አስተማማኙ የአየር ኃይል ቁመና

የኢፌዴሪ አየር ኃይል እንደ ስሙ ኢትዮጵያን ከጠላት የሚከላከል የሉአላዊነት ተገን ነው። እንደመርህ እየተመራበት ካለው የተልዕኮ መነሻ ተነስተን አላማውን መተንተን እንችላለን። የመጀመሪያው የተልዕኮ መርህ የብሄራዊ አየር ምህዳርን መጠበቅ ነው። ይሄ ማለት ለሉአላዊነት ስጋት የሆኑ የጠላትን የአየር ላይ ተልዕኮ በእውቀትና ጥበብ በታገዘ ብቃት መከላከል ነው።

ቀጣዩ የተልዕኮ መርህ ለምድር ጦር ኃይሎች ድጋፍ መስጠት ነው። ስራዬ ብሄራዊ የአየር ላይ ምህዳርን መጠበቅ ነው ብሎ የሚያበቃ ሳይሆን በሉአላዊነት ጉዳይ ላይ ከሌሎች የደህንነት አካላት ጋር ተባብሮ በመስራት በቁርጠኝነት የቆመ ነው። በሀገር ጉዳይ ላይ ለየትኛውም ተጻራሪ ኃይል ዋጋ ለመክፈል በእምነት የቆመ የክብር ደጀን ነው።

ሶስተኛው እንደተልዕኮ ይዞት የተነሳው በጦርነት ወቅት የእርስ በርስ እንቅስቃሴዎችን የማገዝ ኃላፊነትን በብቃት መወጣት ነው። በዚህ የተልዕኮ እሳቤ የእርስ በርስ እንቅስቃሴ ተብሎ የተገለጠው ስለኢትዮጵያ ሲሉ ዋጋ ለመክፈል የተነሱ የሀገርና ሕዝብ አገልጋዮችን ለመጥቀስ ነው። የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከነዚህ አካላት ጋር በመዋሃድ አቅጣጫ በመስጠትና ንቁ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ የበኩሉን የሚወጣ ኃይል ነው።

በአሁኑ ሰዓት በየትኛውም ረገድ ብቁ ቁመናውን በማስመስከር ላይ ይገኛል። ከዘመናዊ ትጥቅ ጀምሮ፣ ከበቁና ከነቁ አብራሪዎችና ቴክኒሺያኖች እስከ አመራር ድረስ በሁሉም ረገድ የተዋጣለት መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች እያስመሰከረ ይገኛል። ከሰሞኑ ደግሞ ህዳር 20 በተከፈተ መርሀ ግብር 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች በማክበር የነበረበትን፣ ያለበትንና ወደፊት የሚደርስበትን የታሪክ ሂደት በመዳሰስ ማንነቱን በግልጽ እያሳየ ይገኛል።

በተለይ እንደ ሀገር፣ የተጣለበትን ኃላፊነትና እየተወጣ ያለውን ግዳጃ ከመቃኘት ለሀገር ክብር ምን ያክል ዘብ እንደቆመ ተጨባጭ በሆነ የትግበራ ሂደት ራሱን በመግለጥ ላይ ነው። ከህዳር 20 ጀምሮ በተለያዩ መርሀ ግብሮች እየተከበረ የሚገኘው የምስረታ በዓሉ ዳር ድንበርን ከመጠበቅና የውጪ ጣልቃ ገብነትን ስጋት የቀረፈ መሆኑን በግልጽ ያሳየ ነው።

ከዚህ ጎን ለጎን በዘመናዊ ትጥቅ የተደራጀ የአየር ኃይል ባለቤትነቱን ያስመሰከረበት መርሀ ግብር ነው። በዚህ ዝግጅት ላይ መግለጫ የሰጡት የአየር ኃይሉ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ፤አየር ኃይሉ ከነበረበት በትጥቅም በአመራርም እዚህ ግባ በማይባልበት ከዛ ዘመን አሁን እስከደረሰበት አስተማማኝ ቁመና ድረስ ያለውን ሂደት አስቃንኝተዋል።

እንደሳቸው መግለጫ፤ ለአየር ኃይሉ መነሳትና በብርቱ ቁመና መቆም የመጀመሪያው ምዕራፍ የመንግሥት ለውጥ መደረጉ ነው። ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተሰሩ ሥራዎች አዳዲስ ትጥቆችን ከመታጠቅ ጀምሮ እንደአየር ኃይል አስፈላጊ የሆኑ ማናቸውም ሁሉ የተሟሉበት ሁኔታን መፍጠር አስችሏል። በተለይ ኤሌክትሮኒክ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ዘመናዊ ሂሊኮፕተሮችንና ዘመኑ የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች ከበቃ የሰው ኃይልና ከአስተማማኝ ብቃት ጋር በመጠቀም ረገድ የተሳካ ሥራ ሠርቷል።

ቀደም ባለው ጊዜ አየር ኃይሉ አይደለም ሀገር ለመጠበቅ ቀርቶ እንደ ተቋም ካልተደራጀበት ሁኔታ ተነስቶ አሁን ያለበት ቁመና ላይ መድረሱ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ያሳያል። ሀገራችን ኢትዮጵያ የነጻነትና የሰላም ፋናወጊ በመሆኗና ከአፍሪካ አልፋ ለመላው ዓለም የመነቃቃት መንፈስን የፈጠረች ብቸኛዋ ሀገር በመሆኗ እንዲህ አይነት ሀገራዊ በዓላት ሲከበሩ ለብቻ ማክበር ያለመደብን ስለሆነ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራትን ጋብዘን በማክበር ላይ እንገኛለን።

አፍሪካ ስትነሳ ኢትዮጵያ መነሳቷ ግድ ነው። ይሄ ጥንታዊ የሰላምና የክብር፣ የሉአላዊነትና የልዕልና ስማችን እንዲመለስ በሁሉም መልክ ሰላም ፈጣሪና ሰላም ሰባኪዎች መሆን ግዴታችን ነው። ይሄን መንገድ በማሳለጥ ደረጃ የአየር ኃይላችን እንደ ፋናወጊ መጠቀስ የሚገባው ነው። በምስረታ በዓሉ ላይ አፍሪካውያንን ጋብዞ እኛ ከእኛ ይዘት ባለው አፍሪካዊ ቀለም በማክበር ላይ ይገኛል።

ህዳር ሀያ የአየር ኃይል ቀን ተብሎ እንዲከበር የተወሰነበት ዋና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አዛዥ የተሾመበትን ቀን በማስታወስ ነው። የአየር ኃይሉ ምስረታው አካባቢ ላይ የሰማይ ባቡር በሚል መጠሪያ ነበር የሚታወቀው። በሂደት ግን ስሙንም ግብሩንም ቀይሮ ሀገርና ሕዝብ በሚመጥን መልኩ ለዛውም በመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አዛዥ ጉዞውን ጀምሮ ከአሁኑ ቁመናው ላይ ደርሷል።

አየር ኃይሉ በዓሉን ሲያከብር አራት ዋና ዋና ቁምነገሮችን ታሳቢ በማድረግ ነው ፤ የሰው ኃይል ልማት፣ ትጥቅ፣ መሰረተ ልማት እና ኢትዮጵያን የሚመጥን የአየር ኃይል ግንባታ። የሰው ኃይል ልማት ለአንድ ሀገራዊ አላማን ላነገበ ተቋም እጅግ ፊታኛ ጉዳይ መሆኑ አያጠያይቅም።

አይደለም የአየር ኃይልን የሚያክል ግዙፍ ተቋም ቀርቶ ለየትኛውም አላማ ላለው ነገር እንደዋነኛ ግብዓት የሚያገለግል ነው። በሚቀጥሉት ጊዜአትም ቢሆን እንደ ዋነኛ የሪፎርም አቅጣጫ ሆኖ ከፊት የሚመጣ ጉዳይ መሆኑን ካለፈው ተሞክሮ መረዳት ይቻላል።

በአየር ኃይል ቋንቋ የሰው ኃይል ልማት ማለት ሰፊና ሁለገብ ጽንሰ ሀሳብ ነው። ብቃትና ንቃትን ከሙያ ስነምግባር ጋር ያጣመረ ተራማጅ አስተሳሰብ ነው። ከግብረገብነት እስከ ተነሳሽነት፣ ከሀገር ፍቅር እስከመስዋዕትነት ድረስ ያለውን የሚያጠቃልል፣ ከሰልጣኝ እስከ አሰልጣኝ ከአመራር እስከ ወታደር ድረስ የሚሸፍን ሰውን ከኃይልና ከልማት ጋር ያዋሃደ እሳቤ ነው።

ትጥቅ ለአንድ ሀገርን አላማ አድርጎ ለተነሳ ተቋም ምን ማለት እንደሆነ ትርጉሙ አይጠፋንም። ሀገርና ሕዝብ፣ ትውልድና ብዙሃነት ለተደባለቁበት ሰላም መር ተልዕኮ ትጥቅና የሰው ኃይል ልማት በእኩል የሚሰለፉ መዳፍና አይበሉባ ናቸው። ለዚህም ነው የአየር ኃይላችን በዘመናዊ የጦር ትጥቅ መዳበርን እንደ ቀዳሚ መስፈርት ወስዶ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው።

ሀገር ከመጠበቅ አኳያ መሰል ተቋማት ሰላምን ከማምጣትም ሆነ ዳር ድንበርን ከማስጠበቅ አንጻር በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የመዳበራቸው ነገር አጠያያቂ አይደለም። ሌላው በሶስተኛ ደረጃ ላይ የተጠቀሰው መሰረተ ልማት ነው። በሁሉም ባይሆንም በአንዳንድ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ላይ ይበል የሚያሰኝ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ አይነት አስተሳሰቦችን እያስተዋልን እንገኛለን።

ከለውጡ በኋላ የመጣው የአየር ኃይል እንቅስቃሴም ይሄን መሳይ ትግበራ ነው። ብሄራዊ የአየር ላይ ምህዳርን ከመጠበቅና ሉአላዊትን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን በመሰረተ ልማት ሰፍቶና ዳብሮ ያየንበት ሁኔታ ነው ያለው።መሰረተ ልማት ምቹ ከባቢን ከመፍጠር የሚጀምር ለሰራተኛም ሆነ ለስራው ንቃትን የሚጨምሩ ማናቸውንም በጎ ሁኔታዎች ያጠቃልላል።

በአየር ኃይል ግቢ ውስጥ እጅግ በርካታ ሥራዎች ለዛውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተከናውነዋል። ከግዙፍ ስታዲየም ጀምሮ ከራስ አልፎ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እስከመስጠት የደረሱ የመዝናኛ ክበባትን ከመስራት እና አካባቢን በአረንጓዴ ከመሸፈን አንጻር የተሳካ ሥራ ሠርቷል በመሥራትም ላይ ይገኛል። ከደህንነት አኳያ ዘመናዊ ካሜራዎችን በማስገጠም ዘመኑ የደረሰበት ደርሷል።

አንድ ተቋም የቱንም ያክል በአመራር እና በሥራ ክፍሎች ቢዳብር ምቹ የሥራና የሰራተኛ አካባቢ ከሌለው ለውጥ ተኮር መሆን አይቻለውም። ሰራተኞች ደስ በሚል ቦታና ሁኔታ ውስጥ ደስ በሚል ስሜትና ንቃት የሚሰሩበት ሁኔታ ካልተፈጠረ አሰሪውንም ሆነ ሰራተኛውን ብርቱ አያሰኘውም። ጥንካሬና የበረታ አመራርነት እንደ አየር ኃይል ከውስጥም ከውጪም በሚወጣ ለለውጥ በተጋ ትግበራ የዘመነ ነው።

የመጨረሻው ኢትዮጵያን የሚመጥን የአየር ኃይል ግንባታ ነው። ሉአላዊነትና ክብር ማንም በምንም የማይደራደሩባቸው ጉዳዮች ናቸው። በአሁኑ ሰዓት የዓለም ሀያላት እኔ እበልጥ እኔ በሚል የኃይል እና የጦር መሳሪያ ፉክክር ውስጥ ናቸው። ይሄ የሚያሳየው ሉአላዊነትና ክብር እስከየት ድረስ እንደሆኑ ነው። የኢፌደሪ አየር ኃይል የምስረታ በዓሉን ሲያከብር እንደ ተልዕኮ ከወሰዳቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ይሄ የሉአላዊነት ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያን የሚመጥን የአየር ኃይል ግንባታ ስንል ብዙ ጉዳዮችን መዳሰስ እንችላለን። መቼም ይሄን ጽንሰ ሀሳብ ለመረዳት በሀሳብ ብዙ መድከም የሚኖርብን አይመስለኝም። የትኛውም ሀገር ራሱን የሚጠብቅበት ከሆነ አስተማማኝ ካልሆነ ደግሞ የማያሳፍር ኃይል ያስፈልገዋል። እኛም ከጥንት ሀያልነታችን ጀምሮ አሁን እስካለንበት ፊተኝነትን መሻት ድረስ የነበረውን ከመመለስ እና ያለውን ከማስቀጠል አኳያ አስተማማኝ ስም መጣኝ የአየር ኃይል ያስፈልገናል።

በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች የይገባኛል ንትርክ ውስጥ በሆንበት በዚህ ጊዜ ጠንካራ የአየር ኃይል መገንባት ለነገ የማይባል የቤት ስራችን ነው። ከዚህ ባለፈ በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ ሆነን በአፍሪካ ተጽዕኖ ለማሳደር የኢኮኖሚ ክንዳችንን በማፈርጠም ላይ እንገኛለን ይሄ ሁሉ መሻት ዝም ብሎ የሚሆን ስላይደለ ተቀናቃኞቻችን እንዲያከብሩን፣ ጠላቶቻችን እንዲፈሩን፣ ከሆነ በሰላም ካልሆነ በመከላከልና በማጥቃት ህልውናችንን ለማስቀጠል የተደራጀ አየር ኃይል ያስፈልገናል።

የሰው ኃይል ልማት፣ ትጥቅ፣ መሰረተ ልማት እና ኢትዮጵያን የሚመጥን የአየር ኃይል አሁን ለሚከበረውም ሆነ ወደፊት ለሚከበረው የአየር ኃይል ምስረታ ቀን ከፊት ሆነው የሚቀጥሉ አበይት የልህቀት ፍሬዎች ናቸው። ሀሳብን ተጠቅሞ ሀገር ከመገንባት አኳያ ብዙ የሰላም አማራጮችን ለመቃኘትና ለመረዳት እድል ከመስጠትም ባለፈ ነገሮችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዳንመለከትም የሚያደርጉን ናቸው። በዚህ ረገድ አየር ኃይላችን ትናንት ያልነበሩ ቢኖሩም ያልደመቁ ብዙ ባለቀለም ስኬቶችን አሳይቶናል።

ወደፊትም እንደ ጥንተ ስማችን ከራስ አልፎ ለሌሎች በሚተርፍ የሰላምና የነጻነት፣ የእርቅና የዲፕሎማሲ ስራዎች ላይ በመሳተፍ የአስታራቂና የሽምግልና ሚናውን እንደሚያስቀጥል ይታመናል። አንዳንድ መነሻዎች የራቀ ነገን የሚዘክሩ ናቸው። ምንም ካልነበረ ሁኔታ ውስጥ ተነስቶ በዚህ ልክ ከበረታ መጪው ጊዜ በብዙ ተስፋ የምንጥልበት እንደሚሆን ተጨማሪ ምስክር አያስፈልገውም።

በአየር ኃይል ቋንቋ የሰው ኃይል ልማት ማለት ሰፊና ሁለገብ ጽንሰ ሀሳብ ነው። ብቃትና ንቃትን ከሙያ ስነምግባር ጋር ያጣመረ ተራማጅ አስተሳሰብ ነው። ከግብረገብነት እስከ ተነሳሽነት፣ ከሀገር ፍቅር እስከመስዋዕትነት ድረስ ያለውን የሚያጠቃልል፣ ከሰልጣኝ እስከ አሰልጣኝ ከአመራር እስከ ወታደር ድረስ የሚሸፍን ሰውን ከኃይልና ከልማት ጋር ያዋሃደ እሳቤ ነው፡፡

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You