“ሙስና ሀገርን እየበላ ያለ ነቀዝ…!”

ሙስና ሀገርን የሚበላ ነቀዝ ነው። የሀገርን አንጡራ ሀብት እየቦረቦረ ጥሪቷን ባዶ ለማስቀረት ሌት ተቀን የሚማስን ተባይ ነው። ዋልጌ ባለሥልጣናት፣ በፍቅረ ነዋይ የታወሩ ደላሎች እና ባለሀብቶች አንድ ላይ ሲገጥሙ፤ ከነዚህ የሌብነት ፊታውራሪዎች ጀርባ ብዛት ያላቸው ዜጎች መሰለፍ ሲጀምሩ ሙስና የተባለው ነቀዝ ሀገርን እንደ ወረርሽኝ ያጠቃታል።

ሙስና በየትኛው ቦታና በየትኛውም ዘመን ሊኖር ይችላል። ነገር ግን የሀገርን ልማት አጥንቱ ድረስ እስከ መጋጥ ከደረሰ ሙስና አንድ አደገኛ ወረርሽኝ ሆኗል ማለት ነው። ሙስና ሀገርን ሊያፈርስ የሚችል የደኅንነት ሥጋት መሆኑን ያስመሰከሩ ሀገሮችን በዘመናችን አይተናል።

የአደንዛዥ ዕጽ፣ የኮንትሮባንድ፣ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ንግድ፣ የንግድ ማጭበርበር ሙስናን ለዓላማቸው ማስፈጸሚያነት ይፈልጉታል። በዓለማችን የተጀመሩ ጦርነቶች እንዳይጠናቀቁ፤ ግጭቶች እንዳይበርዱ፣ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲጋጩ፣ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች አንዱ ሙሰኞች ከዚህ አይነት ቀውሶች ስለሚያተርፉ ነው።

ሙስና ዛሬ የሀገራችን የደኅንነት ሥጋት ሆኗል። ወደ ብልጽግና የምናደርገውን ጉዞ እጅ ተወርች አስሮ ለመያዝ ከጠላቶቻችን እኩል ሙሰኛው እየታገለን ነው። የተስተካከለ ቢሮክራሲ፣ የተቀናጀ መዋቅርና ዘመናዊ አሠራር ለሙስና ተጋላጭነትን ስለሚቀንሱ፣ እነዚህን ለማጥፋት ወይም ለማሰናከል ሙሰኛው ቀን ከሌት እየሠራ ነው።

ሕዝባችን በአገልግሎት አሰጣጥ፣ ከመሬት ጋር በተያያዙ አሠራሮች፣ በፋይናንስ ዘርፍ፣ በሽያጭና ግዥ ሂደቶች፣ በፍትሕ አደባባዮች፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ የሕዝብ ተቋማት ወዘተ. በሚያጋጥመው ሙስና እየተማረረ ነው። በተለያዩ ጊዜያት ከሕዝብ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ከጸጥታ ሥጋቶች እኩል ሙስና የብልጽግና ጉዟችን ዋናው ዕንቅፋት መሆኑን አንስቷል።

መንግሥት በየደረጃው የሚገኘውን መዋቅር በመፈተሽ፣ አዳዲስ አሠራሮችን በመዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎችን እያሳለጠ ሥራዎችን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ በሙስና ወንጀል የሚሳተፉ አመራሮችንና ሌሎች ተዋንያንን ለሕግ በማቅረብ፣ ሙስና ምቹ ሁኔታ እንዳይፈጠርለት ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። ነገር ግን ሀገራችን ያጋጠማትን ጦርነትና ኮሮናን የመሳሰሉ ወረርሽኞች የመንግሥትን ትኩረት ወስደዋል ብለው ያሰቡ ሙሰኞች፣ በየቦታው ተሰግስገውና ኔት ወርክ ዘርግተው፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየሠሩ መሆናቸውን በዝርዝር የቀረበው የጥናት ሪፖርት ያሳያል።

መንግሥት በጸጥታው ዘርፍ እንዳደረገው ሁሉ በሙስና ላይ ጠንካራና የማያዳግም ኦፕሬሽን ማድረግ እንዳለበት የጥናቱ ውጤትና የሕዝብ ውይይቱ ግምገማ ያመለክታል። በአንድ በኩል የመንግሥት ሕጎች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎችና አሠራሮች ለሙስና ያላቸውን ተጋላጭነት የማጥፋት ሥራ ይሠራል። በሌላ በኩል ደግሞ የሙስና ተዋንያንን የማጋለጥና በሕግ የመጠየቅ ተግባር ይከናወናል።

መንግሥት በጥናት በደረሰባቸው የመንግሥት ሹመኞች፣ የመንግሥት ተቋማት ሠራተኞች፣ አቀባባዮችና ጉቦ ሰጪዎች ላይ ምርመራ እያደረገ ይገኛል። ነገር ግን ሙስና በባሕርዩ በረቀቀ መንገድ፣ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ አንዳንድ ጊዜም በሕጋዊነት ሽፋን የሚካሄድ በመሆኑ በመንግሥት ጥናት የተደረሰባቸው አካላትን ብቻ ለሕግ በማቅረብ የሚፈታ አይደለም።

ሙስናን ከሥር ከመሠረቱ ለመንቀል እንዲቻል ከሕግና ከአሠራር ማሻሻያዎች በተጨማሪ፣ የሙስና ተዋንያን ሁሉ ሙስናን እርም እንዲሉ የሚያደርግ ርምጃ ያስፈልጋል። መንግሥት በሙስና ላይ የሚያደርገውን ዘመቻ የሚያስተባብር፣ በጥናት ተለይተው ከቀረቡት በተጨማሪ ሌሎችንም ተዋንያን የሚለይና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሟል።

ይህ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ የተሰጠውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና ትርጉም ያለው ውጤት ለማምጣት እንዲችል የኅብረተሰቡ ሙሉ ትብብር እጅግ አስፈላጊ ነው። ኅብረተሰቡ በሙስና ላይ በሚደረገው ዘመቻ ሊሳተፍ እንደሚገባ በተለያዩ መድረኮች ሲያነሣ ቆይቷል። መንግሥትም ይሄንን የሕዝብ ተሳትፎ በእጅጉ ይፈልገዋል፤ ምክንያቱም ሙስና በዋናነት የሚጠፋው ሕዝብ አምርሮ ሲታገለው ነውና።

በመሆኑም ኅብረተሰቡ የሙስና ተዋንያንን በተመለከተ ያለውን መረጃ፣ ከቂምና ከበቀል ነጻ በሆነ መንገድ፣ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት አድራሻዎች ለብሔራዊ ኮሚቴው በመላክ ሙስናን ለማጥፋት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን። የሚቀርቡ ጥቆማዎች የጠቋሚዎችን ደህንነት ለማረጋገጥ ተገቢውን ጥንቃቄ እና ሚስጥራዊነት በጠበቀ መንገድ ተይዘው ይመረመራሉ።

ብሄራዊ ኮሚቴው የሚወስዳቸው ርምጃዎች እና የእንቅስቃሴው ውጤት በየጊዜው ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ሲሉ የፀረ ሙስና ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማስታወቃቸው አይረሳም። ሀገሪቱን እየተፈታተነ ባለው ሙስና ላይ ጠንካራ ርምጃ ካልተወሰደ የሕልውና አደጋ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው ሲሉ የኢትዮ-ኢንጂነሪግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ አስጠንቅቀዋል።

አምባሳደሩ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በዚያ ሰሞን እንደገለጹት፣ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የተዘረጋው የሙስና ሰንሰለት ውስበስብ ከመሆኑም በላይ በአመለካከትም ሆነ በተግባር በትውልዱ ዘንድ በአጅጉ ሰርጿል። የቀድሞው የኢትዮጵያ ብረታብረት ኢንጂነሪግ ኮርፖሬሽን/ሜቴክ የዛሬው የኢትዮ- ኢንጂነሪግ ግሩፕ 65 ቢሊዮን ብር የት እንደ ገባ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ብሩ በግለሰቦች የተመዘበረ በመሆኑ በወቅቱ የነበሩ የተቋሙ አመራሮች ግማሾቹ ታስረዋል። ግማሾቹ ወደ ውጭ ሀገር ሸሽተዋል። ግለሰቦቹ በገንዘቡ በሀገር ውስጥ ያፈሩት ሀብት ስለሌላቸው በረቀቀ መንገድ ከሀገር እንዳሸሹ ይታመናል። ገንዘቡን ወደ መንግሥት ካዝና የመመለስ እድል እንደሌለም አምባሳደሩ መግለጻቸው ፤“ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው በህብረት እንታገል” በሚል መሪ ሃሳብ በዓለም ለ20ኛ በሀገራችን ለ19ኛ ጊዜ መከበሩ ለዛሬው መጣጥፌ መነሻ ሆኖኛል።

ሙስና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማስተጓጎል ድህነት እንዲንሰራፋ ፤ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ፤ የሕግ የበላይነት እንዳይረጋገጥ ፤ ሕዝባዊ አገልግሎት እንዲዳከም በማድረግ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል። ለዚህ ነው ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊወገድ ይገባል የሚባለው። በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የባለድርሻ አካላት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሐረጎት አብርሃ፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሙስና ደረጃ ምን እንደሚመስል ሲገልጹ ፤ ሙስና በአንድ ሀገር ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ልማት የሚያደናቅፉ ተብለው ከተፈረጁ ችግሮች ወይም ወንጀሎች አንዱ ነው።

ይህንን ወንጀልና ማነቆ ለመፍታት በመንግሥት ደረጃ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ኮሚሽኑም ከተቋቋመበት ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራል መንግሥት በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት፣ ሙስናን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲሠሩ ቆይተዋል።

በክልሎችም በተመሳሳይ መዋቅሮች ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ሲደረግ ነበር። ነገር ግን የሙስና ጉዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ችግሮች እንዳሉበት፣ መቆጣጠርና መከላከል እንዳልተቻለ የሚያሳዩ ጥናቶችም አሉ። ለምሳሌ በ2013 ዓ.ም. ያደረግነው ሀገር አቀፍ የሙስና ቅኝት ጥናት ሙስና በሦስተኛ ደረጃ ሀገራዊ ችግር መሆኑን አሳይቷል። ስለዚህ ይህ የሚያስረዳው ሙስና አሁንም ሀገራዊ ሥጋትና የመልካም አስተዳደር ጠንቅ ነው።

ማኅበራዊ እሴቶችን በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግና በሀገራችን ለሚደረጉ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንቅፋት መሆኑን በተጨባጭ መንግሥት አውቆ አቋም እየወሰደበት ነው። ኮሚሽኑም ያንን ታሳቢ በማድረግ እንቅስቃሴዎች እያደረግን ነው ያለው።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ጥናቶች የሚያሳዩትም ሙስና አሁንም በኢትዮጵያ አስጊ መሆኑን ነው። ከዚህ አንፃር መንግሥት ሙስና የሚያደርሰውን ጉዳትና የደቀነውን አደጋ ለመቅረፍ የተለያዩ አደረጃጀቶች አሉት። መንግሥት የወሰዳቸውም ዕርምጃዎች አሉ። በዚህ መሠረት ተጠያቂነትና ግልጽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ አሠራሮች፣ ሕጎችና ፖሊሲዎችን ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። የሚከናወኑ ሥራዎች ሲታዩም ጥሩ ናቸው ብሎ መውሰድ ያስችላል ይሉናል።

ሙስና ዘርፈ ብዙ ችግር አለው። ዘርፈ ብዙ ችግር አለው ስንል አንደኛ ሕዝብ የሰጠውን ኃላፊነትና እምነት ትቶ ለግል ጥቅም የሚሄድ አመራር፣ ሠራተኛ ወይም አገልጋይ ይኖራል። በዚህ መሠረት ከሕዝብ የተሰጠን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ አለመወጣትና የሕዝብ እምነት የሚሸረሽሩ አሠራሮች ሊኖሩ ይችላሉ።

ከዚህ አንፃር ማኅበረሰቡ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር እንዲከሰት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አለው። ሁለተኛው የኢኮኖሚ ጉዳት ከውጭ አሊያም ከሕዝብ የሚሰበሰበውን ውስን ሀብት ለተለያዩ ሀገራዊ ልማት መዋል የነበረበትን የሕዝብን ሀብት የሚነጥቁና እምነት የሚያጎድሉ፣ ያለውን ሀብት ለግል ጥቅም የሚያውሉ ሊኖሩ ይችላሉ።

ይህም አንድ መገለጫ ነው። ሦስተኛ የሙስና ጉዳት ከኢኮኖሚ ጉዳይ የላቀ ነው። የሙስና ውጤት ንብረትን ከመዝረፍ ጋር ብቻ አያይዘን የምናየው አይደለም። ዘርፉ ብዙ ፖለቲካዊ ቀውስ ያስከትላል። የተረጋጋ ማኅበረሰብና የፖለቲካ አስተዳደር እንዳይኖር አሉታዊ አስተዋጽኦ አለው።

ሙስናን መታገል ካልቻልን፣ በእንጭጩ የሚያስከትለውን ጉዳት ካልገታነውና ካልቀነስነው በሀገራችን ላይ የሚፈጥረው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ነው። ከዚህ አንፃር መንግሥት ባለፉት ሁለት ዓመታት በነበረው ጦርነትና ሌሎች ችግሮች ላይ ዞሮ በነበረበት ጊዜ የሙስና ድርጊቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ተበራክተዋል።

በመንግሥት አገልግሎት አሳጣጥ ላይ የተፈጠረ ተፅዕኖ አለ። ኅብረተሰቡም በዚህ ጉዳይ ላይ የሚያነሳቸው ቅሬታዎች አሉ። ይህንን ሁኔታ መንግሥት መቆጣጠር ካልቻለ ለመንግሥት ብቻ ሳይሆን ሀገር ሆኖ ለመቀጠል አደጋ አለው ሲሉ አቶ ሐረጎት አብርሃ ያሳስባሉ።

ሀገራችን በሙስና ደረጃ የትኛው ተርታ እንደምትገኝ የሚያስቀምጡ ስታንዳርዶች አሉ። እነሱን እንደ አንድ ግብዓት ብንወስድ ችግሩን ማየት እንችላለን። ነገር ግን በመሠረታዊነት እኛ ከራሳችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር በመነሳት ግልጽ የሆኑ ስታንዳርዶችን አዘጋጅተናል። ሀገር አቀፍ የፀረ ሙስና ጉዳይ በሀገር ውስጥ ከሚነሱ ብሔራዊ ችግር ውስጥ በሦስተኛ ደረጃነት ተቀምጧል።

ከኑሮ ውድነትና ከሥራ አጥነት ቀጥሎ፣ ሙስና ብሔራዊ ሥጋት እንደሆነና ሥር የሰደደ ችግር መሆኑን የሚያሳይ ነው። የችግሩ መገለጫ ግን ይህ ብቻ አይደለም። ይህንን ለመመለስም በጥናት ማስደገፍ አለብን። ከዚያ ውጪ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይኖራሉ። ከእነዚህ ችግሮች ጀርባ ደግሞ አንዱ የሙስና ችግር ሊኖር ይችላል ብለን እናስባለን።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም እዚህ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱም በተለያዩ ጥናቶች ላይ ተመሥርተው ነው። እኛም የዚህ ዕሳቤ አካል ነን ብለን እናስባለን። በኮሚሽናችን ሙስናን መከላከል ሥራችን ነው። ስለዚህ በዚህ የሚከሰቱ ችግሮች ካሉ ትኩረት ሰጥተን እንሠራበታለን። ችግሩ ሰፊ በመሆኑ በብሔራዊ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ችግሩን መቅረፍ አለብን ተብሎ የተሄደበት ዕርምጃ አለ። ይህም በጥናትም የተደገፈ ነው ብዬ አምናለሁ።

ሻሎም ! አሜን።

 በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You