ሰማዩ ለብርቱዎች ብቻ ነው – የኢትዮጵያ አየር ኃይል

ስሙ ከሀገር አልፎ በአፍሪካ የገነነ ነው። ጠጋ ብለው ሲመለከቱት ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚመጥን ትልቅ ተቋም ስለመሆኑ በተግባር ያረጋግጣሉ፡፡ ከዚህም አልፎ የሀገር ግንባታ ሂደቱ ምን ያህል የላቀ ደረጃ ላይ እንዳለ ይረዳሉ። የለውጡ መንግሥት ከልማት ሥራውም ጎን ለጎን ሀገርን ከማንኛውም ጠላት ለመከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠሩንም ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ተቋም የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አንዱ ክንፍ የሆነው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከህዳር 20 ጀምሮ 88ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በልዩ ልዩ መርሀ ግብሮች እያከበረ ይገኛል፡፡ ታህሳስ አራት፣ አምስትና ስድስት ደግሞ የበዓሉ አካል የሆኑ ልዩ ልዩ ሁነቶች ይከናወናሉ፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ ሰሞኑን ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጣን የሚዲያ ባለሙያዎች ተቋሙን ለመጎብኘት እድል አግኝተናል። እኔም በጉብኝቱ ካየኋቸው በርካታ የተቋሙ ስኬቶች ጥቂቱን ላካፍላችሁ ወደድኩ፡፡

በርግጥ ስለዚህ ተቋም በዚህ አጭር ጽሁፍ ቀርቶ መጽሀፍም ቢጻፍ በልኩ ማስረዳት ይቻላል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ የተገነባበት መንገድ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሆኖም ግን በጥቂቱ እንካችሁ፡፡

የኢትዮያ አየር ኃይል ትልቅነት የሚታየው ገና ከበሩ ሲገቡ ጀምሮ ነው፡፡ የበሩ መግቢያ ላይ አንድ ጽሁፍ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ “The sky is only for strong person” በግርድፉ ሰማዩ ለብርቱዎች ብቻ ነው፡፡ የሚል ስያሜን ሊይዝ ይችላል፡፡ ይህ ጽሁፍ ተቋሙንና የተቋሙን ሠራተኞች በትክክል የሚገልጽ መሆኑን ለመረዳት ታዲያ ወደ ውስጥ ዘልቀው ስለተቋሙ ጥቂት ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡

ከዋናው በር ወደ ውስጥ ሲዘልቁ በግራና በቀኝ የተዋበ ሥፍራ ያገኛሉ፡፡ ይህ ሥፍራ ታዲያ ዝም ብሎ ለአረንጓዴ ስፍራነት ብቻ የተቀመጠ አይደለም። ልዩ ልዩ አትክልቶች ይመረቱበታል። ከጎመን ጀምሮ ቆስጣና ሰላጣ፣ አበባዎች እና ሌሎች አትክልቶች በልዩ እንክብካቤ በአንድ በኩል ለምግብነት ሊውሉ፤ በሌላ በኩል አካባቢውን በልምላሜ ሊያደምቁ የተዘጋጁ ናቸው፡፡

አዲስ ወደዚህ ተቋም የገባ እንግዳ በዚህ ሥፍራ ጥቂት አረፍ ቢል ምኞቱ እንደሚሆን ከራሴም ፍላጎት መረዳት ችያለሁ፡፡ ይህ ግን ለጥቂት ደቂቃ ብቻ የሚቆይ ስሜት ነው፡፡ ምክንያቱም ወደውስጥ ሲዘልቁ ብዙ ለዓይንና ለውስጣዊ ስሜት ርካታን የሚያጎናጽፉ በርካታ ጉዳዮች አሉና፡፡

ትንሽ ሄድ ሲሉ አንድ በእንክብካቤ የተያዘ የእግር ኳስ ሜዳ ያገኛሉ፡፡ በርግጥ ይህ ሜዳ ከጥቂት ዓመታት በፊት ያልነበረ አዲስ የሪፎርሙ ትሩፋት ነው፡፡ ለጊቢው ግን ልዩ ውበት ከማጎናጸፉም በላይ ወታደር ለስፖርት ቅርብ መሆኑን ያሳያል፡፡ እኛም እንዲህ እንዲህ እያልን አንዱን አይተን ሳንጠግብ ሌላ ከዚያ የማይተናስ ውበት እያየን ወደ ውስጥ መዝለቃችንን ተያያዝነው፡፡

በቅድሚያም የተለያዩ የውግያና ሌሎች ወታደራዊ አውሮፕላኖች እንዲሁም ለልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ቪአይፒ አውሮፕላኖች በረራ ሲያደርጉም ተመለከትን፡፡ የሄሊኮፕተሮቹ እሽክርክሪት፤ ከሩቅ ይገፋተራል፤ የጀቶቹ ድምጽ ደግሞ የውስጥ ስሜት ያርዳል፤ በአጠቃላይ እዚያ አካባቢ ያለው ድባብ አስፈሪም፣ ግርማ ሞገስ ያለው ነው።

አውሮፕላኖቹን ከማብረር ጀምሮ ሁሉንም የግንኙነት ሥራዎችና አጠቃላይ የቁጥጥር ሥራውን ያለምንም የውጭ ዜጋ ጣልቃገብነት የሚያከናውት ኢትዮያውያን ብቻ ናቸው፡፡ ይህ ሲታይ የአየር ኃይላችን በሰው ኃይል ልማት የደረሰበትን የእድገት ደረጃ መረዳት ያስችላል፡፡

የአየር ኃይል ዋና አዛዥ የሆኑት ሌተና ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለበዓሉ መሳካት የሚያስፈልጉ ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችን እየጎበኙ መመሪያዎችን በመስጠትና በማስተካከል ተጠምደዋል፡፡ በተለይ ታህሳስ 4፣5 እና 6 የሚከበረው በዓል ስኬታማ ይሆን ዘንድ ከወዲሁ ምን ተሠራ፣ ምን ይቀራል፤ የሚለውን ጉዳይ ከመደበኛ ሥራቸው ጎን ለጎን አንድ በአንድ ይከታተላሉ፡፡

ይህን የሚያክል ትልቅ ተቋም እንኳን መምራት መጎብኘትና ማወቅም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለሚገነዘብ ሰው ሥራቸው ምን ያህል እረፍት አልባ እንደሚሆን ለመገመት አይከብደውም፡፡ ያም ሆኖ ግን ካላቸው ጥቂት ጊዜ ቀንሰው ስለበዓሉ ጥቂት ነገር ሊነግሩን ተቀላቀሉን፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ እንደሚሉት ፤የኢትዮጵያ አየር ኃይል የአንድ ትውልድ ወይም የአንድ ዘመን ሀብት አይደለም፡፡ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚገነባ ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ሀገርን የሚወክል እንዲህ አይነት ተቋም በየትኛውም ዘመን ቢሆን የራሱን ዐሻራ ትቶ ያልፋል፡፡

ታሪክ እየቆጠሩ የመከላከያን አልያም የአየር ኃይልን ታሪክ ማክበር ተገቢ እንዳልሆነ ፤ ከዚህ ቀደም አየር ኃይል በተለያዩ ወቅቶች በዓል ማክበሩን፤ አከባበሩ ግን የተቋሙን ታሪክ በሚገልጽ እና ተቋሙን በሚመጥን መልኩ አለመከበሩን፤ ችግሩን ለመፍታት የአየር ኃይል ቀን መቼ ይከበር የሚለው ውይይት እና ጥናት መጠየቁን አመላክተውናል፡፡ በዚህ መሠረት የቀደሙ የአየር ኃሃይል አባላትን ያካተተ እና በርካታ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ኮሚቴ በማዋቀር ቀኑ መቼ ይሁን የሚለው መጠናቱን ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምስረታው አካባቢ የሰማይ ባቡር በሚል ስያሜ በውጭ ሀገር ዜጎች ሲመራ እንደነበር ጠቅሰው ፤ተቋሙ አሁን የያዘውን ስያሜ የያዘውና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አዛዥ የተሾመለትን እለት ታሳቢ በማድረግ በዓሉ በየዓመቱ ህዳር 20 እንዲከበር መወሰኑን ገልጸውልናል፡፡

ተቋሙ በየዘመኑ የነበረበት ሁኔታ

ሌተና ጄኔራል ይልማ እንደገለጹት ፤ተቋሙ ቀደም ሲል ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ ሂደቶች ውስጥ ነው ያለፈው፡፡ በነዚህ ሁሉ ሂደቶች ውስጥ የየራሱ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ነበሩት፡፡ አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ሲል ቆይቶ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ግን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ እንዲያልፍ ግድ ብሎታል፡፡

ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ በነበረው ላይ ጨምሮ ተቋሙን ከማዘመን ይልቅ እያፈረሰ ከዜሮ መጀመር በመምረጡ በርካታ ተጀምረው የነበሩ መልካም ሥራዎች ወደኋላ እንደተመለሱ የአየር ሥይል የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ካፒቴን ሻለቃ ሰይድ ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ በወቅቱ ተቋሙ ከሥልጠና አንፃር ጀምሮ የነበረው ጥረት ተጠናክሮ ቢቀጥል ኖሮ ተቋሙ አሁን ከደረሰበትም ደረጃ በብዙ እጥፍ ማደግ ይችል እንደነበር በቁጭት ይናገራሉ፡፡

ሌተናል ጄኔራል ይልማ እንደሚሉት በ2010 ለውጡ ሲመጣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በስም ብቻ የቆመ ባዶ ተቋም ሆኖ ነበር፡፡ በወቅቱ አንድም የማሠልጠኛ አውሮፕላን አልነበረም። ለወታደራዊ አገልግሎት የሚውል አንድም ሂሌኮፕተር አልነበረም። በዚህ የተነሳ ተቋሙ ወረራ ቢገጥመው አንዳችም ለመከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ አልነበረም፡፡

በ2001 እንደተመረቁ የሚናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው ሻለቃ ካፒቴን ሰይድ በበኩላቸው፤ እሳቸው በሚማሩበት ወቅት ከዩኒቨርሲቲ ተመልምለው ወደበረራ ትምህርት ቤት ሲመጡ በቂ አውሮፕላን ባለመኖሩ ለብዙ ጊዜ ልምምድ ሳያደርጉ መቆየታቸውን ፤ በዚህ የተነሳ ተስፋ ቆርጠው እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱ ተመልምሎ የመጣ ተማሪ ምንም ሥልጠና ሳይወስድ ቀጣይ ዙር ሠልጣኝ ይመጣ እንደነበርም በቁጭት ተናግረዋል፡፡

ሪፎርምና አየር ኃይል

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከሪፎርም በፊት የነበረበት ቁመና ከላይ እንደተገለጸው በርካታ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች የበረራ ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ቆመዋል፡፡ የሥልጠና አውሮፕላንም ባለመኖሩ ሥልጠና ለመስጠት የሚቻልበት ቁመና ላይ አልነበረም፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ትላልቆቹ አንቶኖቭ አውሮፕላኖች እና ሚግ 23 የመሳሰሉ ተዋጊ አውሮፕላኖች ለብዙ ጊዜ በመቆማቸው ለሥራ ዝግጁ የሆነ አውሮፕላን አለ ለማለት የማይቻልበት ሁኔታ ነበር፡፡

ነገር ግን በሪፎርም የተወሰደው የመጀመርያው ርምጃ አስፈላጊ የሆኑ የመለማመጃ አውሮፕላኖችን መግዛትና ጥገና የሚስፈልጋቸው አውሮፕላኖች አንዲጠገኑ ማድረግ ነበር፡፡

በዚህ ጊዜ ታዲያ በተለይ ከጥገናው ጋር በተያያዘ ሌላ ፈተና ከፊት ተደቀነ፡፡ ይህም አብዛኞቹ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች የበረራ ሰዓታቸው በመጠናቀቁ ዳግም ወደሥራ ለማስገባት ተጭነው ወደተሠሩበት ኩባንያ መውሰድ የግድ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ በወቅቱ መንግሥት ከነበረበት የፋይናንስ ችግር አንጻር የሚታሰብ አልነበረም፡፡ እናም መላ ማፈላለግ ተጀመረ፡፡

በዚህም መሠረት አውሮፕላቹን እና ሄሊኮፕተሮቹን ከተሠሩባቸው ኩባንያዎችና መንግሥታቸው ጋር በመነጋገር ባለሙያዎች እዚህ መጥው ጥገና እንዲያደርጉ በማግባባት ብዙዎቹን አውሮፕላኖች እና ሄሊኮፕተሮች ወደሥራ ለመመለስ ተችሏል፡፡ በወቅቱ አውሮፕላኖቹንና ሄሊኮፕተሮቹን ወደሥራ ከመመለስም ባሻገር ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ የተገኘው የእውቀት ሽግግር ለተቋሙ ትልቅ እድል የሰጠ ነበር፡፡

ተቋሙ በዚህ መልኩ ራሱን በመጠኑም ቢሆን እንዲያገግም ካደረገ በኋላ በመንግስት ቁርጠኛ ድጋፍ እና በባለሙያዎችና አመራሮች የሌት ተቀን ጥረት በየጊዜው ራሱን እያሳደገና እየተሻሻለ ዛሬ ከሀገር አልፎ ለአፍሪካ ተምሳሌት መሆን የሚችል ተቋም ሊሆን በቅቷል፡፡

የተቋሙ የጥገና አቅም

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የጥገና ማዕከል እጅግ ከፍተኛ አቅም መፍጠር ችሏል። በማዕከሉ ማንኛውም አይነት እውሮፕላን ይጠገናል፤ ይህ ብቻ አይደለም፤ አውሮፕላኖች የበረራ ጊዜያቸውን ሲጨርሱ ወደውጭ ተጭነው በመሄድ ሲደረግ የነበረው ዳግም ወደሥራ የመመለስ ሥራ አሁን እዚሁ ማከናወን የሚችሉ ባለሙያዎችን መፍጠር ተችሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲል ማንዋል የነበሩ እውሮፕላኖች ዲጂታል እንዲሆኑ በማድረግ አቅማቸውን የማሳደግ ሥራም በዚሁ ማዕከል የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ በአጠቃላይ ማዕከሉ ያለምንም ችግር ማንኛውንም አውሮፕላን ከቅድመ በረራ ጀምሮ እስከ ድህረ በረራ ጥገናና ክትትል እንዲሁም ቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን በብቃት የመከወን አቅም ላይ ደርሷል፡፡

የሥልጠና አቅም

የአየር ኃይል የሥልጠና ማዕከል ቀደም ሲል በርካታ ችግሮች የነበሩበት ነው፡፡ ቴክሺያኖችም ሆኑ የበረራ ባለሙያዎች በቂ ግብዓት ባለመኖሩ ትምህርታቸውን ለመከታተል ከፍተኛ ችግር ነበረባቸው፡፡ ከወጡ በኋላም ቢሆን በየጊዜው ራሳቸውን ለማሻሻል የሚያስችል አቅም ባለመኖሩ አብራሪዎች ከሀገር የሚጠፉበት አጋጣሚዎችም የተፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የበረራ ማዕከሉ ራሱን በልዩ ልዩ ቁሳቁስ ከማደራጀቱም በላይ የካሪኩለም/የሥርዓተ ትምህርት ማሻሻያ ጭምር በማድረግ ትልቅ ተቋም መሆን ችሏል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት ከራሱ አልፎ ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሥልጠና ጥያቄዎች የሚቀርብለት ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ባለሙያዎችን ሲያሰለጥንም ነገን ታሳቢ በማድረግ ከቴክኒክ ሙያው በተጨማሪ ተጨማሪ የአመራር ትምህርት ይሰጣል። ይህም ባለሙያዎቹ ለቀጣይ መሪ መሆን የሚያስችላቸውን ክህሎት እንዲያገኙ የሚረዳ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተቋሙ ውስጥ ሠልጣኙና በመደበኛ ሥራ ላይ ያለው ባለሙያ አለባበስም ተመሳሳይ ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሠልጣኞች የራሳቸው የአለባበስ ሥርዓት እንዲኖራቸው በማድረግ ዲሲፕሊን አንዱ መርህ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

ዲሲፕሊን የአየር ኃይል አንዱ መገለጫ ነው። እያንዳንዱ ሠራተኛም ሆነ ተማሪ በጊቢው ውስጥ ሲንቀሳቀስም ሆነ ሲሠራ ወታደራዊ ዲሲፕሊንን በጠበቀ መልኩ ነው፡፡ “discipline is a Soule of a soldier ” የሚለው መርህም በጊቢው ውስጥ ጎልቶ ይስተዋላል፡፡

የሥልጠና ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በኮምፒውተር የታገዘ፣ በቂ የማስተማሪያ ግብዓት የተሟሉለት እና ምቹ የመማርያ ሥፍራ የተመቻቸለት ዘመናዊ ተቋም ሆኗል። ለምሳሌ በማዕከሉ በረራ የሚለማዱባቸው በቂ አውሮፕላኖች፣ ለበረራ ቅድመ ዝግጅት የሚረዱ “የሲሙሌተር” ምስለ በረራ ማካሄጃ መሳሪያዎች፣ ልዩ ልዩ የአውሮፕላን ክፍሎች፣ ዲጂታል መሣሪያዎች ወዘተ የተሟላ ነው፡፡

ምቹ የሥራ አካባቢን የመፍጠር ሥራ

ተቋሙ ከሪፎርሙ በኋላ በትኩረት ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ በጊቢው ውስጥ ያለው የመብራት አገልግሎት የሚቆራረጥ፣ በቂ ውሃ ያልነበረው፤ የኢንትርኔት አገልግሎቱም የማያስተማምን ነበር። በዚህ የተነሳ ተቋሙ ዓለም ከደረሰበት የዘርፉ ቴክኖሎጂ አንጻር ብዙ ክፍተቶች ነበሩበት፡፡

በዚህም የተነሳ ከሪፎር በኋላ አንዱ ተቋሙ ትኩረት ሰጥቶ ያከናወነው አስተማማኝ የመሠረተ ልማት ፍላጎት እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት በጊቢው ውስጥ ታዳሽ ኃይልን በመጠቀም አስተማማኝ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ተገንብቷል፤ የኔትወርክና የውሃ መሠረተ ልማቶችን እንደገና በመገንባት አስተማማኝ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ ደግሞ ለስራው በቀጥታ አስፈላጊ በመሆኑ ተቋሙ ለሚወስዳቸው ማናቸውም ተልዕኮዎች ምቹ ሆኔታ እንዲኖር የሚያደርጉ ናቸው።

ይህ ብቻ አይደለም፤ ተቋሙ ጊቢውን ለእይታ ማራኪ ለማድረግ የሄደበት ርቀት ተቋሙን የሚሠሩበት ብቻ ሳይሆን ዘና እያሉ የሚሠሩበት እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በጊቢው ውስጥ የተተከሉት ዛፎችና ልዩ ልዩ አትክልቶች፣ አረንጓዴ ሥፍራዎች፣ መንገዶችና መዝናኛ ሥፍራዎች ለመኖርያነት ታስበው የተገነቡ በመሆናቸው ለሠራተኛው ደስተኛ ሆኖ እንዲሠራ የሚያደርጉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ካረፈበት ሰፊ ስፍራ አንጻር፤ ለዘመናት ያለ ሥራ የቆየ መሬትን በማልማት ባለፈው ዓመት ከስምንት መቶ ኩንታል በላይ ስንዴ በማምረት ጠጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር ተችሏል።

በዓሉ ለምን ይከበራል

ሌተናል ጄኔራል ይልማ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዓሉን ሲያከበር አራት ዋና ዋና ቁልፍ ሥራዎችን ታሳቢ ያደርጋል፡፡ እነዚህም የሰው ኃይል ልማት፣ ትጥቅ፣ መሠረተ ልማት እና ኢትዮጵያን የሚመጥን አየር ኃይል የመገንባት ተልዕኮ ናቸው፡፡

የሰው ኃይል ልማት የተቋሙ የሪፎርም ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ በተለይ ብቁና ሥነምግባርን የተላበሰ ባለሙያን ማፍራት የተቋሙ ዋነኛ ተልዕኮ ነው። ከዚህ መነሻነት ተቋሙ በሥልጠና ማዕከሉ አማካኝነት ብቃት ያላቸው የበረራ ባለሙያዎችን፣ ቴክኒሺያችና ሌሎች ባለሙያዎችንም በማሠልጠን ለሥራ ዝግጁ እያደረገ ነው፡፡

ለዚህም ተቋሙ ቀደም ሲል ሲሰጥ የነበረውን ካሪኩለም/ሥርዓተ ትምህርት ጭምር በማሻሻል እና ለነገ ተቋሙን ተረክበው ሊመሩ የሚችሉ ባለሙያዎች የተሟላ እውቀትና ክህሎት የሚያገኙበት እንዲሆን እያደረገ ይገኛል፡፡

ከትጥቅ አንጻርም ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አሉ የሚባሉ የውጊያና የሥልጠና ትጥቆችን አሟልቶ የያዘ ተቋም ሆኗል፡፡ መሣሪያዎቹም ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ የተደራጁ ናቸው፡፡

ከመሠረተ ልማት አንጻር ለሥራና ለሠራተኛው ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር በተሠራው ሥራ ተቋሙ በርካታ መሠረተ ልማቶች ገንብተዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በ44 ወራት ጊዜ ውስጥ የተገነባው ስታዲየም፤ ደረጃውን የጠበቀና ለተቋሙ መኮንኖች ብቻ ሳይሆን ለከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጠው የመኮንኖች መዝናኛ ክበብ እንዲሁም የጊቢውን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ዘመናዊ ካሜራዎች ለተቋሙ እድገት የራሳቸውን አወንታዊ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡

በዚህ በዓል ከ26 የአፍሪካ ሀገራት አየር ኃይል የሚመጡ እግዶች የሚገኙ ሲሆን ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎችና መሪዎች አንዲሁም የወዳጅ ሀገራት እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የውጭ ሀገራት እንግዶች እና የሀገር ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች የሚሳተፉባቸው የፓናል ውይይቶች የሚከናወኑ ሲሆን፤ በመጨረሻም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከወዳጅ ሀገራት አየር ኃይሎች ጋር በመሆን የሚያሳዩት የአየር ላይ ትርኢት በአይነቱ ልዩ ሆኖ የሚከበር ይሆናል። በመዝጊያ ሥነሥርዓቱ ላይም ልዩ ልዩ ባለሙያዎች ይመረቃሉ፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የመጣባቸው ወጣ ገባ መንገዶች እና አሁን የደረሰበት ደረጃ ሲታይ ትልቅ ትምህርት የሚቀሰምበት ነው፡፡ በተለይ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በበዓሉ ላይ መታደማቸው ተቋሙ የደረሰበትን ደረጃ ለማሳየትና በዘርፉ ለሌሎችም ተሞክሮውን የሚያካፍልና ተያይዞ ለማደግና ከራስም አልፎ ለሌሎች መከታ ለመሆን የሚያስችለውን አቅም የገነባ ተቋም መሆኑን ለማሳየት ትልቅ እድል የሚሰጥ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ የሕዝብ ሀብት የፈሰሰበት እና ከሕዝቡ የወጡ ልጆች የሚያንቀሳቅሱት ተቋም እንደመሆኑ ስለተቋሙ አጠቃላይ ሁኔታ ለሕዝብ ማሳየት አስፈላጊ ነው፡፡ ሕዝብም ስለራሱ ተቋም የማወቅ መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ይህ በዓል ይህንን ታሳቢ በማድረግ አጠቃላይ ስለተቋሙ መረጃ ለመስጠት የተሻለ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ተቋሙ አሁን ከደረሰበት ደረጃ አንጻር ሲታይ ለነገው ትውልድ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ተቋም ነው፡፡ ስለዚህ ወጣቱ ትውልድ ይህን ተቋም ለመቀላቀል ትልቅ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህ እንዲሆን ደግሞ ስለተቋሙ ነባራዊ ሁኔታ በቂ መረጃ መስጠት አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም በዓሉ እነዚህን እና መሰል ጥያቄዎችን በመመለስ ስለተቋሙ አስፈላጊ መረጃዎችን እንድናገኝ የሚያስችል በመሆኑ የበዓሉ መከበር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የጎላ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአንድ ቀን ጉብኝት ብቻ የሚታወቅና ሊነገርለት የሚገባው ተቋም አይደለም፡፡ ስለተቋሙ እያንዳንዱን ነገር ለመጎብኘት ቀናት አልያም ሳምንታትን ሊወስድ ይችላል፡፡ ነገር ግን እኛ በአንድ ቀን ቆይታችን እጅግ በጣም ጥቂቱን ብቻ ነው ማየት የቻልነው። ወደፊት ስለተቋሙ ለማወቅ ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎችም ሆኑ ባለሙያዎች ግን ብዙ የሚነገር ታሪክ አየር ኃይል ውስጥ እንዳለ ሊገነዘቡ ይገባል እላለሁ፡፡

ቸር እንሰንብት !

ወርቁ ማሩ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You