ኢትዮጵያ በበርካታ ሕብረ ብሔር የተገነባች አገር ነች፡፡ ወጣቱ ትውልድም የዚህ ሕብረ ብሔራዊ ውበት መገለጫ ነው፡፡ ከብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀረጉ የሚመዘዘውና በመላው አገራችን በስብጥር የሚኖረው ወጣት ልዩነቱን ቆጥሮ በጥላቻ አይን ከመተያየት ይልቅ ተከባብሮ መኖሩ ጎልቶ ይታያል፡፡
ይህ አይነቱ ውብ ሥሪት ተፈጥሯዊ እንጂ ሰው ሠራሽ አይደለም፡፡ የፍቅር እንጂ የጥላቻ ምንጭ ሊሆን አይችልም፡፡ የአንድነት እንጂ የመለያየት ሰበብ አይሆንም፡፡ መከበሪያ እንጂ ፈጽሞ መታፈሪያ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያም እነዚህን ዘርፈ ብዙ የውበት አዝራሮቿን እንደመርፌ እና ክር አዋህዳ በፍቅርና በአንድነት ለአያሌ ዘመናት ማኖር ችላለች፡፡
ከጥቂት ዓመታት ወዲህ እነዚህ የመዋደድ፣ የመቻቻልና የመከባበር ውብ ባህሎች ላልተዋል፤ ቀንሰዋል፤ የጥላቻ መልክ ሊይዙም ሥር በመሥደድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አልፎ አልፎም በተግባር ሲከሰት ተስተውሏል፡፡ ወጣቱን የእኩይ ተልዕኮው ማስፈጸሚያ የማድረግ አዝማ ሚያዎችም ታይተዋል፡፡
ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አስተያየታቸውን የሰጡት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ ወጣቶችም፤ የዚህ ዘመን ወጣት በዚች አገር ለሚፈጠር ለውጥም ሆነ ውድቀት፤ በአሉታም ይሁን በአዎንታ በታሪክ ማህደር ሲታወስ እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡ ወጣቱ ታሪካዊ አደራ የተጣለበት መሆኑን ጭምር በየእለቱ ማስታወስ ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአሶሳ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ቃልኪዳን አጠቃ፤ በቋንቋ፣ በእምነት፣ በቆዳ ቀለም እና በመሰል ጉዳዮች አንዱ ከሌላው ቢለያይም ሰው ሆኖ እስከተፈጠረ ድረስ አንድ ነው፤ መከበር አለበት፡፡ በማንነቱ ምክንያት የሰው ልጅ የጥቃት ሰለባ መሆን እንደሌለበት ተናግራለች፡፡
እንደ ወጣት ቃልኪዳን ገለጻ፤ ለእንደነዚህ አይነት ችግሮች መፈጠር፤ “የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር መበራከት፣ ወጣቶች የአገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ በተገቢው አለመገንዘብ እና የአገራችን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አለመቻል፣ የወጣቶች የመዝናኛ እጦት” ምክንያቶች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል መንግስትም ሆነ ወጣቱ ኃላፊነቱን በተገቢው እየተወጣ አይደለም ስትል ትሞግታለች፡፡ በአሶሳ ከተማ እና በአካባቢው የተከሰቱ ብጥብጦችን ለአብነት በማንሳት መንግስት የወጣቶች ሕይወት ከመቀጠፉና በስሜት የተመሩ ቁጣዎች ከመገንፈላቸው በፊት መቆጣጠር ይችል ነበር ስትል ተናግራለች፡፡
ወጣት ቃልኪዳን፤ “እያንዳንዱ ወጣት ምክንያታዊ መሆን አለበት፡፡ የራሴ ብሔር በሚል ከፈጠረው ጠባብ አጥር ወጥቶ ኢትዮጵያዊ በሆነ አስተሳሰብ መቃኘት ተገቢ ነው፡፡ ወጣቱ ሰላም በተናጋ ቁጥር ግንባር ቀደም ተጎጂ እንደሆነ ሁሉ ሰላም ሲኖርም ግንባር ቀደም ተጠቃሚ ስለሚሆን ወጣቱ ነቅቶ ለአካባቢው ሰላም ዘብ ይቁም” ስትል ጥሪዋን አስተላልፋለች፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በሥነ ሥዕል ሙያ የሚተዳደረው ወጣት ገብረየሱስ አስማረ፤ በአገራችን የምንገኘው አብዛኞቻችን ወጣቶች የኢህአዴግ ትውልዶች ነን፡፡ በመሆኑም ያደግንበት መንገድ፣ የተማርንበት መንገድ እና የአኗኗራችን ሁኔታ በማንነታችን ላይ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ብዙዎቻችን እኮ የአገራችንን ብሔራዊ መዝሙር መዘመር አንችልም፤ በትምህርት ቤቶች የአገራቸውን መዝሙር ዘወትር የሚያስቀድሙ አሉ ማለት አይቻልም፤ በክልላቸው መዝሙር ታጥረዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ያደገ ወጣት ክልሉን እንጂ አገሩን ሊያስቀድም እንዴት ይቻለዋል? ስለዚህ የብሔርም ሆነ ሌሎች አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ግጭቶች የዚህ አስተሳሰብ ውጤቶች እንጂ አሁን የተፈጠሩ አይደሉም፡፡
እንደ ወጣት ገብረየሱስ አገላለጽ፤ የተዋቀርንበት መንገድ የስህተቱ ምንጭ ነው፡፡ኢትዮጵያዊ ማንነትን የሚያጎሉ ጉዳዮችን ወጣቱ እየጣለ እንዲሄድና እንዲረሳቸው ተደርጓል፡፡ የእምነት ተቋማት እምነቱን በመስበክም ሆነ ወጣቱን በመገሰጽ የሚያሳርፉት ጫና በእጅጉ ተዳክሟል፡፡ በዚህ ምክንያት ፈጣሪውን የማይፈራ ወጣት ተፈጥሯል፡፡
ሰሞኑን እንዳየነው እዚህም እዚያም በወገኑና በወንድሙ ላይ ዱላ የሚሰነዝር ወጣት መበራከቱ ያሳዝናል፤ ያሳፈራል፡፡ የሚለው ወጣት ገብረየሱስ፤ ወጣቱ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የተመረቀው ሳይቀር በራሱ ተስፋ እየቆረጠ በሱስ እንዲናውዝ ላለፉት ብዙ ዓመታት ሆን ተብሎ ሁኔታዎች ተመቻችተውለታል የሚል እምነት አለኝ ባይ ነው በማለት መንግስትን ተችቷል፡፡
በሌላ በኩል ወጣት ገብረየሱስ፤ “አገራችንን ለማዳን አሁንም አረፈደም፤ ጊዜ አለን፤በተለይ በተለይ ለአብዛኞቻችን ወጣቶች የፌስ ቡክ ተጽዕኖ ቀላል አይደለም፡፡ ስለዚህ ያልተጣራ መረጃ ተሸካሚዎች መሆን የለብንም፡፡ የተረጋገጠና እውነት የሆነን መረጃ ብቻ ማሰራጨትና ማሳወቅ አለብን፡፡ ማመዛዘን ይኖርብናል፡፡ እንደ አንዲት አገር ወጣት ስታስብ አገርህን ጥለህ፤ እንዴት በብሔርህ ውስጥ ትደበቃለህ? ያሳፍራል፡፡ እንደ ወጣትነታችን ኃላፊነታችንን መወጣት ይገባናል፡፡ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ወጣቶችን በመጠቀሚያነት ለዘመናት ተገልግለውብናል፡፡ ስለዚህ በሰከነ መንገድ ማሰብ ግድ ይለናል፡፡ ከማንኛውም ድርጊት በፊት ረጋ ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው፡፡
ባለፉት ጊዜያት ግጭቶች አላስፈላጊ የህይወት መስዕዋትነት የከፈለው የድሃ ልጅ ነው፡፡ ለተለያዩ የትግል አማራጮች ምቹ ሁኔታዎች እያሉ የወጣቶች ደም መፍሰስ የለበትም፡፡ ወጣቶች ነገሮችን በሰከነ ውይይት መፍታት መልመድ ይኖርብናል” ሲል ወጣት ገብረየሱስ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
ወጣት ማርታ ወንዱ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪ ነች፡፡ እርሷ እንደገለጸችው፤ አሁን በመላው ኢትዮጵያ ለወጣቶች ምቹ የመለወጥ እድሎች በእጁ መዳፍ ሥር ይገኛሉ፡፡ እነዚህን አጋጣሚዎች ወደ ውጤት መቀየር ከወጣቱ ይጠበቃል፡፡ ከመቼውም በተሻለ ሐሳቡን ያለገደብና ፍራቻ መግለጽ ችሏል፡፡ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ተሳትፎ ረገድም የሰፊ እድሎች ባለቤት ነው፡፡ ስለዚህ ውሃ በማያነሳ ምክንያት ለብጥብጥ መጋለጥ የለበትም፡፡ የሁላችን አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን በጋራ መጠበቅና ማልማት ይጠበቅበታል፡፡ ወጣቱን የአሉባልታ ሰለባ ለማድረግ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን እያፈሰሱ ለሚያላዝኑት ጆሮን መንፈግ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ሕገ መንግስት ባላት አገር ውስጥ ተገቢው የሕግ የበላይነት ሲከበር በጉልህ መታየት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለአያሌ ዘመናት ተከባብረውና ተዋደው መኖር እንደቻሉ ሁሉ ዛሬም ይችላሉ፡፡ ሴረኞች ስስ ብልትና ወቅት እየጠበቁ የሚፈጥሩትን ሁከት በቅንጅት መመከት ተገቢ ነው፡፡ኢትዮጵያ በጉያዋ በሚገኙ ሁሉም ወጣቶች አስተዋጽኦ የምትገነባና የምትጠበቅ የጋራ ጎጆ ናት፡፡ ልዩነት በአንድነት ሲታጀብ ጉልበት ነው፤ ኃይል ነው፤ ውበት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2011
ሙሐመድ ሁሴን
Your writing style is so engaging and easy to follow I find myself reading through each post without even realizing I’ve reached the end
Your blog has become my go-to source for positive and uplifting content Thank you for consistently delivering high-quality posts
Your blog has quickly become one of my favorites I always look forward to your new posts and the insights they offer
Your blog post had me hooked from the first sentence.
Your writing is so genuine and heartfelt It’s refreshing to read a blog that is not trying to sell something or promote an agenda
Love this blog! The content is always so relevant and insightful, keep up the great work!
Your writing is so genuine and heartfelt It’s refreshing to read a blog that is not trying to sell something or promote an agenda
This blog is a great mix of informative and entertaining content It keeps me engaged and interested from start to finish
Your blog has been a constant source of support and encouragement for me I am grateful for your words of wisdom and positivity