የሰላም ዋጋው ስንት ነው?

ተጨንቆና ተጠብቦ ቤት ያፈራውን አዘጋጅቶ እንግዳን መቀበል የተለመደ ኢትዮጵያዊ ባህል ነው:: በተለይ የገጠሩ ማህበረሰብ ደግሞ ወተቱን፣ እርጎውን፣ ጠላና የማር ጠጁን አማርጠው፤ ምግቡንም ጨምረው ያላቸውን ያለስስት ከአክብሮት ጋር አቅርበው ማስተናገድ የተለመደ ነው:: ከከተማ ለሄደ ሰው ደግሞ ልዩ አክብሮት አላቸው:: ወደ ገጠሩ ሲሄዱ ይሄ ሁሉ ነው የሚናፍቀው::

ኢትዮጵያ ሰላም ከራቃት ወዲህ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሄድኩ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖኛል:: ምክንያቱ ግልጽ ነው:: ያለው የፀጥታ ሁኔታ ስጋትና ፍርሃት ውስጥ ስለከተተን እንቅስቃሴያችን ተገትቷል:: ለዚህም ነው ሰሞኑን ለአዲስ አበባ ከተማ ቅርብ በሆነው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ወልመራ ወረዳ አንደኛ በርፈታ(በርፈታ ቶኮፋ) ቀበሌ ወደገጠሩ ወጣ ባልኩበት ጊዜ የናፈቀኝን የገጠሩን ማህበረሰብ የአክብሮት መስተንግዶ፣ የአካባቢውን ንጹህ አየር፣ ሁሉ ነገር እንደ አዲስ ብርቅ የሆነብኝ::

ሀገራችንን የገጠማት የሰላም እጦት እንዲህ በፍቅርና በአክብሮት አብሮ የሚኖረውን ህብረተሰብ በየአጋጣሚው እንዳይገናኝ፣ እንዲራራቅ እርስበርሱም እንዳይተማመንና በጥርጣሬ እንዲተያይ ስጋት ውስጥም እንዲወድቅ አድርጎታል:: እኔም ስለ ሰላም የተረዳሁት በተለይም ሰላም ያለውን ዋጋ የተገነዘብኩት ፤ በርፈታ ቶኮፋ ቀበሌ ለአንድ ቀን በነበረኝ ቆይታ ነው::

ከሩቅ የመጡ እንግዶች ናቸው ብለው ነው ቤት ያፈራውን ያለስስት አቅርበው በአክብሮት የተቀበሉን:: ምንም እንኳን የሄድነው ለሥራ ቢሆንም፤ በመስተንግዶአቸው እንግድነት እንዳይሰማን አድርገውናል:: በጋራ ማዕድ መቋደሱና መጫወቱም አብሮነታችንን የሚሳይ ነበር::

ረዘም ላለ ጊዜ ወደ ገጠር ወጣ ባለማለቴና በሕዝብ ለሕዝብ መካከል ልዩነት እንደተፈጠረ አድርገው አንዳንዶች እንደሚያወሩት ተቀይረው የመሰሉኝ ነገሮች እንዳልተቀየሩ ነው ያረጋገጥኩት:: የገጠሩ ነዋሪ አስፈሪ ሳይሆን ሰላም ነው:: ሰላም ልማት ፈላጊ ማህበረሰብ ነው:: በገጠሩ የሚኖረው ማህበረሰብ ዛሬም የልማት ጥያቄ አለው:: መልማት፣ማደግ ነው ፍላጎቱ::

እኔን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞች በቀበሌ የተገኘነው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የማያገኘውን የገጠሩ ማህበረሰብ የኃይል ፍላጎት በገጠር ኢነርጂ አማራጭ/ የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ ነው:: የቀበሌው ነዋሪዎች የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆናቸው የነበራቸው የደስታ ስሜት በቃላት የሚገልጽ አልነበረም::

በተለይም ሴቶች እጅግ በጣም ነበር የተደሰቱት:: ምክንያቱ ግልጽ ነው:: የገጠሯ ሴት ለማብሰያ ማገዶ ለመልቀምና ውሃ ለመቅዳት የምትደክመው ድካም ከጥንት ጀምሮ የምናውቀው ጉዳይ ነው:: በኩበትና በእንጨት ጪስ ለዓይን እና ለመተንፈሻ አካል የጤና ችግር የሚጋለጡ ሴቶች ቁጥርም ቀላል አይደለም::

ጤናቸው እንዲጠበቅ፣ድካማቸውም እንዲቀንስ መንግሥት ከተለያዩ ለጋሽ ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራ ያለውን የኃይል አማራጭ ነው የቀበሌ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆን የቻሉት:: እንዲህ የማህበረሰብ ችግር የሚፈቱ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻለው ግን ሰላም ሲኖር ነው:: የሰላም ዋጋም የሚታወቀው እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎችን በነፃነት መተግበር ሲቻል ነው::

ዛሬ የፀጥታ ስጋቱ በከፋባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ይህን የልማት ሥራ ተደራሽ ወይንም መተግበር አልተቻለም:: አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ነው የገጠሩን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ የልማት ሥራ እየተሠራ ያለው:: የፀጥታው ስጋት የልማት ሥራን በማደናቀፍ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት እንዳይኖር የሚያደርግና የማህበረሰብንም እድገት ወደኋላ የሚያስቀር እንደሆነ ይኸው እውነታ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል::

ይህን የልማት ሥራ የሚደግፉ ዓለምአቀፍ ተቋማትም የገንዘብም ሆነ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ የሚነሳሱት ሰላም ሲኖር ነው:: የፀጥታ መደፍረስ የድጋፍ እድሎችንም ያሳጣል:: የልማት ሥራዎችን በኢትዮጵያ አቅም ብቻ መወጣት ስለማይቻል የለጋሾችን ድጋፍ ለማግኘት ሰላሟ የተጠበቀ የተረጋጋች ሀገር ልትኖረን ይገባል::

ሀገራዊ የሰላም እጦቱ የልማት ሥራን በማደናቀፍና በሕዝብ ለሕዝብ አንድነት ላይም እያሳደረ ያለው ተጽእኖ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም:: በኔ እምነት ባልጠበቅነው ሁኔታ ነገሮች መልካቸውን ስለቀየሩ እንጂ በውስጣችን የቆየውን አብሮነት የማጣት፣የመለያየት ፍላጎት የለም::

ሀገራችን በገጠማት የሰላም እጦት ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች መሄድ ስጋት በመሆኑ ያለውን ትክክለኛ እውነታ እንዳናይ ሆኗል:: በጥርጣሬና በፍርሃት እንድንሸበብም አድርጎናል:: እንዲህ እንድንሆን ለሚፈልጉ ወገኖች እድል መስጠት አለብን ብዬ አላምንም::

ማህበረሰብ ለማህበረሰብ ግንኙነቱ የጠነከረ ከሆነ፣ እንዲቋረጥ እየተደረገ ያለው ማህበራዊ ትስስር ብቻ ሳይሆን፤ አንዱ ለሌላው በችግሩና በደስታው እንዳይደርስ፣ በኢኮኖሚም አቅም እንዳይፈጥር ነው:: በገጠሩ የተመረተው የግብርና ውጤት ከተማ የሚኖረው ካልገዛ የኢኮኖሚ አቅም አይፈጠርም:: ማህበረሰብ ለማህበረሰብ ግንኙነቱ የጠነከረ ከሆነ ግን በመካከላችን ሆነው ሊያለያዩን የሚሞክሩትን ማስቀረት የሚቻልበት እድል እንደሚኖር አልጠራጠርም::

ኢትዮጵያ በውስጥ በገጠማት የፀጥታና የጦርነት ችግር፤ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው ከጎኗ ከመቆም ይልቅ የተለያየ ጫና በማድረግ ሊያዳክሟት በሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ሀገራት በተፈጠረባት የኢኮኖሚ ጫና አጣብቂኝ ውስጥ መቆየቷ ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው::ይህንንም ጫና አሸንፎ ለመውጣት የሚደረገው ጥረት ፈታኝ ነው።

በተለይም በውስጥ ባለው አለመረጋጋት የዜጎች ህይወት፣ ንብረት እያጣች ነው:: ይህም በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዋ ላይ ትልቅ ጫና እያሳደረባት ይገኛል:: ሰላም ለማስፈን ፍላጎቱና ዝግጁነቱ ከሌለ ችግሩ ተባብሶ ልንወጣው የማንችለው አረንቋ ውስጥ እንዳይከተን ልብ ሊባል ይገባል:: በፀጥታ መደፍረስ ያጣነውን መልሶ ለመጠገን ብዙ የቤት ሥራ ስለሚጠብቀን የእስካሁኑ ጉዳት ይበቃናል::

ኢኮኖሚው እንዲያገግም፣ ማህበራዊ ትስስሩም ወደነበረበት እንዲመለስ፣ ፖለቲካውም ከስብራቱ እንዲጠገን ማድረግ፤ ያለችንን አንድ ሀገር መታደግ የምንችለው በጠረጴዛ ዙሪያ ሆኖ በመመካከር ነው:: ሰላማችንን መመለስ የምንችለውም እኛው ኢትዮጵያውያን ነን:: የሰላም ዋጋ በገንዘብ አይተመንም:: ለሰላም ልባችን ክፍት ይሁን::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You