
አዲስ አበባ፡- በበተያዘው በጀት ዓመት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ 44 ሺህ ቤቶች እንደሚገነቡ የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር መዓረግ የአማራ ክልል ከተሞች ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አህመዲን ሙሀመድ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመቅረፍ 44 ሺህ ቤቶች ይገነባሉ፡፡
እንደ አህመዲን (ዶ/ር) ገለጻ፤ ቤቶቹ በሪልስቴት፣በማህበራት በማደራጀት፣ ለግለሰቦች የቤት መስሪያ ቦታ በመስጠት እንዲሁም በመንግሥት የሚገነቡ ናቸው፡፡
ከከተሞች ማደግ ጋር ተያያዞ የሚፈጠሩ ችግሮች በአግባቡ መምራትና መግራት ካልተቻለ ብዙ ጉዳቶች አሉት፤ ከዚህም አንዱ የነዋሪዎች የቤት እጦት ችግር ዋነኛው ነው፡፡
በከተሞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦት መሰረታዊ ችግር ነው ያሉት ዶክተር አህመዲን፤ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች ያለውን የቤት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ፈጣን የሆኑ የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በአጭር ጊዜ ተገንብተው ለነዋሪዎች እንዲተላለፉ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ዶክተር አህመዲን አክለውም፤ የሚገነቡት ቤቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ለቤት መስሪያ ግብዓት ከማሟላት አንጻር ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉ ሲሆን፤ በተጨማሪም ለቤት ግብዓት የሚሆኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጎንደርና ባህርዳር ከተሞች ላይ ፈጣን የኮንክሪት ማምረቻ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ደብረብርሃን ከተማ ላይም ለቤት ግንባታ የሚውል ካናል ማምረት የሚያስችል ኢንዱስትሪ ወደ ሥራ ገብቷል ያሉት አህመዲን (ዶ/ር)፤ እነዚህን ጅምር ተግባራት ወደ ውጤት መቀየር እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ለቤት መስሪያ ብለው ወስደው ለተለያየ አገልግሎት በሚያውሉ አካላት ላይ ክትትል እንደሚደረግም ነው ዶክተር አህመዲን የገለጹት፡፡
የቤት ግንባታ ጋር ተያይዞ የራሱ የአሰራር መመሪያ ይፈልጋል፤ ይንንም በሚመለከት የአሰራር ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
እንደ አህመዲን (ዶ/ር) ገለጻ፤ በክልሉ ስምንት የ”ጂኦ ፖሉታንት” ከተሞች አሉ ያሉ ሲሆን፤ በከተሞቹ የነገውን ትውልድ ጥቅም የሚያስከብርና ለአደጋ የማያጋልጥ ስትራቴጂክ እቅድ እየተዘጋጀ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በስምንቱ ከተሞች መዋቅራዊ ፕላን ሲዘጋጅ ቴክኖሎጂ፣ ዲጂታላዜሽን እንዲሁም ስማርት ሲቲን ታሳቢ ያደረገ ሥራ እንዲሰሩ የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በከተሞቹ የነዋሪውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ የመሰረተ ልማት ስራዎች የተሟሉ እንዲሆኑ በተለይ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በተለመደው መስራት ብቻ ሳይሆን ቴክኖሎጂን ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ባህርዳር፣ ደብረብርሃን፣ ጎንደር፣ ደሴ፣ ወልዲያ፣ ደብረታቦር፣ ደብረማርቆስና ኮምቦልቻ በክልሉ ወደ “ስማርት ሲቲነት” ከሚያድጉ ከተሞች መካከል ናቸው፡፡
ልጅዓለም ፍቅሬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም