ጀግናና ጀግንነትን አብዝቶ ይወዳል። የሚሊቴሪ ልብስ የለበሰ ወታደር ሲያጋጥመው እጅ ነስቶ መሄድን ይመርጣል። የሚኒቴሪ ልብስ ልክ እንደባንዲራ መከበር አለበት ብሎ ያምናል። አባቱ አቶ መታፈርያ ከኃይለሥላሤ መንግሥት ጀምሮ ሀገራቸውን በውትድርና ያገለገሉ ስመ ጥር ጀግና በመሆናቸውም ሁልጊዜ የአባቱን ጀብዱ መተረክ አይሰለቸውም። በዚሁ ባህሪውም ከጓደኞቹ ከገብረየስ ገብረማርያምና ከተሰማ መንግሥቴ ጋር ይጨቃጨቃል።
ለውትድርና የተለየ ፍቅር ያለው ዘውዴ መታፈርያ እንደምኞቱ ወታደር አለመሆኑ ያንገበግበዋል። ይህንን ቁጭቱን ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች መግለጽ ይወዳል። በተለይም ደግሞ የቀድሞ አባቶቻችንን ጀግንነት ውሎ ልቡን በሃሴት ይሞላዋል።
ዝነኛ ከሆኑት የጥላሁን ገሰሰ ዜማዎች ውስጥም ፤-
“የጀግኖች ደም ጥሪ ቃሉ ቀሰቀሰኝ፤ ለታሪክ አደራ ለድል ታጠቅ አለኝ”
የሚለውን ዘፈን አብዝቶ ይወደዋል።
‹‹ኢትዮጵያን በኮርያ፣ በኮንጎ ፣ በሩዋንዳ፣ ቡርንዲና ላይቤሪ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሱዳንና በሶማሊያ ጠላትን እየመከቱ ፤በፈንጂ ላይ እየተረማመዱና አንገት ለአንገት እየተናነቁ ጀብዱ የሚፈጽሙ ጀግኖች ናቸው። በየዘመኑ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የተዳፈሩ ሁሉ እድል አልቀናቸውም፤ የተሳካ ታሪክም የላቸውም። በጀግኖች ኢትዮጵያውያን ድል እየተመቱ ተመልሰዋልና። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች በፍጹም የሀገር ፍቅር፤ በፍጹም ታማኝነት በደማቸው የሀገርን ሉዓላዊነት አጽንተዋል። የአምስት ዓመታቱ የእምቢተኝነት ተጋድሎ ኢትዮጵያውያንን በኃይል አንበርክኮ መግዛት እንደማይቻል ከዓድዋ ቀጥሎ፤ ለዓለም ትምህርትን ሰጥቶ ያለፈ ነው።
ኢትዮጵያውያን አንድነት መለያቸው፤ ማሸነፍ ታሪካቸው ነው። ኢትዮጵያውያን ሲተባበሩ የማይደረምሱት ተራራ፣ የማያሸንፉት ጠላት ፣ የማይወጡት አቀበት አይኖርም። ኢትዮጵያ ነጻነቷን አስከብራና የጥቁር ሕዝቦች መከታ ሆና የዘለቀችው በሕዝቦቿ ትብብርና አንድነት ነው።
ትናንት ኢትዮጵያውያን ዓድዋ ላይ ቅኝ ገዢዎችን አሳፍረው መልስዋል። በወቅቱ በመሪው አጼ ምኒልክና በተለያዩ ሀገረ ገዢዎች መካከል አለመግባባትና ቅራኔ ቢኖርም ሁሉም ነገር ከሀገር በታች ነውና ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው ወራሪውን የጣሊያን ጦር በአንድነት ድል ነስተዋል። በዚህም ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋል፤ ከዛም አልፎ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆነዋል። አንድት ኃይልም እንደሆነ ለቀሪው ዓለም የማይፋቅ ታሪክ ጽፈዋል።
በአጼ ምኒልክና በተለያዩ ገዚዎች መካከል ያለውን ልዩነት ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለመውረር የተነሳው የፋሺሽት ኃይል በኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ ተደቁሶ ወደ መጣበት ከመመለሱም ባሻገር ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ልዩነት ቢኖርም ኢትዮጵያን ለማዋረድና ለመበታተን ለሚመጣ ኃይል ክፍተት እንደማይሰጡ ትምህርት ሆኗል።
በተመሳሳይ መልኩም ተስፋፊው የሶማሌ ወራሪ ኃይልም በ1969 አካባቢ ኢትዮጵያ ተዳክማለች በሚል ስሁት ዕሳቤ እስከ ድሬዳዋ ድረስ ዘልቆ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈጽሟል። በወቅቱ ገና በሁለት እግሩ ያልቆመውን የደርግ መንግሥት በቀላሉ አሸንፈዋለሁ በሚል ቀቢጸ ተስፋና የኢትዮጵያውያንም አንድነት ላልቷል በሚል ምኞት በዚያድ ባሬ የሚመራው የሶማሌ መንግሥት ታላቋን ሶማሊያ እመሰርታለሁ በሚል ቅዠት ኢትዮጵያን ለመውረር ቢነሳም ሶስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ በመትመም ወራሪውን ኃይል አሳፍረው መልሰውታል።
ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ በየጊዜው የሚነሱ ወራሪዎችን ድል ነስተው ከማባረራቸውም ባሻገር ሀገራቸውን በሚያሻግሩ ልማቶችም ላይ በጋራ የመረባረብ ታሪክ አላቸው። የኢትዮጵያውያን የዘመናት ትልም የሆነው የህዳሴ ግድብ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። በቅርብ ጎረቤቶቻችን ሴራ ለዘመናት በከንቱ ሲፈስ የቆየውን የዓባይ ግድብ በመገደብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ክንዳቸው ዛሬ ለብርሃን አብቅተውታል። በተባበረ ክንድም ለዘመናት የተበተቡንን ገመዶች በመበጣጠስ ‹‹የአይቻልምን›› እሳቤን ወደ ‹‹ይቻላል›› መንፈስ ቀይረውታል።
ኢትዮጵያ ከውጭ ወራሪዎች ባሻገር የውስጥ ባንዳዎችም በየጊዜው እየተነሱ ሀገሪቱን ለማዳከምና ለማፈራረስ ቢሞክሩም በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ እየተደቆሱ ምኞታቸው ጉም ሆኖ ቀርቷል።
ዛሬም ጀግንነታችን ቀጥሏል። አይበገሬነታችን ዛሬም ህያው ነው። በዚህ ልንኮራ ይገባል ብሎ›› ወደ ጓደኞቹ ተመለከተ።
የዘውዴን ሁኔታ ሲመለከት የቆየው ተሰማ መንግሥቴ በዘውዴ መታፈርያ ሃሳብ ቢስማማም አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንደሚያሳስበው ገለጸ።
‹‹የምትለውን እቀበላለሁ። ከጀግና ሕዝብ የወጣ ጀግና ሠራዊት አለን። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት መገለጫ ጥግ ነው። ሠራዊቱ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣ በመሆኑ እራሱን ለሕዝብና ለሀገር አሳልፎ ይሰጣል፤ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትን ለማስከበርና የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ መስዋዕትነትን ይከፍላል። በዱር በገደሉ ይዋደቃል። ደሙን ያፈሳል፤ አጥንቱን ይከሰክሳል።
ኢትዮጵያውያን ከጥንት እስከ ዛሬ በደምና አጥንታቸው ታሪክ ሲሰሩ፤ ሀገር ሲያቆሙና ኢትዮጵያን ሲታደጉ ኖረዋል። ሀገሬን አላስደፍርም፤ ማንነቴን አላዋርድም፤ ባንዲራዩን አላስረግጥም በማለት በዱር በገደሉ ደማቸውን ሲያፈሱ፤ አጥንታቸውን ሲከሰክሱ ኖረዋል። ዛሬም የዚሁ ውርስ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በደምና አጥንቱ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና አንድነት በማስከበር ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጀግንነቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማማበት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር ጀግና ሠራዊት ነው። ሠራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለዓላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጨለማን ማሻገር የሚችል ልበ ሙሉ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰላም ጊዜ የልማት አርበኛ በጦርነት ወቅት ጀግና ሆኖ በስኬት በመራመድ ላይ ይገኛል።
የአንድ መከላከያ ኃይል እምቅ አቅምና ጥንካሬ፤ የመለኪያ መስፈርቶቹ፤ የሠራዊቱ ብቃትና የውጊያ ዝግጁነት የታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሣሪያና በታጠቀውም መሣሪያ በየትኛውም የመሬት ገጽ ላይ ለመጠቀም ያለው ችሎታና ብቃት ሀገርን ለመከላከል በውስጥ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ተሰልፎ ያስመዘገበው ድልና ስኬት ከዚህም አልፎድንበር ዘለል ተልእኮን በመወጣት ረገድ ያሳየው ወይንም የሚያሳየው ብቃት የአቅሙን ልኬት ሊያሳዩ የሚችሉ ናቸው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ዳር ድንበር ከማስከበሩም ባሻገር በጎረቤት ሀገራት ጭምር ተልዕኮ በመውሰድ ሰላምን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ ቀደም ሲልም በላይቤሪያ፣ በሩዋንዳና ቡሩንዲ ሀገራት ተሰማርቶ ሰላም ማስከበር የቻለ የህዝብ ልጅ ነው። ይህም ብቃት ሊገኝ የቻለው ከሠራዊቱ ተፈጥሯዊ ባህሪ ባሻገር በየጊዜው እየተደረገለት በመጣው አቅም ግንባታ ሥራዎች አማካኝነት ነው።
ሆኖም በየስርቻው ሠራዊቱን ሲያጥላሉ የሚውሉና ሠራዊቱ ፈርሶ ሀገርም ጭምር እንድትፈርስ የሚታትሩ የጥፋት መልዕክተኞች እንዳሉም ግን መረዳት ይገባል›› ብሎ ሃሳቡን ከማሳረጉ ገብረየስ ገ/ማርያም ሃሳቡን ቀበል አደረገና በውስጡ አምቆት የነበረውን ተነፈሰ።
‹‹የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን በልማት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ለሀገሩ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገነቡ ድድዮችና መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ የግብርና ምርቶች በመሰብሰብ፣ የአርሶ አደሩን ምርቶች ከተባይና ከተፈጥሮ አደጋ በመጠበቅ የዜግነት ግዴታውን የሚወጣ የሕዝብ ልጅ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም የተፈናቀሉና ከቀያቸው የተሰደዱ ወገኖችን በመንከባከብና ካለው ላይ ለዕለት ጉርስ የሚሆን ገንዘብ በማዋጣትም ሕዝባዊነቱን የሚያሳይ ሠራዊት ነው።
ሆኖም ይህ ጀግንነቱና ሕዝባዊነቱ የማይዋጥላቸው ወገኖች ሌት ተቀን ሲያብጠለጥሉት የሚውሉ ከሃዲዎችም አሉ። እነዚህ ከሃዲዎች ከውጭ በሚላክላቸው ፍርፋሪ በመታለል ሀገራቸውን ሲሸጡ ይታያሉ።
የተዳከመች ኢትዮጵያን መፍጠር የሚፈልጉ አካላት በሠራዊቱ ላይ የሚከፍቱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ሠራዊቱን ከዓላማው ባያዘናጉትም የእነዚህ ሰዎች እኩይ ተግባር ግን ሊወገዝ ይገባል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ቃለ መጠይቅም ሠራዊቱ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ የከፈቱት እነዚህ ሰዎች ምንም ጥያቄ የሌላቸው ቅጥረኛ ባንዳዎች ናቸው። ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሠራዊት በመሆኑ ምክንያት ሀገሪቷ የመከላከል አቅሟ እንዲዳከምና እንዲሸረሸር በማድረግ ለጥቃት ተጋላጭ የሆነች ሀገር እንድትፈጠር የሚሰሩ ኃይሎች ናቸው። ›› ብሎ ሰሞነኛ አጀንዳ አከለበት።
በውይይቱ የተመሰጠው ዘውዴ መታፈርያ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ሃሳብ የሚያጠናክር ሃሳብ አነሳ።
‹‹ሠራዊቱ ተበትኗል፣ በጀነራል ተጣልቷል፣ ጀነራል እገሌ ተቀቷል፣ የቁም እስረኛ ሆኗል የሚሉና ሌለች ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚለቁ አካላት ይገርሙኛል። መከላከያን ስለማያውቁት እንጂ ቢያውቁት ኖሮ ይህን መሰል መረጃ ባልለቀቁ። መከላከያ በጠንካራ አለት ላይ የተገነባ ነው፤ በወሬ የሚናድ ሥብዕና የለውም። እንኳን አሁንና ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠላትን የሚያርበደብድ ትንታግ ኃይል ነው።
ሠራዊቱ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጠላትን በህብረት የሚያጠቃ እንደ አንበሳ ቦታውን የማያስደፍር ጀግና ነው። ሠራዊቱ ድል የሚፈጥር፣ ሞትን የሚያሸንፍ፣ ለድንገተኛ ክስተት የማይበገር፣ ፍላጎቱን ለዓላማው የሚያስገዛ፣ የነፃነትን ዋጋ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ ጨለማን ማሻገር የሚችል ሞራልና ጉልበት ያለው፣ በልማትና በጥፋት መካከል የማይፈርስ ጠንካራ ግንብ ነው።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አፈጣጠር ልዩ የሚያደርገው ከሕዝቦች አብራክ የወጣ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ከሕዝብ ጎን በመቆምና በመታገል የሕዝብ ትግል ግንባር ቀደም ተዋናይ ከሆነው ትውልድ ጭምር የተፈጠረ መሆኑ ነው። ይህ ተፈጥሮው በሀገሩ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ በተሠማራባቸው ሀገሮችም የተረጋገጠ ነው። ሕዝባዊነቱ ከሌሎች ሀገሮች ሠራዊቶች በመሠረቱ የተለየ ሆኖ እንዲታይና የሕዝብ ፍቅርና አለኝታነትን እንዲጎናፀፍ አስችሎታል። የሠራዊታችን መሠረታዊ እሴት በጠንካራ ዲሲፒሊን ከራስ በላይ የሀገርና የሕዝብ ጥቅም ማስከበር ላይ የተመሠረተና የሕገመንግሥቱ የመጨረሻ ምሽግ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባ ነው።
ሆኖም ተሰማ እንደተናገረው ይህንን ጀግና በማጥላላት እና በማሳነስ ሀገርን ለማፍረስ ቆርጠው ተነሱ ዘመናችን ጉዶች እዚህ እዛም ብቅ ብቅ ብለዋል። መከላከያን በራሳቸው መንደር ውስጥ እየወሸቁ አንሰው ሊያሳንሱት ሲሞክሩ አይተናል፤ ታዝበናል።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሠራዊታችንንም በማጠልሸትም ኢትዮጵያን ለማሳነስም በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ታይተዋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በወሬ የማይፈታ እና ለአፍታም ቢሆን በወሬና እና አሉባልታ የማይበገር መሆኑን ማመን ይገባል። ሰላምን በማወክ ከግጭት ማትረፍ የሚፈልጉ አካላትም አዋጪው ሰላምና ፣ ሰላም ብቻ መሆኑን መረዳት ይገባቸዋል። ለሁላችንም የሚያወጣው ይህ ነው›› በማለት ንግግሩን ቋጨ።
ሶስቱ ጓደኛሞች ለመጀመርያ ጊዜ በአንድነት የተስማሙበት ሃሳብ በመሆኑ ሶስቱም መለኪያቸውን አንስተው ደስታቸውን ገለጹ።
አሊ ሴሮ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም