ከሕግም ከባህልም በማፈንገጥየምናተርፈው ጥፋት ነው

ቀላልም ሆነ ከፍ ያለ ግጭት መነሾው የፍላጎት አለመጣጣም ሊሆን እንደሚችል ይታመናል:: ይህ እንደ የሁኔታው ቢለያይም ፣ በመጀመሪያ ለግጭት የሚያንደረድረው በግለሰቦች ወይም በቡድኖች መካከል የአመለካከት ልዩነት ሲፈጠር ነው:: ልዩነቱ እያደገ ሲመጣም አለመደማመጥን ብሎም አለመግባባትን ሊያስከትል ይችላል::

ይህ በሰው ልጅ የእለት ተእለት መስተጋብር ውስጥ የሚጠበቅ ነው። ለውጥን ለማነቃቃት እንደ አንድ አቅምም ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ችግር የሚሆነው አለመግባባቶቹ በሰላማዊ መንገድ በውይይት መፈታት ካልተቻለ ነው ፤ ይህ ደግሞ ሀገርን ሕዝብን ሊጎዳ የሚደርስበት ደረጃ ሊደርስ ይችላል። ችግሩ ላለፉት ሶስት አስርቶች መታዘብ እንደቻልነው በባለ ብዙ ታሪክ ሀገራትን ሳይቀር ከመኖር ወደ አለመኖር ወስዷቸዋል፤ ሕዝቦቻቸውን በትኖ ከፍ ያለ የመከራ ገፈት ቀማሽ አድርጓቸዋል ።

ግለሰባዊ ወይም ቡድናዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ አለመግባባቶች በኛም ሀገር በየዘመኑ ሀገርና ሕዝብን ብዙ ዋጋ ማስከፈላቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ችግሩ አሁን ላለንበት ድህነትና ኋላ ቀርነት ተጠቃሽ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ለመናገር አይከብድም።

በተለይ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ እያስተናገድናቸው ያሉ የተዛቡ አስተሳሰቦችና አስተሳሰቦቹ የወለዷቸው ተግባሮች ፤ በታሪካችን ባልታየ መልለኩ ሕዝባችንን እንደ ሕዝብ ብዙ ያልተገቡ ዋጋዎች እያስከፈሉ ነው። የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገዎቻችን የስጋት ምንጭ እየሆኑ ነው።

ከለየላቸው የይዋጣልን ሽለላና ቀረርቶ ባለፈ ፤ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን የጦር አውድማ በማድረግ በመርዛማ መልዕክቶች ሕዝብና ሕዝብን ለከፋ እልቂት ለመዳረግ ፤ ብዙ የተዛቡ እና የውሸት ትርክቶች ተፈጥረው አደባባዮችን ሞልተው ተሰምተዋል። በሟርት የተሞሉ መልእክቶች ሕዝባችንን ለከፋ ጭንቀት ዳርገዋል፤ ተስተውለዋል ::

በዚህ መርዛማ መልዕክት መነሻነት ብዙዎች ተጎድተውበታል:: በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በሚለጠፉ “በሬ ወለደ” መረጃ እና ከፋፋይ መልዕክት ሆኗል። በጥቂት የነገር ፊትአውራሪዎች አማካይነት የከረረ ስሜት ውስጥ እንዲጋቡ ተደርጓል :: በዚህም ሕዝባችን የከፈለው ዋጋ ጠባሳው ገና አልሻረም።

ባልተገባ እና ባልተገራ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ በሚለጠፍ ባዶ ሙገሳና ከንቱ ምኞት ተነሳስተው የሥልጣን ጥማታቸውን ለማርካት የተንቀሳቀሱ ጥቂት አይደሉም። በዚህም ምክንያት ያደጉበትንና የኖሩበትን ቀዬ ለቀው ለመሰደድ የተገደዱ ዜጋዎቻችን ቁጥር በቀላሉ የሚታሰብ አይደለም:: በዚህ ኢትዮጵያዊ ባልሆነ ተግባር ሕዝቡ ትከሻው ከሚሸከመው በላይ በሆነ ፈተና ውጥ እንዲያልፍ ሆኗል:: ሰላም ርቆትም ከርሟል::

ግጭት የማይቀር እና ያለ መሆኑን የሰው ልጅ ተገንዝቦ ተስማምቶ በወሰነው የግጭት መፍቻ መንገድ እና ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት እየተጠቀመ ዘመናትን ተሻግሮ እዚህ ደርሷል። አሁንም ዘመኑን በሚዋጅ መንገድ ልዩነቶችን በማስተናገድ ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት እየተሠራ ነው::

በሀገራችንም ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ ማስታረቅ የሚያስችሉ ባህላዊ የእርቅ ሥርዓት አላቸው:: በነዚህ ሥርዓቶች ያጠፋ ይቀጣል፤ በደል የደረሰበት ደግሞ ይካሳል:: በዘመናዊውም ቢሆን አንድ ሰው ጥፋት ሲያጠፋ የሚቀጣበት መንገድ እንዲሁ በተለያዩ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ሰፍረው የምናየው ነው::

ይሁንና እነዚህን ሀገር በቀል ባህላዊ የግጭት አፈታት የእርቅ ሥርዓቶች ሆነ ዘመናዊ የሕግ አግባቦችን መጣስ ለብዙዎች የመብት ያህል እየተለመደ መጥቷል:: ድሮ ድሮ የሽማግሌ ቃልም ሆነ ተግሳጽ ይከበራል፤ እንዲያውም ‹‹ሰማይ ቢቀደድ ሽማግሌ ይሰፋዋል›› እስከመባልም በሀገር ሽማግሌዎች ይታመንባቸው እንደነበር ይታወቃል:: ዛሬ የሽምግልና ሥርዓቱም ሆነ ሕጉ ተገፍተዋል::

የሀገር ሽማግሌን አለማክበራችንም ሆነ ለሕግ አለመገዛታችን የሚያላትመን ከከፋ ነገር ጋር ነው:: ባህላዊ ሥርዓቱንም ሆነ ሕጉን ማክበር ለአብሮነቱም ሆነ ለዘላቂ ሰላሙ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው:: ለዚህ ደግሞ ዋጋ መክፈል የግድ ይለናል:: ዋጋ መክፈል የሚጀምረው ትንሽ የሚመስልን ነበር እንቢ ማለት የሚያስችል እራስን መግዛት ሊሆን ይችላል::

ለምሳሌ አንድ በየትኛውም የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚ የሆነ ግለሰብ መረጃዎችን ከማየት በዘለለ በገዛ የግል አካውንቱ ሊያጋራቸው የሚያስባቸውን መረጃዎች ከመለጠፉ አስቀድሞ ደጋግሞ ሊያስብበት ይገባል:: ራሱ የሚያጋራውን መረጃ ከመለጠፉም ሆነ በሌላ አካል በተጋራ መረጃ ላይ አስተያየቱን ከመሞነጫጨሩ በፊት ‹‹ላጋራ ያስብኩትም ሆነ አስተያየት ልሰጥበት የተመኘሁት ነገር በሌላው ላይ ሊያሳድር የሚችል ተጽዕኖ አለው? ወይስ የለውም? የሚለውን በአግባቡ ማጤን ይኖርበታል::

እንዲሁ ግን በማን አለብኝነት የሚለጥፍ አሊያም አስተያዩቱን የሚሰነዝር ከሆነ መርዛማና አጥንት ሰባሪ ቃላትን በመጠቀም እንደዋዛ የሚለጣጥፋቸው መረጃዎች የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚውን የሚጎዳ፤ ራስንም ለአደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን መረዳት አለበት::

ልክ አንድን ቦምብ አጥምዱ እንደማስቀመጥ የሚቆጠር ነው:: ይህን ማድረግ ግን ጉዳቱ ለአንባቢው አሊያም ለአድማጩ ብቻ አይደለም:: ቦምቡን አጥምዶ ለሚያስቀምጠው አካልም ጭምር እንጂ:: ቦምቡን አንዴ አጥምዶ ማስቀመጥ ይቻል ይሆናል፤ ባጠመደው ቦምብ ላለመመታት ማስተማመኛ የሚሆን ነገር አይኖርም :: ከሕግ ተጠያቂ ከመሆን አያመልጥም ::

ብዙዎቻችን ምን ያህል ግንዛቤው ይኑረን አይኑረን አላውቅም እንጂ የጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ አለ:: ሕግ አለማወቅ ደግሞ ከተጠያቂነት እንደማያስመልጥ ራሱ ሕጉ ያስቀምጣል:: የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዋጅ መውጣቱ ሆን ተብሎ የሚሰራጩ የጥላቻ እና የሐሰተኛ ንግግሮችን በሕግ መከላከልና መቆጣጠር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም ይታመናል::

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ለማኅበራዊ ስምረት፣ ለፖለቲካ መረጋጋት፣ ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሠብዓዊ ክብር፣ ለብዝሃትና ለእኩልነት ጠንቅ በመሆኑም ጭምር አዋጁ መውጣቱ ተመላክቷል:: ለአብነት ያህል ብቻ ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል፤ ማንኛውም ሰው በአዋጁ አንቀጽ አራት መሠረት የተከለከለውን የጥላቻ ንግግር ያደረገ እንደሆነ እስከ ሁለት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር ሁለት ሺ ያልበለጠ መቀጮ እንደሚቀጣ አዋጁ ይደነግጋል::

በጥላቻ ንግግሩ ምክንያት ደግሞ በግለሰብ ወይም በቡድን ላይ ጥቃት የተፈጸመ እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ ቀላል እስራት መሆኑንም ያሳውቃል:: ይህና መሰል ድንጋጌዎች እያሉ ዛሬም የክፋትን ጥግ የምናሳይ ብዙዎች ነን:: ጥቂት የማይባሉ የማኅብረሰብ አንቂ ነን ባዮችን ጨምሮ ሌሎችም አካላት ጥረታቸው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በሰላም እንዲኖር ሳይሆን ዜጋው ከሚደርስበት ሰቆቃ ለማትረፍ ነው::

እንዲያውም በሚለጣጥፉት እና በሚቀበጣጥሩት የሐሰት ትርክት ኹከትና ጥላቻን ካልዘሩ የእለት እንጀራቸው የተነፈጋቸው ያህል የሚቆጥሩ አሉ:: አሁን አሁን የነዚህ ግለሰቦች የችግሩ ጫና ከልክ እያለፈ መጥቷል:: ሙስና፣ የኑሮ ውድነት እና የሰላም እጦት የሚያንገላታው ሕዝብ ተጨማሪ የጠብ አጫሪነት አካሄድን መሸከም የሚችልበት አቅም የለውም::

አሁን ላይ ሀገሪቱ እየተጋፈጠች ያለውን ፈተና ለማለፍ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እንደገና ማጠናከር ለተሻለ መግባባት በር ከፋች ነው። በዚህ ላይ መሥራት ጠቃሚ ነው የሚል አተያይ አለኝ:: ከዚህ ጎን ለጎንም ከሕግም ሆነ ከሀገር ሽማግሌዎች ምክር ማፈንገጥ መጋጋጥን ያመጣልና ልናስብበት ይገባል:: በተጨማሪም እርስ በእርስ መነጋገሩና መወያየቱ ለመግባባት ቁልፍ ጉዳይ ነውና ራስን ለውይይትና ምክክር ማዘጋጀቱም ብልህነት ነው :

ወጋሶ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You