ለምህረት የተዘረጉ እጆችን መቀበልሀገርን ከጥፋት መታደግ ነው

 እውቁ ግሪካዊ ጸሐፊ እና የታሪክ ሰው ሔሮዶቱስ የጦርነትን አስከፊነት “ In peace, sons bury their fa­thers. In war, fathers bury their sons!” “በሰላም ጊዜ ልጆች አባቶቻቸውን ይቀብራሉ፤ በጦርነት ጊዜ አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ” በሚል ገልጾታል። ይህም የጦርነትን እጅግ አስከፊ ገጽታን ብቻ ሳይሆን የሰላምን ጥቅምና አድማሳዊነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። በርግጥ ከመጣንበት መንገድ አንጻር የጦርነትን አስከፊነት፣ የሰላምን አቻ የለሽነት ከኢትዮጵያዊያን በላይ የሚያውቀው አለ ብሎ መናገር ይከብዳል።

ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት እርስ በእርስ ተዋግተን አይተነዋል። ይህም ሆኖ ከትናንቶቻችን መማር ባለመቻላችን፣ ዛሬም ከጦርነት አዙሪት አልወጣንም። ለሁለት ዓመት በዘለቀው የትግራይ ጦርነት ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት ተፈጥሯል። አሁን የአማራ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ፍላጎታቸውን በጠብመንጃ አፈሙዝ ማስፈጸም የሚሹ ኃይሎች የሀገሪቱን ሰላም እየተፈታተኑ ነው።

እነዚህ ኃይሎች ውድ የሰላም አመራጮችን እንዲመለከቱ፣ ከኃይል አማራጭ ወጥተው ወደ ድርድርና ውይይት እንዲመጡ በተደጋጋሚ ጥሪዎች ቢቀርቡም ለጥሪው ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኝ አይደሉም። ከአንዳንዶች ጋር /ከአሸባሪው ሸኔ / የተለያዩ ድርድሮችን ረጅም ርቀት ተሄዶ ቢደረግም ውጤታማ መሆን አልተቻለም።

በየትኛውም ሀገር በትጥቅ የታገዘ አለመግባባትና ግጭት እጅግ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ካስከተለ በኋላ በዘላቂነት ሲቋጭ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት ሳይሆን በሰላማዊ ውይይት እና ድርድር ነው። የዓለም ታሪክ እንደሚያስረዳውም ጦርነት ለሰላም በተዘረጉ እጆች እንጂ በመሣሪያ እጦት አይቆምም ።

በተለይ አሁን ባለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ለሰላም ሃሳብን በሃሳብ ከማሸነፍ የተሻለ አማራጭ የለም፤ ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻለውም በሰላማዊ ድርድር፣ በምህረት እና በይቅር ባይነት ነው። ይህንን አለመገንዘብ ከሁሉም የከፋ ጊዜን የሚዋጅ አስተሳሰብ የማታጥ አልፋና ኦሜጋ ነው።

ደም አፋሳሹ የትግራይ ጦርነት ብዙ ጉዳትን ካስከተለ በኋላም ቢሆን በሰላማዊ ድርድር ተቋጭቶ አዎንታዊ ውጤትን አሳይቶናል።

የለውጥ ኃይሉ ወደ ስልጣን ከመጣ ማግሥት ጀምሮ /ከዛም በፊት/ ይሄንኑ በመገንዘብ ለሀገራችን ሰላም ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀሱ አይዘነጋም። በተለይም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል /በትግራይ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና እናቶችን ያካተተ ቡድን የሰላም መንገድ ጠራጊ አድርጎ ተንቀሳቅሷል።

ወደ ጦርነት ከተገባም በኋላ ቢሆን መንግሥት ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ታግሶ፣ ስለሰላም ጥሪዎችን ሲያቀርብ ነበር። በጦርነቱ የኃይል ሚዛኑ በእጁ በሆነበት ጊዜም ቢሆን፤ ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑን አምኖ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም ትልቁን ድርሻ ተጫውቷል ፡፡

በትግራዩ ጦርነት መንግሥት በዚህ ደረጃ ሆደ ሰፊ ሊሆን የቻለው በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት/ መንፈስ የተቋጩ ጦርነቶች ዘላቂ ሰላም እንደማያሰፍኑ ከመገንዘብ ብሎም፤ ሰላምን ለማጽናት ካለው ብርቱ ፍላጎት አንጻር እንደሆነ ይታመናል። ከተግባሩም መረዳት የምንችለው ይሄንኑ ነው።

በዚህም በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የቆየውን ጦርነት በሰላማዊ ስምምነት በመቋጨቱ የትግራይ ሕዝብ እናቶች እንባ ታብሷል። መንግሥት ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ ከማድረግ ካለው ኃላፊነት አንጻር ችግሮችን በሆደ ሰፊነት በድርድር ፣ በምህረት ለመፍታት የሄደበት ርቀት ውጤት አስገኝቷል።

ይህም ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት በማስቆም ረገድ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል። በዚህም የመንግሥትን ሰላም ፈላጊነት ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይቀር በተግባር አይተነዋል። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን፤ እንደ ፕሪቶርያው ሁሉ ከአሸባሪው ሸኔ ጋር ያለውን አለመግባባት በውይይት ለመፍታት ወደ ታንዛኒያ ዳሪሰላም በመጓዝ ሰላምን ፍለጋ ባዝኗል።

መንግሥት ቀደም ባሉት ጊዜያት ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን ከሃሳብ ይልቅ በጠብመንጃ ለማስፈጸም ተደራጅተው ‘ዱር ቤቴ ‘ ካሉት ቡድኖች ጋር ለመነጋገር ተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል። በዚህም በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል፣ በኦሮሚያ ፣ በሱማሌ ፣ በአማራ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ በርካታ የታጠቁ ኃይሎች የተዘረጉላቸውን የሰላም እጆች ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ በመቀላቀል መደበኛ ሕይወታቸውን እየኖሩ ይገኛሉ።

እነዚህ ለሰላም የተዘረጉ የመንግሥት እጆች ዛሬም አልታጠፉም። ከመንግሥት ባህሪ አንጻር መቼም ሊታጠፉ እንደማይችሉ መገመት የሚከብድ አይሆንም፤ ለዚህም ከሰሞኑ በአማራ ክልል ለወራት የዘለቀውን የሰላም እጦት ለመፍታት መንግሥት ለታጠቁ ኃይሎች ጥሪ ማድረጉ አንድ ተጨባጭ ማሳያ ነው ።

በክልሉ ለወራት የዘለቀው የሰላም እጦት ሕዝቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴውን በአግባቡ እንዳይመራ ችግር ፈጥሮበታል፤ በተለይ ድጋፍ የሚሹ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይበልጥ እንዲጎዱ አድርጓል፤ እያደረገም ይገኛል። የክልሉን ሕዝብ ነገዎች ተስፋ እያደበዘዘ ስለመሆኑም ለመናገር የሚከብድ አይደለም ።

በክልሉ ውስጥ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ መንግሥት ያቀረበው የሰላም ጥሪ የሕዝቡ ፍላጎቱ ጭምር እንደሆነ በተለያየ መልኩ ታይቷል። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ሲካሄዱ በነበሩ የሰላም ውይይቶች የክልሉ መንግሥት የሰላም አማራጮችን በመዘርጋት ክልሉ ወደ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ እንዲያረጋግጥም ኅብረተሰቡ ሲጠይቅ ተሰምቷል፡፡ መንግሥት ካለው የሰላም ፍላጎት እንዲሁም ከሕዝቡ ጥያቄ በመነሳት የሰላም ጥሪው ተደርጓል።

መንግሥት እንደ ትግራዩ ሁሉ ዛሬም የኃይል ሚዛኑ ቢኖረውም የሰላም እጆቹን በመዘርጋት ሆደሰፊነቱን እያሳየ ነው። ምክንያቱ ድብቅ አይደለም። ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻለው ችግሮቻችን በሰለጠነ ወይም በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍታት ያስፈልጋልና ነው። በአውደ ውጊያ ከሚገኝ ድል ይልቅ በሰላማዊ ድርድር፣ በምህረት ፣ በይቅር ባይነት የሚገኘው ድል ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደርጋታልና።

የሰላም ጥሪው ከሀገር አልፎ ለራሳቸው ለታጠቁ ኃይሎች የሚበጅም ነው፡፡ ስለሕዝብም ሲሉ ሰላምን እንዲመርጡና ምህረት እንዲደረግላቸው እድል የሚሰጥ ነው። አለመግባባቶች በንግግር እንዲፈቱ የሚያስችል ነው። የሰላም ጥሪው ግጭት እና ውድመት እንዲቆም፣ በማኅበረሰቡ መካከል መደማመጥ እንዲሰፍን እንዲሁም መረጋጋትና ልማት እንዲመጣ የሚያስችል ጭምር እንደሆነም ይታመናል።

መንግሥትም ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ መፍታቱ ሁሌም የተሻለ አማራጭ በመሆኑና የሕዝብን እፎይታ ከልብ በመሻት የሰላም ጥሪው ማድረግ መቻሉ ሆደ ሰፊነቱን ይናገራል። ከዚህም በላይ የጀመረውን የሕዝባችንን ሕይወት የመለወጥ /ድህነትን ታሪክ የማድረግ ፈታኝ ትግል ስኬታማ እንዲሆን ሰላም ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ስለመሆኑም ያለው ግንዛቤ ከፍ ያለ ነው። ከትናንት ስህተቶቻችን የመማሩንም ጉዳይ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ይህ የመንግሥት ስለ ሰላም ያለው ቁርጠኝነት፤ ከባህሪው የመነጨ ከመሆኑ አንጻር ከፍ ያለ እውቅና ሊሰጠውና ሊበረታታ የሚገባ ነው፤ ከግጭት አዙሪት የመውጫ ትልቁ /ዋነኛ መንገድ ስለሆነም እያንዳንዱ ዜጋ ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ሊደግፈው ይገባል። የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታ የሚወስን ከመሆኑ አንጻርም የሁሉም ዜጋ ትኩረት ሊሆን ይገባል።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች በመንግሥት የተደረገውን የሰላም ጥሪ የማይደገም እድል እንደሆነ በመገንዘብ አጋጣሚውን በአግባቡ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ለዚህ ምንም ዓይነት ምክንያት መፍጠር አይጠበቅባቸውም።

የመንግሥትን ጥሪ ተቀብሎ ፊትን ወደ ልማት ማዞር መቻል ሀገርን የሚያጸና እንጂ፤ አንገት የሚያስደፋ ተግባር አለመሆኑን መረዳት ይገባል። አያት ቅድም አያቶቻችን ዛሬ በኩራት ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን፣ በስሟ የምንምልባትን ሀገር አጽንተው ሊያቆዩልን የቻሉት፤ የሃሳብ ልዩነታቸውን በይደር፤ የሀገር ፍቅራቸውን በልባቸው አድርገው ነው። በመሳሪያ አፈሙዝ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማስፈጸም የሚደረግ አካሄድ ሀገር አፍራሽ ነው። የሁላችንም ጎጆ ለሆነችው ሀገራችን / ኢትዮጵያ የሚበጅ አይደለም።

ዳንኤል ዘነበ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You