የሰላምን ፍሬ ለመብላት ስለሰላም እንሥራ

ኢትዮጵያ ከመንግሥት ለውጥ ወዲህ በበርካታ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክዋኔ ውስጥ አልፋለች። አያሌ፣ አዳዲስ፣ ያልተሰሙና እንግዳ ክስቶችንም አስተናግዳለች ። በነዚህ አምስት የለውጥ ዓመታት ጉዞ ውስጥ በኢትዮጵያ ከተከሰቱና አሁንም ድረስ ሀገሪቱን እየፈተኑ ካሉ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሰላምና ደህንነት እጦት ነው።

በተለይ ለውጡ ከመጣ ከሁለት ዓመት ወዲህ ማንነትን፣ ወሰንን፣ የፖለቲካ ልዩነትንና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎችን ተከትለው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች፣ የሰላምና ፀጥታ መደፍረሶች ተፈጥረዋል። የሰዎች በሰላም ወጥቶ መግባትና የደህንነት ሁኔታም አደጋ ላይ ወድቆ እንደነበር ይታወቃል።

የለውጡ መንግሥት የተፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የበኩሉን ጥረት ቢያደርግም ችግሩን ግን እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ሊፈታ አልቻለም። የተለያዩ ጥያቄዎች የነበራቸው ፖለቲከኞችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ መንግሥት የበኩሉን ጥረት ቢያደርግም ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ኃይልን እንደአማራጭ በመውሰዳቸው በሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት ሊረጋገጥ አልቻለም።

በእንዲህ ሁኔታ የቀጠለው የሀገሪቱ የሰላምና ደህንነት ችግር ተባብሶ በመጨረሻ ሀገሪቱን ወደከፋ ጦርነት ከቷታል። ከድጡ ወደማጡ እንዲሉ በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት የሀገሪቱን የሰላምና ደህንነት ሁኔታ ይበልጥ አደጋ ውስጥ ከቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ይኸው ጦርነት የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ከማሳጣት ባሻገር በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል። በይበልጥ ደግሞ ጦርነቱ የተካሄደባቸው የትግራይ፣ አማራና አፋር ክልሎች የችግሩ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል። ከነዚህ ክልሎች ባሻገር ጦርነቱ በሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ፣ ሰላምና ደህንነት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሯል።

የሰሜኑ ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ፕሪቶሪያ ላይ በድርድር ከተፈታ በኋላ በሀገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ቆይቷል። ምንም እንኳን ጦርነቱ በሀገሪቱ ላይ መጥፎ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ ቢሆንም የሰላም ዋጋ ከፍ ያለ ነውና ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ መፈታቱ ለመላው ሕዝባችን ትልቅ እፎይታ ፈጥሯል።

አሳዛኙ ነገር ሕዝባችን በትግራይ የነበረው ግጭት በሰላም ስምምነት በተጠናቀቀ ማግስት (በፕሪቶሪያው ስምምነት) በአማራ ክልል አዲስ ግጭት መቀስቀሱ ፤ግጭቱም መልሶ ሀገሪቱን የሰላም ችግር ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓል።

መንግሥት በአማራ ክልል የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በተመሳሳይ መልኩ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ቢያደርግም በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ኃይልን እንደአማራጭ በመውሰዱ ችግሩን መፍታት ሳይቻል ቀርቷል ።

ችግሩ ከክልሉ መንግሥት አቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱም ፤ የክልሉ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥት ባቀረበው ጥያቅ መሠረት መከላከያ ሠራዊቱ ወደ ክልሉ ገብቶ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሰፊ ኦፕሬሽኖችን አካሂዷል፤ እያካሄደም ነው። በዚህም ክልሉ አንጻራዊ ሰላም ማግኘት ችሏል።

በሌላ በኩል በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውና መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጀው ሸኔ ትጥቁን ፈትቶ ወደሰላም እንዲመጣ ከሀገር ውጪ በታንዛኒያ ዳሬሰላም ድርድሮች ቢያደርጉም ቡድኑ በሚያነሳቸው ዘመን ያለፈባቸው ጥያቄዎች የተነሳ ውጤታማ ሊሆን አልቻለም። እንዲያም ሆኖ ግን መከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የተለመደ ኃላፊነቱን ተወጥቷል ፤ እየተወጣም ይገኛል።

ሰላምን ለማምጣት በመንግሥት በኩል ከሁለቱም ኃይሎች ጋር ለመነጋገርና ለመወያየት የተደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከስምምነት መደረስ ባለመቻሉና ሁለቱ ቡድኖች ኃይልን አስቀድመው አሁንም ድረስ እንቅስቃሴ እያረጉ በመሆኑ በሀገሪቱ የሚፈለገው ሰላምና ደህንነት አልመጣም።

የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በየአካባቢው ከተከሰቱ ግችቶች ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የተከሰተው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና እሱን ተከትሎ የመጣው የኑሮ ውድነት ሀገሪቱን ለተጨማሪ አደጋዎች ማጋለጡ የማይቀር ነው። የሥራ አጥነት ከማስፋፋት አንስቶ ፤ የወንጀል ድርጊት እንዲባባሱ አቅም መሆኑ አይቀርም። ይህም በራሱ ሀገራዊ ሰላሙ ላይ የሚኖረው አሉታዊ ተጽእኖ ቀላል አይሆንም ።

ከላይ የተዘረዘሩት ምክንያቶች የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ከማናጋት በዘለለ ሀገሪቱን በብዙ መልኩ ወደ ኋላ እየጎተታት ስለመሆኑ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም። ምንም እንኳን ድርቅና ረሀብ ተፈጥሯዊና ከእኛ አቅም በላይ በሆነ ምክንያት የተፈጠረና በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ቢፈጥሩም፤ ከራሳችን ችግር የሚመነጩት ግጭቶችና አለመግባባቶች በራሳችን የሚፈቱ ከመሆናቸው አንጻር በነሱ ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሠራ ይገባል።

መቼም ሰላም ሲኖር ነው ሠርቶ መግባት የሚቻለው። ሰላም ሲኖር ነው ልማቱ የሚፋጠነው። ሰላም ሲኖር ነው ከልማት ትሩፋቶች ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው። ሰላም ሲኖር ነው ሀገር የምታድገው። ሰላም ሲኖር ነው ሁሉም የሚሆነው። ያለ ሰላም ምንም የለም። ከዚህ አንፃር ማንም ቢሆን የሰላምን ዋጋ ከቶውንም ቢሆን መረዳት አያዳግተውም።

የሰላምን ዋጋ የተረዳ ሁሉ ለሰላም እጁን መዘርጋት አለበት። ርግጥ ነው ኑሮ ሰማይ ወጥቷል። ህብረተሰቡ ከመንግሥት ብዙ ነገር እንዲሻሻልለት ይጠብቃል። ያለበት የኢኮኖሚ ችግር እንዲፈታለት ይፈልጋል። በርካታ ጥያቄዎች አሉት። ግን ደግሞ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት የሀገሪቱ ሰላምና ደህንነት በቅድሚያ ሲረጋገጥ ነው። ይህ እውን እንዲሆን ህብረተሰቡ ለሰላሙ ዘብ መቆም ይኖርበታል። ለሰላም መረጋገጥ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረትም መደገፍ ይጠበቅበታል።

በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፋችሁ የፖለቲካ ሃይሎችና የሃይል አማራጭ ወስዳችሁ ጠበንጃ ያነሳችሁ ሃይሎችም ብትሁኑ በቅድሚያ ሰላምና ደህንት በሀገሪቱ እንዲሰፍን መሥራት ይጠበቅባቹሃል። ለሰላም ቅድሚያ ስጡ። የተዘረጉ የሰላም አማራጮችን በመቀበል ስለሰላም ያላችሁን ቁርጠኝነት በተጨባጭ ግለጹ። እንወክለዋለን ለምትሉት ሕዝብ ያላችሁን ከበሬታ አሳዩ ።

መንግሥትም ቢሆን ስለ ሰላም የዘረጋቸውን እጆቹን፤ በሆደ ሰፊነት ጠብቆ በመቆየት እንደ ሀገር ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ሰላምና ደህንነት የሀገሪቱ የትኩረት አጀንዳ አድርጎ ሊሠራ ይገባል። የኑሮ ውድነቱ በማህበረሰቡ ላይ የፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ጫና በተዘዋዋሪ በሀገሪቱ ፀጥታና ደህንነት ላይ ሊፈጥር ከሚችለው አደጋ አንጻር የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻልና ገቢውን ለማሳደግ የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

የዛሬ ችግሮቻችን በአንድ ምሽት የተፈጠሩና በአንድ ምሽት መፍጥሄ ሊገኝላቸው የሚችሉ አይደሉም። ለረጅም ጊዜ ሲገላበጡ የመጡ ከመሆናቸው አኳያ የሁሉንም ትግስት የሚጠይቁ ናቸው። ነገሮች እስኪስተካከሉና መስመር እስኪይዙ ድረስ ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ እንስጥ። መንግሥት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር እየሠራ ያለውን ሥራ በመደገፍ ነገ እና ከነገ ወዲያ የሰላምን ጣፋጭ ፍሬ ለመብላት ራሳችንን እናዘጋጅ!!

 አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You