እናትነትን እናት ሆኖ ከማየት የበለጠ ህመሙ ገብቶት በልኩ ሊያስብ የሚችል ሰው ጥቂት ነው። መውለድ ሞቶ መነሳት ነው እስኪባል ድረስ ይህን ሁሉ ፍጥረት ለዓለም ያበረከተች እናት በእረፍት ራሷን ትጠግን ዘንድ አራስ ቤት የሚባል ውብ ባህል በሀገራችን ተለምዷል። የአራስነት ወቅቱ አልቆ ወደ ውጭ ሲወጣ ድካሙም ህመሙም አልፎ በአዲስ ጥንካሬ መመለስ የተለመደ ነው።
እናም ከአንድ እስከ ሁለት ወራት የሚቆየውን የአራስነት ጊዜ እናቲቱ ተማሪ ከሆነች አይገባትም የተባለለት መመሪያ የትምህርት ሚኒስቴር አወጣ የተባለ እለት ብዙ አስተያየቶች ተሰምቷል። ምንም እንኳን ተማሪ ሴቶች እንዲወለዱ ባይበረታታም ተደራራቢ ችግሮችን አልፈው የትምህርት ቤት ደጅ የረገጡትንስ ተማሪዎች በምን መልኩ እናስተናግዳቸው? አንድ ዓመት ከሚዘገዩ ለምን የማካካሻ ሁኔታ አይፈጠርላቸውም ? የልጅቷን መብት አይጋፋም ወይና ሌሎች አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።
በወሊድ ምክንያት ከ15 ቀናት በላይ የምትቀር ተማሪ የዓመቱን ትምህርት እንደማትጨርስ የሚደነግግ መመሪያ ተረቀቀ የሚል ዜና በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ከተሰማ በኋላ ከአስተያየቶቹም በተጨማሪ ቁጣቸውን የገለፁም አልታጡም።
ዜናው የትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀው የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎች ምዘናና የክፍል ዝውውር ረቂቅ መመሪያ፣ አንዲት የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪ ከ15 ቀናት በላይ በወሊድ ምክንያት ከትምህርቷ የምትቀር ከሆነ በዚያው የትምህርት ዘመን ትምህርቷን መቀጠል እንደማትችል መደንገጉን ያሳያል።
ተማሪዋ ለ15 ተከታታይ ቀናት በወሊድ ምክንያት የምታርፍ ከሆነ ትምህርቷን መቀጠል እንደማትችል የሚገልጸው ረቂቅ መመሪያ፣ ለ16 ቀናትና ከዚያ በላይ ለሆኑ ቀናት የምትቀር ከሆነ በዚያ ዓመት ስትከታተል ከነበረው ትምህርት የምትታገድ መሆኑን ያስረዳል።
ሆኖም ተማሪዋ በቀጣዩ ዓመት ትምህርቷን መቀጠል የምትፈልግ ከሆነ፣ ‹‹ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ›› መቀጠል እንደምትችል ይፈቅዳል።
የአጠቃላይ ትምህርት ተማሪዎችን (1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል) ያሉ ተማሪዎች ከክፍል ክፍል የሚዘዋወሩበትን አሠራር በዝርዝር የሚያስረዳው መመሪያው፣ ማንኛውም ተማሪ በአንድ የትምህርት ዘመን ለ12 ቀናት ከትምህርት ገበታው የሚቀር ከሆነ ትምህርቱን እንዳይቀጥል እንደሚደረግ ይገልጻል።
ይህ ዜና ከወጣ ቀን ጀምሮ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን በርካቶች ተቃውሟቸውን ቢያሰሙም በአደባባይ ለመቃወምና አቋምን በግልፅ ለማስቀመጥ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን የቀደመው አልነበረም።
የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋሙን በዚህ መልክ አስቀምጧል። እኛ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ሠራተኞችና አባላት ከአጋር የሴቶች መብት ድርጅቶች ጋር በመሆን የትብብር ጥሪ እናቀርባለን።
እንደሚታወቀው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው ረቂቅ መመሪያ ክፍል አራት፣ አንቀጽ 15፣ ተራ ቁጥር 5 መሠረት “አንድ ተማሪ በወሊድ ምክንያት 15 ተከታታይ የትምህርት ቀናት ካረፈች በኋላ ትምህርቷን መቀጠል ትችላለች፣ ሆኖም ግን 16 ቀናትና ከዚያ በላይ ከትምህርት ገበታዋ ከቀረች ከዘመኑ ትምህርት ትታገዳለች።” የሚል ረቂቅ መመሪያ አውጥቷል።
ይህ ረቂቅ መመሪያ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ መብትን በእጅጉ የሚገድብ ከመሆኑም በላይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን አወንታዊ የድርጊት ድንጋጌዎች የሚንድና የሴቶችን መሠረታዊ የመማር መብቶች በግልጽ የሚነፍግ ነው። በተጨማሪም እድል ለመስጠት የተጀመረውን አካታች አካሄድ የሚያደናቅፍና ወደኋላ የሚጎትት አካሄድ ነው።
ልጅ መውለድ በሴቶች ትምህርት ላይ ተደራራቢ ጫና እንደሚፈጥር አጠያያቂ አይደለም። የወሊድ ፈቃድ መከልከል እና ሴቶች ትምህርታቸውን እንዳይቀጥሉ አማራጮችን መገደብ ደግሞ በሴቶች የትምህርት እንቅስቃሴዎች ላይ ተጨማሪ እንቅፋቶችን መፍጠር ነው። ይህ ረቂቅ መመሪያም ለሴቶች ሌሎች አማራጮችን ከመፍጠር ይልቅ እንዳይበቁና በህብረተሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መሳተፍ እንዳይችሉ የሚያደርግ ቀጥተኛ ጥቃት ነው። በመሆኑም በዚህ ኢፍትሃዊ ርምጃ ላይ ጠንካራ የውትወታ/ሙገታ ዘመቻ በማድረግና ጫና በመፍጠር እንድትተባበሩንና ከጐናችን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ የሚከተለውን ጥያቄ ከዚህ በታች ለተዘረዘሩት አካላት እናቀርባለን::
ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ መብትን በእጅጉ የሚገድብ ረቂቅ መመሪያ አውጥቷል። ይህ ረቂቅ መመሪያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት የሴቶች እና የወንዶች እኩልነት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች፣ ትምህርትን፣ ሥራን እና ፍትሃዊ የሀብት ተደራሽነትን እና አስተዳደርን ጨምሮ የሚሰጠውን መብት ተጠቃሚነት በእጅጉ የሚነፍግ ነው።
ሴቶች በዚሁ ሕገ መንግሥት የተደነገጉትን መብቶችና ጥበቃዎች ሲያገኙ ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው የሚሉትን እና በእርግዝና እና በወሊድ ምክንያት የሚመጡ ጉዳቶችን ለመከላከል እና ጤናቸውን ለመጠበቅ የቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት፣ መረጃ እና አቅም የማግኘት መብት አላቸው የሚሉትን እና ሌሎች ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ህጎች የሚጥስና የሚቃረን በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጉዳዩን እንደገና እንዲያጤነውና ከሚመለከታቸው መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አስፈላጊውን ድጋፍ፣ መረጃና ትምህርት በመስጠት በፍጥነት ማስተካከያ እንዲያደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሕገ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ እና መንግሥት በምን ዓይነት መንገድ እንደሚመሰረት፣ እንደሚመራና እንደሚተዳደር፣ የሥልጣን ምንጭ ክፍፍልና የቁጥጥር ሂደትን የሚያመላክት፣ የዜጎችን ጥቅል መብትና ግዴታ የሚተነትን፣ የመንግሥት አካላት አደረጃጀት፣ ኃላፊነትና ተግባር የሚያስቀምጥ፣ የሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚና ተርጓሚ አካላት የሚመሩበትን መርህ የሚያስቀምጥ፣ የመንግሥት ቅርጽ ሥልጣንና የሥልጣን ወሰን የሚዘረዝር፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ፣ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚነካና ጥቅል አቅጣጫ የሚያመላክት ነው። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ሴቶች የወሊድ ፈቃድ መብትን በእጅጉ የሚገድብ ረቂቅ መመሪያ አውጥቷል።
ይህ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት የሴቶች እና የወንዶች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በፖለቲካዊ ዘርፎች እኩልነትን የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ሴቷ ትምህርትን፣ ሥራን፣ የሀብት ተደራሽነትን እና አስተዳደርን የማግኘት መብቷን የሚጥስና የሚቃረን በመሆኑ ጉባኤውም የሀገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በተሟላ መንገድ ሥራ በሴት ተማሪዎች የወሊድ ፈቃድ ረቂቅ መመሪያ ዙሪያ የቀረበ የጋራ ጥሪን አስመልክቶ በሴቶች መብት ዙሪያ ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማዋል አስተማማኝ ዋስትና ሊሰጥ ታምኖበት የተቋቋመ በመሆኑ፤ ይህን ረቂቅ መመሪያ በፍጥነት ማስተካከያ እንዲደረግበት የድርሻውን እንዲወጣ ጥያቄያችንን እናቀርባለን።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ተቋም እንደመሆኑ በሕገ መንግሥት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚያወጡትን ሕጎችና መመሪያዎች የመከታትልና የማስፈፀም ሥልጣኑን መሠረት በማድረግ ይህ ረቂቅ መመሪያ የሴቶችን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚቃረን፣ የወሊድ ፈቃድ የማግኘትና የመጠቀም መብታቸውን የሚከለክልና ሌሎች ተያያዥ መብቶችን የሚነፍግ ረቂቅ መመሪያ በመሆኑ ተገቢው የማስተካከያ ርምጃ እንዲወሰድበት የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ለሚዲያ አካላት በሙሉ ሚዲያዎች በጎም ሆነ ክፉ ተጽእኖ የመፍጠር ከፍተኛ አቅም ያላቸው እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ይህ ረቂቅ መመሪያም የሴቶችን መብቶች የሚንዱና ለሌሎች ተጨማሪ ተግዳሮቶች የሚዳርግ ነው። ስለሆነም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጉዳዩን እንደገና እንዲያጤነውና ወደፊትም በሴቶች ላይ መሰል ድርጊቶች እንዳይቀጥሉ ጫና በመፍጠር የሴቶችን ጉዳይ የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጉዳይ እንዲሆን በማድረግና ጉዳዮችን እስከ መጨረሻው ተከታትሎ ለሕዝቡ በማሳወቅ የበኩላችሁን ሚናና ኃላፊነት እንድትወጡ እንጠይቃለን።
ለሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጫና የሚፈጥሩ ሕጎችና ፖሊሲዎች ሲወጡ ችግሩን ከግምት በማስገባት ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ የውትወታ (advocacy) ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ታደርጉ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ለመላው የህብረተሰብ ክፍሎች ሴቶች እንደማንኛውም ዜጎች በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የወሊድ ፈቃድ የማግኘትና የመጠቀም፣ የመሥራት፣ የመማር፣ ወዘተ… መብት አላቸው። ስለሆነም ተገቢ ያልሆኑ ምክንያቶችን በመፍጠር ሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመብት ረገጣዎች ዝም ሊባሉ አይገባም። ስለሆነም ማንኛውም ህብረተሰብ በሴት ተማሪዎች የወሊድ ፈቃድ ረቂቅ መመሪያ ዙሪያ የቀረበ የጋራ ጥሪን አስመልክቶ በሴቶች መብት ዙሪያ ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ሴቶች የወሊድ ፈቃዳቸውን በአግባቡ የመጠቀም መብታቸው እንዲከበር ያገባኛል በማለት የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግና ጫና እንዲፈጥር የሴቶች የወሊድ ፈቃድ መብት ረገጣዎችን የማይታገስ ህብረተሰብ እንዲፈጠር እንጠይቃለን። በማለት አቋማቸውን አስቀምጠዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር በዚሁ ጉዳይ ላይ ምን አስተያየት አለው ስንል ላቀረብነው ጥያቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዋ ወይዘሮ አመለወርቅ ህዝቅኤል እንዳሉት ጉዳዩ ረቂቅ የሆነ ገና ውይይት ተደርጎበት ተግባር ላይ የሚውል መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል።
ማንኛውም ተማሪ በአንድ የትምህርት ዘመን ለ12 ቀናት ከትምህርት ገበታው የሚቀር ከሆነ ትምህርቱን እንዳይቀጥል እንደሚደረግ የሚገልፅ መመሪያ መኖሩን የጠቀሱት ሕዝብ ግንኙነቷ በዚህ መመሪያ መሠረት የወላድ ሴቶች በምን መልኩ ሊቃኝ ይችላል፤ በምንስ ሁኔታ ነው እናትነትና ትምህርትን ጎን ለጎን አብሮ ማስኬድ የሚቻለው የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር እየተወያዩ መሆኑን አመልክተዋል።
ከተለያዩ የሴት አደረጃጀቶች፤ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቂ ውይይት ከተደረገ በኋላ ውሳኔው ላይ የሚደረስ በመሆኑ ውሳኔ ያልተሰጠውና ተግባራዊ ባልሆነ ጉዳይ ላይ ግን ጊዜ በናባክን መልካም ነው ብለዋል።
ያም ሆነ ይህ በብዙ ትግል ትምህርት ገበታዋ ላይ የተገኘችትን እናት ተስፋ የማያጨልም ውሳኔ ቢወሰን መልካም ነው። ሴቷም መድረስ ያለመችበት ህልሟ ጋር ለማድረስ አደናቃፊ የሆኑ አሠራሮችና ሕጎች ሊወጡ አይገባም። ይህ እንዳይሆንም የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል በሚል መልእክት ልሰናበታችሁ ወደድኩ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም