የትምህርት ጥራት ጉዳይየማያገባው አካል የለም

በትምህርት ጥራት ላይ የሚታዩ ችግሮች አሁን ላይ ለሚታዩ ሀገራዊ ችግሮች ምክንያት ነው ብሎ ማሰብ ማጋነን ሊሆን አይችልም። በአግባቡ ያልተማረ፤ በተማረው ትምህርት እራሱን/ማንነቱን መቀየር ያልቻለ ትውልድ፤ በአንድም ይሁን በሌላ ለራሱ፣ ለቤተሰቡና ለሀገሩ የችግር ምንጭ መሆኑ የማይቀር ነው።

ይህንን ታሳቢ በማድረግም ሀገራት ለትምህርት ከፍተኛ ሀብት መድበው፣ በትኩረት ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላል። እንደ ሀገር የጀመሩትንና በብዙ እያተረፋቸው የሚገኘውን ሥልጣኔ/ዘመናዊ አስተሳሰብ/በተሻለ መልኩ ማስቀጠል የሚያስችል ትውልድ በመፍጠር ሥራዎች ተጠምደው ማየትም የተለመደ ነው።

በተለይም ለዜጎቻቸው /በየዘመኑ ለሚመጣውና ለሚሄደው/ በሚሰጠው የትምህርት ጥራት ጉዳይ ላይ በየትኛውም ሁኔታ መደራደር የሚያስችል ክፍተት የላቸውም። የሚሰጡት ትምህርት የሚፈልጉትን የሠለጠነ የሰው ኃይል ስለ ማፍራቱ ቀን ከሌሊት የሚተጉበት ጉዳይ ነው።

ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮች አራት መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳሏቸው በትምህርት ባለሙያዎች ዘንድ ይነገራል። እነሱም የመምህራን ብቃት ማነሳ፣ በዘርፉ የሚታየው የትምህርት ስብራት፣ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት እና የአካባቢያዊነት አስተሳሰብ (በሁኔታዎች መተሳሰር) ናቸው።

ከጥራት መጓደል የተነሳም ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች ትውልድን ራዕይ አልባና ተስፋ ቢስ ሊያደርጉ የሚችሉ፤ ሀገርንም እንደ ሀገር ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ናቸው። በኛም ሀገር ካሉ አሁናዊ ችግሮች በስተጀርባ ይህ ሀገራዊ የትምህርት ጥራት ችግር ዋነኛ ተጠቃሽ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

ችግሩን ለመፍታት በመንግሥት በኩል ሰፊ ሥራዎች ታቅደው ወደ ሥራ ተገብቷል። ትምህርት ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ በየደረጃው ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ዜጎች ለራሳቸው እና ለሀገራቸው ዛሬና ነገዎች ባለ ብዙ ተስፋ እንዲሆኑ ለማስቻል ከፖሊሲ ጀምሮ በተለያዩ ትምህርት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናትን መሠረት ያደረጉ ተጨባጭ ተግባሮች እየተከናወኑ ነው ።

የከፍተኛ ትምህርት ሪፎርም፣ የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና፣ የትምህርት ዲጂታላይዜሽን ሪፎርም፣ በጦርነት ምክንያት ከፊል እና ሙሉ በሙሉ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን በአዲሱ ‹የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ዲዛይን›› ጽንሰ ሃሳብ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች የዚሁ እውነታ ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።

የተለየ ስጦታ ያላቸውን ተማሪዎች በመለየት በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በፍልስፍና እና በሌሎች ዘርፎች የሚማሩበትን ዕድል ለማመቻቸት እንዲያግዝ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ግንባታቸው የተጀመሩ 50 አዳሪ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ የሚደረግ ሀገራዊ ጥረት ተደርጎ የሚወሰድ ነው ።

የመምህራን እና ርዕሰ መምህራን አቅርቦት እና ብቃት ለማጎልበት፣ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት ችግርን ፣የትምህርት ምዘና እና ሥርዓት ትምህርት ለማሻሻል፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በተልዕኮ እና በመስክ ለመለየት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ከሚሠሩ ሥራ የሚጠቀሱ ናቸው።

የትምህርት ጥራት ጉዳይ ‹‹የእከሌ ሥራ ብቻ ነው›› ተብሎ የሚተው አይደለም። ሥራውን ለትምህርት ቤቶች፣ ለመምህራን፣ ለመንግሥት ወይም ለወላጆች መተው ሊያስከትል ከሚችለው ሀገራዊ ጥፋት አንጻር ተገቢ አይደለም። በየትኛውም መመዘኛ የሚበረታታ አይደለም።

ልጆች ከሕጻንነታቸው ጀምሮ ለትምህርት የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማስቻል። ግንዛቤያቸውን ወደ መሬት የሚያወርድ አስቻይ ሀገራዊ ሁኔታን ማመቻቸት ያስፈልጋል። ይህ የንባብ ባሕል ጨምሮ፤ ለፈጠራና ምርምር የሚሆን አዕምሯዊ ዝግጁነትን መፍጠር የሚጠይቅ ነው። ለዚህም የወላጆች አስተዋፅዖ ከፍያለ ነው።

ከዚህ የሚቀጥለው ለፈጠራና ምርምር የተዘጋጀን አዕምሮ የሚሸከም፤ የትምህርት ሥርዓት መቅረጽን የሚመለከት ነው። ይህ የትምህርት ፖሊሲን፣ ሥርዓተ ትምህርትን፣ የመምህራንን እና የትምህርት ባለሙያዎች ብቃት የሚመለከት መሠረታዊ ጉዳይ ነው። ይህ በአብዛኛው ቀደም ሲል የነበረውን/ ውጤታማ ያልሆነውን የትምህርት ሥርዓት መፈተሽን የሚመለከት ነው። ከጠንካራና ደካማ ጎኑ በመነሳት ማስተካከያ መውሰድ ነው፣ እነዚህን በአሁኑ ሰዓት ትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ መንገዶች በአብዛኛው እየተገበራቸው ያሉ ጉዳዮች ናቸው።

የመምህራን ብቃት ለማሳደግ ያቀዳቸው ሥራዎች፣ በተማሪዎች እና በመምህራን በኩል የሚስተዋለውን የእንግሊዝኛ ቋንቋን ለማሻሻል የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች የተለያዩ የማስተማሪያ ሞጁሎችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች፣ ተማሪዎች የእንግሊዝኛ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችል/ከድረ ገጽ (ዌብሳይት) አውርደው/ የሚጠቀሙበት ቴክኖሎጂ መልማቱ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጀመሩ አበረታች ሥራዎች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር እንዳመለከቱት፤ ሀገራችን ትምህርትን ለሁለንተናዊ ዕድገት ከመጠቀም ይልቅ የፖለቲካ ትግል መሣሪያ አድርጎ ለመጠቀም የሚደረግ ትንቅንቅ የፈተና አስተዳደር ሥራን ውስብስብ ከማድረጉም ባሻገር ከፍተኛ ጉዳትም ሲያደርስ ቆይቷል።

የትምህርት ጥራት ችግር ውስብስብ እና የረዥም ጊዜ በመሆኑ ችግሮቹ በአንድ ጀምበር የሚፈታ አይደለም። ትምህርት ቤቶችን ከአዋኪ ነገሮች የፀዱ፤ ከፖለቲካ አስተሳሰብ የነጹ እና የፀዱ መሆንም ይጠበቅባቸዋል። ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ፤ ከታች እስከ ላይ ባለው የሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ኃላፊዎችን ርብርብ የሚጠይቅ ነው።

ከዚህ ባለፈም ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን ለማውጣት እና ጥራት ያለው፣ በአግባቡ የሠለጠነ የሰው ኃይል ለገበያው ለማቅረብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና መስጠት በትምህርት ዘርፉ ከተወሰዱ የሪፍርም ሥራዎች መካከል ይጠቀሳል። ፈተናው መሰጠቱ ተማሪዎች የተሻለ እውቀት፣ አመለካከትና ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው ፤

ከትምህርት ጥራት ጋርም ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው በመሆኑ ለቀጣሪዎች፣ ለቤተሰብና ለሀገር ብቁ ዜጋን ከመፍጠር ባሻገርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል።

በ2015 ዓ.ም ይፋ በተደረገው የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤት መሠረት፤ ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ ሦስት ነጥብ ሁለት በመቶ ተማሪዎች ብቻ እንዳለፉ መገለጹ ይታወሳል። ይህም የትምህርቱን ዘርፍ በሚገባ ለማጤን እድል የሰጠ ነው። በተጨማሪም ተማሪዎች እርስ በእርስ የሚኮራረጁበት አጋጣሚ በመጥበቡ የግድ ማጥናት እንዳለባቸው አስገዳጅ ሁኔታ ፈጥሯል ።

ለትምህርት ጥራት በግል የተቋቋሙ ከቅድመ አንደኛ እስከ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድርሻቸው ከፍተኛ ነው። በትምህርት ቤቶቹ ያለውን የትምህርት አሰጣጥ ወጥነት ባለው መንገድ መከታተል፤ መፈተሽ ለሚሰጡት ትምህርት ጥራቱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋል። በመንግሥት በኩልም ጣልቃ መግባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ/የቀደሙ አሳሪ ሕግና መመሪያዎችን በመከለስ/ቁጥጥር፣ ክትትል እና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

‹‹የተማረ የት ደረሰ?› እና መሰል ትርክቶች አሁን ያለው ትውልድ ስለ ትምህርት ያለው አመለካከት ዝቅተኛ እንዳይሆን ያሰጋል። ይህ አስተሳሰብ አድጎ እና ሰፍቶ የመጪው ትውልድ ላይ ጫና ከማሳደር አልፎተርፎ ሀገርን የወላድ መካን እንዳያደርግ ተግቶ መሥራት ያስፈልጋል።

በምስጋና ፍቅሩ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You