የቅኝ ገዥዎች ፍላጎት ማስፈጸሚያ የነበሩ የዓባይ ውሃ አጠቃቀም ውሎች

ዓባይ የሚለው የአማርኛ ቃል አንዳንዶች የወንዞች ሁሉ አባት ከሚለው የመጣ ነው ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ አታላይ፣ ቀጣፊ፣ ለኢትዮጵያ ያልጠቀመ ከሃዲ በሚለው ይበይኑታል፡፡ ቃሉ ላልቶ ሲነበብ ከሚፈጥረው ትርጓሜ በመነሳት ዓባይ ውሸታም ማለት እንደሆነም የሚናገሩ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ኦሪት ዘፍጥረት ምዕራፍ 2፤ ቁጥር 13 ላይ ወንዙ ፈለገ-ጊዮን ተብሎ የሚጠራው ይኸው ወንዝ እንደሆነ የሚስማሙ አሉ።

የዓባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አንድ አስረኛ ግዛት የሚሸፍን ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ የአየር ፀባዮችን ያስተናግዳል። በታላላቅ ሐቆይች አካባቢ የኢኩዋቶሪያል አየር ንብረትን፣ ከምስራቅ አፍሪካ የታቺኛው ክፍል ሲነሳ የትሮፒካል፣ ከዚያም ነፋሻማውን የኢትዮጵያ ከፍታ አምባ አቋርጦ በረሃማና ምድረ በዳማ በሆነው የሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ክልል ዘልቆ ሜዲትራኒያን ባህር በመግባት ጉዞውን ይጨርሳል፡፡

በዚህ ረዥም የጉዞ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሱዳን፣ ግብጽና ደቡብ ሱዳን አቋርጦ ያልፋል። ኢትዮጵያ የዓባይ ንዑሰ ተፋሰስ የሆነው የጥቁር ዓባይ ምንጭ ነች፡፡ እስከ 86 በመቶ የሚደርሰውም የናይል ወንዝ ውሃ የሚመነጨውም ከዚቹ ሀገር ነው፡፡ ይህ የውሃ ድርሻዋም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባለሙሉ መብትና ባለብዙ ተጽዕኖ አሳራፊ ሀገር እንድትሆን አስችሏታል፡፡

ታሪክ ፀሐፊው የአረብ ተወላጅ አልማኪን እንደፃፈው፤ በፋቲሚድ ሥርወ-መንግሥት በሱልጣን አቡታምሊን አልሙስታንዚር የአገዛዝ ዘመን (1035-1094) ግብጽ የሚደርሰው የዓባይ ወንዝ ውሃ መጠን ከ1089-1090 ባለው ጊዜ አካባቢ በመቀነሱ ሱልጣኑ የግብጽ ቤተ-ክርስቲያንን ፓትርያርክ አባሚካኤልን ከፍ ያለ ገጸ-በረከትአስይዞ በኢትዮጵያውያን የተቋረጠውን የዓባይን ወንዝ እንዲለቁ ለመለመን ወደ ኢትዮጵያ ልኳቸዋል። ጉዞውም በ1092 እና 1094 ዓ.ም መሀከል ባለው ጊዜ ውስጥ ነበር።

ሌላው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አንድ ኮረብታ እንዲፈርስ ባዘዘ ጊዜ የውሃው መጠን በአንድ ሌሊት ሶስት ጫማ ከፍ ብሎ አደረ ሲል ተርኳል፡፡ በዘመኑ የነበረው የኢትዮጵያ ንጉሥ የዛግዌውይምርሀነ ክርስቶስ እንደነበር ዘውዴ ገ/ሥላሴ የተባሉ ምሁር ‘የዓባይ ተፋሰሶች ዓለም አቀፋዊ ችግር’ በሚል ርዕስ በሳፈሩት ጽሑፍ ላይ ጠቁመዋል፡፡

ሆኖም ከቅኝ ግዛት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ያላትን መብትና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጣች መጥታለች፡፡ በተቃራኒው ቀደም ሲል ለኢትዮጵያ ሲገብሩና ሲመለዱ የነበሩት ግብጾችና ሱዳኖች የቅኝ ገዢዎችን በተለይም የእንግሊዝን ተጽዕኖ ፈጣሪነት በመጠቀም የበላይነቱን ለመያዝ ሞክረዋል። የተዛባ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብቶችን በመጠቅስ የመከራከሪያ አጀንዳ አድርገው ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

በታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ መብቶች ላይ ተመስርተው በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከሚቀርቡ የመብት ክርክሮች መለስ ዓባይን አስመልክቶ እስከአሁን ያለውን ሕጋዊ ሁኔታ በዋናነት የሚወስኑ ሁለት ሰነዶች ናቸው፣ የመጀመሪያው በቅኝ ግዛት ዘመን እ.ኤ.አ ግንቦት 7 ቀን 1929 በታላቋ ብሪታኒያና በግብፅ መካከል የተደረገው ስምምነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ከሰላሳ ዓመት ቆይታ በኋላ ከነጻነት ወዲህ እ.ኤ.አ ኅዳር 8 ቀን 1959 በሱዳንና ግብጽ መካከል የተፈረሙ ስምምነቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ሁለት ስምምነቶች በሚፈረሙበት ወቅት እንግሊዝ ከላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ሱዳንን፣ ታንዛኒያን፣ ኡጋንዳን፣ እና ኬንያን በመወከል ግዴታ ከመግባትዋ ውጭ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራት ተካፋይ አልነበሩም፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ በወቅቱ ነፃ ሀገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ በስምምነቱ ተካፋይ መሆን ቢገባትም በሂደቱ በጋራ መብትዋን እንድትወስን ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳይቀርብላት ቀርቷል፡፡

በ1929 እና 1959 በተደረጉት ስምምነቶች መሠረት ግብጽ በዓባይ ላይ የፍሰቱን ባለቤትነት መብት ስትጎናፀፍና በተጠቃሚነት ረገድም ከ55ቢሊዮን ኪዩብ በላይ ድርሻ እንዲኖራት ሱዳንም 18 ቢሊዮን ኪዩቢክ የውሃ መጠን ድርሻ እንዲኖራት ተደርጓል። ከ86 በመቶ በላይ የውሃው ባለቤት የሆነች ኢትዮጵያ ግን ቅንጣት ታክል የውሃ ድርሻ እንዲኖራት አልተደረገም፡፡

እነዚህ ሁለቱ ስምምነቶች እስከዛሬም ድረስ በሕዳሴ ግድብ ላይ በሚደረጉ ውይይቶች እንደማጣቀሻ እየቀረቡ ግብጾች በማደናገርያነት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ። ሰሞኑንም አራተኛው ዙር የመጨረሻው ድርድርም በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት ያህል ሲካሄድ ቆይቶ ያለ ውጤት ተበትኗል፡፡ ለውይይቱ ያለ ውጤት መበተን ዋነኛው ምክንዓትም ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን አቋሟን በመያዟ ኢትዮጵያ ባልፈረመችው ውል እንድትገዛ በግብጽ በኩል ከፍ ያለ ፍላጎት በመኖሩ ነው። ይህ ደግሞ “ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ” የሚለውን ሀገራችንን ተረት የሚያስቀውሰን ነው፡፡

ለዛሬ በግብጽ በተደጋጋሚ በመከራከሪያነት የሚቀርቡትን በታሪክ ሰነድም የቅኝ ግዛት ውሎች ተብለው የሚጠሩት የትኞቹ ናቸው? እነዚህ ውሎች ከኢትዮጵያውያን ጋር ያላቸውስ ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለውን በአጭሩ እንመልከት ፡፡

1929 ውል

በ19ኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ፣ እንግሊዝ ግብጽን በቁጥጥሯ ካስገባች በኋላ፣ ግብጽን አረጋግቶ ለመግዛት ዋናው ቁልፍ የዓባይ ውሃ መሆኑ እንግሊዝ ተረዳች፡፡ ግብጽ ውስጥ ለመደራጀትና በስዊዝ ቦይ ላይ እንግሊዝ ያላትን ስትራቴጂ ይዛ ለመቀጠል ከፈለገች፣ የዓባይ ውሃ ያላንዳች እክል ወደ ግብጽ ግዛት እንዲዘልቅ ማድረግ ዋናው ዘዴ መሆኑን ተገነዘበች፡፡

ይህንኑ መነሻ በማድረግ እንግሊዝ በቅኝ ግዛት የያዘቻቸውን ሀገራት (ሱዳን፣ ኬንያ፣ ታንጋኒካና ኡጋንዳን) በመወከል ከግብጽ ጋር በ1929 ባደረገችው ስምምነት ወደ ግብጽ የሚደርሰውን የዓባይን ውሃ መጠን የሚቀንስ ማንኛውም ተግባር በወንዙ ላይ እንደማይከናወን ቃል ገብታለች፡፡ ስምምነቱ በእንግሊዙ የግብጽ ኮሚሽነር እና በግብጽ የሚንስትሮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሞሃመድ መሃመድ ፓሻ መካከል የተፈረመ ሲሆን በአስዋን አናሳው ግድብ ያለው ውሃና ወንዙ ከጥር እስከ ሐምሌ በየዓመቱ የሚኖረው ፍሰት ሙሉ ለሙሉ ለግብጽ ጥቅም እንዲውል ደንግገዋል::

መነሻ በሆነው የናይል ኮሚሲዮን ሪፖርት መሠረት ሱዳን በየዓመቱ 4 ቢ.ኩ.ሜ. ውሃ ከተጠቀሱት ወቅቶች ውጭ ብቻ ለመጠቀም ሲፈቀድላት ግብጽ ትልቁን ድርሻ በመውሰድ በአማካይ 48 ቢ.ኩ.ሜ. የወንዙን ፍሰት እንድትቆጣጠር አስችሏታል፡፡ በተጨማሪም በወንዙ ላይ የሚከናወኑ ማናቸውንም ፕሮጀክቶች ግብጽ የመቆጣጠርና የመከታተል መብትን ተጐናጽፋለች፡፡

በዚህ ስምምነት መሠረት የእንግሊዝ ግዛት በሆኑት በሱዳን፣ በኬንያ፣ በታንጋኒካና በኡጋንዳ በዓባይና በገባር ወንዞቹ ላይ ወይም መነሻ በሆኑት ሐይቆች ላይ ማንኛውም የግንባታ ሥራ በተለይም ከመስኖና ከኃይል ማመንጨት ጋር የተያያዙ፣ ወይም ግብጽ የሚደርሰውን የውሃ መጠን የሚቀንሱ ወይም በሌላ መንገድ በግብጽ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የግንባታ ሥራዎች ያለ ግብጽ ፈቃድ እንዳይሰሩ ይከለክላል፡፡

የ1929 ስምምነት በቀዳሚነት ሁለት ነጥቦችን የሚመለከት ሲሆን በመጀመሪያ የግብጽን ጥቅም የሚጐዳ ማናቸውም ተግባር የግብጽ መንግሥት ካልተስማማ በቀር በዓባይ ውሃ ላይ ሊከናወን እንደማይችል፤ በሌላም በኩል ደግሞ ወንዙ ላይ የሚካሄድ የግንባታ ተግባር በግብጽ መንግሥት ቁጥጥር ሥር እንደሚከናወን የሚገልፅ ነው፡፡

የአካባቢው ቅኝ ገዢ የነበረችው እንግሊዝ በዓባይ ወንዝ ላይ የበላይነቷን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያን በከፊል የውሉ አካል ለማድረግ ሞክራለች፡፡ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እና እንግሊዝ ግንቦት 15 ቀን 1902 አዲስ አበባ ላይ በተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የዓባይን፣ የጣና እና ሰባት ወንዞችን የተፈጥሮ ፍሰት ሙሉ ለሙሉ የሚደፍን ተግባር እንዳታከናውን የሚከለክል ቃል ኪዳን ነው፡፡

በውሉ የእንግሊዝኛ ቅጂ መሠረት ከታላቅዋ ብሪታኒያ እና ሱዳን መንግሥት ጋር አስቀድሞ ሳይስማሙ፣ በአማርኛው ቅጂ ደግሞ ከብሪታኒያ መንግሥት ብቻ ጋር አስቀድመው ሳይስማሙ ንጉሠ-ነገሥት ምኒልክ ወንዝ ተዳር ዳር የሚደፍን ሥራ እንዳይሰሩ ወይንም ለመሥራት ፈቃድ እንዳይሰጡ ግዴታ ገብተዋል፡፡ ስለሆነም ምንም እንኳን ግብጽ በወቅቱ በሱዳን ላይ የጋራ አስተዳደር ስልጣን (co-domini) የነበራት ቢሆንም ስምምነቱ በዋናነት እንግሊዝ፣ ሱዳንን እና ኢትዮጵያን ብቻ የሚያሳትፍና የሚስገድድ መሆኑ ግልጽ ሆኖ እናገኘዋለን።

ባጠቃላይ በዓባይ ውሃ ላይ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት ለግብጽ ያበረከተው የ1929 ስምምነት የግብጽን መንግሥት ወዳጅነት ለማፍራትና የእንግሊዝን የፖለቲካ ጥቅም ለማዳበር የታቀደ እንጂ በተለመደው የኢንተርናሽናል ሕግ ውስጥ ዋጋ እንደሌለው የሕግ ሊቃውንት እና ጸሐፍት በተለያዩ ወቅቶች ሲወተውቱ ኖረዋል፡፡

1959 ውል

በእንግሊዝና ግብጽ መካከል የተደረገው እ.ኤ.አ የ1929 ስምምነት በሌላ ፍትሐዊና ሚዛናዊ በሆነ ስምምነት እንዲተካ ግብጽ ጽኑ ፍላጎት ነበራት። በተለይም ስምምነቱ ሱዳንን ያላሳተፈ በሁለቱ ቅኝ ገዢ ሀገራት መካከል ብቻ የተደረገ በመሆኑና በተጨማሪም የሱዳንን ጥቅም በሚጐዳ አኳኋን የተፈጸመ መሆኑን ሱዳኖች አበክረው ያነሱ ነበር፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው እ.ኤ.አ በ1929ኙ ስምምነት ሁለቱ የግርጌ ሀገራት ማለትም ግብጽ በዓመት 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ስታገኝ ሱዳን 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ እንዲደርሳት ተደርጎ ነበር፡፡

በዚህ የውሃ ክፍፍል ያልተደሰቱት ሱዳኖች በየጊዜው በርካታ ጥያቄዎችንና ተቃውሞዎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል። ይህ የሱዳኖች ኩርፊያ ያሰጋቸው ግብጾችም አዲስ ውል ለመፈራረም ተዘጋጁ። በዚህም የ1929ኙ ስምምነት እንዳለ ሆኖ ኅዳር 8 ቀን 1959 ወንዙን የሚከፋፈሉበትን የማሻሻያ ስምምነት ፈርመዋል፡፡ በአዲሱ ስምምነት መሠረት ግብጽ በዓመት 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲሁም ሱዳን በዓመት 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡

አድሏዊና ኢፍትሃዊ የሆኑት የ1929ኙም ሆነ የ1959ኙ ስምምነቶች ከ86 በመቶ በላይ የናይል ውሃ ምንጭ የሆነችውን ኢትዮጵያን ያገለሉ ነበሩ፡፡ በዚህም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ከፍተኛ ቁጭት እና ሀገራዊ እልህ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡ ይህ ሀገራዊ ቁጭትና እልህም ጊዜው ፈቅዶ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ተጣለ፡፡ የኢትዮጵያውያንም የዘመናት ቁጭት ተመለሰ፡፡

በሌላ በኩል የወንዙ አካባቢ ሕዝቦች ቁጥር እየጨመረ በመሄዱና ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ጥቅም ላይ የማዋል ፍላጎታቸው እያደገ በመሄዱ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች በወንዙ የላይኛው ክፍል የሚገኙ ሀገራት ስለዓባይ ውሃ አጠቃቀም ከዚህ በፊት የተፈረሙትን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች በመንቀፍ እንደማይቀበሉት በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በተደጋጋሚ አሳውቀዋል፡፡

እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮም የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ (Nile Basin Initiative) የተሰኘ ጊዜያዊ የትብብር ማዕቀፍ በማቋቋም አንድ ልዩ የናይል ቤዚን ኮሚሽን ለመመስረትና በዓለም አቀፍ ሕግ ይዘት የተቃኘ ተፋሰስ-አቀፍ ውል ለማዘጋጀት በናይል የሚኒስትሮች ካውንስል በኩል ድርድር ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ግብጽና ሱዳን የፈረሙት የ1959 ስምምነት የዓባይን ውሃ ሀብት ከአሥር የተፈሰሱ ተጋሪ ሀገሮች ለሁለቱ ብቻ የሚያከፋፍል በመሆኑ ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ስምምነት ሆኖ ሌሎቹን ተጋሪ ሀገሮች ለማስገደድ እንደማይችል የሕግ ሊቃውንቱ እና ጸሐፍት ሲወተውቱ ኖረዋል፡፡ ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያ ጨምሮ በሁሉም ዘንድ የሚነሳ ነው፡፡

ኢትዮጵያም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር ተከታታይነት ያላቸውን ድርድሮች በማድረግና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ አካሄድን በመከተል ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ እግረ መንገዷንም የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከ94 በመቶ በላይ በማድረስ መጪውን ብሩህ ተስፋ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች፡፡

ሆኖም ከድሮ እስከ ዘንድሮ ውዝግብ የማያጣው የዓባይ ውሃ ከሀገርና አህጉር አልፎ ዓለም አቀፍ መወያያ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም በፀጥታው ምክር ቤት የታየ አነጋጋሪ አጀንዳ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አይበገሬዎቹ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ ዳር እስኪደርስ ድረስ የሚያግዳቸው ተራራ፤ የሚያዳልጣቸው ቁልቁለት አይኖርም፡፡

እስማኤል አረቦ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You