የስቶክ-ገበያ ነገር

 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ‘ስቶክ ማርኬት’ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ በሕዳር ወር መጀመሪያ ሰሞን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምርጥ ሃሳብ” ሲሉ ያሞካሹት ‘ስቶክ ማርኬት’ መቼ ወደ ሥራ እንደሚገባ ባይገልጹም በዚሁ የገበያ ሥርዓት አማካኝነት የኢትዮ ቴሌኮም “የተወሰነ” ድርሻ ለገበያ እንደሚውል፤ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ አየር መንገድንና ሌሎች የመንግሥት ድርጅቶች በተመሳሳይ መንገድ “የሕዝብ” እንደሚሆኑ፤’ስቶክ ማርኬት’ በተለያዩ ሥራ የተሰማሩ ዜጎች ከስራቸው ጎን ለጎን በታላላቅ ድርጅቶች ላይ ‘ኢንቨስት’ አድርገው እንዲጠቀሙ እንደሚያደርግ ጠቁመው “የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋል” ብለዋል።

የስቶክ ገበያ ወይም ማርኬት ለሕዝብ ሽርክናዎችን ወይም ሼርስ በመሸጥ ካፒታልን የማሰባሰቢያ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ነው። በተለይ ታላላቅ ኩባንያዎች ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋፋት፤ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና ለአጠቃላይ እድገት የስቶክ ማርኬት ሀብት በማሰባሰብ የማይተካ ሚና አለው። ኩባንያዎች ባሰባሰቡት በዚህ ሀብት ለዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ምርታማነትን በመጨመር ሀገራዊ ኢኮኖሚን በማሳደግ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።የስቶክ ገበያ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና ሀገራዊ ቁጠባን ለማሳደግ ያበረታታል።

ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች ያለባቸውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች በፈለጉ ጊዜ ሽርክናቸውን ወይም ሼራቸውን በስቶክ ማርኬት ለመሸጥ ያስችላቸዋል።ዜጎች ከኩባንያዎች ሼር በመግዛት ባለቤት ስለሚሆኑ ጤናማ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ያደርጋል።እነዚህ የስቶክ ማርኬት ጠቀሜታዎችን ለማረጋገጥ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት፤ ኢንቨስተሮች ስለ ስቶክ ማርኬት እውቀትና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማስተማርና አስፈላጊ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ግድ ይላል።

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የፌርፋክስ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ሊቀመንበር ናቸው። የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮችም በቅርበት ይከታተላሉ። ለስቶክ ማርኬት ‘የድርሻ ገበያ’ የሚል አቻ የአማርኛ ትርጉም ልንሰጠው እንችላለን ይላሉ። ኩባንያዎች የኩባንያውን የባለቤትነት ድርሻ ለገበያ ያቀርባሉ። ሰዎችም ይህን ድርሻ ከገዙ በኋላ ኩባንያው ትርፋማ በሆነ መጠን ያላቸውን ድርሻ መልሰው በመሸጥ ወይም ከትርፍ ክፍፍል ትርፋማ የሚያደርግ አሠራር ነው ሲሉ ለቢቢሲ ይገልጻሉ። አቶ ዘመዴነህ ኢትዮጵያ የስቶክ ገበያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ ብትሆንም የስቶክ ገበያ ጽንሰ ሃሳብ ለሀገሪቱ ገበያ አዲስ አይደለም ይላሉ። በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ጥምረት የሚቋቋመው የስቶክ ገበያ በዋናነት የሚከተሉትን ጥቅሞች ለኢትዮጵያ ይዞ እንደሚመጣ ይገልጻሉ።

የካፒታል ገበያ በርካታ የሀገር ውስጥ ባንክ እና ኢንሹራንሶች ሲመሠረቱ እና ከምሥረታቸውም በኋላ የአክሲዮን ድርሻዎችን ሲሸጡ መቆየታቸውን በማስታወስ፤ የስቶክ ገበያን ከዚህ የተለየ የሚያደርገው፤ ይፋዊ በሆነ መልኩ ተደራጅቶ ቁጥጥር እየተደረገበት በግልጽ መገበያየት ማስቻሉ ነው ይላሉ። የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ (ኢኤስኤክስ) እውን ሲሆን፤ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙም ሆነ ማስፋፋት ሲፈልጉ አክሲዮኖቻቸውን ለመሸጥ ይከተሉት የነበረውን ረዥም መንገድ እንደሚያሳጥርላቸው፤ “እነዚህ ኩባን ያዎች ሲቋቋሙ ስቶክ ኤክስቼንጅ ስላልነበረ በጣም ረዥም ሂደት በማለፍ ለእያንዳንዱ ሰው እየዞሩ ነው ሼር የሚሸጡት። ይህ ረዥም ጊዜ እና ገንዘብ ይወስዳል። አዋጭም አይደለም” ይላሉ ዘመዴነህ።የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ መመሥረት አንዱ ጥቅም አዲስ ለሚመሠረቱም ሆነ ለነባር ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን መፍጠሩ ነው ይላሉ።

ካፒታል ማሰባሰብ ለሚፈልጉም ስቶክ ገበያ መልካም አማራጭ እንደሆነ አቶ ዘመዴነህ ያስረዳሉ።“ጥሩ ሐሳብ ኖሯቸው የካፒታል እጥረት ላለባቸው ሰዎች ይጠቅማል። ዛሬ ላይ ከባንክ ብድር ማግኘትም አስቸጋሪ ነው። ለዘመድ ወይም ለጓደኛ ሼር የመሸጥ ሂደትም ቀላል አይደለም። ስቶክ ማርኬት አዲስ ለሆኑም ይሁን መስፋፋት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች የካፒታል ገበያን ይፈጥራል።”በአሁኑ ጊዜ ግዙፍ መንግሥታዊ ኩባንያዎች ወደ ግሉ ዘርፍ እየተሸጋገሩ እንደሆነ በማስታወስ፣ እነዚህ ከመንግሥት ወደ ግሉ የሚዘዋወሩት ግዙፍ ኩባንያዎችን ሲገዙ የቆዩት ጥቂት ግለሰቦች እና ኮርፖሬሽኖች መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ኢኤስኤክስ ሲመጣ ግን መንግሥት የሕዝብን ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማከፋፈል ይችላል።“ስቶክ ማርኬት ላይ አንድ ሼር በአምስትም፣ በአሥርም ዶላር ሲሸጥ ሁሉም የየአቅሙን በመግዛት ኢትዮጵያ ያካበተችውን ሀብት ማከፋፈል ይቻላል” ሲሉ ያብራራሉ። እነዚህ ወደ ግሉ ዘርፍ የሚዘዋወሩ ኩባንያዎች ወደ ስቶክ ገበያው ሲገቡ፣ ሁሉም የአቅሙን ያህል ባለቤት እንደሚሆንና ይህም የሀብት ክፍፍልን ያመጣል። ቁጠባ እና የኢንቨስትመንት አማራጭን ማስፋት የኢትዮጵያን ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ እውን ሲሆን የቁጠባ ባህልን ከፍ እንደሚያደርግ አቶ ዘመዴነህ ይናገራሉ።

ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ኪሳራ አያስከትልም ብለው በሚያስቡት ዘርፍ ላይ ብቻ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ ይገኛሉ።“ገንዘብ ያላቸው ሰዎች የቤት ልማት ላይ ብቻ ትኩረት ሲያደርጉ ይታያል። የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ደግሞ ተጎድቷል። ይህም ኢንቨስት የሚደረግባቸው ዘርፎችን ውስን በማድረግ የቁጠባ አለመመጣጠን ይፈጥራል። ስቶክ ማርኬቱ ግን ውጤታማ በሆነ መንገድ ካፒታል በሁሉም ዘርፎች ላይ ማሰራጨት ያስችላል።

ግልጽነት፦ ሌላኛው መልካም አጋጣሚ የድርሻ ገበያዎችን በቀላሉ፣ ግልጸኝነት በሰፈነበት መልኩ መግዛት እና መሸጥ ማስቻሉ ነው። ምን ያህል ሼር በምን ያህል ዋጋ ለገበያ እንደቀረበ ግልጽ ነው።“ሰዎች ስልካቸው ላይ በሚጭኑት መተግበሪያ በቀላሉ የገበያ ድርሻዎችን መግዛት እና የገዙትንም መሸጥ ይችላሉ” ይላሉ አቶ ዘመዴነህ።

የባንክ ባለ አክሲዮኖች ዓመት ጠብቀው ትርፍ ከመከፋፈል ውጪ በቀላሉ ያላቸውን አክሲዮን መሸጥ አይቻላቸውም። ኢኤስኤክስ እውን ሲሆን ግን በቀላሉ አክሲዮን የመሸጥ ዕድል ይዘረጋል።

ከበርካታ አሥርት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የኬንያው ‘ናይሮቢ ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ’ ወደ 60 ገደማ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎችን ይዟል።አቶ ዘመዴነህ የኢትዮጵያው ሴኪዩሪቲስ ኤክስቼንጅ በሁለት ዓመታት ውስጥ ከ50 ያላነሱ ኩባንያዎችን በውስጡ ይይዛል የሚል ተስፋ አላቸው።የስቶክ ገበያውን ሊቀላቀሉ የሚችሉ ኩባንያዎችን ስናስብ በብሔራዊ ባንክ ጠንካራ ቁጥጥር የሚደርግባቸውን 18 ባንኮች እና ከ18 የማያንሱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መዘንጋት የለብንም ይላሉ።“ሁሉም የስቶክ ገበያውን ላይቀላቀሉ ይችላሉ።

ቁጥሩን 30 ብለን እንያዘው። 20ያው ከየት ይመጣል? ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ባለቤትነታቸው በቤተሰብ ደረጃ የሆነ ግዙፍ ኩባንያዎች ስቶክ ማርኬት ላይ ለመግባት ዝግጁ የሆኑ ይኖራሉ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሆኑ የውጭ ኩባንያዎች አሉ። ኮካ ኮላ፣ ሃይኒከን፣ ዩኒሊቨር እና ቶታልን ማንሳት ይቻላል። የእኔ ግምት ከ40 እስከ 70 ነው” በማለት ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።ይህ ማለት ግን ሁሉም ኩባንያዎች በአንድ ቀን ይገባሉ ማለት አይደለም። ቁጥራቸው በጊዜ ሂደት የሚጨምር ይሆናል።

ቢቢሲ በአንድ ወቅት በስቶክ ገበያ ትርፍ እና ኪሳራ እንዴት ያጋጥማል?ሲል ለአቶ ዘመዴነህ ላቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ፤ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ስቶክ ገበያ ምንድን ነው? እንዴትስ መሸጥ እና መለወጥ ይቻላል? የሚለውን እንመልከት። ስቶክ ገበያን በቀላል ቋንቋ ለመረዳት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አዘወትረው የሚጠቀሙትን ቀላል ምሳሌ እንውሰድ።

‘ሀ’፣ ‘ለ’ እና ‘ሐ’ የሚባሉ ሦስት ምናባዊ የሞባይል ስልክ አምራች ኩባንያዎች አሉ እንበል።እርስዎ 6 ዶላር አውጥተው ከእያንዳንዱ ኩባንያ የሁለት ዶላር የገበያ ድርሻ ይገዛሉ።’ሀ’ ለገበያ ያቀረበው ሞባይል ስልክ ባትሪው እየፈነዳ ሰዎችን ለጉዳት እየዳረገ መሆኑን የሚያመለክት ሪፖርት መውጣት ይጀምራል።የ’ለ’ ኩባንያ የሆነው ምርት ደግሞ ባትሪው በፍጥነት እያለቀ ከተጠቃሚዎች ቅሬታ ይደርሰዋል።የ’ሐ’ ምርት የሆነው ሞባይል ስልክ ግን በአግባቡ ይሠራል።ይህ በገበያ ላይ ያጋጠመው ክስተት በሦስቱ ኩባንያዎች ስቶክ ገበያ ዋጋ ላይ ለውጥ ያመጣል።የአንድ ኩባንያ ምርት ጥራት ሲወርድ የዚያ ኩባንያ ፈላጊዎች ይቀንሳሉ።

በተቀራኒው አንድ ኩባንያ ትርፍማ የሚያደርገውን ውሳኔ ወስኖ ትርፍ ሲያጋብስ፣ የትርፉ ተቋዳሽ መሆን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍ ይላል። በዚህ መሠረት ባትሪው እየፈነዳ ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጠ ያለው የሞባይል ኩባንያ ድርሻ በከፍተኛ መጠን ሊወርድ ይችላል። በሁለት ዶላር የገዙትን ድርሻ መልሰው መሸጥ ቢፈልጉ ከግማሽ ባነሰ ዋጋ እንኳን የሚገዛዎትን ላያገኙ ይችላሉ። ይህ ሞባይል አምራች ኩባንያ ሲከስር እርስዎም የኩባንያው ባለድርሻ እንደመሆንዎ ኪሳራ ያጋጥምዎታል።

ስለዚህ በኩባንያ ‘ሀ’ ላይ ያደረጉት ኢንቨስትመንት ኪሳራን ያስከትላል።የ ‘ሐ’ ምርት የሆነው ስልክ ግን በገበያ ተፈላጊነቱ ሲጨምር የኩባንያው ዋጋም ከፍ ይላል። ምናልባት በሁለት ዶላር የገዙትን የኩባንያውን ድርሻ፣ አሁን ላይ በ4 ዶላር ሸጠው ትርፍ ሊያገኙ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ።

በ”The Ethiopian Economiat View” ድረ ገጻቸው ቢዝነስ ፣ ኢኮኖሚክስና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመጻፍ፤ ማህበራዊ ሚዲያውን በተለይ ፌስቡክን ለበጎ አላማ በማዋል የሚታወቁት የኢኮኖሚክስ ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ ስለ ስቶክ ማርኬት ታሪካዊ ዳራ በማህበራዊ ሚዲያ ባጋሩን ገለጻ፤መደበኛ ቁጥጥር የሚደረግባቸው የመገበያያ ገበያዎች ሊኖሩ ይችላሉ (የክፍያ ሥርዓታቸው በመደበኛ የፋይናንስ ተቋማት በኩል ሊያልፍ ይችላል)፡፡

ነገር ግን የስቶክ ገበያ (Stock Market) ካምፓኒዎችን ለበርካታ ህዝብ የመሸጥ እና የመግዛት ሂደት የሚመራበት የገበያ አይነት ነው፡፡ስቶክ ገበያን ለመጀመር በአውሮፓ የቀደሙ ሀገራት ቢኖሩም እንግሊዛውያን የስቶክ ገበያን 1773 (የለንደን የስቶክ ገበያ/London Stock Exchange በቡና ቤት/በካፌ ውስጥ በመገናኘት ግብይት ጀመሩ። በአሜሪካ የመጀመሪያው የስቶክ ገበያ የተቋቋመው በፊላደልፊያ በ1790 ሲሆን ከ2 ዓመት በኋላ 1792 ገበያው ወደ New York’s Wall Street ተዘዋውሯል፡፡

በመደበኛ ገበያ ገንዘብ/ብር መገበያያ ሆኖ ሲያገለግል በስቶክ ገበያ ግን መተማመኛ ወረቀት/ቦንድ መገበያያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ የስቶክ ገበያ በሂደት እየዘመነ በመምጣት በወቅቱ ለገዢ እና ለሻጭ ይሰጥ የነበረው ሰርተፍኬት ሲሆን አሁን ላይ ወደ ዲጂታል ሰነድነት ተዘዋውሯል፡፡ይህንን ድርጅትን ለበርካታ ሰዎች የማሻሻጥ ሥራ የሚሰሩ በህግ እን በደንብ የሚቋቋሙ እና ቁጥጥር የሚደረግባቸው የስቶክ አሻሻጮች/Stock Exchanges ይባላሉ (ለምሳሌ በአሜሪካ መደበኛ የፋይናንስ ሁኔታን ከሚቆጣጠሩት በተጨማሪ ራሱን የቻለ Securities and Exchange Commission አለ)፡፡ የተቆጣጣሪ ድርጅቶች ሚና ለተገበያዮች በቂ ጥበቃ መሰጠቱን ማረጋገጥ፤ ፍትሃዊ ገበያ መኖሩን ማረጋገጥ፤ ጤነኛ የካፒታል ዝውውር መኖሩን ማረጋገጥ፤ ወዘተ ነው፡፡

በዓለም ላይ ታዋቂ የመንግሥት፤ የመንግሥት እና የግል እንዲሁም የግል የስቶክ አሻሻጭ ድርጅቶች ያሉ ሲሆን! በዓለም ላይ ግዙፎቹ የስቶክ ገበያዎች መካከል ዋናዎቹ የአሜሪካኖቹ (New York Stock Exchange እና NASDAQ)፤ የጃፓኑ (Tokyo Stock Exchange)፤ የቻይናዎቹ (Shanghai Stock Exchange እና Hong Kong Stock Exchange)፤ የእንግሊዙ (London Stock Exchange) ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ስቶክ (ሰነድ መዋእለ ንዋይ) ለማገበያየት የሚቋቋሙ ድርጅቶች የ25 ከመቶ የመንግሥት እና 75 ከመቶ የግል ባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ይሆናሉ። የስቶክ ገበያ የንብረት ሻጭ እና ገዢን የማገናኘት እና ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያደርጉ ተቋማት ናቸው (እንደቀጥተኛ ማለትም ሻጭም ገዢም ቀርበው እንደሚገበያዩበት የገበያ አይነት ይቆጠራል)፡፡ ይህ ገበያ አዋጪ ዋጋ፤ በቀላሉ ክፍያ የመለዋወጥ እና ታማኝነት ያላቸው የነጻ ገበያ ባህሪ አላቸው፡፡

ካምፓኒዎች ላላቸው ድርጅት ተጨማሪ ካፒታል በሚፈልጉ ጊዜ ወይም አዲስ ድርጅት ለማቋቋም ምን ያህል ካፒታል እንደሚፈልጉ እና የት እንዲሸጥላቸው እንደሚፈልጉ ለነዚህ ስቶክ አገበያዮች ያሳውቃሉ፡፡ ከዚያ እነዚህ የስቶክ አገበያዮች ባላቸው ፕላትፎርም በተባለበት ቦታ በሙሉ አክሲዮኑን ለሽያጭ በማቅረብ ከገዢ ገንዘብ በመቀበል የድርጅቱን ድርሻ ስለመግዛቱ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ይሰጣሉ ማለት ነው፡፡

በስቶክ ግብይት ወቅት የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከፍ እና ዝቅ ባለ ቁጥር ሻጭ ድርጅትም ሆነ አክሲዮን ገዢ የአክሲዮን ትርፋቸው ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል! ይህንን በሙሉ እነዚህ የአክሲዮን ገበያዎች ይመሩታል (አንድ ሰው አንድ አክሲዮን ቀድሞ አክሲዮኑን ከገዛ ሰው ከገዛ ሁለተኛ ገበያ ይባላል! ምክንያቱም ከድርጅቱ በቀጥታ ሳይሆን ከገዢ ስለገዛው ነው፡፡ የአክሲዮን ገበያዎቹ ለሰሩበት ከሻጭ እና ከተሳታፊዎች የአገልግሎት ክፍያ ያገኛሉ፡፡

በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት በኢትዮጵያ የስቶክ ህግ እና ሥርዓት በአግባቡ ስላልነበር በዚህ ወቅት ባንኮች በውክልና የተለያዩ አክሲዮኖችን እያሻሻጡ እንዳሉት ማለት ነው፡፡የስቶክ ገበያዎች መኖር ሻጭም ሆነ ገዢ ስለገበያው እና ስለፍትሃዊ የመሸጫ ዋጋው በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ በስቶክ ገበያ ሰንሰለት ውስጥ የሚሳተፉት የስቶክ ገበያ አመቻቾቹ፤ ሻጮች፤ ገዢዎች እና ደላሎች (ለምሳሌ አንዳንዶች እንደቋሚ ቁስ አክሲዮኖችን ገዝተው ሲወደድ የሚሸጡ አሉ!) ናቸው፡፡

የስቶክ ገበያ መኖር ትንንሽ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ወደ ትርፍ ሊያመጡ ወደሚችሉ የአክሲዮን ገበያ በመግባት ትርፍ እንዲያገኙ፤ የካፒታል ፍላጎት ያላቸው ሰዎች/ድርጅቶች ካፒታል በመፍጠር ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ እና በኢኮኖሚው ውስጥ ፈጣን የገንዘብ እንቅስቃሴ እንዲኖር የማድረግ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ሲኖራቸው የውጪ ባለሀብቶችን ከመሳብ በተጨማሪ ከተፈጠረው የካፒታል እድገት በሚፈጠር ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚው የሥራ እድል እና የግብር ገቢው እንዲያድግ ያደርጋል፡፡

ሻሎም ! አሜን።

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You