የግብርናውን የተለወጠ መንገድ የተከተለው የማዳበሪያ አቅርቦት

በሀገሪቱ የግብርና ምርትና ምርታማነት እያደገ መጥቷል፤ ለእዚህም በዋና ዋና ምክንያትነት ሊጠቀሱ ከሚችሉት መካከል መንግሥት ለአርሶ አደሩ ማደበሪያ በድጎማ እያቀረበ ያለበት ሁኔታ አንዱ ነው። ይህንንም መንግሥት ከሶስት ዓመት በፊት 15 ቢሊዮን ብር፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ 21 ቢሊዮን ብር ለማዳበሪያ መድቦ ከሠራበት ሁኔታ መረዳት ይቻላል።

ዘንድሮም ከእስከ አሁኑም የሚልቅ ገንዘብ ለማዳበሪያ ተመድቦ ግዥ እየተፈጸመ ነው። የዘንድሮው የማዳበሪያ ወጪ 930 ሚሊዮን ዶላር መጠየቁን የግብር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም የ 14 ነጥብ 79 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ተፈጽሟል። አስቀድሞ የተገዛው ማዳበሪያም በከፍተኛ ርብርብ ሀገር ውስጥ መግባት ከጀመረ ቆይቷል።

ማዳበሪያ መግዛት አንዱ ከፍተኛ ሥራን የሚጠይቅ ተግባር ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ማዳበሪያውን ወደ መሀል ሀገር ከዚያም አርሶ አደሩ ዘንድ በፍጥነት ማድረስ ነው። የቱንም ያህል ገንዘብ ለማዳበሪያ ቢመደብ ማዳበሪያው በወቅቱ ከወቅቱም ቀደም ብሎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አርሶ አደሩ እጅ መድረስ ይኖርበታል።

ማዳበሪያ ከወደብ በማንሳትና ወደ ክልል በማሰራጨት በኩል ቀደም ሲልም ጥሩ ተሞክሮ አለ። እንዳለፉት ዘመናት ሁሉ ማዳበሪያ ወደብ በደረሰ ቁጥር ከባድ መኪኖችና የባቡር አገልገሎት ማዳበሪያ ማጓጓዝን የሥራቸው ሁሉ ቅድሚያ እንዲያደርጉት ሆኖ የማጓጓዙ ሥራ ይካሄዳል፤ ዘንድሮም ይኸው በከፍተኛ ርብርብ እየተፈጸመ ነው።

በዚህ ሁሉ ድካም ሀገር ውስጥ የገባው ማዳበሪያ አርሶ አደሩ እጅ እንዲገባ ከማድረግ አኳያ ባለፉት ዓመታት ክፍተቶች ተስተውለዋል፤ ይህንንም በአንዳንድ ክልሎች አርሶ አደሮች ሲያነሱ የነበረው ቅሬታም ይህንኑ ይጠቁማል፤ የባለፈው ዓመት ቅሬታ ግን ሞቅ ያለ ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ የላቀ ገንዘብ ለማዳበሪያ መድቦ እየሠራ ባለበት ሁኔታ ነው።

ለእዚህ ቅሬታ ከተለያዩ የመንግሥት አካላት ይሰጡ የነበሩ ምላሾችም የአርሶ አደሩን ቅሬታ ያጤኑ ነበሩ ማለት ያስቸግራል። ማዳበሪያው ማህበራት መጋዘን ውስጥ እንዳለ በመጠቆም (የሌለውን ማዳበሪያ) መጋዘን ውስጥ ያስቀመጡ አካላት በአስቸኳይ ለአርሶ አደሩ እንዲያደርሱ ማሳሰቢያ የሚሰጡ አካላትም ነበሩ። ማዳበሪያ ላይ ለተነሳው ቅሬታ አንዱ ችግር ግዥ ሂደት ላይ ከተፈጠረ ችግር የመነጨ ቢሆንም፣ በወቅቱ ግን አልተነገረም።

እንደሚታወቀው ያለፈው ዓመት የማዳበሪያ ግዥ የዘገየበት አንዱ ምክንያት በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት ነው። እነዚህ በግብርና ግብዓቶችና ምርቶች አቅርቦት የሚታወቁ ሁለት ሀገሮች ጦርነት ውስጥ ሲገቡ ኢትዮጵያ ብቻ አልነበረችም የታወከችው ። ከእነዚህ ሀገሮች ስንዴ ፣ ማዳበሪያና የመሳሰሉትን ግብዓቶችና ምርቶች የሚገዙ የዓለም ሀገሮችም ናቸው። ኢትዮጵያ በወቅቱ ኤልሲ ከመክፈትና ከመሳሰሉት ጋር ተያይዘው የተፈጠሩ ችግሮችም ነበሩባት፤ በዚህ ላይ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፤ በወቅቱ መንግሥት ሰፊ መግለጫዎችን ሰጥቷልና።

ብዙ ፈተና አልፎ ሀገር ውስጥ ገብቶ ክልሎች እጅ የደረሰው ማደበሪያ ለሕገወጦች ሲሳይ የሆነበት ሁኔታ ታይቷል። በክልሎች ማዳበሪያ በሕገወጥ መንገድ ይዘዋወር ነበር፤ አርሶ አደሩ የማዳበሪያ ያለህ ሲል በነበረበት ወቅት እነዚህ ሕገወጦች በድጎማ ለአርሶ አደሩ መቅረብ ያለበትን ማዳበሪያ በውድ ዋጋ ሲቸበችቡት ነበር።

በአንዳንድ ክልሎች አርሶ አደሩ የማዳበሪያ ያለህ እያለ ሲጮህ ማደበሪያ በአደባባይ በሕገወጦች መቸብቸቡ ተጠቁሟል፤ በዚህ ሕገወጥ ተግባር ውስጥ ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣናትም /አመራሮች/ ተሳትፈውበታል።

በሲዳማ ክልል በርካታ ባለሥልጣናት በዚህ ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በማደበሪያ ላይ በዚህ ልክ ሕገወጥነት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፤ ትልቅ ቀውስ ነበር።

ያለፈው ዓመት የማዳበሪያ ጉዳይ ብዙ ያነጋገረበት ወቅት ነበር። የግብርናው ሥራ ቆሞ በማይጠብቅበት በዚያ የዘር ወቅት የማዳበሪያው አቅርቦት ዘገይቷል፤ ለቀበኞች ተዳርጓል። ከዚህ ውጪም የመኸር ወቅት የዘር ሥራ እየተጠናቀቀ ባለበት ነሀሴ ወር መጨረሻ አካባቢ ማዳበሪያ ወደ ሀገሪቱ ቢገባ ብዙም የሚፈይደው የለም። ምን አልባት ዘግይተው ለሚዘሩ ሰብሎች፣ ለመስኖ እርሻ ሊጠቀም ይችላል።

መንግሥት ዘንድሮ ያ ችግር እንዳይመለስ የሚያስችል ርምጃ ወስዷል። በማዳበሪያ ግዥ ላይ በርካታ ማሻሻያዎችን አድርጎም ማዳበሪያ ለማቅረብ እየሠራ ነው። ከችግር መማር ይሏል ይሄ ነው። መረጃዎች እንዳመለከቱት፤ ዓምና የመጀመሪያዋ ማዳበሪያ የጫነች መርከብ ጅቡቲ የደረሰችው ታህሳሰ 18 ቀን 2015 ነበር፤ ዘንድሮ የመጀመሪያውን ማዳበሪያ የጫነችው መርከብ ጅቡቲ ወደብ የደረሰችው በጥቅምት ነው። ከዚያም በመቀባበል ወደ መሀል ሀገር መጋዘን እንዲደርስ እየተደረገ ያለበት ርብርብም ሌላው ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው።

እንዲገባ የታቀደው ማዳበሪያ መጠንም ለግዥው የተመደበው ሀብትም ከፍተኛ መሆኑ ሲታይ ባለፈው ዓመት የታየው ችግር እንዳይደገም የተወሰደ ርምጃ ብቻ አይደለም ብሎ መውሰድ ይቻላል። በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ትልቅ እምርታ የታየበት ዘመን ላይ መደረሱን እንዲሁም የግብርናው የምርት ወቅት መጨመርንም ያመለክታል።

ማዳበሪያውን በወቅቱ አርሶ አደሩ ዘንድ ማድረስ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩ ነው፤ ይህ መሆኑ ባለፈው የመኸር ወቅት በማዳበሪያ አቅርቦት መጓተት ሳቢያ በአርሶ አደሩ የቀረበው ጥያቄ ዘንድሮ እንዳይደገም ያስችላል። የማዳበሪያ ቀበኞች ቀና ቀና የሚሉት እጥረት ሲፈጠር እንደመሆኑ እጥረቱ መፍትሄ ስለተቀመጠለት እርማቸውን ያወጣሉ ብሎ መውሰድ ይቻላል። ለነገሩ አመለኞች እጥረት ሲፈጠር ብቻ አይደለም ሕገወጥ ድርጊቱን የሚፈጽሙት፤ ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠርም ነው። ይህን ሕገወጥነት ለመቆጣጠር ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል።

የዘንድሮውን የማዳበሪያ አቅርቦት ከዚህ ሁሉ በላይም ሊነገርለት ባይ ነኝ። የማዳበሪያ አቅርቦቱ ሀገሪቱ የተያያዘችውን የግብርና ሥራ ስፋት ታሳቢ ያደረገ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። ከመኸርና በልግ ወቅት በተጨማሪ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እየተካሄደ ነው። ማዳበሪያው ሀገር ውስጥ የገባበት ወቅትም፣ መጠኑም ይህንን ሁሉ ታሳቢ ነው ማለት ይቻላል።

በበጀት አመቱ ከ800 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብርና ምርት ለማምረት ታቅዷል። ይህን ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ለማምረት እንደማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶች በስፋትና በፍጥነት መቅረብ ይኖርባቸዋል። ዘንድሮ ለማቅረብ የታቀደውን ማዳበሪያም ሆነ የቀረበበት ፍጥነት የታሰበውን እቅድ ለማሳካት ትልቅ ሚና ይኖረዋል።

እንደሚታወቀው ፤አርሶ አደሩ በመኸር እርሻው ሙሉ አቅሙን አሟጦ እንዲጠቀም እየተደረገ ይገኛል። በምንም አይነት መልኩ ማሳ ጦም እንዳያድር እየተደረገ ነው፤ ርግረጋማ ሥፍራዎች ለግብርና ሥራ እየዋሉ ናቸው፤ የበቆሎ ሰብል በእሸቱ በእጅጉ እንደሚፈለግ ይታወቃል፤ ሰብሉን በእሸቱ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግና ማሳውን በሌላ ሰብል በመሸፈን ተጨማሪ ምርት እንዲሰጥ እየተሠራ ነው።

በዓመት አንዴ ከማምረት እየተወጣ ነው። ሁለትና ሶስቴ ማምረት ውስጥ ተገብቷል። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሰፋፊ ሥራዎች እየተሠሩ ያለበት ሁኔታም ይህን ያመለክታል። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በተጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት ሶስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ፣ በቀጣዩ ዓመት 25 ሚሊዮን ፣ ባለፈው ዓመት ደግሞ 47 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ተገኝቷል።

በልማቱ የሚገኘው ስንዴ በየዓመቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ዘንድሮ በዚህ የስንዴ ልማት 117 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ ለእዚህም ሶስት ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በዘር እንደሚሸፈን ይጠበቃል። ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚገኘው ምርትም በዘር የሚሸፈነው ማሳ ብዛትም በየአመቱ እያደገ መጥቶ ነው እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው።

ይህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ከመኸር በተረፈ ማዳበሪያ የሚሠራ አይነት አይደለም፤ ልማቱ እየሰፋ እንደመምጣቱ ራሱን የቻለ የማዳበሪያ አቅርቦት ይፈልጋል። የማቅረቢያው መንገድም ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆን ይኖርበታል። የዘንድሮ ማዳበሪያ አቅርቦት ብዛትም የመስኖ ልማቱ በሚጀመርበት ወቅት መድረሱ ይህን ልማት በእጅጉ ታሳቢ ያደረገ ነው ብሎ መናገር ይቻላል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱ በየጊዜው እየጨመረ ነው፤ በመኸር ወቅት ለማግኘት የሚታቀደው ምርትም እንዲሁ እየጨመረ ይመጣል፤ በዚህ ላይ የበልግ ወቅት አለ፤ የማዳበሪያ አቅርቦቱም ይህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ዘንድሮ እንደተሠራው ሁሉ በቀጣይም በትኩረት መሥራት ይገባል።

ዘካርያስ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 5 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You