የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ በዱባይ

የአየር ንብረት ለውጥ ድርቅ፣ ጎርፍ፣ የውሃ መጥለቅለቅ፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና ቅዝቃዜ በማስከተል በሀገር ላይ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ የሚጎዱት ለአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ሀገራት ብቻ ሳይሆኑ፤ በዓለም ላይ ያለ ማንኛውንም ሀገር ተጎጂ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል።

ኢትዮጵያም ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መከሰት ያላት ድርሻ ወይም አስተዋጽኦ እጅግ ዝቅተኛ ቢሆንም፤ ሌሎችም ባላቸው አበርክቶ በየጊዜው ከፍተኛ ጉዳት እያስተናገደች ትገኛለች። በተቃራኒው የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ጉዳቱን ለመቀነስ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥና ታዳሽ ኃይል የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና ለተያያዥ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥታ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናት።

ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር በመጀመሪያው ዙር ለአራት ተከታታይ ዓመታት ባከናወነችው ተግባር አበረታች ውጤቶችን አስመዝግባለች። አሁን ደግሞ በሁለተኛው ዙር ለምግብነት የሚውሉ የአትክልት ችግኞችን ማዕከል ባደረገ መልኩ ተከላውን በማካሔድ ከባለፈው በተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብሯን አጠናክራለች።

ይህንኑ አጠናክራ የተያያዘችውን የአረንጓዴ ዐሻራ እንቅስቃሴን መሠረት በማድረግ ሰሞኑን በአረብ ኤምሬትስ በዱባይ ከተማ በተካሄደው ኮፕ 28ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ ለእይታ አቅርባለች። ኤግዚቢሽኑ በጎብኚዎች አድናቆትና የትብብር ድጋፍ ማስገኘቱም በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተዘግቧል።

በዚህ መልኩ ሥራዎችዋን ማሳወቋና አድናቆትንም ማግኘቷ እያከናወነች ላለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ለምታደርገው ጥረት ምን አቅም ይፈጥርላታል? የተጀመረው ሥራ እንዲጠናከር ምን ይጠበቃል? በሚሉት ላይ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚከተለው ትንታኔ ሰጥተዋል።

በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ ዐሻራና ሰው ዘራሽ ደን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አበሩ ጠና፤ ኢትዮጵያ በዱባይ የተጠቀመችው መልካም አጋጣሚና ተገቢ እንደሆነ በአድናቆት ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ለዓለም ለማሳወቅና ያደጉ ሀገሮች ባላደጉ ሀገሮች ላይ የሚያስከትሉትን ተጽእኖ ለመቀነስ ከፍተኛ አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

እንደ አቶ አበሩ ማብራሪያ፤ እንዲህ ባለ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ሥራን ማሳየት ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሥራን የሚያግዝ የገንዘብም ሆነ የተለያየ የድጋፍ ትብብር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ለማግኘት ያስችላል። ዓለም አቀፉ ተቋም ድጋፍ ለማድረግ ጥረቶችንና የተሰሩ ሥራዎች ማየት ይፈልጋል።

ነገር ግን አንዳንድ ድጋፍ የሚያደረጉ ድርጅቶች ቢኖሩም፤ ኢትዮጵያ ውጤት እያስመዘገበች የምትገኘውበአብዛኛው በራስዋ በምታደርገው እንቅስቃሴ መሆኑን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ለማጠናከርና አሁን ካለው ስኬት በላይ ለማስመዝገብ፤ የቴክኖሎጂ፣ የገንዘብ ድጋፎች ያስፈልጋል። እነዚህን ድጋፎች ካደጉ ሀገሮች ማግኘት ከተቻለ፤ በሰው ኃይል ረገድ ችግር ባለመኖሩ አቀናጅቶ መሥራት እና ትልቅ ውጤት ማምጣት ይቻላል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ተሾመ ሶሮምሳ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በዱባይ በተካሄደው ጉባኤ ላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ በማቅረብ ሥራዋን በማሳየት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ማድረጓ ተገቢም አስፈላጊም መሆኑን አመልክተዋል። እንደዋዛ የሚታይ ጉዳይ አይደለም ብለዋል። በአንድ በኩል ልምዷን ለማካፈል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለአየር ሁኔታ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እንደሚያዘጋጃት ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ዐሻራ እንደማንኛውም ፕሮጀክት ሁሉ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት ፕሮፌሰር ተሾመ፤ ድጋፍ መኖሩ ሥራዎችን በቶሎ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ አቅም እንደሚሆን አመልክተዋል። በራስ አቅም መሥራት የሚደገፍና አስፈላጊ እንደሆነ ቢታምንም ከቁርጠኝነት ያለፈ እንደማይሆን ጠቁመዋል።

እንደ ፕሮፌሰር ተሾመ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መሬት የነካ ትልቅ ሥራ እየሠራች ነው። ከዚህ በኋላ የሚጠበቅባት የተጠናከረ ሪፖርት ለዓለም አቀፍ ማቅረብ ነው። የተሰሩ ሥራዎችን ለዓለም አቀፍ ማቅረብ ላይ ክፍተት ይስተዋላል። ከዚህ ቀደም የተራቆቱ (የተጎሳቆሉ) መሬቶች መልሶ እንዲያገግሙ ሥራዎችን ለመሥራት እ.ኤ.አ በ2011 በጀርመን ሀገር በዓለም አቀፍ በተፈረመው የቦን ቻሌንጅ ውል ስምምነት ላይ ኢትዮጵያም አንዷ ፈራሚ ሀገር ናት።

ሀገሮች እ.ኤ.አ በ2020 በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር የተጎሳቆለ መሬት መልሶ እንዲያገግም ሥራዎችን ለመሥራት ነበር የተፈራረሙት። በወቅቱ ኢትዮጵያ 15ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬት መልሶ እንዲለማ እንደምትሰራ ፈርማ ነበር። ይሁን እንጂ ሥራውን በተመለከተ ለዓለም አቀፍ ሪፖርት ማቅረብ ላይ ክፍተት ይስተዋላል። ይሄ መስተካከል አለበት ብለዋል።

የዘርፉ ባለሙያዎች በአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ጥንካሬ እና ክፍተት ያሏቸውንም አንስተዋል። አቶ አበሩ በጥንካሬ ያነሱት፤ ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በማድረግ ረገድ የቆየ ተሞክሮ ቢኖራትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሕዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የተሰሩት ሥራዎችና የተሰጠው ትኩረት የላቀ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር ተነሳሽነቱን ቢወስዱም በየደረጃው ያለው አመራር፣ ህብረተሰቡ በንቃት መሳተፍና ሁሉም የየድርሻውን መወጣቱ የልማቱ ሥራ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የተውጣጡ አመራሮች ጭምር የተካተቱበት ኮሚቴ ተዋቅሮ እንዲመራ መደረጉ ኢትዮጵያ በአረንጓዴው ልማት ውጤታማ እንድትሆን እንዳስቻላትም አስረድተዋል።

አቶ አበሩ እንዳሉት፤ እስከ አሁን በተሰሩት ሥራዎች አበረታች ውጤቶች ቢመዘገቡም ካለፈው ተሞክሮ ትምህርት በመውሰድ በሁለተኛው ዙር ቁጥር ላይ ሳይሆን፤ ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጓል። የተመረጡ ዘሮች እንዲቀርቡ፣ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚያስገኙና ለምግብነት የሚውሉ ችግኞችም እንዲካተቱ ከማድረግ በተጨማሪ፤ በችግኝ ተከላ ወቅት መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ፣ ከተተከሉ በኋላም መደረግ ስላለበት እንክብካቤ፣ በአጠቃላይ ቀደም ሲሉ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን በማረም እንዲሁም ባለቤት እንዲኖረው ማድረግ ከቅድመ ጥንቃቄዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው ብለዋል።

በ2016 በጀት ዓመትም ሥራዎችን ቀድሞ ለመሥራት ከክልሎች ጋር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል። አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በማህበረሰብ ላይ ስላመጣው ለውጥም ሆነ እንደሀገርም የተገኘው ውጤት የጥናት ሥራ እየተሰራ እንደሆነና ጥናቱ እንደተጠናቀቀ ይፋ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

አቶ አበሩ ክፍተት ካሏቸው መካከል የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ አለመኖርን ይጠቀሳል። ለደን፣ ለእርሻና ለተለያየ ልማት የሚውል መሬትን ለይቶ በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ ችግሮች መኖራቸውን ያመለክታሉ። በዚህ በኩልም ትኩረት ቢሰጥ የተጠናከረውን የአረንጓዴ ልማት በስኬታማነት እያረጋገጡ መሄድ ይቻላል።

እንደ አቶ አበሩ ገለጻ፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ወደ 54 ሄክታር መሬት ተጎድቷል። የተጎዳው መሬትም በትክክል የደን፣ የእርሻ ወይም የግጦሽ ስለመሆኑም መለየት አልተቻለም። የተጎዳውም መሬት መልሶ እንዲያገግም ሥራዎች መሠራት አለባቸው። መሬቱ ካገገመ በኋላ ደግሞ ለተገቢው ልማት እንዲውል በፖሊሲ መደገፍ ይኖርበታል።

ፕሮፌሰር ተሾመ፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ከአራት ዓመታት በፊት የጀመረችውን ሥራ በአድናቆት ይገልጻሉ። በኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ አጀንዳ ሆኖ በትኩረት መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ የተደረገው ከሀገራዊ ለውጥ በኋላ እንደሆነና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የተሰራው ሥራም እጅግ በጣም ጥሩ የሚባል እንደሆነ በዘርፉ በመምህርነትና በጥናት ሥራ እንደቆየ ባለሙያ እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል። ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱ በዘርፉ ላይ እንዳለ ሰው ደስተኛ እንደሆኑም ተናግረዋል።

እንደ እንግሊዝ ያሉ ያደጉ ሀገሮች ፍልስፍናቸው ወይም አጀንዳቸው አረንጓዴ ዐሻራ (ግሪን ኢኮኖሚ) ነው። ጉዳዩን ሀገራዊ አጀንዳ ከማድረግ ባለፈ ያላቸው ፍልስፍናም እጅግ የረቀቀ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው ያስታወሱት። ፍልስፍናውም ታች መሬት ድረስ የወረደ ተግባር ማከናወን እንደሆነም አመልክተዋል። ኢትዮጵያም እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ ከዚህ አንጻር እንዲታይ የሚያስችላት እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ ደረጃ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴም ዓለም ሊያውቀው ይገባል ብለዋል።

‹‹የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሌጋሲ መቀጠል አለበት። እንደባህል ልንወስደው ይገባል። ለምንተካው ትውልድ ማሰብ ይኖርብናል።›› ያሉት ፕሮፌሰር ተሾመ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ሥራ ሙሉ ለሙሉ በባለሙያ መታገዝና ሳይንሱን በሚያውቅ ሰው መመራት አለበት የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። በዘርፉ ላይ ያሉ ተመራማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊያበረክቱ ስለሚችለው አስተዋጽኦም ሊታሰብበት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ በንቅናቄ የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ እያንዳንዱ ዜጋ ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስምረውበታል።

ኢትዮጵያ በአረብ ኤምሬትስ በዱባይ ከተማ በተካሄደው ኮፕ28ኛው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ያቀረበችው የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ የተባበሩት አረብ ኤምሬት የነዳጅና ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ሱልጣን አሕመድ አልጃቢር፣ የቀድሞ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሌርን ጨምሮ የጉባኤው ታዳሚዎች የጎበኙት ሲሆን፤ አድናቆትንም አግኝቷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማቃለል በጋራና በትብብር መሠራት እንዳለበት አስገንዝበዋል። የአረንጓዴ ልማት ሥርዓት ለመዘርጋት እንሰራለንም ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ብላ በመሰየም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሆነች ይታወሳል። በመጀመሪያው ዙር ባደረገችው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ከ25 ቢሊየን በላይ የተለያዩ የዛፍ ችግኞች በመትከል አጠናቅቃ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ተሸጋግራለች። በመጀመሪያው ዙር የተገኘው አበረታች ውጤትና ተሞክሮ ለሁለተኛው ምዕራፍ የበለጠ የሚያነሳሳና የበለጠ አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችል ሆኖ ተገኝቷል። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በሁለት ዙሮች 50 ቢሊየን የዛፍ ችግኞችን በመትከል ሀገሪቱን አረንጓዴ የማልበስ እቅድና ግብ ይዛ በመሥራት ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለው አረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ከራስዋ አልፋ ጎረቤት ሀገሮችንም ለመድረስ በተግባር እያሳየች የምትገኝ ሲሆን፤ በአረንጓዴ ልማት መርሐ ግብር የሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመቀነስና ለመቆጣጠር ከሚከናወነው ተግባር በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል፣ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም ወጣቶች ተደራጅተው ችግኝ በመትከል ገቢ በማመንጨት እራሳቸውንም ሆነ ሀገርን እንዲጠቅሙ በማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየሰራች ነው።

ኢትዮጵያ የዛፍ ችግኞችን የመትከል ልምድ እንዳላት የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። የዛፍ ጥቅምን የሚረዳ ማህበረሰብ እንዳላትም ይታወቃል። ይሁን እንጂ በሰው ሠራሽና በተለያየ ምክንያት ባጋጠማት የደን መመናመን ለከፋ ጉዳት ተዳርጋለች። ይህን ጉዳት ለመመለስ እና በአጠቃላይ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ መጠነ ሰፊ ሥራዎች በማከናወን ላይ ትገኛለች።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You