ለሠላም ለተዘረጉ እጆች መልስ መስጠት የሕዝባዊነት አንዱ መገለጫ ነው

ለአንድ ሀገርና ሕዝብ ሁለንተናዊ እድገት የሚመነጨው ከሠላም ነው። ያለሠላም የአንድን ሀገር ነገዎች ቀርቶ ዛሬ ምን ሊመስል እንደሚችል መተንበይ አይቻልም። ከፍያለ ማኅበረሰባዊ ማንነት መገንባትም የሚታሰብ አይደለም ።

በተለይም አሁን ባለው፤ በብዙ ፍላጎቶች በተጨናነቀው ዓለም፤ የሠላም ጉዳይ ከሁሉም በላይ ከፍ ያለ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ለእዚህ ደግሞ ባለፉት ሦስት አስርተ ዓመታት ከሀገርነት ወደ ሁከትና ግጭት ሜዳነት የተለወጡ ሀገራትና የሕዝቦቻቸውን አሁናዊ ሁኔታ ማጤን ተገቢ ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ስለሠላም የሚያዜሙ አንደበቶች እንዳሉን ብዙ ተብሏል፤ ለእዚህ የሚሆንም መንፈሳዊ ፣ ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቶች ያሉን ነን። እነዚህ እሴቶች እንደ ሕዝብ አስተሳስረውን እስከ ዛሬ ሀገር እንድንሆን አስችለውናል ።

ጥያቄው ግን ኢትዮጵያውያን በዚህ ተጨባጭ እውነታ ውስጥ ሆነው፤ መቼ እና ለምን ያህል ጊዜ ያለጦርነት በሠላም እና መረጋጋት መኖር ቻሉ የሚለው ነው። በእርግጥ ምላሹም ብዙ ምርምርና ጥናት የሚሻ አይደለም። በሀገሪቱ የለየለት ጦርነት እንኳን ባይኖር በግጭት አዙሪት ውስጥ መኖሩዋ የአደባባይ ምስጢር ነው ።

በአፄዎቹ፣ በደርግም ሆነ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት ሀገሪቱ ፍፁም በሆነ ሠላምና መረጋጋት ውስጥ አልነበረችም። በሁሉም ዘመን ወጣ ገባ የሚሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች ነበሩ። ከለውጡ ማግስት ጀምሮም ስለ ሰላም ብዙ ተስፋዎች የነበሩ ቢሆኑም፣ ሀገሪቱ ጦርነት እና ግጭት ሲፈራረቅባት ከርሟል።

በትግራይ ክልል የነበረው ጦርነት የታሰበውን ሀገራዊ ሠላምና መረጋጋት አደጋ ውስጥ በመክተት በአጠቃላይ የነበረውን የሠላም ድባብ ረብሾታል፣ ሀገርና ሕዝብን ያስከፈለውም አላስፈላጊ ዋጋ ለግምት የሚከብድ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ለሞት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ለስደት፣ በቢሊዮን የሚቆጠር ሀብት ለውድመት ዳርጓል።

በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት ከበርካታ የሠላም እና የሽምግልና ጥረቶች በኋላ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተደረሰው የሠላም ስምምነት ጦርነት የሚቆምበት ሁኔታ ላይ መስማማት ተችሏል። በዚህም በአካባቢው ከጥይት ነፃ የሆነ ቀጣና መፍጠር ተችሏል ።

የትግራይ ጦርነት ካበቃ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሌላ ግጭት በአማራ ክልል በጽንፈኛ ኃይሎች ተቀስቅሷል። ግጭቱ አሁንም ሀገርና ሕዝብን አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈለ ነው። በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎቹ የክልሉን ሕዝብ ሠላምና መረጋጋት ችግር ውስጥ ከመክተት ባለፈ፣ የእለት ተእለት የሕይወት መስተጋብሩን አደጋ ውስጥ ከተውበታል ።

ከአማራ እና ከትግራይ ክልል በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልልም አሸባሪው የሸኔ ታጣቂ ኃይል በተመሳሳይ በክልሉ ሠላምና መረጋጋት እንዳይሰፍን፣ ባለው አቅም/ ከፍ ባለ ጭካኔ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ከቡድኑ ጋር ላለው ችግር ሠላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ በመንግስት በኩል እስከ ታንዛኒያ የዘለቀ ድርድር ቢካሄድም የሚጠበቀውን ሠላም ማምጣት አልተቻለም ።

አንደ ሀገር መንግሥት፣ ሕዝቡ ምሑራኑና ፖለቲካን ልሂቃኑ ባገኙት አጋጣሚ አለመግባባቶችን በውይይት እና በድርድር መፍታት ያስፈልጋል፣ ታጣቂዎች መሣሪያቸውን ጥለው ወደ ሠላማዊ ትግል መግባት አለባቸው፤ በሚል የተለያየ ጥሪዎች ቢያቀርቡም እስካሁን ሀገርን ወደ መረጋጋት የሚያመጣ ምላሽ አልተገኙም።

ከዚህ ይልቅ ግጭቶችን የሚያባብሱ እልኸኝነትና እንቢተኛነቶች እንደቀጠሉ ነው። ሀገሪቱን ወደ ከፋ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ጽንፈኛ ትርክቶች፤ በተዛቡ እና በውሸት መረጃዎች የሚጠናከሩ ሆሆታ የበዛባቸው የብዙኃን መገናኛ/የፌስ ቡክ፣ የዩቲውብ ..ወዘተ/

 ጩኸቶች ተበራክተዋል።

ዜጎች ብረት ይዞ ግጭት ውስጥ መግባትን፤ ከፍ ሲል ደግሞ ጦርነት ውስጥ መግባት እና የጦርነት ዜና መስማት ሰልችቶናል በማለት ላይ ናቸው። ሠላም እንዲሰፍን ያላቸውን የጸና ፍላጎት በተለያየ አጋጣሚዎችም እየገለጡ ነው፤ ይህ የዜጎች ፍላጎት የመንግሥት ፍላጎት በመሆኑ መንግሥት ለጥያቄያቸው ምላሽ እየሰጠ ነው ።

ብረት ካነሱ ቡድኖች ጋር ለመወያየት ያለውን ፍላጎት በየጊዜው ከመግለጥ ባለፈ በተጨባጭ በደቡብ አፍሪካ እና በታንዛኒያ ስለ ሠላም ድንበር ተሻግሮ ረጅም ርቀት ተጉዟል። ስለ ሠላም ያለውን ትኩረት የሠላም ሚኒስትር በማቋቋምም በተጨባጭ አሳይቷል ።

ሀገራቱ ዘላቂ ሠላም ማስፈን እንዲቻልም ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የዕርቀ ሠላም ኮሚሽንን፣ ብሔራዊ የተሐድሶ ኮሚሽንን፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽንን ማቋቋም እና ለሥራቸው የሚመቹ አዋጆችን ከማውጣት ጀምሮ የተለያዩ እገዛዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል።

ይህ በመንግሥት በኩል የሚታየው የሠላም ቁርጠኝነት ሊበረታታ በብዙ መልኩ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው። በሕዝብ በኩል የሚታየውን የሠላም ፍላጎት እና ተማፅኖ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ለማስቻል እንደ አንድ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ።

በተቃራኒው ለረባ ላረባው ጥያቄ በቡድን ተደራጅተው ብረት አንግበው ሕዝብንና ሀገርን በማሸበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ኃይሎች በጽንፈኛ እና ታሪካዊ ጠላቶቻችን አይዞህ ባይነት፤ የጀግና ጀግና ጨዋታ አሁንም የንጹሐንን ሕይወት በጠራራ ፀሐይ እያጠፉ፣ ንብረት እየዘረፉ እና እያወደሙ ግጭትን እና ጦርነትን ለጥፋት ተልዕኳቸው ዋነኛ አማራጭ አድርገው ቀጥለዋል።

በእርግጥ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ቡድን በሆነ ጉዳይ ጥያቄ ሊኖረው ይችላል። ጥያቄ መኖሩ በራሱ ችግር አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም። ችግሩ ጥያቄውን አግባብ ባለው መልኩ መቅረብና መልስ ማግኘቱ ላይ ነው። የተሻሉ አማራጮችን ወስኖ የመንቀሳቀስ ጉዳይ ላይ ነው ።

በየትኛውም ሁኔታ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት ለዚህ የሚሆን የአስተሳሰብ መሠረት መገንባት ለየትኛውም ማኅበረሰብ አዋጭ እንደሆነ ይታመናል። አብዛኛው የሰው ልጅ የታሪክ ትርክትም ይህንኑ እውነታ የሚያጸና ነው። ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገዎችንም ብሩህ ለማድረግም ይህ እውነት አልፋና ኦሜጋ ነው ።

ከዚህ ባለፈ በይዋጣልን፤ በአቅም እንፈታተን ላይ የተመሠረተ በአሸናፊ ተሸናፊ ትርክት የተገዛ የትኛውም አይነት አካሄድ ማንንም ተጠቃሚ አድርጎ አያውቅም። አክሳሪ እንጂ አትራፊ የሆነበት የታሪክ አጋጣሚ የለም። ለሀገርና ለሕዝብ ይዞት የሚመጣው ጦስ ለወሬ የሚመች አይደለም። ለዚህ ደግሞ ከኛ የተሻለ ምስክር ሊሆን የሚችል አይኖርም ።

የሕዝብ ጥያቄ በሠላም በሆነበት ሁኔታ፤ ሠላማዊ አማራጮችን መቀበል በምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ሊታጠር የሚገባ አይደለም። በተለይም የሰላም እጦት እንደ ሀገር ብዙ እያስከፈለን ባለበት ሀገራዊ ዓውድ፤ በየትኛውም መልኩ የተዘረጉ እጆችን ተቀብሎ ማስተናገድ ለሕዝብ ያለንን ከበሬታ መሳያ አንዱና ዋነኛው መንገድ ነው።

ከዚህ አንጻር ዛሬም ቀደም ባሉት ጊዜያት መንግሥት የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል የሕዝባችንን ሕይወት ለመለወጥ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ፍሬያማ እንዲሆኑ ላቀረባቸው የሠላም ጥሪዎች የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ምላሽ ሊሰጡ ይገባል።

ከሁሉም በላይ ለሀገርና ለሕዝብ ፍላጎቶች ለመገዛት፣ ቁጭ ብሎ መነጋገር፤ መደማመጥ፤ ከዚህም ባለፈ በልዩነት ውስጥ ሆኖ፤ ልዩነትን እንደ ውበት ተቀብሎ መኖር የሚያስችል የአዕምሮ ውቅር መፍጠርና በሱ እየተገዙና እየተገሩ መኖርን መለማመድ ይኖርብናል።

ሠላም!

ፌኔት ኤልያስ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You