የውጭ ምንዛሪን ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅምተግባር ላይ ለማዋል

 ኢኮኖሚዋ በግብርና ላይ ለተመሠረተ ሀገር የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ምን ማለት እንደሆነ ለቀባሪው ማርዳት ይሆንብኛል:: የዛሬ ዋነኛ አጀንዳዬ የውጭ ምንዛሪ አስፈላጊነትን ሳይሆን፤ የውጭ ምንዛሪ አግባብ ላለው ነገር እየዋለ ነው ወይ የሚለውን ለማንሳት ነው::

ምንም እንኳን የሀገራችን የንግድ ሁኔታ በሰበብ የተሞላ ቢሆንም የዶላሩ እጥረት እውነትነት እንዳለው አይካድም:: ዛሬ ገበያው ላይ ለትልቁም ለትንሹም ዕቃ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን እንደምክንያት ማቅረብ እየተለመደ ነው:: የዶላር ጉዳይ የቆየውን የኢትዮጵያውያንን ተከራክሮና ተደራድሮ የመገበያየት ተሞክሮንም እያስቀረ ነው::

ነጋዴዎች አስቀድመው የዶላር አቅርቦት ችግርን በማንሳት አፍ ያስይዛሉ:: አብዛኞቹ ነጋዴዎች የዶላር እጥረትን የገበያ ማሳመኛ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው:: በሀኪም የታዘዘላቸውን መድኃኒት ከብዙ ፍለጋ በኋላ ካገኙ ዋጋው የሚቀመስ አይሆንም ለዚህም ምክንያቱ ተመሳሳይ ነው።

እንደ ስኳርና ደም ብዛት ያለባቸው የማይቋረጥ መድኃኒት የሚወስዱ ህሙማን እየተቸገሩ፣ ለግብርናው የሚውል የአፈር ማዳበሪያና ተያያዥ ግብአቶች ግዥ ለመፈጸም ተግዳሮት ሆኖ ገበሬው እየተጨነቀ፣ በመለዋወጫ እቃ አቅርቦት ችግር አምራች ኢንዱስትሪዎች የሥራ ማሽኖቻቸውን መጠገን ባለመቻላቸው ሥራቸው እየተስተጓጎለ፣ አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም የሚያስችል ሥራ ለመሥራት እንደሀገር ፈተና በሆነበት በዚህ ወቅት የውጭ ምንዛሪ ለእነዚህ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ሳይሆን፤ አንገብጋቢ ላልሆኑ ነገሮች ግዥ ሲውል እንታዘባለን::

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ዜጎች በውጪ ምንዛሬ አጠቃቀም ዙሪያ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማድረግ ጀምሮ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ፣የዶላር ማእቀብ ቢጥልም፣አሁንም በተፈቀዱ የተለያዩ አማራጮች የውጪ ምንዛሪ መሰረታዊ ለሆኑ ሸቀጦች ከመዋል ይልቅ፣ለመዋቢያ (ኮስሞቲክስ) በስፋት ሲውል እየተስተዋለ ነው።

የቦንዳ ልብስ የሚባለውን ልባሽ ጨርቅ ጨምሮ፣ አርቲፊሻል ፀጉር(ሂማን ሄር) እና የውበት መጠበቂያ( ሜካፕ) በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው በስፋት ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ፣ በየመንደሩ ባሉ የውበት ማስዋቢያ እና የቦንዳ ጨርቆች መሸጫ ሱቆች ለዓይን ሞልቶ ማየት የተለመደ ነው ::

በተለይ ደግሞ አሁን ላይ በመዲናችን አዲስ አበባ የከተማ ሴቶች ያለሜካፕ እንዳትታዩ የተባሉ ይመስል ከወጣት እስከ አዋቂ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሁሉ በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ:: ቀደም ሲል ሴቶች የበለጠ አምረውና ደምቀው ለመታየት ጥረት ሲያደርጉ የሚስተዋሉት በሰርግ እና የተለየ ጥሪ ሲኖራቸው ነበር::

ለመዋቢያ የሚጠቀሙት ግብአትም እንዲህ እንዳሁኑ ከውጭ የተቀዳ ባህልን የተከተለና በውድ ዋጋም የሚገዛ አልነበረም:: አሁን ላይ ግን ለየት ብሎ የመታየቱ ሁኔታ የዘወትር እየሆነ ፤ የሚዋቡበትም ግብአት ሙሉ ለሙሉ ከውጭ በዶላር ተገዝቶ የሚመጣ ነው::

የፊት ቆዳን ለማሳመር ወይንም ሜካፕ ለመደረግ የተለያዩ ግብአቶች ያስፈልጋሉ:: የፊት ቆዳ ካማረ በኋላ የዓይን ኩል፣አርቲፊሻል ሽፋሽፍት፣የከንፈር ቀለም፣አርቲፊሻል ጥፍርና የጥፍር ቀለም ተጨማሪ መዋቢያዎች ናቸው:: መዋቢያው ደረጃ ስላለው የሚጠየቀው ክፍያም እንደደረጃው የተለያየ ነው:: ክፍያውም የሚቀመስ አይደለም::

ግብአቱ ከውጭ በዶላር ተገዝቶ እንደሚገባና በብዙ ችግር እንደሚያስገቡት አስቀድመው ስለሚነግርዎት ያለዎት አማራጭ አገልግሎት ሰጪዎቹ በሚሏችሁ ዋጋ መጠቀም ነው:: አንዳንዶቹም ግብአታቸው ጥራት እንዳለውና ከሌሎች የተሻለ እንደሆነ አግባብተው ስለሚነግሯችሁ የሚጠይቁትን ከፍ ያለ ክፍያ ለመክፈል ይገደዳሉ::

የሚገርመው ግን ተጠቃሚው እነዚህን ሁሉ አውቆ ነው እየተጠቀመ ያለው:: ፍላጎት መኖሩን የሚያሳየው ደግሞ እንደአሸን በፈላው መሸቀጫ ውስጥ እንደፈጣን ምግብ (ፋስትፉድ) ሁሉ ፈጣን የመዋቢያ አገልግሎት የሚሰጡ መኖራቸው ነው:: ወደ አንዱ መሸቀጫ ጎራ ብሎ በስሱ ቀባ ቀባ ብለው እስከ አንድሺ ብር ከፍለው ይወጣሉ:: በማሳመር(ሜካፕ) ሥራ ላይ የተሰማሩት እንደሚሉት ጥራት ላለው ሥራ ከፍ ያለ ክፍያ ይጠይቃሉ:: የሜካፕ ማሰልጠኛዎችም እንዲሁ በመዲናዋ መስፋታቸውን በሶሻል ሚዲያና በማስታወቂያዎች ከምንሰማውና ከምናየው መረዳት እንችላለን::

አንዳንድ የስልጠና ተቋማትም እራሳቸውን ዓለምአቀፍ (ኢንተርናሽናል) ብለው በመሰየማቸው ለስልጠና የሚጠይቁት ክፍያም ከፍ ያለ ነው:: ለአንድ ወር ለአንድ ሰልጣኝ እስከ 65ሺ ብር በማስከፈል ስልጠና የሚሰጡ ማሰልጠኛዎች እዚሁ መዲናችን ውስጥ ይገኛሉ:: ስልጠናው የሚውለው ግብአት በውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሀገር ነው የሚገባው::

ግብአቱ ስላላቸውና የሙያው ባለቤት ለመሆን የሚፈልጉ እንዳሉም ነው ይሄ የሚያሳየው:: ተጠቃሚዎች በመኖራቸው ነው በግዥ ከውጭ እየገባ ያለው:: ቀልድ ይሁን እውነት አንድ ወቅት ላይ ከሴቶች አናት ላይ አርቲፊሻል ፀጉር ነቅለው የሚያመልጡ መስፋፋታቸው እየተነገረ ነበር:: ይህ ሁኔታ በስፋት ሲነገር የነበረው መንግሥት አርቲፊሻል ፀጉርን ጨምሮ ቅንጦት ለሆኑ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንደማይፈቅድ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ነበር::

ምንም እንኳን እነዚህ አቅርቦቶች አያስፈልጉም የሚል ድምዳሜ ባይኖረኝም ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ብዬ አልወስደም:: ውበት ከውስጥ ነው ከሚሉ ወገኖች ነኝ:: ከላይ አምሮና ተውቦ ለመታየት የሚደረገው ጥረት ጊዜያዊ ነው:: የተሰራው ሜካፕ ሲጠፋ የሌሎችን እይታ የሚስብ ውበት አይኖረንም:: ይቀንሳል:: ሌላው በአርቲፊሻል እራስን ለማሳመር የሚደረገው ጥረት በራስ መተማመን ማሳጣቱ ነው::

በሜካፕ እራስዋን ማስዋብ የምታዘወትርና አርቲፊሻል ፀጉር የምትጠቀም ሴት የሜካፕ ጥገኛ ነው የምትሆነው:: የዚህ መዘዙ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ያለባትን ሀገር የበለጠ ችግር መፍጠር ብቻ ሳይሆን፣ ተጠቃሚውም የሚያገኘው ጥቅም ዘላቂ ባለመሆኑ ለስነልቦና ጉዳት መዳረጉ ነው::

ለመዋቢያ የሚውለው ግብአት ጥራት አስተማማኝነትም ጥያቄ ውስጥ የሚገባ በመሆኑ በቆዳ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የማይሽር ጠባሳ ሊያሳርፍ ይችላል:: ‹‹ሲያጌጡ ይመላለጡ››የሚባለው አይነት እንዳይሆን መጠንቀቁ የተሻለ እንደሆነም ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል:: ስለዚህ ከላይ ለማማር ጥረት ከማድረግ ይልቅ ለውስጥ መጨነቁ የተሻለ ነው የሚል እምነት አለኝ::

ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል ከተቻለ ውበት ይጠበቃል:: የጤና ችግር ሲያጋጥም ደግሞ ታክሞ ለበሽታው የሚሆን መድኃኒት ያስፈልጋል:: ይህን ሁሉ በማመዛዘን ቅድሚያ ሊሰጠው ለሚገባው ቅድሚያ መስጠት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባርና ኃላፊነት ነው::

ዜጎች በየትኛውም መልኩ በእጃቸው የገባውን ዶላር ሀገርና ሕዝብን በሚጠቅም ተግባር ላይ የማዋል የዜግነት ግዴታ እንዳለባቸው ይሰመኛል፣ በተለይም አሁን ላይ ሀገርና ሕዝብ በብዙ ችግሮች እየተፈተኑ ባለበት ሁኔታ ባለን አቅም ለወገኖቻችን ችግር መድረስ ይጠበቅብናል።

መንግሥትም አላስፈላጊ ለሆኑ ሸቀጦች ሊሰጥ ነበረውን የውጪ ምንዛሬ ከማቆም በተጨማሪ ፤የውጭ ምንዛሪው በየት በኩል ሾልኮ እየወጣ መሆኑን ማረጋገጥ፤ ቅድሚያ የማይሰጣቸው ሸቀጦች በየትኛውም ሁኔታ ወደ ሀገር ውስጥ በስፋት የማይገቡበትን መንገድ አግባብ ባለው መልኩ ተቆጣጥሮ ማስቆም ይጠበቅበታል::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You