የድብደባው መዘዝ

ሌሊት ነው። ሕይወት በፕላኔታችን ላይ ከጀመረው ክስተቶች መካከል አንዱ። ሌሊት የብዙ ክስተቶች ባለቤት ነው።ከጨለማው ጎን ለጎን በሰማይም ሆነ በምድር እልፍ አእላፍ ክስተቶች ይከናወናሉ፤ይፈጸማሉ።

ሌሊት ይዞት የሚመጣውን ጨለማ ደግሞ አብዛኞቻችን እንፈራዋለን። በጨለማ ፍርሃት እንዲሁ የተከሰተ ሳይሆን ማታ ላይ በከተሞቻችን የሚሰሙ አደጋን ያዘሉ እውነታዎች ያሳደሩት ተፅእኖ ውጤት ነው። ጨለማ ድንግዝግ ስለሆነ ይዞት የሚመጣው ነገር አይታወቅም። ከእይታ በሻገር የሰውን ህይወት የሚነጥቅ፤አካል የሚያጎድልና የሚያስደነግጥ ክስተት ሳይታሰብ ሊከሰት ይችላል።

ሌሊት ፀሐይ ከጠለቀችበት እስከምትወጣበት ያለው ጊዜ ነው። ይህ ማለት ነጠላ ኮከብ ስለ ሆነ የፈለክዋ ግማሽ በራስዋ ጥላ ስትሆን ነው። ምድር በ24 ሰዓት ውስጥ እየዞረች ነጠላ ፀሐይ እያላት በስተኋላው ጥላ ወይም ሌሊት ይሆናል ማለት ነው።

የሌሊትንና አስፈሪ ግርማውን ያነሳሳሁት ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 8፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ግንፍልፍል ባርና ሬስቶራንት አካባቢ የተፈጠረን ጥቃት ለማንሳት ስለወደድኩ ነው።

ለዚህ ታሪክ መነሻ ይሆንን ዘንድ የተዘጋ መዝገብን እንድናገላብጥ ለፈቀዱልን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ባልደረቦች የከበረ ምስጋናን በማቅረብ ታሪኩን እናካፍላችሁ። መልካም ንባብ።

የሌሊት ተረኛ ሕግ አስከባሪዎች

ሕግን ማስከበር ስራቸው የሆኑ የሕግ አካላት ናቸው። በፈረቃቸው ሕግን ሊያስከብሩ የሌሊቱን ፀጥታ ሊጠብቁ በተመደቡበት የሥራ ቦታ መገኘታቸው ነበር። በወርሃ ጥር ሰማዩ ፈክቶ መርፌ ቢወድቅ ማንሳት የምታስችል ጨረቃ ሰማዩ ላይ ተንሰራፍታለች። ውቡ ሌሊትን ከየጭፈራ ቤቱ የሚወጡት የሙዚቃ ድምፆች ባላወኩት ኖሮ ፍፁም ሰላማዊና የረጋ መንፈስ ውስጥ የሚከት አይነት ነበር። ፖሊሶቹ በግምት ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ሲሆን በእግራቸው እየተዘዋወሩ በነበሩበት ወቅት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ግንፍልፍል ባርና ሬስቶራንት አካባቢ ደረሱ።

ቦታው ላይ እንደ ደረሱ ከልክ በላይ በመጠጣቱ የተነሳ ከአስተናጋጆች ጋር ተጋጭቶ ክርክር እየገጠመ የነበረ አንድ ወጣት ተመለከቱ። በጨረቃ ብርሃን የደመቀው፤ ቀዝቀዝ ያለ የንፋስ ሽውታ ፊትን በሚዳስስበት ቀን የፀጥታ ኃይሎቹ ፍፁም የተረጋጋ ስሜት ውስጥ ነበሩ።

ድምፅ ወደ ሰሙበትም አቅጣጫ ያቀኑትም ረጋ ብለው ነበር። በአካባቢው ሲደርሱም ድንገት የተመለከታቸው እየበጠበጠ የነበረው ፀጋ ዘአብ የተባለው ወጣት እግሬ አውጪኝ ብሎ መሮጥ ጀመረ። ፖሊሶቹ ወጣቱን ቆሞ በሰላም እንዲያነጋግራቸው ቢጠይቁትም ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ሩጫውን በፍጥነት ቀጠለ። ያን ጊዜ አለመታዘዙ ያበሳጫቸው የሕግ አካላት አሯሩጠው ያዙት። ከዛም አንደኛው በእግሩ ጠልፎ መሬት ላይ ከጣለው በኋላ ይመቱት ጀመር።

በጠረባ መሬት ላይ የተዘረጋውን ወጣት በንዴት በእርግጫ ሆዱን እና ደረቱን አንደኛው ሲመታው ፣ ሌላው ደግሞ በወደቀበት በእርግጫ በሽጉጡ አካል ሆዱንና ግንባሩን በመምታት የሆዱ አካል እንዲጎዳ አደረገው። ሰላምን ለመጠበቅ የወጡት ኃይሎችም ሰላም አደፈረሰ ያሉት ላይ ከባድ ጉዳት አደረሱበት።

ወጣት ፀጋ ዘአብ

ወጣት ነው። ቅልብለብ ያለ፤እዚህም እዛም መርገጥ የሚያደስተው። ምንም የረጋ ነገር የለወም። ለአንድ ሰአት አንድ ቦታ መቀመጥ ሞት የሚሆንበት አይነት ወጣት ነው። ቁንጥንጥ የሚባል አይነት ልጅ። በተለይ ደግሞ ፖሊስ ሲያይ ነፍሱ በአፉ ወጠታ ልትወድቅ ትደርሳለች። መተንፈስ ያቅተዋል።

ፊትለፊቱ ሲመጡበት መንገድ አሳብሮ መሄድ ምርጫው ነው። ምንም አይነት ጥፋት ባያጠፋም በመርበትበት ስለሚመለከታቸው እነሱም በጥርጣሬ አይን ይመለከቱታል። ከያዙኝም አይለቁኝም ብሎ ስለሚያስብ ሁልጊዜ እንደአይጥና እንደድመት መሯሯጥ ስራቸው ነው።

በእለቱም ግንፍልፍል ባርና ሬስቶራንት ገብቶ ራቱን በልቶ መጠጣት ከጀመረ ሰአታት አልፈዋል። ጥጉን ይዞ ስለነበር ባልተለመደ ሁኔታ የመረጋጋት ስሜት ይታይበት ነበር። በመጀመሪያ ከምግብ ጋር የተወሰኑ መጠጦችን ሂሳብ ከፈለ፤ ከዛ ሞቅ እያለው ሲሄድ ያለወትሮው አንድ ቦታ ተቀምጦ መጠጥ መደጋገም ጀመረ። ያለ እቅድ ብዙ ጠጥቶ ኖሮ የያዘው ገንዘብና የጠጣው መጠጥ አልመጣጠን ብሎት ተጨነቀ።

እንደ አማራጭ የወሰደው ሮጦ ማምለጥን ነበር። ሮጦ ለማምለጥ ሲወጣ የተያዘው ወጣት ያለውን ሰጥቶ እንዲለቁት ቢማፀንም አልረዳ ብለውታል። እንኳን ጭቅጭቅ ገጥሞት ለወትሮውም ክርክር የማይወደው ቁንጥንጥ ወጣት በፀብ መንፈስ እየጮኸ ሲናገር ነበር የፀጥታ አስከባሪዎች በቦታው የደረሱት።

ወትሮም ፖሊስ ሲያይ ነፍስያው የምትረበሽበት ወጣት እዛ ቦታ በመገኘታቸው ደንግጦ እግሬ አውጪኝ ብሎ አመለጠ። ሩጫውን አቁሞ በእርጋታ እንዲያነጋግራቸው ቢጠይቁትም አሻፈረኝ ብሎ ሩጫውን ቀጠለ። ያኔ ነው እንግዲህ ስካር ባወላከፈው እግሩ እየተዳፋ የሚሮጠውን ወጣት በቀላሉ የደረሰው ሕግ አስከባሪ በእግሩ ጠልፎ የጣለው።

ውስጡ የነበረው የቀደመ ፍርሃት ያንዘፈዘፈው ወጣት ከወደቀበት ተነስቶ ለመሮጥ ሲታገል ሌሎቹ ሕግ አስከባሪዎች ደርሰው በርብርብ ይቀጠቅጡት ጀመር።

እንቅልፍ ያንገላጀጃት የባሩ አስተናጋጅ

ያለወትሮዋ ድካም ተሰምቷታል። ሰሞኑን በተደጋጋሚ ጠጪዎች ሂሳብ እየያዙባት እየሄዱ ደመወዟ መቆራረጡ ስላስከፋት በንቃት ሂሳቧን መቆጣጠር የሚገባት መሆኑን አምናለች። በእለቱ ግን ከተለመደው ጊዜ ውጪ እንቅልፍ እያስቸገራት ነው።

እሷ ስታስተናግዳቸው የነበሩ ሰዎች በሙሉ እየከፈሉ በጊዜ መሄዳቸው ሀሰቧን ቀለል አድርጎላታል። አንድ የባሩ ደንበኛም ቀድሞ ከፍሎ መጠጣት ቢጀምርም፤ እየደጋገመ ሲሄድ ግን ሂሳቡ እየበዛ ልጁም ነገር አለሙን እየረሳው መሄዱ አሳስቧታል።

በዚህ በኩል ደግሞ እንቅልፏ ከቁጥጥሯ ውጪ ሆኖ አይኗን እያስከደናት ነው። ባንኮኒውን ደገፍ ብላ እያንቀላፋች የነበረችው ወጣት ̋ወጣልሽ…̋ የሚል ደምፅ ነበር ሸለብ ካደረጋት እንቅልፍ ያባነናት።

እንደፈራችው ወጣቱ ሂሳቧን ይዞ ሹልክ ብሎ ሊወጣ ሲል አይን ለአይን ተገጣጠሙ። እሱም እንዳትይዘው በማሰብ ፍጥነቱን ጨምሮ መውጫ በሩ ጋር ደረሰ። ምንም ቢፈጥን ግን እጅብ ብለው ከመጡት የባሩ አስተናጋጆች ሊያመለጥ አልቻለም።

ሂሳቡን እንዲከፍል ሲጠየቀም ያለውን እያሳየ ሌላ ቀን እንደሚያመጣና እንዲለቁት መለመን ጀመረ። በተደጋጋሚ ሂሳብ የተወሰደባት አስተናጋጅ ግን በቁጣ እንደማይሆን ስትናገር ነው እንግዲህ ጫጫታውና ውዝግቡ የተፈጠረው።

በኋላም የፀጥታ ኃይሎች ደርሰው በወጣቱ ላይ ያደረጉትን ነገር ስትመለከት ̋ምነው ገንዘቡ በቀረብኝ” በማለት በፀፀት ስትንገበገብ መቆየቷን ጓደኞቿ ተናግረዋል። በዛች በጨረቃ በደመቀች ሌሊት ነው እንዲህ ይሆናል ተብሎ ያልተገመተው ጥፋት የደረሰው።

ያልታሰበው ጥፋት

ንዴትና የወጣቱ አጉል መፍጨርጨር እልህ ውስጥ የከተታቸው የፀጥታ አካላት ሟች ፀጋ ዘአብ የተባለውን ወጣት 2ኛ ተከሳሽ አሯሩጦ በእግሩ ጠልፎ መሬት ላይ በመጣል በእርግጫ ሆዱን እና ደረቱን ሲመታው፣ 1ኛ ተከሳሽ ሟች በወደቀበት በእርግጫ በሽጉጡ አካል ሆዱንና ግንባሩን በመምታት የሆዱ አካል እንዲጎዳ በማድረግ ተበዳይም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ መጋቢት 26/2014 ዓ.ም ህይወቱ አለፈ።

በእለቱ የሰሩት ጥፋት እንደሚያስጠይቃቸው ሲገነዘቡ ወደህክምና ተቋም ቢወስዱትም በህይወት ሊቆይ ባለመቻሉ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 540 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

ሕግን ለማስከበር፤ የሕዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ የእለት ስራቸው ላይ የተሰማሩት የፀጥታ ኃይሎች ስሜታቸውን መቆጣጠር ባለመቻላቸው ብቻ ያልታሰበ ጥፋት ሊያደርሱ በቅተዋል።

በዚህም ምክንያት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ሟችን አሯሩጠው በመያዝ በእርግጫ በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርጋችኋል ባላቸው ሁለት ተከሳሾች ላይ ክስ መስርቶባቸዋል።

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ

የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ ዋና ሳጅን እዩኤል ፍቃዱ፣ 2ኛ ደበበ ወዱ የተባሉ ተከሳሾች ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት 8፡00 ሰዓት ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ግንፍልፍል ባርና ሬስቶራንት አካባቢ ሟች ፀጋ ዘአብ የተባለውን 2ኛ ተከሳሽ አሯሩጦ በእግሩ ጠልፎ መሬት ላይ በመጣል በእርግጫ ሆዱን እና ደረቱን ሲመታው፣ 1ኛ ተከሳሽ ሟች በወደቀበት በእርግጫ በሽጉጡ አካል ሆዱንና ግንባሩን በመምታት የሆዱ አካል እንዲጎዳ በማድረግ ተበዳይም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ መጋቢት 26/2014 ዓ.ም ህይወቱ ያለፈ በመሆኑ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 540 ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት ሰው መግደል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

 ውሳኔ

 በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው የወንጀል ድርጊቱን አልፈፀምንም ፤ጥፋተኛም አይደለንም ያሉ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ 9 የሰው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች አቅርቦ በበቂ ሁኔታ ያስረዳ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ የቀረበባቸውን ክስ እና ማስረጃ እንዲያስተባብሉ ብይን ተሰጥቷል።

በሰጠው ብይን መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ስድስት፣ 2ኛ ተከሳሽ ሶስት የመከላከያ ምስክር አቅርበው ቢያሰሙም የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ማስተባበል ባለመቻላቸው ተከሳሾች ይከላከሉ በተባለበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት በቅጣት አወሳሰን መመሪያው መሰረት ተወስኗል።

1ኛ ተከሳሽ 3 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በእርከን 31 ስር በ12 ዓመት ጽኑ እስራት፣ 2ኛ ተከሳሽ ላይ 1 የቅጣት ማቅለያ ተይዞለት በእርከን 33 ስር በማሳረፍ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት፣ እንዲቀጡ ሲል ወስኖባቸዋል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You