ኢትዮ ቴሌኮም አራት አዳዲስ አገልግሎቶችን በይፋ አስጀመረ

አዲስ አበባ፡- ኢትዮ ቴሌኮም “voLTE” የተሰኘ የላቀ የድምፅና የምስል ጥራት ያለውን አገልግሎት ጨምሮ አራት አዳዲስ አገልግሎቶችን ትናንት በይፋ አስጀምሯል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት “voLTE” (Voice over LTE) የተባለው አገልግሎት ለደንበኞች ከተለመደው የድምፅ ጥሪ አገልግሎት እጅግ የላቀ የድምፅና ምስል ጥራት የሚያቀርብ ነው።

አገልግሎቱ ፈጣን የስልክ ጥሪ ለማድረግ፤ የአካባቢ የድምፅ ብክለት ለማስቀረት፤ ዳታ ሳይበራ የድምፅ ወይም የቪድዮ ጥሪዎችን በመቀየር የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

“voLTE” የቪዲዮ ጥሪ አገልግሎት ከነባሩ የድምፅ የአገልግሎት ታሪፍ ጋር ተመሳሳይ ሲሆን አገልግሎቱን መጠቀም ለመጀመር ተጨማሪ ክፍያ እንደማያስፈልግም ተገልጿል።

በአዲሱ አገልግሎት ደንበኞች በየትኛውም የውጭ ሀገራት በሚጓዙበት ጊዜ አስተማማኝ የሮሚንግ እና የኢንተርኮኔክት አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ። የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለመሆን ስማርት ስልክ እና የ4ጂ ወይም 5G ሲም ካርድ ያስፈልጋል ተብሏል።

ኢትዮ ቴሌኮም ትናንት በይፋ ያስጀመረው ሌላው አገልግሎት “ሪች ኮሚዩኒኬሽን” (RCS/RBS) ሲሆን ይህ አገልግሎት የግለሰብና የቢዝነስ ደንበኞች የመደበኛ የመልዕክት አገልግሎትን ተጠቅመው ከፊደል መልዕክት ባሻገር የፎቶ ወይም የቪዲዮ መረጃዎችን፣ ኢሞጂዎችን፣ የድምፅ ክሊፖችንና መልዕክቶችን፣ የአድራሻ (location Information) እና በርካታ አሁናዊ (real-time) መረጃዎችን የሞባይል ዳታን ወይም ዋይፋይን በመጠቀም ለማጋራት የሚችሉበት ነው።

አገልግሎቱ በአንድ ጊዜ ባልተገደበ የቃላት መጠን መልዕክት ለመላክ፣ የቡድን ውይይት /group chat/ ለማድረግ፣ የቪዲዮ ጥሪዎችን ለማድረግ፣ ሰነድን ለማጋራት እና ደህንነቱ የተጠበቀ መልዕክት ለመላክ ያስችላል ተብሏል።

ሦስተኛው አዲስ አገልግሎት የዘርፈ ብዙ ሚዲያ መልዕክት (MMS) ሲሆን የቪዲዮና የድምፅ ፋይሎችን ለመላክ እና ለመቀበል፣ በርካታ መልዕክቶችን ለተለያዩ ተቀባዮች በአንድ ጊዜ ለመላክ እንዲሁም ከ1600 ፊደላት በላይ የሆኑ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ/ለመላክ እና የተላከው መልዕክት መቼ እንደደረሰና እንደተነበበ ለማወቅ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

ኢትዮ ቴሌኮም ያስጀመረው አራተኛው አዲስ አገልግሎት የድምፅ መልዕክት (VMS) ሲሆን፣ አገልግሎቱ ደንበኞች ከኔትወርክ ሽፋን ውጭ ሲሆኑ፤ ስልካቸው በሌላ ጥሪ ሲያዝና ሲዘጋ ወይም በተለያየ ምክንያት የስልክ ጥሪ መቀበል በማይችሉበት ጊዜ ደዋዮች በድምፅ መልዕክት የተቀረጸ መልዕክት እንዲያስቀምጡላቸው በማድረግ፣ በተመቻቸው ጊዜ የተቀመጠላቸውን የድምፅ መልዕክት እንዲያዳምጡ የሚያስችል መሆኑ ተነግሯል።

ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት 73ነጥብ 4 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳሉት የገለጸ ሲሆን 34ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You