ዘመኑን የሚመጥን ትውልዶች እንድንሆን

የሥልጣኔ አስጀማሪ የነበረችውን ሀገራችንን እስኪ የበለጸጉ ናቸው ከሚባሉት ሀገራት ጋር እናነፃፅራት፡፡ ከዛሬ አንድ ሺህ ዓመታት በፊት ምን ላይ ነበሩ? እኛ ምን ላይ ነበርን? ከዛሬ መቶ ዓመት በፊት ምን ላይ ነበሩ? እኛ ምን ላይ ነበርን? ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ምን ላይ ነበሩ? እኛ ምን ላይ ነበርን? ዛሬ ምን ላይ ነው ያሉት? እኛ ዛሬ ምን ላይ ነው ያለነው? ይህ ልዩነታችን ለምን መጣ?

ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት ዛሬ የሥልጣኔ ቁንጮ ናቸው በሚባሉ ሀገራት ይደረጉ የነበሩ ዘግናኝ ነገሮች በያኔው ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ አይደረጉም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ያኔ ትሠራቸው የነበሩ የጥበብ ሥራዎችን አይሰሩም ነበር፤ ይባስ ብሎ አንዳንዶቹ እንደ ሀገር ራሱ አልተፈጠሩም ነበር፡፡ እንደ ላሊበላ አይነት (ከ900 ዓመታት በፊት) ሚሊኒየም ተሻጋሪ ሥራዎች አልነበሯቸውም፡፡ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሌሎች የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ሀገራትም ዘግይተው በነቁ ሀገራት ተቀድመዋል ፡፡

ከመቶ ዓመታት በፊት የአውሮፓ ሀገራት በእርስበርስ ጦርነት ይተላለቁ ነበር፡፡ አንደኛውን የዓለም ጦርነት ጨርሰው ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት እያሟሟቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሴት መሪ በነበረባት ጊዜ (ንግሥት ዘውዲቱ 1909 ዓ.ም) ዛሬ የዓለም ልዕለ ኃያል የሚባሉ ሀገራት ሴት ተወካይ እንኳን አልነበራቸውም፡፡ አሜሪካ የምትባል ኃያል ሀገር የመጀመሪያ ሴት ሴናተር ያቀረበችው በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1923 (የዛሬ መቶ ዓመት) ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ ግን በፍጥነት እየበለጡን ሄዱ፤ የመብቶች ሁሉ መስፈርት የሚወጣው በእነርሱ ሆነ፡፡ በተለይም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ ነገሮቻቸው የሰለጠነ ሆነ፡፡ በሀገሮቻቸው መካከል ያለው ድንበር በአዲስ አበባ ውስጥ በክፈለ ከተሞች መካከል እንዳለው ድንበር ልብ የማይባል ሆነ፡፡ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ምን ላይ ነበሩ? ብለን ብናስታውስ ልዩነታችን ሰማይና ምድር ሆኗል፡፡

ዛሬስ? ልዩነታችን እየሰፋ ሄዶ የሌላ ዓለም ፕላኔት እስከሚመስሉን ድረስ ዜጎቻችን ለመኖር የሚመኟቸው ሆኑ፡፡ የመሠልጠን መለኪያዎቻችን ሆኑ፡፡ የሰብዓዊ መብት መለኪያዎች እነርሱ ሆኑ፡ ፡ ዘመናዊነት ሲባል መለኪያው የእነርሱ አኗኗር ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ ለምን ሆነ? ለምን እንደ እነርሱ አልሆንንም? ምኞታችን የሰለጠኑት ሀገራት መሄድ ከሚሆን ይልቅ ለምን ሀገራችንን ማሠልጠን አልፈለግንም?

ሀገራችንን ለማሰልጠን የመጀመሪያውና ዋናው ነገር ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ ግዴታው የሁሉም ዜጋ ነው፡፡ ጉዳዩን ለመንግሥት ወይም ለተፎካካሪ ፖለቲከኞች ብቻ መተው ለውጥ አያመጣም፡፡ የሰለጠኑ ሀገራት እዚህ የደረሱት እንደ ዜጋ ስለነቁ ነው፡፡ በአንድ መንግሥት (ፓርቲ) ብቻ እዚህ ላይ አልደረሱም፡፡ የሚመጣው ያለፈውን በማስቀጠል እና ዜጋው ደግሞ በሰለጠነ መንገድ ሀገሩን ስለሚያገለግል ነው፡፡

በሀገራችን ይህን ለማምጣት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ሰሞኑን በብዙ አካባቢዎች ሥልጠና እየሰጠ ነው፡፡ የሥልጠናው አንዱ ዓላማ ይህ ግንዛቤ እንዲኖረን ነው፡፡ ተሳትፎው እንደ ሕዝብ መሆን ስላለበት ነው፡፡ ሁሉም መመካከርና ቁጭ ብሎ ማሰብ ስላለበት ነው፡፡ ይህን ዕድል መጠቀም አለብን፡፡

በአንዳንድ ጉዳዮች ቀደም ያለውን ትውልድ እንወቅሳለን፡፡ እንዲህ ባያደርጉ ኖሮ፣ እንዲህ አድርገውት ቢሆን… እንላለን፡፡ ዳሩ ግን እኛ ያንን ለማስተካከል የሚፈለገውን ያህል ርቀት አልሄድንም፡፡ ዘመኑን የሚመጥን የነቃ ትውልድ መሆን አልቻልንም፡፡ ዘመኑ የደረሰበት የሥልጣኔ ደረጃ ላይ ካልደረስን ለቀጣዩ ትውልድ የምናስተላልፈው የተበላሸች ሀገር ነው፡፡

ለዚህም ተወቃሽ ትውልዶች እንሆናለን፡ ፡ ከሰለጠኑት ሀገራት ጋር በ100 ዓመት እንኳን ያልተስተካከለ ሰፊ ልዩነት የፈጠርነው ቶሎ ባለመንቃታችን ነው፡፡ በዚህ አያያዛችን በቀጣይ 100 ዓመታትም ቢያንስ ልዩነቱን እንኳን አናጠበውም ማለት ነው፡፡በዚህ ጉዳይ ወደ ውስጣችን አብዝተን ልናስብ ይገባል።

ለቀጣዩ ትውልድ ማሰብ አለብን፡፡ ሲሆን የምናየው ነገር ግን በአብዛኛው ወደኋላ የሚጎትት ነው፡፡ የፖለቲከኞቻችንን እና ምሁራኖቻችንን ክርክር እንኳን ልብ ብለን ስናየው ወደፊት ምን መሆን አለበት ከሚለው ይልቅ ባለፉት ክስተቶች ላይ ነው፡፡ ቀጣዩ ትውልድ ምን አይነት መሪ መፍጠር አለበት ከሚለው ይልቅ ያለፉት መሪዎች ምን አይነት ነበሩ የሚለው ላይ ነው፡፡

በቀጣይ እንዲህ አይነት እኩልነት መስፈን አለበት ከሚለው ይልቅ እገሌ እገሌን ጨቁኖ ነበር የሚለው ላይ ነው ትርክታችን ፡፡ ያለፈው ሁሉ አልፏል፤ አሁን እሱን ላለፈው ትውልድ ትተን ስለወደፊቱ ነው መመካከር የሚገባን፡፡ እንዴት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ 200 ዓመት ወደኋላ ተመልሶ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ከነበረ ትውልድ ጋር ራሱን ያወዳድራል?

እንደ ዜጋ በብዙ ጉዳዮች ላይ ፈጥነን መንቃት አለብን፤ ዘመኑን በሚመጥን ንቃት ላይ ስለመኖራችን ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል፡ ፡ እንደ ዜጋ ምን ይጠበቅብኛል፣ እንደ ማህበረሰብ ምን ይጠበቅብናል፣ እንደ ሀገር ምን ይጠበቅብናል፣ እንደ ትውልድ ምን ይጠበቅብናል… የሚለውን ማሰብ ዘመኑን ለመዋጀት ዋነኛው መንገድ ነው፡፡ አለበለዚያ የሰለጠነ ሀገር እየተመኙ መኖር ክስረት ነው፡፡ ለልጅ ልጅ ችግር ማስተላለፍ ነው፡፡

ምናልባት አንዳች በሰለጠነው ሀገር በመገኘታቸው ስለነጋቸው አስተማማኝ ዋስትና አለኝ ብለው ያስቡ ይሆናል፡፡ የሰው ሀገር ግን የሰው ነው፡፡ ‹‹ማን እንደ ሀገር!›› የሚለው በጣም ስለተደጋገመ የተለመደ አሰልቺ ነገር ይመስለን ይሆናል፤ ዳሩ ግን ራቅ እና ሰፋ አድርጎ ሲያስቡት እውነት ነው፡፡

ቀጣይ የዓለም ሁኔታ ወዴት እንደሚሄድ አይታወቅም፡፡ የዓለም የሕዝብ ብዛት እየጨመረ ሲመጣ በሀገራቸው አሁን ላይ ያሉ የውጭ ሀገር ዜጋ እጣ ፈንታቸው አይታወቅም ፤አሁን የሚታየው ዓለም አቀፍ የኑሮ ውድነት በዚሁ ከቀጠለ ነገ ላይ ይዞ የሚመጣው ነገር ምን እንደሚሆን በድፍረት መናገር አይቻልም፡፡

ሀገራችን ልትሆን በምንመኘው መልኩ ሆና እንድትገኝ ሁሉም የሀገሩ ጉዳይ ባለቤት ሆኖ ሁሉም በልቡ ፤በቤቱ ሊመካከር ይገባል፡ ፡ ለምንድነው እንዲህ የሆንነው? ምን ሳናደርግ ቀርተን ነው? መፍትሔውስ ምንድነው? ምን ማድረግ አለብን? የሚለውን ጊዜ ወስዶ ሊያሰላስል ይገባል፡፡

በችግሮች ዙሪያ ጣቱን በሌሎች ላይ ከመቀሰሩ በፊት ፤ የችግሮቹን ምክንያት ለማወቅ ገለልተኛ ሆኖ ማሰብ ፤ መፍትሔ በማፈላለግ ሂደት ውስጥም የሱ ኃላፊነትና ሚናን ለይቶ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ በዝምታ የችግሩ አካል ላለመሆን ራስን መግራት ያስፈልጋል ፤ይህ አሁነኛ የችግሮቻችን መፍቻ ዋነኛ መንገድ ነው።ይህም ዘመናችንን የሚመጥን ትውልድ እንድንሆን የተሻለ እድል ይሰጠናል ።

ሚሊዮን ሺበሺ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You