አትሌቲክሳችን ወዴት እያመራ ነው?

ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝብ ዘንድ ስሟ ገኖ ከሚጠራባቸው መስኮች ዋነኛው የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። ይህ ገናና ስም ዝም ብሎ በዘፈቀደ የተገኘ አይደለም። ከጀግናውና ታሪካዊው አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ አንስቶ አያሌ ከዋክብት አትሌቶች ብዙ ፈተናዎችን አልፈው ደምና ነጭ ላባቸውን አፍሰው ባስመዘገቧቸው ሕያው ድሎች የተገኙ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን የምንጊዜም የዓለም ከዋክብት አትሌቶች የተለዩ የስፖርቱ ዓለም ጀግኖች ሆነው የሚከበሩባቸው በርካታ ገፊ ምክንያቶች አሉ። ዘመናዊ ሥልጠና በደረሰበት ሳይደርሱ በብዙ የሕይወት ፈተናዎች አልፈው ባልሸነፍ ባይነት ወኔና ጀግንነት በባዶ እግራቸው ሳይቀር ዘመን የማይሽራቸው ድሎችን ማስመዝገብ መቻላቸው አንዱ ነው።

በሳይንሳዊ ሥልጠናዎች መታገዝ ከጀመሩ ወዲህም የሌላው ዓለም አትሌቶች ተፈጥራዊ ባልሆነ መንገድ ብቃትና አቅምን በሚያሳድጉ ቴክኖሎጂና መድኃኒቶች ታግዘው ፍትሐዊ ባልሆነ ፉክክር በአቋራጭ ድል ለመጨበጥ ሲጣጣሩ ነፃ ሆነው መቆየታቸው ሌላው ገድላቸው ነው።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአትሌቲክሱ የቅርብ ተፎካካሪያችን ኬንያ ሳትቀር ከዋክብት አትሌቶቿ በስፖርት የተከለከሉ አበረታች ንጥረ ነገሮችን(ዶፒንግ) ተጠቅመው በመገኘት ሲታመሱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከዚህ ቅሌት ጋር ስማቸው እምብዛም ሲጠራ አልነበረም።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ይህ አደጋ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች ላይም እያንዣበበ መጥቷል። የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይም ከሆነ ቆይቷል። ይህ የንፁሕ ስፖርት ነቀርሳ የሆነ አደጋ በኢትዮጵያ በእንጭጩ ባለመቀጨቱ አሁን ላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት በዚህ ቅሌት ውስጥ የተገኙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ቁጥር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። መድኃኒቱን ተጠቅመው ተገኙ የሚባሉትም ትልቅ ስም ያላቸው አትሌቶች አልነበሩም። አሁን ግን ነገሮች እየተቀየሩ መጥተዋል። ለዚህም ሰሞኑን በዶፒንግ ቅሌት ውስጥ ከተገኙ 10 ያህል አትሌቶች ሀገራችንን በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች የወከሉ ትልቅ ተስፋ የተጣለባቸው ኢትዮጵውያን አትሌቶች መካተታቸው አንዱ ማሳያ ነው ።

ይህም ኢትዮጵያ የአበረታች ቅመሞች ተጠቃሚ በሆኑ አትሌቶች ብዛት ‹‹A Category›› (ቀይ መብራት) ውስጥ መግባቷን የሚገልፁ አስደንጋጭ ዜና ይዞ መጥቷል። “ይህንን ችግር አስመልክቶ ሰሞኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ብዙ ያልተጠበቁ መረጃዎች /ጉዶች/ ወጥተዋል። የአትሌት ኤጀንቶች(ወኪሎች) ለአትሌቶች አበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው በስፋት ተወስቷል።

በመግለጫው እንደተገለጸው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው የአትሌት ወኪሎች 23 ብቻ ናቸው። ሕገወጦቹ ግን ከ300 በላይ በላይ ደርሰዋል። እነዚህ ወኪሎች ያለመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ እንደልባቸው ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ ነው፤ በየጫካው/ የልምምድ ቦታ ሳይቀር እየተገኙ አትሌቶቻችንን በዶፒንግ እየበረዙ ነው።

ለአትሌቶች ድጋፍ በመስጠት ሽፋን የአትሌቶች ተወካዮች፣ ከውጭ የሚመጡ አሠልጣኞች፣ ደላሎች ነገሩን እያባባሱና ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን እያደረጉ ነው። የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ባለመሥራታቸው ችግሩ ሰፊና ስር እየሰደደ ሊመጣም ችሏል።

ማንም የውጭ ዜጋ የመኖሪያ ፍቃድ ሳይጠይቅ መድኃኒቶችን ይዞ አትሌቶች ልምምድ በሚሠሩበት ስፍራ ድረስ ዒላማ አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ቀደም ብሎም ሲነገር የነበረ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የተወሰደ አስተማሪ እርምጃ ባለመኖሩ ችግሩ መቋጫ አላገኛም ።

ሙያው ከሚፈቅደው ሕግ ውጪ አንዳንድ የመድኃኒት መደብሮችና የጤና ባለሙያዎች መድኃኒቱን ባልተገባ መንገድ ከውጪ በማስገባት አትሌቶች ልምምድ በሚሠሩባቸው ቦታዎች ሳይቀር በስፋት እያቀረቡ ነው። ኬንያ በጉዳይ ቀደም ብላ ነቅታ አትሌቲክሷን ከዚህ አደጋ ለመታደግ ከሀገሯ ያባረረቻቸው ደላሎች፣ የአትሌት ተወካዮችና አሠልጣኝ ነን የሚሉ ግለሰቦች ኢትዮጵያን መሸሸጊያ አድርገው አትሌቲክሱን እየመረዙ ይገኛሉ።

ከ100 በላይ የውጭ ሀገር ሰዎች የአውሮፕላን ቁጥጥርን በመፍራት በመኪና ጭምር ወደ ሀገር ውስጥ በመግባት ይህንን ተግባራቸውን መቀጠላቸው ከላይ የተጠቀሰው ችግር አይነተኛ ማሳያ ነው። ጉዳይ ተባብሶ የቀጠለና ከመሆኑ ጋር በተያያዘ /የሚጠረጠሩ አትሌቶች በመብዛታቸው ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች መድኃኒቶች ባለሥልጣን ኢትዮጵያን ለመቅጣት ትንሽ ምክንያት ብቻ እየጠበቀ እንደሚገኝም የውስጥ ምንጮች ያመለክታሉ ።

በአሁኑ ወቅት በኤሽያና በተለያዩ ሀገራት የሚወዳደሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በስፋት እየተጠረጠሩ ነው። በተለይም ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ለውድድር ስለማይልክ በቱሪስት ቪዛና በንግድ ቪዛ እየወጡ ውድድራቸውን የሚያደርጉ አትሌቶች ችግሩን እንዲባባስ ዋነኝ ተጠቃሽ እየሆኑ ነው።

ፌዴሬሽኑ የት እንኳን እንዳሉ የማያውቃቸውና ተወዳድረው ሲያዙ ብቻ የሚያውቅ አትሌቶች መኖራቸው፤ ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር ለመፍትሔው ለመምከር እያስገደደው ይገኛል ።

በርግጥ እንደ ሀገር ቀደም ሲል ችግሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን ውስጥ የተካተተ ቢሆንም በአግባቡ ሥራ ላይ አለማዋሉ፤ ችግሩን ከሚያባብሱ አካላት ይልቅ የቅጣት እርምጃው አትሌቶች ላይ ብቻ የሚያተኩር መሆኑ ለችግሩ መባባስ አንዱ ምክንያት እንደሆነም የሚያነሱ አሉ ።

ችግሩ ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የንጹሕ አትሌቲክስ ስም የሚያጠለሽ ስለሆነ ምንም ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም። አጓጊ ሽልማቶችና ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ጥቂት አትሌቶች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚሠሩት ስህተት እልፍ ጀግኖች የገነቡትን የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ክብርና ዝና እንዳይንደው ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅብናል።

ጉዳዩ እየሞቀና እየበረደ ስር ወደ መስደድ እየተጓዘ በመሆኑ ትክክለኛ ባለቤት ኖሮት እልባት ማግኘት ይኖርበታል። ችግሩ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቁጥጥር በላይ በመሆኑም ጉዳዩን በበላይነት የሚመራ ሀገራዊ ኮሚቴ ሊቋቋም ይገባል።

አበረታች መድኃኒት የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ስጋት ውስጥ የከተተ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድና ከስሩ ነቅሎ ለመጣል የብዙ ባለድርሻ አካላት ርብርብን እንደሚጠይቅ ታውቆ አስቸኳይ የባለድርሻ አካላት ስብሳባ መጠራቱ ጥሩ ጅምር ነው። አንድ መፍትሔ ይዞ እንዲመጣም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ ርምጃዎችን እንደ ሀገር መውሰድ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።

የዶፒንግ የሕግ ጥሰቶችን በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 526 ላይ የተደነገገውን ተግባራዊ ለማድረግና በቀጣይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በየእርከኑ አጠናክሮ ማስቀጠል ለነገ የሚባል ሥራ መሆን የለበትም። መንግሥት በፖሊስና በደህንነት ተቋማት ለችግሩ ተጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን በመለየት በጥብቅ ክትትል በወንጀሉ እየተሳተፉ የሚገኙ ግለሰቦችና ፋርማሲዎችን አድኖ የማያዳግም እርምጃ ሊወስድ ይገባል።

በውድድር የሚሳተፉ ስፖርተኞችም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የችግሩ ሰለባ እንዳይሆኑ ለእያንዳንዷ ጥቃቅን ነገር ጥንቃቄ ሊለያቸው አይገባም። የቀደምት አትሌቶችን ፈለግ በመከተል በአሠልጣኞቻቸው የሚሰጣቸውን ሠልጠና በመቀበል እና የተፈጥሮ አቅማቸውን በመጠቀም ስፖርቱን ሊከውኑ ይገባል ።

አበረታች ቅመሞች በመጠቀም ለማሸነፍ መሞከር ውጤቱ ጊዜያዊ ነው። ተፈጥሯዊ ውጤት አይደለም። አንድ ቀን ውርደት ያስከትላል። ጉዳቱ የግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም በገንዘብ የማይተመን ጥፋት እንደሚያመጣ ለአፍታም ቢሆን ሊዘነጋ አይገባም።

ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባቸዋል። የፀረ-ዶፒንግ ጉዳይ በመዋቅራችው ውስጥ አካቶ ተግባራዊ ማድረግ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። እንደ አገር በባለሥልጣን ደረጃ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች መድኃኒቶች ተቋም ችግሩን ለመፍታት የጀመራቸውን ሥራዎች አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ።

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You