በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሰፊ እድሎችን ለመጠቀም

ኢትዮጵያ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በገጠር፤ 20 ከመቶ የሚሆነው ደግሞ በከተማ እንደሚኖር መረጃዎች ያመለክታሉ። በከዚህ የተነሳም የከተሜውም የምግብ እህል አቅርቦት በአብዛኛው በገጠር በሚኖረውና በግብርና በሚተዳደረው ሕዝብ ቀንበር ላይ የወደቀ ነው።

ይህ እውነታ በአሜሪካ የተለየ መልክ ይይዛል። በሀገሪቱ 94 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የሚኖረው በከተሞች ነው፤ ስድስት በመቶ ብቻ ነው ገጠር ላይ ኑሮውን የሚያደርገው። እነዚህ ስድስት በመቶ አርሶአደሮች ግን በከተማ የሚኖረውን 94 በመቶ ሕዝብ አብልተው፣ አጥግበውና ለርዳታ የሚሆን የምግብ ምርት ጭምር አምርተው ያድራሉ። እንዴት ተቻላቸው የሚለው ትልቁ ጥያቄ ነው።

አንድ ሀገር ረሃብን፣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማሸነፍ ሲነሳ የግድ ግብርናውን ማዘመንና በተሻለ ፖሊሲ እንዲመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ጎን ለጎን ደግሞ ተፈጥሮን መንከባከብና ለዚያ የሚመጥን ሥራ መሥራት ይገባል። ከተሞች ሲስፋፉ፣ ኢንዱስትሪዎች ይሰፋሉና ይህንን የሚመጥን እንቅስቃሴ ማድረግም ተገቢ ነው።

አርሶ አደሩ ከከተማው የተሻለና ከተማውን የሚያስተዳደር አካል እንደሆነ እንዲሰማውም በተለያየ መልኩ መደገፍ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ይመከራል። ዘመኑን ተረድቶ በግብርናው ላይ የተሻለ የአመራረት ዘዴን እንዲከተልም ማበረታታት ተገቢ ነው ።

ከዚህ ውስጥ አርሶ አደሩን ለመስኖ ግብርና እራሱን እንዲያዘጋጅ፤ ተጠቃሚ እንዲሆን ዘርፉን ከማስተዋወቅ ጀምሮ አስፈላጊውን እገዛ ማድረግ አንዱ ነው። ይህ አካሄድ በተለይም እንደ ሀገር በምግብ እህል እራሳችንን ለመቻል ለጀመርነው ጥረት ትልቅ አቅም አንደሚሆን ይታመናል ።

ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ለመስኖ ግብርና /ለበጋ ስንዴ ልማት/ በተሰጠው ልዩ ትኩረት ፈጣን የሚባል ስኬት እንደ ሀገር እየተመዘገበ ስለመሆኑ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። አርሶአደሩ ገና የዝናብ ወቅትን ከመጠበቅ እየወጣ በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያመርትበት ሁኔታ እየተስተዋለ ነው።

ከዚህ ቀደም ለእርሱ ልዩ የሕይወት ምዕራፉ መጀመሪያም መጨረሻውም የመኸር ወቅት ብቻ ነበር። ዛሬ ግን በተፈጠረለት እድል ለማምረት መጨረሻ የለውም። ከአንዴም ሁለቴ እና ከዛም በላይ የሚያመርትበት እድል እየተፈጠረለት ነው። እንደ ሀገር ተፈጥሮ የሰጠችንን መልካም እድል እየተጠቀመ ግብርና የኢትዮጵያ ትልቅ አቅም የሚሆንበትን ተጨባጭ ውጤት እያሳየም ይገኛል።

ሀገሪቱ ሰማኒያ ሚሊዮን ሔክታር የሚጠጋ የሚታረስ መሬት እያላት፤ አሥራ አምስት ሚሊዮን ሔክታር ብቻ፤ የዝናብ ወቅትን በመጠቀም እያረሰች ይህንን ጥልቅ ሀብት ለማልማት የሄደችበት መንገድ ለብዙ ችግር ዳርጓት ቆይቷል። በምግብ እህል እራሷን ሳትችልም ዘመናትን ለማስቆጠር የተገደደችበት ሁኔታ የአደባባይ ምስጢር ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ኅዳር 14 ቀን 2016 ዓ.ም በወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የዜና ዓምድ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር መለስ መኮንን ያሉትን እናንሳ። “ኢትዮጵያ ለስንዴ ምርት በጣም አመቺ በመሆኗ በዓመት በሦስት ዙር የስንዴ ልማት በማካሄድ ውጤታማ ለማድረግ እየሠራች ትገኛለች”።

“በዘንድሮ ዓመት የስንዴን ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት እየተሠራ ነው፤ በያዝነው ዓመት በበጋ በመስኖ ልማት ብቻ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል በመሸፈን 147 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል። እስካሁን ድረስም ቀድመው መዘራት በሚገባቸው አካባቢዎች ርብርብ በማድረግ ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ ዘር መሸፈን ተችሏል። ምርት እየተሰበሰበ በሚገኙባቸው አካባቢዎችም ወዲያው ወደ እርሻ ሥራ እንዲገቡ እየተደረገም ነው። ”

ሀገሪቱ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት በዓመት አንድ ቢሊዮን ያላነሰ የአሜሪካ ዶላር እንደምታወጣ ያወሱት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ባለፉት አራት ዓመታት ስንዴ ልማቱ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ይህንን ወጪ ለማስቀረት ተችሏል። ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን የማልማት አቅም ከማሳየቱም በላይ ራስን በምግብ እንዴት መቻል እንደሚቻል ልምድ መቅሰም ያስቻለ ነው።

አሁን ባለው ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ላይ ጥሩ አቋም ተይዟል። ባለፉት አራት ዓመታት በስፋት በመሠራቱም ስኬታማ የስንዴ ልማት ሥራው እንደ ሀገር እየታየ መጥቷል። ስኬታማ እንዲሆን ያስቻሉት ነገሮች ደግሞ በርካታ ናቸው። አንዱና ዋነኛው ግን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ካሉ ሀገሮች በተለየ መልኩ ሁሉም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት፣ የተስማማ አየር፣ በቂ የውሃ ሀብት ያላት ሀገር መሆኗ ነው።

አሁን የተጀመረውን የመስኖ ልማት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ብዙ አማራጮችን ቢኖሩም፤ በቅድሚያ ግን ተጀምረው ለመጠናቀቅ ዓመታት እየፈጀባቸው የሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ማስገባት ተገቢ ነው። ከዚህ አንጻር መንግሥት በዚህ በጀት ዓመት ለመስኖ ፕሮጀክቶች 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መድቦ እየተንቀሳቀስ መሆኑ ይበል የሚባል ነው ።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በ2016 ዓ.ም 28 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው እየተካሄደ ይገኛል። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 13ቱን በከፊል ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህ ደግሞ በከፊል ሲጠናቀቅ ሁለት ሺህ 450 ሄክታር መሬት ወደ ልማት መግባት የሚችልበት ሁኔታን ይፈጥራል።

ሀገራችን በተፈጥሮ የበለጸገች ሀገር መሆኗ በግብርናው ዘርፍ ስኬታማ ለመሆን ሰፊ እድሎች አሏት። እነዚህም እድሎች በአግባቡ ለመጠቀም አሁን ላይ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው ከቀጠሉ ብዙ ነገሮቻችን ታሪክ መሆናቸው የማይቀር ነው። ከጠባቂነት ወጥታ ለሌሎች የምትተርፍ መሆኗዋ ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም ! ። ሰላም!!

መንግሥት

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You