በርካቶች እንደሚስማሙበት ሴት ልጅ በአንዲት ውድ ሀገር ትመሰላለች:: ሀገር ማለት ቀለሟ ደማቅ፣ ትርጓሜዋ ብዙ ነው:: ምንጊዜም ለሁሉም መኖሪያና ምልክት ሆና ትሰየማለች :: ሁሌም የማንነት መለያ ናትና ትውልድን በዘመን ሚዛን እያሻገረች ትኖራለች::
ሴት ልጅ ማለትም እንደ ሀገር ሁሉ የትውልድ ዐሻራ ናት:: እናት፣ እህት ፣ ልጅና ሚስት ነችና ለማንነት መሠረትና መድረሻ ሆና ትዘልቃለች::
በአንድ ቃል ተወስኖ በብዙ የሚተረጎመውን ‹‹ሴት›› ይሉትን ታላቅነት አክብሮ የያዘ ቢኖር አንዳች አይከስርም :: እናቱን የሚወድ፣ ሚስቱን የሚያከብር፣ እህቱን የሚጠብቅ ፣ ልጁን የሚያሳድግ ሁሉ መቼውንም ከህልውናው እውነታ ፈቀቅ አይልምና::
ተደጋግሞ እንደሚባለው ‹‹ሴትን ልጅ ማስተማር ሀገርን እንደማስተማር ይቆጠራል›› ሴት ቁምነገረኝነቷ፣ ብልሀትና ዘዴዋ ከራሷ አልፎ ለሀገርና ወገን ካስማ ሆኖ ይቆማል :: ሴት ልጁን በወጉ ያሳደገ ፣ በትኩረት ያስተማረ ቤተሰብ ለዛሬው ድካሙ ነገን በእጥፍ ይከፈለዋል:: ከምንም በላይ ግን ሴት ልጅ ከጥቃትና በደል ስትጠበቅ ፍሬዋ ያምራል ፣ ዓላማዋ ይሳካል :: ይህ ይሆን ዘንድም የወንዶች አጋርነት በተግባር ዕውን ሊሆን ግድ ይላል::
እንደ አሮፓውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1991 በካናዳ ‹‹ሞቲሪያል ›› ከተማ የሚገኙ ሴቶች የዘመኑን ፆታዊ ጥቃትን በማውገዝ ፣ ድርጊቱን የሚቃወም እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀመሩ:: ወቅቱ የሴትን ልጅ ጥቃት ለመከላከል ይቻል ዘንድ ድምጾች ከፍ ብለው የሚሰሙበት ነበር ::
በሞንቲሪያል ከሚገኝ አንድ ኮሌጅ እንቅስቃሴውን ያካሂዱ የነበሩ በርካታ ሴቶች የብዙሃን ዓይንና ጆሮ በመሆን ትኩረትን ሳቡ:: ዓላማቸውን የተረዱ ወገኖችም ከጎናቸው ቆመው ቃላቸውን አስተጋቡ:: ‹‹የሴቶች መብት ይከበር ፣ ጥቃት ይቁም›› ይሉት ሃሳብ ያልተዋጠለት አንድ ግለሰብ ግን ውስጠቱ ከሌሎች ተለየ:: ይህን መልዕክት አምርሮ ጠላው፣ ተጠየፈው ::
የሰውየው ስሜት በጥላቻ ብቻ አልቆመም:: ያነገተውን መሣሪያ እንዳጠበቀ ወደ ኮሌጁ ቅጥር ጥሶ ገባ :: ታጣቂው ጥይቱን አቀባብሎ መተኮስ ሲጀምር አፍታ አልቆየም:: ዒላማው በሰዎች ፣ በተለይም በሴቶች ላይ ነበር::
በዕለቱ የሴቶች ጥቃትን ሲያወግዙ ከነበሩት መካከል 14 ሴቶች በታጣቂው ጥይት ሕይወታቸውን ተነጠቁ:: ይህ አሳዛኝና አስደንጋጭ ድርጊት ግን የጥቂት በጎ አሳቢ ወንዶችን ስሜት ነካ :: የጥይት ሠለባ የሆኑትን እህቶቻቸውን ዓላማ አድምቆም ከሕይወት ነጣቂው ድርጊት በተቃራኒ ለመቆም አስቻላቸው::
እነዚህ ወንዶች የሴቶቹን ድንቅ ዓላማ አልዘነጉም:: ድርጊቱን ከመቃወም ባለፈ በወንዶች የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም የሚያስችለውን የነጭ ሪቫን ዘመቻን ማካሄድ ጀመሩ :: ወንዶቹ ለሴቶች አጋርነታቸውን በገሀድ ያሳዩበት ይህ ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጣጠሉ በመላው ዓለም ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም::
እ.ኤ.አ ህዳር 16 ቀን በ1999 በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በተወሰነው መሠረት የነጭ ሪቫን ቀን በመላው ዓለም ዕውን እንዲሆን ተደረገ:: በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም ጥቃት ለመከላከል የወንዶች አጋርነት የሚታይበት ይህ ጊዜ ዛሬ ላይ አስራስድስቱን ቀናት ለፀረ- ፆታዊ ጥቃት ትኩረት በመስጠት ይንቀሳቀሳል::
ከህዳርዳር 16 እስከ ታህሳስ 1 በሚኖሩት አስራ ስድስት ቀናት ሀገራችንን ጨምሮ በመላው ዓለም የጸረ – ፆታ ጥቃት የንቅናቄ ዘመቻ ይካሄዳል:: በነዚህ ቀናት የሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ዋንኛ ትኩረት ወንዶች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን የመከላከል አጋርነታቸውን ለማሳየት ነው:: ይህ ዕውን እንዲሆንም ነጭ ሪቫን በደረታቸው ላይ በማኖር አለኝታነታቸውን ይገልጻሉ::
ዘንድሮ ይህ ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ32ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ ተከብሯል:: በሀገራችን የተከበረው ይህ የፀረ- ፆታ ጥቃት ዘመቻ
‹‹መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አልልም›› የሚል መሪ ቃልን የያዘ ነው :: የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኦሮሚያ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ ጋር በመተባበር ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ባካሄደው የጸረ ፆታ ጥቃት ቀን ለዕለቱ የተለየ ትኩረት በመስጠት በርካታ ሃሳቦች ተነስተውበታል::
በኃይሌ ሪዞርት በተዘጋጀው በዚሁ የንቅናቄ መድረክ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዝግጅቱ ለታደሙት ተሳታፊዎች ዕለቱን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል:: ፕሬዚዳንቷ እንደገለጹት አሳሳቢ ለሆነው የሴቶች ጥቃት ትኩረት በመስጠት ዘንድሮ በሀገራችን የተከበረው የንቅናቄ ዘመቻ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው::
‹‹መቼም፣ የትም፣ በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አልልም ›› በሚል መርህ መከበሩም እስከዛሬ በሴቶች ጉዳይ የነበረውን ዘመን ያስቆጠረ ዝምታ ለመስበር የሚያስችል ነው::
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉበዔ ሴቶችን አስመልክቶ በርካታ የሕግ ማዕቀፎችን አጽድቋል:: ፕሬዚዳንቷ እንደሚሉት የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ ያላለቀና ለዘመናት ይዘነው የምንጓዘው ጉዳይ ነው:: በታሰበው ልክ ችግሮች አለመፈታታቸው ግን ተገቢ ለውጦች አልመጡም:: ለዚህ እውነታ መፍትሄ ለመስጠትም ገና ብዙ መሥራት የሚያሻው ይሆናል:: ፆታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶች በሴቶች ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍ ያለ ነው::
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ለታዳሚዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት ይህን ጊዜ ስናከብር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታውቁት የአስራ ስድስት ቀናት የጸረ- ፆታ ጥቃት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገን ሌሎች ጊዜያትን በመርሳት ሊሆን አይገባም:: እያንዳንዱ ሰው ምን ላድርግ ሲል የሚከውነው ተግባር ሌሎችን ከወደቁበት የሚያነሳ ሊሆን ያስፈልጋል::
‹‹ተገቢው የሕግ ማዕቀፍን ማውጣት ብቻ ሳይሆን ተገቢው ግንዛቤን ተጨባጭ የሚባል ተግባር ሊኖር ግድ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ የሰላም ዕጦት በሚታይባቸውና በሥራ ቦታዎች ለሚስተዋለው የሴቶች ጥቃት የተለየ ትኩረት ማድረግ ግድ ይላል:: በዓይን የማይታዩና የማይዳሰሱ፣ ውስጥን የሚጎዱ ሥነልቦናዊ ጥቃቶችም በራስ መተማመነን ይነጥቃሉና ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል::
በእለቱ ሃሳባቸውን ለታዳሚዎች ያጋሩት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ጾታዊ ጥቃትና ጎጂ የሚባሉ ልማዶች በሀገራችን የሚገኙ በርካታ ሴቶች በሁሉም ዘንድ በሚካሄዱ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ በንቃት እንዳይሳተፉ በማድረግ የድርሻቸውን እንዳይወጡ እንቅፋት ይሆናል::
ሚኒስትሯ እንደገለጹት ይህ ችግር ዕንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር ሴቶች ከሚገኙ ቱርፋቶች ሁሉ ተቋዳሽ እንዳይሆኑ መሰናክል የሚሆን እኩይ ተግባር ነው::
ጾታዊ ጥቃት የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ሕጻናት የመጪውን ተስፋና ዕድላቸውን በማጨለም የልማት ቅበብሎሹ ከትወልድ ወደ ትውልድ በተሳካ ሁኔታ እንዳይሻገር የሚያደርግ በመሆኑ ሁሉም ሊያወግዘውና ሊቃወመው ይገባል::
የአስራስድስቱ ቀናት የጸረ- ጾታዊ ጥቃት እንቅስቃሴ በነጭ ሪቫን መለያ የሚታወቅ ነው:: ሚኒስትሯ እንዳሉትም በዋንኛነት ወንድ አጋሮች በእህቶችና ሕጻናት ላይ ጥቃት እንዳይደርስ ቃላቸውን የሚያድሱበት፣ ቃል የሚገቡበትና ተግባራዊ ምላሽ የሚሰጡበት የንቅናቄ ዘመቻ ይሆናል::
ፆታዊ ጥቃት በሴቶችና ሕጻናት ላይ በደረሰ ጊዜ ጉዳቱ አካላዊ ብቻ አይሆንም:: ጉዳቱ የከፋ ሥነልቦናዊ ስብራት አለው:: የጤና ችግሮችን ጨምሮም ውስብስብ ለሚባሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች አጋልጦ ይሰጣል:: ከድርጊቱ መከሰት በኋላ በአብዛኛው ማህበረሰብ ዘንድ የሚኖረው የተዛባ አመለካከት ችግሩን ለማባባስ የሚኖረውን ድርሻ ላቅ ያለ ያደርገዋል::
ሚኒስትሯ እንዳስገነዘቡትም ይህን መሰሉን የማይበጅ እሳቤ በማስወገድ ከተጎጂዎች ጎን መቆም ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚጠበቅ የሃላፊነት ድርሻ ይሆናል::
በዚህ ረገድ የኢፌዴሪ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ጾታዊ ጥቃት ከግለሰብ አንስቶ በሀገርና በማህበረሰብ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ ከግምት ውስጥ ያስገባል:: ከዚህም ተያይዞ ለሴቶችና ሕጻናት ሠብዓዊ መብት መከበር ጉልህ አስተዋጽኦ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከማጽደቅ ባሻገር ለማሠራት ዕንቅፋት የሆኑ ሕጎችን በማሻሻል አዳዲስ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጦች ላይ ትኩረት ያደርጋል::
እንደሚኒስትሯ ገለጻ የተቋማትን አቅም በማጠናከር የተቀረጹ የሕግ ማዕቀፎችን በሥራ ላይ እንዲውሉና ስኬታማ እንዲሆኑ ጠንካራ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይተዋል::
የሚኒስቴር መሥሪያቤቱ በሴቶችና ሕጻናት ላይ ዕድሜና ጾታን መሠረት አድርገው የሚፈጸሙ ጎጂ ባህላዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ግብረሃይል መቋቋሙን የገለጹት ሚኒስትሯ የአስፈጻሚ አካላትን አቅም በሥልጠና ለማጎልበትም ጥረቱ እንደሚቀጥል ተናግረዋል::
የአስራስድስቱን ቀናት የንቅናቄ ዘመቻ በማክበር እለቱን አስበውና አክበረው በጉባዔው መሀል ለተገኙ ወንዶች በሙሉ ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋናቸው አቅርበዋል:: ዕለቱን አስመልክተው የፍትህ ሚኒስቴርን በመወከል በስፍራው የተገኙት አርሚያስ የማነ ብርሃን (ዶ/ር) እንዳሉት በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመከላከል ለአስራስድስት ቀናት ብቻ ትኩረት መስጠት ተገቢ አይሆንም ::
በእሳቸው ዕምነት እንደጉዳዩ ክብደት ዓመቱን በሙሉ መንቀሳቀስና መሥራት አስፈላጊና ግዴታ ይሆናል:: የሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ ዘርፈ ብዙ እንደመሆኑ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሕግ ተቀርጾ ስትራቴጂ ተነድፎ ሊሠራበት ይገባል:: እንደ ኤርሚያስ (ዶ/ር) ገለጻ ጥቃቱን ከመከላከል ባሻገር ይህን ዓላማ ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ተነድፎ ተጠናቋል::
በብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አማካኝነት የተነደፈውና በሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ላይ የተዋቀረው ሃሳብ መብትና ግዴታዎችን አካቶ የያዘ ነው:: የጉዳቱ ሰለባዎች ከሚደርስባቸው የጤና፣ የሥነልቦናና አካላዊ ጉዳቶች አኳያ መልሶ ለማቋቋም የበርካታ ተቋማትን የሃላፊነት ድርሻ የሚጠይቅ ይሆናል::
እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ አስተባባሪ ኮሚቴ በ2001 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በውስጡም 19 ተቋማትን ያካተተና በፍትህ ሚኒስቴር አስተባባሪነት፣ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት የሚመራ ነው::
የመግባቢያ ስምምነቱ ስለመፈረሙ የገለጹት ኤርሚያስ (ዶ/ር) ሁሉንም የፍትህ ተቋማት ጨምሮ የተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በአጋርነት የሚሳተፉበት ስትራቴጂ ስለመሆኑ ተናግረዋል::
ኤርሚያስ (ዶ/ር) 19 ኙም ተቋማት በተሰጣቸው የሥራ ድርሻ መሠረት ሃፊነታቸውን በወጣት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ:: በሴቶችና ሕጻናት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመዋጋት፣ የፖሊሲ፣ የሕግ የአሠራርና ስትራቴጂ መስመሮችም ተዘርግተዋል::
አግባብነት ያላቸው ሕጎችና ፖሊሲዎች በሚመለከታቸው አካላት ተመርምረው ስለመጽደቃቸው የገለጹት ኤርሚያስ (ዶ/ር) እንዳስፈላጊነቱ የቴክኒክና የአማካሪ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውን ጭምር አስታውቀዋል:: ተግባራዊ የሚባል የአምስት ዓመት ስትራቴጂ የተነደፈለት ይህ አደረጃጀት በአሁኑ ጊዜ ዕቅዱን አስገምግሞ ለማፀደቅ ችሏል::
ከዚህ ባሻገር ዓላማቸውን በሴቶችና ሕጻናት ፍትህና እንክብካቤ ላይ ያደረጉ ማዕከላት በአዲስ አበባና በክልሎች መቋቋማቸውን የገለጹ ሲሆን ጥቃቱን ለመከላከል የሚያስችል የብሔራዊ ስትራቴጂ ዕቅድ ተነድፎ ይፋ ለማድረግ የሚያስችል ፍጻሜ ላይ መድረሱን ገልጸዋል::
ከዚሁ ጎን ለጎን ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በመለየት አፈጻጸማቸውን ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ መሆኑ ተጠቁሟል::
በመድረኩ ላይ እንደተነሳው የተነደፈውን የስትራቴጂ ዕቅድ የሚመለከታቻው አካላት ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል:: ይህ የድርጊት መርሀግብር ሴቶችና ሕጻናት ከጥቃት ስጋት ነጻ የሚሆኑበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው:: በዚህ ሂደትም ለነዚህ ወገኖች የተቀናጀ አገልግሎት ተደራሽ ሚሆንበት አሠራር ተግባራዊ ይደረጋል::
ሴቶችና ሕጻናት በሚደርሳባቸው ጾታዊ ጥቃት ለሚያጋጥማቸው አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳቶች ችግሮችን በተገቢው መንገድ መፍታት አስፈላጊና ተገቢ መሆኑን በስትራቴጂው ያረጋገጠው መርሀግብር አሠራሩን ወደ ትውልድ ላማሻገር አበክሮ ለመሥራት ተዘጋጅቷል::
ከ2016 ዓ.ም እስከ 2020 ዓ.ም ድረስ ተቀርጾ ተግባራዊ የሚደረገው ብሔራዊ ስትራቴጂ በሕግ አግባብ ጸድቆ ወደስራ ለመግባት ግዴታዎቹን ያጠናቀቀ ሲሆን ይህ ስትራቴጂም በዕለቱ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ይፋ በመሆን በሕግ አግባብ ጸድቆ ለመመረቅ ችሏል:: በዕለቱ መርሀግብር ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክብርት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ጨምሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ሀደ ስንቄዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል::
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም