በኪሮሽ የሚሰሩ የክር አልባሳት ዲዛይነር

ኢትዮጵያውያን ክርን በመጠቀም በእጅ ለሚሰሩ የሹራብ አልባሳት አዲስ አይደለንም። ከመዘነጫነት ባለፈ እናቶቻችን የቤት እቃዎቻቸውን ለማስዋብ ኪሮሻቸውን (ጥበቡን ለመሥራት የሚጠቅሙበትን መሳሪያ) ተጠቅመው፣ ሹራቦችን በተለያዩ ዲዛይኖች ይሰራሉ። ሙያውን ከራሳቸው አልፎ ለልጆቻቸው ያስተምራሉ። ይህ የእጅ ሥራ ጥበብ ውጤት ዘመናትን የተሻገረ የኢትዮጵያውያን መገለጫ ነው።

አሁን አሁን ደግሞ በክር በሚሰሩ የሹራብ አልባሳት በፋሽን ኢንዱስትሪው በስፋት ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለሙያው ፍቅር ያላቸው ወጣቶች በኪሮሽ የሚሰሩ የሹራብ አልባሳት ሥራን እያስተዋወቁ ይገኛሉ። በተለይ በክር የሚሰሩ የሹራብ አልባሳት የብዙዎችን ቀልብ እንዲስብ እያደረጉ ናቸው።

ወጣት የአምላክ ፍቃዱ ትባላለች። በፋሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ በእጅ ሥራ ውጤቶች ማምረት ሙያ ላይ ተሰማርታለች። በባህሪዋም ለየት ያሉ አልባሳትን ታዘወትራለች። ከዚህ ፍላጎቷ በመነሳት የእጅ ሥራ ውጤት የሆኑ በተለያየ ዓይነት ክር የሚሰሩ ልብሶችን በእጇ በመሥራት ለገበያ ታቀርባለች። አልባሳቱን ዲዛይን አድርጋና ሰርታ ከማቅረብ ባለፈ ሙያውንም ፍላጎት ላላቸው ሰዎች ታስተምራለች። ኪያ የእጅ ሙያ ማሰልጠኛ በሚል ትምህርት ቤትም ከፍታለች። ማሰልጠኛው በዘርፉ የመጀመሪያው መሆኑንም ነው የምትገልጸው።

ወጣት የአምላክ በክር የሚሰራ የእጅ ሙያውን የተማረችው ተማሪ በነበረችበት ወቅት ነው። በትርፍ ጊዜዋ በበይነ መረብ ላይ የሚገኙ የተለያዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በማየት ነበር ራሷን በሂደት ያስተማረችው። የምትሰራቸውን ልብሶች በቅርቧ ያሉ ሰዎችና ቤተሰቦቿ መውደድ እንደጀመሩ የምትገልጸው የአምላክ፣ የእጅ ሥራዎቿን ከራሷ አልፎ ለሌሎች ሰዎች ጭምር በስጦታ መልክ ትሰጥ እንደነበርም ታስታውሳለች።

የአምላክ በክር በሚሰሩ የእጅ ሥራ አልባሳት ላይ ያላትን ችሎታ በተለያየ ጊዜ ብታዳብረውም ወደ ገበያ ለማቅረብ ግን ሃሳቡ አልነበራትም። ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በማርኬቲንግ ሲሆን ተቀጥራ በምትሰራባቸው ቦታዎች ላይ በትርፍ ጊዜዋ እነዚህን የክር አልባሳት ትሰራለች። ይህንን የተመለከቱ ወደ ቢሮዋ የሚመጡ ሰዎችም ሥራዋን መውደድ ይጀምራሉ፤ ይህ ብቻም ሳይሆን እንድትሰራላቸው ጥያቄ ያቀርቡላት ጀመር። ያን ጊዜ ነው የተለያዩ ትዕዛዞችንም ተቀብላ መሥራት የጀመረችው።

በብዛት ትእዛዝ መቀበል የጀመረችውና ገበያውን የተቀላቀለችው በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ነበር። በጊዜው የተለያዩ ማህበራዊ ገጾችን በመጠቀም ትእዛዝ መቀበልና ሽያጭ ማከናወኑን ቀጠለችበት።

የአምላክ ክሮችን በመጠቀም አልባሳቱን በተለያዩ ቀለሞችና የክር ዓይነቶች ዲዛይን አድርጋ የምትሰራ ሲሆን፣ በዚህም ጋወኖችን ፣ ሹራቦችን፣ ሱሪዎችን፣ የብርድ መከላከያ ስካርፎችን፣ ኮፍያዎችን እና ሌሎች አልባሳትን እያመረተች ለገበያ ታቀርባለች። በተለይ በብዛት ለሴቶች የተለያዩ አማራጮች ያሏት ሲሆን ፣ ለወንዶች እንደ ሹራብ ዓይነት አልባሳት ተፈላጊ መሆናቸውን ትናገራለች። በሌሎች ሀገራት በጣም የተለመዱና በኛ ሀገር ግን ብዙም ያልታወቁ ዲዛኖችን ክርን በመጠቀም መሥራት እንደሚቻል ገልጻለች።

የአምላክ እንደምትናገረው፤ ክርን በመጠቀም የተለያዩ አልባሳትን መሥራት ይቻላል፤ የበጋ ወቅት በሚሆንበት ጊዜ ቀለል ያሉ አላባሽ ልብሶች ፣ ቀሚሶች የምትታዘዝ ሲሆን፣ በክረምት ወቅት ደግሞ ክርም በባህሪው ስለሚሞቅ ጋዋን፣ ሹራብ ፣ ለብርድ የሚሆኑ ልብሶች ትእዛዝ ይቀርብላታል። በክር ከሚሰሩ ልብሶች በጣም የሚወደዱት ጋወኖች እና በተለምዶ ቶፕ የሚባሉት ከላይ የሚለበሱ ልብሶች ናቸው።

እነዚህን የእጅ ሥራዎቿን በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች እና በምታውቃቸው ሰዎች አማካኝነት ታቀርባለች። በመቀጠልም በተለያዩ ባዛሮች ላይ በመሳተፍ ሥራዎቿን ማስተዋወቅና በሰፊው መሸጥ የሚያስችላትን ዕድል አገኝታለች።

የምትሳተፍባቸው መድረኮች በአብዛኛው የውጭ ሀገር ዜጎች የሚሳተፉባቸው መሆናቸውን ጠቅሳለች። እነርሱ ለእጅ ሙያ ትልቅ ቦታ እንደሰጡ ገልጻ፣ ከእነርሱ የምታገኘው ማበረታቻ እንደጠቀማት ትናገራለች። በሀገር ውስጥ የሚገኙ ሰዎችም በአሁኑ ወቅት በኪሮሽ ለሚሰሩ የእጅ ሥራ አልባሳት ያላቸው አመለካከት እየተቀየረ መምጣቱን ገልጻለች። ይህም በዚህ ላይ ተሰማርተው የሚሰሩ ሰዎችን እንደሚያበረታታም ነው የተናገረችው ።

የአምላክ የምትሰራቸው አልባሳት ተፈላጊ ቢሆኑም ለመሥሪያ የሚሆኑ የክር ግብዓትና ሌሎች ቁሳቀስ በሀገሪቱ አለመኖሩ እንደ ተግዳሮት እንደሆነባት ጠቁማለች። ሌላው እንደ ምክንያት የምታነሳው ጉዳይ በሀገር ውስጥ የሹራብ ክር ተብለው የሚሸጡት ጥራታቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ነው። በተለምዶው የዳንቴል ክር የሚባለውን ለመጠቀም ደግሞ የአልባሳቱን ጥራት ይቀንሳል ትላለች። እሷ ግን ጥራታቸውን የጠበቁ ክሮችን ከውጭ በማስመጣት እንደምትሰራ ጠቅሳ፣ ለግብዓት እጥረቱ መፈጠር እንደ ምክንያት የሚነሳው በስፋት በክር የሚሰሩ አልባሳት መጠቀም በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ አለመሆኑ ነው ትላለች። አቅራቢዎች ላይ ችግር እንዳለም ጠቁማለች።

እሷ እንዳስታወቀችው፤ ጥራት ያላቸው የክር ዓይነቶች ዋጋቸው ውድ በመሆኑ ምክንያት የእጅ ሥራ ባለሙያዎች በዚያ ዋጋ ገዝተው ለመሥራት እና መልሰው ለደንበኞቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ ይቸገራሉ። የኢንዱስትሪው ትልቁ ፈተና በተመጣጣኝ ዋጋ የግብዓት አቅርቦት ማግኘት አለመቻል ነው።

የአምላክ የክር አልባሳት በመሥራት በማህበራዊ ድህረ ገፅ ማስተዋወቅ በመጀመሯ ምክንያት ምርቶቿ ተፈላጊነታቸው እየጨመረ ነው። ወደ ሙያው የሚገቡ ዲዛይነሮችም እንዲሁ እየተበራከቱ መጥተዋል። በማሰልጠኛ ተቋሙ የሚማሩትም በርክተዋል። በተለይ ትርፍ ጊዜያቸውን ተጠቅመው ተጨማሪ ሙያ የሚፈልጉ ሰዎች የእሷን ትምህርት ቤት ተመራጭ እያደረጉት ይገኛሉ።

‹‹በአሁኑ ሰዓት ከኪሮሽ ሥራ ውጭ የሻማ አሰራር፣ የቤት ውስጥ የግድግዳ ጌጦች የሚያስተምሩ አምስት ባለሙያዎች አሉን። በኛ ተቋም ተምረው የግላቸውን ሥራ የጀመሩ ሰዎችም አሉ›› የምትለው የአምላክ፤ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የሥራ እድል መፈጠር መቻሏን ትገልፃለች።

በእጅ ሥራ ሙያ ላይ ያለንን አመለካከት በመቀየር ይበልጥ ትኩረት አድርገን ብንሰራ ከዚህ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንችላለንም ትላለች። ይህ ዘርፍ ገና ያልተነካ መሆኑን ጠቅሳ፣ በርካታ ወጣቶች በሙያው ላይ ቢሰማሩ የተሻለ የገቢ ምንጭ መፍጠር እንደሚችሉ ጠቁማለች።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You