ለሩሲያ ኃያልነት ትልቅ አቅም የሆነው የሕዝቧ ትጋት!

በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተፈተነችው የሶቭየት ኅብረት እ.አ.አ. በ1991 ስትፈርስ ሩሲያ ሌላኛዋ የዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገር ሆና ቀጥላለች። የኃያልነቷ መገለጫ ዋንኞቹ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚዊ አቅሞቿ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ።

በመሬት ስፋቷ ከዓለም አንደኛ የሆነችው ሩሲያ የበርካታ ተፈጥሮ ሃብት ባለቤትም ነች። በተለይም ሩሲያ በዓለም በነዳጅ ዘይት ምርት ቀዳሚ ከሆኑት አገሮች አንዷ ስትሆን፤ በተለይ ለአውሮፓ በዋነኛነት የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ ታቀርባለች።

እ.ኤ.አ. በ 2022 በሩሲያ ውስጥ ያለው የነዳጅ ዘይት ምርት 548 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነበር፤ በቀን ከዘጠኝ እስከ 10 ሚሊዮን በርሜል በላይ ድፍድፍ ነዳጅ ታወጣ ነበር።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ሩሲያ አውሮፓ ከምትፈልገው የተፈጥሮ ጋዝ 40 ከመቶ የሚሆነውን ታቀርባለች። ይሁንና አሁን ላይ ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባችው ጦርነት ምክንያት የአውሮፓ ኅብረት ለጣለው ማዕቀብ ምላሽ ለመስጠት፤ መጠኑን ቀንሳለች።

በወታደራዊ አቅሟ ግዝፈት የምትታወቀው ሩሲያ የኒኩሌር አረር ከታጠቁ ጥቂት ኃያላን ሀገራት ተርታ የምትሰለፍ ነች። ከወራት በፊትም “ግዙፍ” የኒውክሌር ጥቃት የማድረስ አቅሟን የሚፈትሽ ልምምድ ማከናወኗ የሚታወስ ነው።

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ለሁለንተናዊ ዝግጁነት በሚል መርሕ የወታደሮቿን ቁጥር አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ለማድረስ ምልምላ እያከናወነች ነው። በባሕር ሰርጓጅ መርከቦችና በስለላ ድርጅቷ አማካኝነት እራሷን ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ላይ ነች።

ይህ የወታደራዊ አቅሟ በኢኮኖሚውም በአግባቡ የተደገፈ ነው፤ በዓለም የስንዴ ምርት ታላቅ እምርታ ላይ ከመድረሷ ባሻገር በብረታብረትና በኢንዱስትሪ ምርቶች ወታደራዊ መሣሪያዎችን በሚያመርቱ ማዕከላቷ አማካኝነት ከበርካታ ሀገራት ጋር ጥብቅ ኢኮኖሚያዊ ቁርኝት ፈጥራለች።

ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በማጎልበጽ ላይ ስትሆን፤ ከምሥራቅ አፍሪካ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጋር በተለያዩ የኢኮኖሚ አማራጮች ያላትን መስተጋብር በማጠናከር ላይ ትገኛለች።

ከተለያዩ ሀገራት የተውጣጡ የሚዲያ አባላትም ይህችኑ ታላቅ ሀገር ለመጎብኘት ወደ ሩሲያ ተጉዘዋል፤ እኔም የቡድኑ አባል በመሆን ሀገሪቱን የመጎብኘት እድል አግኝቻለሁ። በዚያ የነበረኝን ቆይታም በወፍ በረር እንዲህ አቀርበዋለሁ።

ሞስኮን እንደመግቢያ

በሞስኮ ዙሪያ አራት የአየር ማረፊያዎች አሉ። ከኢትዮጵያ፣ ከግብጽ፣ ከቱርክ፣ ከተለያዩ የዓረብና የእስያ ሀገራት የተውጣጣን ጋዜጠኞችም ሞስኮው ቭኖኮቮ በተሰኘው አየር ማረፊያ አድርገን ወደከተማዋ ዘለቅን። ከዜሮ በታች እስከ 12 ዲግሪ ሴልሺየስ የሚደርሰው የሞስኮ ቅዝቃዜ ኮፍያና የሹራብ ጓንት አድርገው እንኳን አጥንት ሰርስሮ የሚገባበት ኃይል አለው።

በመዲናዋ አውራ ጎዳናዎች በብዛት የሚታዩት ተሽከርካሪዎች ናቸው፤ እግረኞች እምብዛም ናቸው። ለዚህ ምክንያቱ የከተማዋ ቅዝቃዜ ስለመሆኑ ለመገመት አይከብድም። ለከተማዋ መጠሪያ የሆነው ግዙፉ የሞስኮቫ ወንዝ እንኳን ወቅቱ በረዷማ በመሆኑ ረግቶ ተቀምጧል፤ በዚህ ምክንያት ፈጣን ጀልባዎች ከእንቅስቃሴ ተገትተዋል።

የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መቀመጫ ክሬምሊን ቤተ-መንግሥት ደግሞ ግርማውን እንደተላበሰ ይታያል። የሞስኮ ጥንታዊ ሕንጻዎች፣ በሥነ-ሕንጻ ውብታቸው የደመቁት አብያተ ክርስቲያናትና መስጂዶች፤ የሶሻሊዝምን ርዕዮተ-ዓለም የሚያንፀባርቁት ግዙፍ ሐውልቶች፣ የጠፈርተኛው ዩሪ ጋጋሪን የፑሽኪንና የተለያዩ ጸሐፊዎችን ማስታወሻ ሐውልቶች ለከተማዋ ድምቀት ናቸው።

በመንገድ ዳር የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ደግሞ ባለቤት አልባ እስኪመስሉ ድረስ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች አይታዩባቸውም። ምክንያቱ ደግሞ ማንም ነዳጅ መቅዳት የፈለገ አሽከርካሪ የገንዘብ ካርዱን አውጥቶ የሚፈልገውን ያክል ከቀዳ በኋላ በእራሱ ከፍሎ የሚሄድበት አሠራር በመተግበሩ ነው።

የሩሲያ ዋነኛ የኢኮኖሚ አቅም የሆነ የተፈጥሮ ጋዝ በመኖሪያና ንግድ ቤቶች ውስጥ ለኃይል ምንጭነት ስለሚውል በሞስኮ ሕንጻዎችና መኖሪያ ቤቶች አቅራቢያ የጋዝ ማስተላለፊያ መስመሮችን ማየት የተለመደ ነው። ይሄው ጋዝ በሚሰጠው ሙቀት ታግዘው በርካታ የሞስኮ ነዋሪዎች ሥራቸውን በተሻለ ቅልጥፍና ያከናውናሉ።

እኛም የሞስኮ ቆይታችንን ጋብ አድርገን ለዋናው ጉብኝት ወደወደብ ከተማዋ ሴንት ፒተርስበርግ ለማቅናት ተዘጋጀን። 635 ኪሎ ሜትሮች የሚዘልቀውን ጉዞ በፈጣኑ ሜትሮ ባቡር ተያያዝነው። ምቾችና ፍጥነትን የተላበሰውን የባቡር ጉዞ አራት ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠናቀን ወደ ሆቴላችን ገባን።

የትራክተር ማምረቻ ማዕከል

የሩሲያ መርከቦች ወደአውሮፓና የተለያ ሀገራት ምርቶችን ከሚያመላልሱባቸው ሰባት ዋና ዋና ግዙፍ ወደቦች መካከል የሴንት ፒተርስበርግ ወደብ አንዱ ነው። ወደቡ ከብረታ ብረት ምርቶች እስከ ነዳጅ ዘይት ይጓጓዝበታል።

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተወለዱት በዚችው የወደብ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ ነው። በከተማዋ የሚገኘውን ኮንስታንቲኖቭስኪ ቤተ-መንግሥት የሀገሪቷ መሪ በተለያዩ ጊዜያት እንግዶችን ለመቀበል ይጠቀሙበታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራው የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የልዑካን ቡድን በሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም በተዘጋጀው የሩሲያ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሲሳተፍ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የተገናኙት በዚህችው ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ በሚገኘው ቤተመንግሥት ነበር።

በባልቲክ ባሕር ላይ በፊንላንድ ባሕረ ሰላጤ ራስጌ የምትገኘው፤ በቀድሞ ስሞቿ ፔትሮጋርድ እና ሌኒንግራድ በመባል የምትታወቀው ሴንት ፒተርስበርግ ከእኛዋ አዲስ አበባ ጋር እህትማማች ከተማ ነች። እህትማማችነቱ በሁለቱ ከተሞች መካከል በሕዝብ ትራንስፖርት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጤና፣ በትምህርትና በማኅበራዊ መስኮች በጋራ መሥራትን ዓላማ ያደረገ ነው።

የወደብ ከተማዋ ሴንት ፒተርስበርግ የፖለቲካና የንግድ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎችም መናኸሪያ ናት። የጋዜጠኞች ቡድኑም ዋነኛ የጉብኝት ማዕከል የሆነው ኪሮቬትስ የተሰኘው ትራክተሮችና የተለያዩ ማሽነሪዎች የሚመረቱበት ግዙፍ ማዕከል ነው።

የራሱ ብረት ማቅለጫና ማሽነሪ መገጣጠሚያዎች እንዲሁም ጠንካራ ሠራተኞች ያሉት ማዕከሉ የጦር መሣሪያዎችን እንደሚያመርት ታሪኩ ያስረዳል። የባቡር ሐዲድና የተለያዩ መርከቦችን የሚመረቱባቸውን ማዕከላት ትተን 200 ሔክታር ላይ ያረፈው የትራክተር ፋብሪካ መጎብኘታችንን ቀጠልን።

በዓመት አራት ሺህ 300 የተለያዩ የፈረስ ጉልበት ያላቸው ትራክተሮችን የሚገጣጠምበት ፋብሪካው የሞተር ክፍሉን ብቻ ሳይሆን እያንዳንዷን ቡሎን ጭምር ያመርታል። 24 ሰዓት የሚሠራበት ማዕከሉ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ ሠራተኞች እንዳሉት የጉብኝቱ አስተባባሪ ሩሲያዊቷ ኢቭጄኒያ ፓቭሊዩኮቫ አስረዳችን።

በሩሲያ የትራክተር ማምረቻ ታሪክ ቀደምት ከሚባሉት መካከል የሆነው ፋብሪካው ከሀገሩ አልፎ ለተለያዩ ዓለማትም ምርቱን ያቀርባል። ኢትዮጵያም ትራክተሮችን በመግዛት ከፋብሪካው ምርቶች ተቋዳሽ እንደሆነች ተነገረን። ኬንያ፣ ግብጽና ለተለያዩ ሀገራት ምርቶቹን እየተረከቡ የሚገኙ ተጨማሪ ሀገራት ናቸው።

እስከ 460 የፈረስ ጉልበት አቅም ያላቸውን ግዙፍ ትራክተሮች ይገጣጠማሉ። ከጥቃቅን የትራክተሩ ክፍሎች አንስቶ ግዙፉ ጎማውና ሙሉ ሲስተሙ በላብራቶሪ ፍተሻ ተደርጎበት ለአገልግሎት ይበቃል።

እያንዳንዱ የትራክተር ክፍል የሚመረትባቸው 500 ማሽኖች ኮምፒውተራይዝድ ሲስተም ተገጥሞላቸዋል። ከዚህ ባለፈ ፋብሪካው ቡልዶዘሮች እንዲሁም ለግግር በረዶ ማንሻ አሊያም ለአፈር መጋፊያ የሚሆኑ ተሽከርካሪዎችን አምርቶ ለአገልግሎት ያውላል።

ፋብሪካው በ50 ቢሊዮን የሩሲያ ሩፕል ወጪ የማስፋፊያ ፕሮጀክት እያከናወነ ሲሆን፤ ምርቶቹን ከእጥፍ በላይ ለማሳደግ ውጥን ይዟል። ማዕከሉን ካየን ከአንድ ቀን በኋላ ደግሞ ታውራስ ፌኒክስ የተሰኘውን የተለያዩ የማሸጊያዎች ማሽኖች የሚገጣጠሙበትን ፋብሪካ የመጎብኘት ዕድል ገጠመን።

የማሽን ማምረቻ ማዕከሉ

ከአንድ ሺህ 500 በላይ ዘመናዊ ማሽኖች ያሉት ፋብሪካው የብርጭቆ፣ የውሃና የተለያዩ ጭማቂዎች፣ የግሉኮስ መድኃኒት እንዲሁም የዱቄት ወተትና የተለያዩ አይነት የከረጢት ማሸጊያዎችን የሚያዘጋጁ ማሽኖችን አምርቶ ለአገልግሎት ያበቃል።

ማሽኖችን ለማምረት የሚረዱ የተለያዩ መሣሪያዎች ቅርጽ የሚወጣባቸው ሦስት የብረት ማቅለጫ ክፍሎች በዘመናዊ መልክ ተገንብተውለታል። በፋብሪካው ከሚመረቱ ማሽኖች አንዱ የለስላሳ መጠጦች ማሸጊያ ኮምፒተራይዝ ማሽን ይገኝበታል። ማሽኑ ጠርሙሶችን አምርቶ ጠርሙሶቹን አጥቦና አድርቆ መጠጦችን ለማሸግ የሚረዳ ነው፤ በደንበኞች ትዕዛዝ መሠረት ይመረታል።

የተለያዩ ቴክኒካል ሂደቶችን አልፈው ለገበያ የሚወጡ የማሸጊያ ማምረቻ ማሽኖች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ መሆናቸውን የፋብሪካው የኤክስፖርት ክፍል ኃላፊ ኢቭጄኒ ቦንዳሬብ ገለጻ አደረጉ።

ፋብሪካው 800 ሠራተኞችን ይዞ በዓመት የተለያዩ መጠን ያላቸውን 900 ማሽኖች ያመርታል። እራሱን የቻለ የሜካኒካል ዲዛይን ክፍል ያለው ፋብሪካው በሮቦት ጭምር የታገዘ አሠራርን ተግባራዊ አድርጓል። ሁሌም ሥራ አለ፤ በምሳ ሰዓት እንኳን ሰዎች ይቀያየራሉ እንጂ የሚቆም ሥራ የለም።

ሩሲያኖች ጠንካራ ሠራተኞች ናቸው። ኮስታራ ፊታቸው በሥራ ብቻ የተጠመደ ነው። የማሽን ማምረቻ ፋብሪካውን እንቅስቃሴ እየተዟዟርን ስንጎበኝ ማንም በአጠገባቸው ቢያልፍ ትኩረት ካደረጉበት ሥራ ለሰከንድ ዝንፍ እንደማይሉ ተመለከትን።

ቀጣዩ ጉዟችን ወደ ኖቮሮሲይስክ ከተማ ሆነ። ከአራት ሰዓታት የአየር በረራ በኋላ እ.አ.አ. በ2014 የክረምት ኦሎምፒክን በደማቅ ሁኔታ በማዘጋጀቷ ወደምትታወሰው ሶቺ ከተማ ደረስን። በሶቺ ጣፋጭ የዓሣና የአትክልት ምግቦችን ከቀማመስን በኋላ በአውቶቡስ የስድስት ሰዓታት ጉዞን በማድረግ በጥቁር ባሕር ዳርቻ በተቆረቆረችው ጥንታዊቷ ኖቮሮሲይስክ ከተማ ገብተን አረፍ አልን።

የስንዴ ማዕከሏ ሌላኛዋ የወደብ ከተማ

ኖቮሮሲይስክ በአንጻራዊነት የተሻለ ሙቀት አላት፤ እንደሌሎች በረዷማ የሩሲያ ከተሞች አይደለችም። አምስት ዲግሪ ሴክሺየስ በሆነው የአየር ፀባይ ያለጓንትና ኮፍያ መንቀሳቀስ ይቻላል።

ከተማዋ ከፍተኛ የስንዴ ምርት ወደተለያዩ ሀገራት የሚጓጓዝበትን ወሳኙን ወደብ በጉያዋ ይዛለች። ከዚህ ባለፈ የኖቮሮሲይስክ የስንዴ ማከማቻ ማዕከል /ግሬይን ፕላንት/ በየቀኑ ለተለያዩ የዓለም ሀገራት የሚላከውን ስንዴ ያጓጉዛል። እንደ ሩሲያ የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ከሆነ እ.አ.አ. በ2023/24 የምርት ዘመን ሀገሪቱ 135 ሚሊዮን ቶን የግብርና ምርት ትጠብቃለች፤ ከዚህ ውስጥ 90 ሚሊዮን ቶኑ የስንዴ ምርት እንደሚሆን ይገመታል።

ሩሲያና ዩክሬን በድምሩ ከአንድ አራተኛ በላይ የሚሆነውን የዓለም ስንዴ ወደ ውጭ ይልካሉ። ፕሬዚዳንት ፑቲንም ባዘዙት መሰረት ከ25 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ቶን የሚደርስ ስንዴ ለዚምባብዌ፣ ለቡርኪና ፋሶ፣ ለሶማሊያ፣ ለኤርትራ፣ ለማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክና ለማሊ እየተከፋፈለ ይገኛል።

ይሄው ስንዴ በዋነኛነት የሚጓጓዘው ከኖቮሮሲይስክ ስንዴ ማከማቻ ማዕከል ነው። ማከማቻ ማዕከሉ እያንዳንዳቸው ከ40 እስከ 100 ሺህ ቶን ምርት የሚይዙ የተለያዩ ዘመናዊ ጎተራዎች አሉት። ስንዴውን ከማከማቻው በአሳንሰር ተጠቅመው ወደመርከቦች የሚያጓጉዙ ከሰባት በላይ የባቡር መስመሮች አገልግሎት ይሰጣሉ። ሠራተኞች ድምጽ እንኳን ሳያሰሙ የዓለምን ትልቁን የስንዴ ምርት ያሰራጫሉ፤ ከሥራቸው ዝንፍ የለም።

ከማዕከሉ በዓመት ስምንት ሚሊዮን ቶን ምርት ወደተለያዩ ሀገራት ይላካል። በወር በአማካይ 25 መርከቦች ስንዴና የተለያዩ እህሎችን ጭነው በጥቁር ባሕር ላይ ጉዟቸውን ያደርጋሉ። የኖቮሮሲይስክ የስንዴ ማከማቻ ማዕከል /Novorossiysk Grain Plant, JSC/ የምርት ክፍል ምክትል ዳይሬክተር ሱትቼንኮ ኢቭጌኒይ እንደተናገሩት፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን ባዘዙት መሠረት ወደኤርትራና ማሊ የሚጓጓዘው ስንዴ በመርከብ ላይ ነው።

የኖቮሮሲይስክ ወደብ በግዙፍ ጫኝ መርከቦች የተከበበ ነው። ትላልቅ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከወደቡ ወደተለያዩ ከተሞች እንቅስቃሴያቸውን ያደርጋሉ። በአጠቃላይ ከተማዋ የምርት እንቅስቃሴ የሚሳለጥባት ማዕከል ናት ቢባል ማጋነን አይሆንም።

እኛም የሩሲያን የኢኮኖሚና ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎች ጉብኝት አጠናቀን በመጣንበት አኳኋን ጥቁር ባሕርን አግድም እያየን ወደ ሶቺ ከተማ በአውቶብስ ጉዟችንን ተያያዝነው። በአሜሪካና አውሮፓውያን የተለያዩ ማዕቀቦች የተወጠረችው ሩሲያ እራሷን በምግብ ከመቻል አልፋ ሌሎችንም ለመርዳት የቻለችው በሥራና በሥራ ብቻ ነው።

ሩሲያኖች በዚያ በረዶ ለወራት በሚዘንብበት ምድር ላይ አይደለም ስንዴና የተለየዩ ሰብሎችን ማምረት ይቅርና መኖር በራሱ ከባድ በሚመስልበት የአየር ንብረት ጠንክረው በመሥራት ሀገራቸውን ለውጠዋል። በኢንዱስትሪ አብዮቱና በሕዋ ሳይንስ ምርምሩ እንዲሁም በሚሊታሪ አቅማቸውን እራሳቸውን በማጠናከር ከዓለም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገሮች ተርታ መሰለፍ ችለዋል።

ይህ በራስ አቅም እራስን የመገንባት ምስጢር ታዲያ በእኛም ሀገር መሠረት ይይዝ ዘንድ እየተመኘሁ ከሶቺ ወደሞስኮ – ከሞስኮ ወደአዲስ አበባ የሚደረገውን በረራ ለመጀመር ተነሳሁ። በታላቅ ትግል አቅሟን ያስመሰከረችው ሩሲያ ዕውነትም የትጋት ተምሳሌት ነችና ኢትዮጵያውያን ከግዙፏ ሀገር ዜጎች ብዙ የምንማረው የሥራ ባህል አለ!

ጌትነት ተስፋማርም

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You