ሰላምና የዲፕሎማሲ ስኬታችን

ሰላም ፋይዳው ቀላል አይደለም። ለሰው ልጅ መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ሕይወት፣ ከዛም ባለፈ ለፍጥረታትና ለአጠቃላይ ተፈጥሯዊው ሥነ ምህዳር በቀዳሚነት የሚያስፈልግ ማህበራዊ እሴት ነው። ከዚህ የተነሳም ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለሰላም ከፍ ያለ ሥፍራ መስጠት እና ዘብ መቆም ይጠበቅበታል።

ሰላም የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት /በቅድመ ሁኔታዎች የሚገዛ/ በመሆኑ ስለ ሰላም በማህበረሰብ ውስጥ የማያቋርጥ ግንዛቤ መፍጠር ፤ ለሰላም በቂ እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል። የተማረውም፣ ያልተማረውም፣ትልቁም፣ ትንሹም በሰላም ዙሪያ በቂ ግንዛቤ አግኝቶ ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

ካለፉት ዓመታት ካየነው የሰላም እጦት አሁን ላይ እያየነው ያለው አንፃራዊ ሰላም፤ ሰላም የቱን ያህል ዋጋ እንዳለው በተግባር ማየት አስችሎናል፤ ስለ ሰላም የተሻለ አረዳድ ይዘን ለሰላማችን ዘብ እንድንቆም እድል ፈጥሮልናል።በዓለም አቀፍ መድረኮችም ደብዝዞ የነበረውን ገጽታችንን እያጎላው ይገኛል።

ሀገራችን ውስጣዊ ሰላሟና አንድነቷ ሲጠናከር ገፅታዋ በዓለም መድረክ በበጎ ይጎላል። ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማሲ በባለብዙ ወገን ግንኙነቶች ተሳትፎዋ መንደርደሪያውም ይኸው ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ነው። ሰላሙ የፀና፣መረጋጋቱ የታወቀ ሀገርና ሕዝብ በሌሎች መሰል ሀገራት የወዳጅነት ቀይ ምንጣፍ የሚዘረጋለት ልምዱን እንዲያጋራ የክብር ጥሪ የሚደረግለት መሆኑ ይታወቃል።

በዲፕሎማሲ መርህም የሀገራት ወዳጅነት ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ውስጣዊ አንድነት ወሳኝ መሆኑ ግልፅ ነው። ሰላምና መረጋጋታቸው የማይናወጥባቸው ሀገራትም በባለብዙ መድረኮች የፊት አውራ ሆነው የምንመለከታቸውም ለዚሁ ነው። የዘርፉ ጠበብቶችም ውጭው ውስጥን ይመስላል ይላሉ። በርግጥ ይህ ብያኔ እንደ የሀገራት የፖለቲካ ርዕዮትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አንፃር መታየት ይኖርበታል።

ዓለም ደግሞ አሁን በተለዋዋጭ ሂደት ውስጥ ናት። ግጭትና ጦርነት አዳዲስ የሆኑ አሰላለፎችን እያስተናገደች ትገኛለች። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የባለብዙ ወገን መድረኮች እየጨመሩ፣ ወጥና አንድ ዓይነትነት ብቻ የዲፕሎማሲ ሥርዓት እየተዳከመ ይመስላል። አዲስ ቡድን በማደራጀት የቡድን አባት የመሰሉ ሀገራትም እየበረከቱ ናቸው።

ኢትዮጵያ በገለልተኝነት ፖሊሲዋ በጋራ ትብብር ጥቅሞቿን እያስጠበቀች ነው። ባለፈው ሰሞን “በኮምባክት ዊዝ አፍሪካ” ጉባኤ ሀገርን ሊጠቅሙ በሚችሉ አጀንዳዎች ወሳኝ የዲፕሎማሲ ድል አስመዝግባለች። ወደ ወሳኙ የአፍሪካ ቀንድ መግቢያና የዲፕሎማቲክ መናገሻዋ አዲስ አበባ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብም፣ የንግድ ግንኙነትን ለማሳደግም በጠቃሚ መድረኮች ላይ እየታደመች መሆኗን እየተመለከትን ነው።

በሃያኛው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ጉባኤ ላይም ሁሉን አካታችና ቀጣይነት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት መንገድ በመከተል ብሎም የኢኮኖሚ ዘርፎችን በማብዛት ብልፅግናዋን ለማምጣት፣ የኑሮ ልዩነትን ለማጥበብ ለሕዝቦችና ለዓለም መፃኢ ሕይወት አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ አመላክተዋል።

በአየር ንብረት ጉባኤም ወሳኝ ሚናዋን አሳይታለች። የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ዐሻራ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኅልውናና የምግብ ዋስትና ማረጋገጫና የሥራ እድል የሚፈጠርበት አንዱ ዘርፍ መሆን ከቻለ ዓመታት መቆጠር ጀምረዋል። በዚህም ሀገራችን እ.ኤ.አ ከ2019 ጀምሮ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብርን ተግባራዊ ስታደርግ ቆይታለች። በመርሃ ግብሩም እ.ኤ.አ እስከ 2026 ድረስ 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ይህን ስናሳካ በአንድ ልብ ተነስተን ለአንድ አላማ ቆመን ለነገው ትውልድ የተሻለች ሀገርን ለማስረከብ አልመን ነው። ሕፃን አዋቂ፣ ሴት ወንድ ሳንል በአንድ ጀምበር በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን ተክለናል። በእነዚህ ዓመታት ሀገራችን ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎችን በሚገባ ሰርታ አሁን ደግሞ እነዚህን ሥራዎቿን በዓለማቀፉ መድረክ ለዓለም እዩልኝ እያለች ነው።

በቅርቡም በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ዱባይ በተካሄደው ኮፕ-28 በአረንጓዴ ልማት ጉባኤ ላይ የአየር ንብረት ለውጥን ለመገዳደር ያከናወነችው የኢትዮጵያ ልምድ ቀርቧል። በተመሳሳይ የዲፕሎማሲ መድረክም የሀገር መልካም ገጽታ ጎልቶ የወጣበት ሆኗል። በዱባይ ሀገራችን የከወነችው ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነው።

ባሳለፍነው ኅዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተከፍቶ ለአስራ ሁለት ቀናት በተካሄደው በዚህ ጉባኤ ላይም ባለፉት አምስት ዓመታት ለዓለም ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎችን በሚገባ የሠራችው ሀገራችን፣ ይህንን ጥረቷንና ፍሬዋን የሚያሳይ የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ ለእይታ አቅርባ በተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ተሳታፊዎች ተጎብኝቷል። አውደ ርዕዩ በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገበችውን ስኬት እና ሌሎች ተሞክሮዎችን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስተዋወቅም መልካም አጋጣሚ ፈጥሯል።ኢትዮጵያ በአውደ ርዕዩ ይዛ በቀረበችው የአካባቢ ጥበቃ ውጤት በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት መሪዎች ጭምር ተደንቀዋል።

መሪዎቹ ባደረጉት ንግግር ሁሉ በዘርፉ ኢትዮጵያን በጥሩ ተሞክሮነት ሲያነሱ ተስተውለዋል። ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ከራሷ አልፋ ለጎረቤት ሀገራት እያደረገች ያለችውንም ድጋፍ እንደ አንድ ተሞክሮ እንደሚጠቀስ አስታውቀዋል።

ይህን ተንተርሰን በቀጣይ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በልዩነት ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው አረንጓዴ ዐሻራ ይሆናል የሚል እምነት መያዝም እንችላለን። ይህ ዓለም አቀፍ መድረክ የዓለም ሀገራት መሪዎች ስለ አየር ንብረት ለውጥ፣ ስለምግብ ዋስትናና ስለሌሎችም ዓለማችንን ስጋት ስለደቀኑባት ጉዳዮች መፍትሔ ፍለጋ ለመምከር የተሰበሰቡበት እንደመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ ሥራዋን ፍሬዋን ማሳየቷ በመድረኩ ከብዙዎች መልካም ምላሽና አድናቆት ማግኘቷ ዓለም በደከመበት ግን ጥረትን በሚፈልገው የአየር ንብረት ለውጥ በቁርጠኝነት እየሠራች እንደሆነ ለማሳየት ረድቷል።

በዚህም የካርበን ልቀት መጠንን ዜሮ ለማድረግ ኢትዮጵያን መሰል ለዓለም ፈተና መፍትሔ ሰጪ ሀገራትን በእውቅናም በገንዘብም መደገፍ ዓላማው ባደረገው ጉባኤ ኢትዮጵያ ሥራዋ ገንኗል። ስሟም በምሳሌነት ተጠቅሷል። ይህም ለዓለም ቀውስ የራሷን መፍትሔ እያስቀመጠች ላለችው ሀገራችን በአረንጓዴ ዐሻራና በሌሎችም የልማት ሥራዎቿ በዓለም ድጋፍና ተቀባይነት እንድታገኝ ከማድረግ ባለፈ ገፅታዋን የሚገነባ፣ ስሟን በመልካም የሚያስነሳ ስለሆነ ፋይዳው የጎላ ነው።

በኢኮኖሚ ያደጉ ሀገራት መሪዎች ጭምር ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ላይ እያከናወነች ባለችው ተግባርና ባስገኘችው ውጤት መደነቃቸውን ገልጸዋል። የዓለም ሕዝቦች ሁሉ የጋራ ችግር የሆነውን፣ የጋራ ርብርብንም የሚጠይቀውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት መሥራቷና በሥራዋም ውጤት እያስገኘች መሆኑ መታየቱ ብዙ ትሩፋት አለው።

አንዳንድ ሀገራት ቃል ይገባሉ። የአካባቢ የአየር ለውጥ ያሳስበናል፤ በመሆኑም ይሄን እንሠራለን፤ ያን እንሠራለን ይላሉ። በተጨባጭ ሥራ ላይ ሲታይ ግን እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አልሰሩም። በተለይ እኤአ በ2015 በፓሪስ ሀገራት በአካባቢ አየር ጥበቃ ላይ ተሳትፎ ለማድረግና ቁርጠኛ ለመሆን ዓለማቀፍ ስምምነት አድርገዋል። በስምምነቱ ላይ ከመገኘት ባለፈ መሬት ወርዶ የሠሩት ሥራ ግን አይታይም።

በተቃራኒው የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመከላከል ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየሠራች ነው። ይህ ለኢትዮጵያ ቀጠናዊ ሚናዋን ከፍ በማድረግ ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነቷን ለመጨመር እጅጉን ይረዳል። ኢትዮጵያ በተግባር የቀረጸቻቸው ፕሮጀክቶች የዲፕሎማሲ አቅሟን እየጨመሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

ቀጠናዊ የመሪነት ሚናዋም እንዲጨምር ያደርጋል። ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በረሃብ፣ በስደትና በመሰል መጥፎ ታሪኮች የሚታወቅ አካባቢ ነው። ኢትዮጵያ የዚህ አካባቢ አንዷ አካል ሆና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ከፍተኛ ሥራ መስራቷ የተለየች ያደርጋታል።

እየከወነች ያለችው ተግባር ከምሥራቅ አፍሪካ አልፋ ለአፍሪካና ለሌሎች ዓለም ሀገራት ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ስለሆነ በርግጥም ቀጠናዊ ሚናዋን ከፍ ያደርጋል። ይህ ሚና ደግሞ በዋናነት የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ተሰሚነት ይጨምራል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት መጠቀስ የሚችለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ በብዙ ፈተናዎች በተተበተበው ቀጠና ላለችው ኢትዮጵያ አንድ ሌላ ስሟን በመልካም የሚያስነሳ ተግባር ሆኗል። ይህ የሚፈጥረው ቀጠናዊ ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ የዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነት ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ሀገሪቱ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ከሌሎች ያደጉት ሀገራት ይልቅ የተሻለ ተግባራትን ፈፅማለች። ይህም በተለያዩ ሀገራት ተቀባይነቷ እንዲጨምር ያደርጋል። በዓለም ላይ ጎልታ እንድትታይ አድርጓታል። ሥራዎቿ ገፅታዋን ከመገንባት ባለፈ ዓለም አቀፍ ተቀባይነትንና ድጋፍን እንድታገኝ ፋይዳቸው የጎላ ነው።

ይህም በቀጣይ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በልዩነት ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋናው የአረንጓዴ ዐሻራ ይሆናል የሚል እምነት የብዙዎች እንዲሆን ያደርጋል። ለሀገሪቱም በቀጣይ ለምትሰራቸው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ሥራዎች አቅምና የበለጠ ተነሳሽነትን ይፈጥራል።

ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች ያሉባት ሀገር ነች። በተለይ ከኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ ድጋፍ ያስፈልጋታል። የገንዘብ፣የቴክኒክ፣ የቴክኖሎጂና የአቅም ግንባታ እገዛ ያስፈልጋታል። በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ግንባር ቀደም ሆና በምትሠራበት ጊዜ የዲፕሎማሲ ትስስሯ ይጠናከራል። ከእነዚህ ድጋፍ ሰጪ ሀገራት ጋር በሚኖራት ግንኙነት በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች ቀጣይነት ያለው ትስስር የመፍጠር አጋጣሚ ይፈጥርላታል።

ይህ ሁሉ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ከሁሉም ጋር ፍቅርና ትብብርን የምታስቀድም ሀገር ለመገንባትና በዚያው ልክ ደግሞ ተጠቃሚነቷ እንዲሰፋ ያስችላል። ይህንንም ከላይ በተመለከቱት መረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል። በተለይ አስተማማኝ ሰላም ለገዘፈ ዲፕሎማሲያዊ ድል ያለውን ፋይዳ በጥልቀት ተረድተን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሁላችንም የበኩላችንን ማዋጣት አለብን።

ከላይ የጠቀስናቸው ዓለም አቀፍ መሰል መድረኮች በግጭትና ባለመረጋጋት ሊስሏት ለሚሞክሩት መገናኛ ብዙኃን መልካም ገፅታችንን ለማሳየት ይጠቅማሉና የበለጠ ሊሰራባቸው ይገባል። ዓለም አቀፍ መድረኮችን የሀገራችንን መልካም ገፅታ ለመገንባት ልፋትና ፍሬዎቻችንን ለማሳየት መጠቀማችን የሚመሰገን ነው። በቀጣይም በጥንካሬ ሊሰራበት ይገባል።

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You