የኑሮ ውድነቱ ፈተናና መውጫ መንገዱ

 ባለንበት ወቅት የኑሮ ውድነት በሩን ያላንኳኳበት ሰው አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ ‹‹የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አልቻልንም፤ በየቀኑ በምርትና በአገልግሎት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እየተደረገ በመሆኑ መኖር ከብዶናል›› የሚል ምሬት መስማት ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል። ምን መስማት ብቻ በኑሯችን ላይ የሚያሳድርብን ጫና ይለያይ እንጂ አብዛኛዎቻችን የዚሁ ችግር ሰለባም ሆነናል።

የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ፣ ጦርነት፣ የበሽታ ወረርሽኝ በምርቶች ላይ የሚታይ ዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ለኑሮ ውድነቱ እንደአሳማኝ ምክንያት ይጠቀሳሉ፡፡ እርግጥ ነው፤ እነዚህ ችግሮች ሲከሰቱ ገበያ መደነቃቀፉ አይቀርም፡፡ ምርት ከአንድ ሀገር ወደ ሌላ ሀገር፤ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሊዘዋወር አይችልም፡፡ ነዳጅ በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ከሚጫወተው ሚና አንጻር ድንገት የዋጋ ጭማሪ ሲደረግበት ከእርሱ ጋር ተያይዞ በአገልግሎቶችና በምርቶች ላይ ጭማሪ መምጣቱ የማይቀር ነው፡፡

በምግብ፣ በቁሳቁስ፣ በአገልግሎት እና በሌሎችም ላይ እለት ተእለት እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያሸቀበ ነው፡፡ አንዳንዶች ችግራቸውን አምቀው የቤቴን በቤቴ ብለው ተቀምጠዋል፤ የባሰባቸውም ጎዳና ወጥተው ምጽዋት እስከመጠየቅ ደርሰዋል፡፡ ይህንን ሀቅ ለማረጋገጥ አካባቢያችንን እና ጎረቤቶቻችንን መቃኘት በቂ ነው፡፡

አንዳንድ ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ተፅእኖዎች ለኑሮ ውድነቱ መፈጠር እንደምክንያት መጠቀሳቸው እውነትነት ቢኖረውም ከፊል እንጂ ሙሉ ድርሻ ይኖራቸዋል የሚል እምነት ግን የለኝም። ምክንያቱም አንዳንዶቹ የዋጋ ጭማሪዎች ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ የሚፈጥሯቸው ናቸው፡፡

እርግጥ የምንከተለው ነጻ ገበያ ነው፡፡ ነጻ ገበያ በሰለጠነው ዓለም እና በእኛ ማህበረሰብ ዘንድ እየተተረጎመ የሚገኘው ግን በተለያየ መንገድ ነው፡፡ የነጻ ገበያ እሳቤ በነጋዴው ማህበረሰብ ዘንድ ከምርት አቅርቦት፣ ጥራትና ከዋጋ አንጻር የተፎካካሪነት መንፈስን በመፍጠር አገልጋዩንም ተገልጋዩን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንጂ፤ ጥቂት ነጋዴዎች ምርትን አጋብሰው በመጋዘን እያከማቹ፤ በሚፈልጉት ሰአት እየቆነጠሩና የፈለጋቸውን ዋጋ እየጨመሩ የሚሸጡበት የገበያ ሥርዓት አይደለም።

ዛሬ በሀገራችን ለተፈጠረው የኑሮ ውድነትም ሆነ ችግሩን ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ ያደረገው ይሄው በነጋዴዎቻችን ዘንድ የሚስተዋለው የአስተሳሰብ መዛነፍ ነው፡፡ የሀገርና የህዝብን ችግሮች የመክበሪያ መንገድ አድርጎ ማየትና ይህንኑም ያለ ይሉንታ ተግባራዊ ማድረግ።

በርግጥ በየወቅቱ እንደምንሰማው መንግሥት በተለያዩ መንገዶች የኑሮ ውድነቱን ለመቀነስ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በተለያዩ መንገዶች ይደጉማል። በመቶ ሚሊዮን ዶላሮችን ወጪ በማድረግም ከውጪ አስፈላጊ ሸቀጦችን ገዝቶ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በዝቅተኛ ዋጋ ያቀርባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በሸማቾች ሪቮልቪንግ ፈንድ በርከት ያለ ገንዘብ በሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበር ውስጥ እንዲንሸራሸር ማድረጉን መግለፃቸው ይታወሳል።

ከዚህ በተጨማሪ ቅዳሜ እና እሁድ በየቦታው የምናገኘው የእሁድ ገበያ የኑሮ ውድነትንና በገበያ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ለማረጋጋት ታስቦ በመንግሥት ተግባራዊ የተደረገ ነው። በነዚህ ገበያዎች ማህበረሰቡ በሌላ ቀን በውድ ዋጋ የሚገዛቸውን እቃዎች በተሻለ ዋጋ መገበያየት እንዲችል ማድረግ ችሏል፡፡

ገበሬው ያመረተውን ምርት በቀጥታ ያለደላላ ጣልቃ ገብነት ራሱ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማድረስ የሚችልበትን መንገድ ለማመቻቸት የገበያ ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑም የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከተሰሩ ስራዎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህ ትልቅ እና ሊበረታታ የሚገባ ተግባር ነው።

ስራው ገበሬው ያመረተውን ምርት በቀጥታ ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ማድረስ እንዲችል ማድረግ መቻል እና ማህበረሰቡም ምርቱን ካመረተው ገበሬ በቀጥታ መግዛት መቻሉ በመሃል በደላሎች ምክንያት የሚኖረውን የገበያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ለመግታት ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡

ከዚህም ባለፈ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ ነው። ለዚህም አሁን ላይ የተጀመረውንና ውጤታማ የሆነውን የበጋ መስኖ ስንዴ በስፋት በመላ ሀገሪቱ መተግበር ያስፈልጋል። በሌሎች የምግብ እህሎች የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችንም ማስፋት ያስፈልጋል።

ገበሬው ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለተጠቃሚ ምርቱን ማድረስ እንዲችል ለማድረግ የተጀመረው የገበያ ማዕከላት ግንባታም አጠናክሮ ከመቀጠል ባለፈም፤ በማእከላቱ የሚከናወኑ ግብይቶች ሥርዓት እንዲዙ ማድረግም በተመሳሳይ መልኩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ከዚህ ባሻገር የንግዱ ማህበረሰብ የህብረተሰቡ አንድ ክፍል እንደመሆኑ መጠን ከጥንት እስካሁን አብሮን የኖረውን የመተሳሰብ ባህላችንን ማስቀጠል ይኖርበታል፡፡ በእንደዚህ አይነት ጊዜ ሁሉም ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ በመተሳሰብ ነገሩ ከዚህም በላይ ከባድ እንዳይሆንብን መንቀሳቀስ ይኖርበታል፡፡

ይህን ስል የማህረሰቡን ችግር የሚረዱ ነጋዴዎች ቢኖሩም በዚያው ልክ እኔ ብቻ ልጠቀም ባይ ነጋዴዎችም በስፋት ስለመኖራቸው ለመጠቆም ፈልጌ ነው፡፡ ያለ ትርፍ ህዝባችን ያለበት ችግር የማይታያቸው ስግብግብ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የሚወሰዳቸውን የመፍትሄ እርምጃዎች በቀላሉ ውጤት እንዳያመጡ የነዚህ አይነት ነጋዴዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነውና መታረም ይጠበቅባቸዋል።

ቲሻ ልዑል

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You