰውን አደጋ አነሳን እንጂ እራሱ ግጭቱ እየበላው ያለውን፣ የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ከዚሁ ጋር አክለን እንየው ብንል ስሌቱ የቱን ያህል የከፋ እንደሚሆን ማሰብ አይከብድም፤ በችግሮቻችን ላይ የከፋ ተጨማሪ ችግር ይዞ ስለመምጣቱ ሁለቴ ማሰብ የሚጠይቅ አይሆንም ።

ከሁሉም በላይ በየሥፍራው ንፁህ ሕይወታቸውን እያጡ ያሉት ዜጎች፣ ረሀብ እየቀጣቸው ያሉት ወገኖች፣ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ የህብረተሰብ ክፍሎች … ወዘተ ሲታሰቡ አሁኑኑ ለሰላም በር አለመክፈት ማለት በእነዚህ ሁሉ ላይ መጨከን ነውና ጉዳዩ ጊዜ የሚሰጥ አይደለም።

አሁን ጥያቄው “ምን ይደረግ?”፣ “ምን እናድርግ?” የሚል እንደሚሆን ለማንም ግልፅ ነው። መደረግ ያለበት ከላይ እንዳልነው ከተዘፈቅንበት ጦርነት መውጣት፤ ጨክኖ ምርጫን ሠላም እና ሠላም ላይ ብቻ በማድረግ ለሕዝብ ሠላም እና ደህንነት መሥራት ነው።

ነፍሳቸውን ይማረውና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ተለይተው የሚታወቁባቸው በርካታ አገላለፆች ያሏቸው ሲሆን፤ አንዱም “ደህና ሁን ጠብመንጃ” የሚለው ነው። ፕሮፌሰሩ የዋዛ ሰው እንዳልነበሩ የሚታወቅ ነው። በመሆናቸውም ዝም ብለው “ደህና ሁን ጠብመንጃ” እንደማይሉም የታወቀ ነው።

በሌላ መንገድ “ጠመንጃ ነካሽ አለ” እያሉን ነው። በቀላሉ ከጠመንጃ ነካሽነት ተላቅቆ ጠብመንጃን “ደህና ሁን” የሚል ሰው እንደማይኖር እየነገሩን ነበር። እንዳሉትም ሰውየው “ደህና ሁን ጠብመንጃ”ን በአደባባይ ከለቀቁት ከ25 ዓመታት በላይ ቢያልፍም ትንቢት ይመስል ይኸው እስካሁን ደፍሮ፣ ለሀገርና ለወገኑ ብሎ “ደህና ሁን ጠብመንጃ” ያለ አልተገኘም።

ስለ ሠላም ብሎ፣ ለሠላም ተገዝቶ ∙ ∙ ∙ ለሠላም እጁን የሰጠ አልተገኘም። የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይትን የደፈረ ወፍ የለም። ይባስ ብሎ ነገር አለሙ ሁሉ “ጠብንጃ ፈርስት!!” እየሆነ ያለ ይመስላል። ከፕሮፌሰሩ “ደህና ሁን ጠብመንጃ” ወዲህ እጅግ የከፋ ጦርነት አካሂደናል። አሁንስ አይበቃንም???።

አትዮጵያ፣ ሠላም ለኪ!!! (ሰላም ላንቺ ይሁን!!!)

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 16 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You