አማራጭ የባሕር በር – የጋራ መልማት መሻት ነው

 ሰጥቶ ስለመቀበል እንደ መግቢያ

በበርካታ የዓለማችን ድንበር ተጋሪ ሀገራት መካከል የሚነሱ አለመግባባቶች የሀገራቱን ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚያስችል በሠጥቶ መቀበል መርህን ሊመሩ እንደሚገባ፤ ይታመናል። ለዚህም የህንድና የቻይናን ተሞክሮ ለአብነት ማየቱ በቂ ነው::

ህንድ፣ ባንግላዴሽ፣ ቻይና እና ኔፓል ድንበር ተጋርተው የሚኖሩ ሀገራት ናቸው:: ህንድ ከባንግላዴሽ በሰጥቶ መቀበል (give and take) መርህ፤ ቻይና ከኔፓል የሁለትዮሽ አሸናፊነትን መርሕ ባደረገ መንገድ (win win achieved by both sides) የሀገሮቻቸውን ጥቅም ማስከበር ችለዋል::

በሕዝብ ብዛት የዓለማችን ቁጥር አንድና ሁለት የሆኑት ቻይና እና ህንድም በተመሳሳይ መልኩ የሕዝቦቻቸውን እኩል ተጠቃሚነት ባደረገ መንገድ ችግሮቻቸውን ፈትተዋል:: በድንበሮች አካባቢ ያሉ ሕዝቦች ታሪካዊ፣ ሥነ- ልቦናዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች ሕዝቦቹን ከመለያየት ይልቅ የበለጠ ተቀራርበው እንዲኖሩ አስችለዋቸዋል።

ሮዢንግ ጉዎ ‹‹Cross-Border Resource Management›› በተሰኘው መጽሐፉ ሦስተኛ ዕትም ላይ፤ ሁለት ድንበር ተጋሪ ሀገራት በመካከላቸው በድንበር ዙሪያ የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቀድመው መሬት ላይ ያለውን እውነታ በማጤን እና የሕዝቦቻቸውን የጋራ ፍላጎት በመመልከት የሰጥቶ መቀበል መርህን ሊተገብሩ እንደሚገባ ገልጿል::

ይህ ሊሆን የሚገባው ወደፊት በሁኔታዎች ወይም በጊዜ ሂደት ሁኔታዎች መልካቸውን ቀይረው አለመግባባት ቢፈጠር እና ወደ ግጭት ቢገባ፤ ሁለቱ ድንበር ተጋሪ ሀገራት ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር መላው ሕዝቦቻቸውን ማስተባበር ስለሚኖርባቸው፤ ከወዲሁ የሕዝቦቻቸውን ይሁንታ ለማረጋገጥ የሕዝቦቻቸውን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስለሚያስፈልጋቸው ነው::

የሰጥቶ መቀበል መርህ ውጤታማ እንዲሆን ችግሮችን ከነመፍትሄዎቻቸው ሊያካትት በሚችል ፓኬጅ ሊቀረጽ ይገባል:: የሀገራቱን የሕዝቦች እና መንግሥታት ታሪካዊ ዳራ ከአሁናዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አነጻጽሮ፤ በድንበሮቹ አካባቢ የሚገኙ ሀብቶችን ያለ ምንም አድልኦ የሀገራቱን ሕዝቦች በጋራ ተጠቃሚ ማድረጉም ትኩረት ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባ ነው።

የወደብ ጉዳይ ወቅታዊነት

ኢትዮጵያ ከኤርትራ፤ ኬንያ፤ ሶማሊያ ወዘተ ጋር በንግድ ላይ በተመሠረተ የጋራ ስምምነት አማራጭ፣ የባሕር መዳረሻ በሮች የመጠየቅም ሆነ የማግኘት መብት እንዳላት ይታመናል። በተለይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ድንበርና የውሃ አካላት ከመጋራት ባለፈ የሁለቱ ሀገራት ሕዝቦች ሥነ-ልቦናዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና በሰው ልጆች መካከል ለዘመናት አብሮ በመኖር በሚገለፁ፣ በሚታዩና በማይታዩ ረቂቅ መስተጋብሮች የተቆራኙ ናቸው::

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መባቻ ጀምሮ ጣሊያን አውሮፓ ውስጥ የገጠማትን መሸነፍ ተከትሎ በሞግዚትነት ይዛ የቆየችውን ኤርትራን ለቃ መውጣቷን ተከትሎ ፤ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በሪፍረንደም እንድትዋሀድ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችንም አከናውነዋል።

ይህንን ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲናገሩ ‹‹በንጉሡ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጉዳይ በኮንፈዴሬሽን ነበር:: ያኔ የነበረው መንግሥት ‹ኮንፈዴሬሽኑ አያስፈልግም፤ እኛ እንሻላለን፤ ጠንካራ ነን› ብሎ ፌዴሬሽኑን ቀደደው:: የቀደደው መንግሥት ወድቆ የተቀደደበት ኃይል ደግሞ ‹የለም› ብሎ ታግሎ ዘመናት ከፈጀ በኋላ ኤርትራ ሀገር ሆነች:: ይህ የትናንትናው ማታወሻችን ነው›› ብለዋል::

ታሪክ ደግሞ ብዙ ያስተምረናል:: በሰጥቶ መቀበል መርህ ለጋራ ጥቅም እንጂ በማንም ላይ የተለየ ኃይል የመጠቀም ፍላጎት በኢትዮጵያ በኩል እንደሌለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው አረጋግጠዋል::

ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ የባህር መዳረሻ በር ጉዳይ ጨርሶ አለመነሳት ብቻ ሳይሆን ከሁሉም አዕምሮ እንዲጠፋ ለማድረግ ተሞክሯል:: ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት 47 ሚሊዮን ሕዝብ ይዛ አጠቃላይ ምርቷም ከ12 ቢሊዮን ዶላር ባልዘለለበት ጊዜ በቢዝነስ ሕግ ተስማምታ፣ ሁለት የወደብ አማራጮችን (አሰብንና ጅቡቲን) ትጠቀም ነበር:: በ1990 ዓ.ም በሁለት ታሪካዊ ቁርኝት ባላቸው ሀገራት መካከል ጦርነት ተቀስቅሶ ለሁለት ዓመት ሲዘልቅና በመጨረሻ ጦርነቱ በስምምነትና በእርቅ ሲቋጭ አሰብ ወደብ ቀርቶ በጅቡቲ ላይ ብቻ መንጠልጠሉ ግድ ሆነ::

አሁን ኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥሯ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ ዘልሎ ከአፍሪካ በሁለተኛነት አስቀምጧታል:: የወጪ ገቢ ንግዷም ከ20 ዓመታት ወዲህ ብቻ ከሃያ እጥፍ በላይ አድጓል:: አጠቃላይ ምርቷም ከ160 ቢሊዮን ዶላር በላይ እያደገች ያለችን ሀገር ይዞ የብዙ ሀገራት ዐይን ያረፈበትን የጅቡቲን ወደብ ብቻ እየተጠቀሙ መሰንበቱ እንዴት ያዋጣል? ጉዳዩ አጠቃላይ ለቀጣናው ሕዝቦች የጋራ ጥቅም የሚበጅና በተለይም ቀጣዩ ሀገር ተረካቢው ትውልድ ወጣቱ እፎይ የሚልበት በመሆኑ ሊተባበርና ለተግባራዊነቱ ከመንግሥት ጎን ሊቆም ይገባል::

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እያደገ በሄደ ቁጥር እና የወጣቱም ሆነ የሌላው የህብረተሰብ ክፍል ፍላጎትና የወጪ ገቢ ንግዱ የዚያኑ ያህል ስለሚጨምር ተጨማሪ አማራጭ የባሕር በር የግድ ያስፈልገናል:: የቀይ ባህርም ሆነ የሶማሌላንድ፣ የሶማሊያም ሆነ የኬንያ አማራጮችን አማትሮ ከወዲሁ በጋርዮሽ ጥቅም ላይ በመመስረት መፍትሄ ማበጀቱ ነገ ሳይሆን ዛሬ ማለቅ አለበት:: በሰጥቶ መቀበል መርህ ጎረቤት ሀገሮችም የሚጎድላቸውን እንዲሞሉ የእኛ ትብብር የሚያሻቸው ሲሆን በእኛም በኩል የሚጎድለንን እነሱ ጋር ካለው እንድናሟላ በማድረግ በጋራ መጠቃቀም የሚቻልበት ወቅት አሁን ይመስለኛል::

በየክልሎች የሚገነቡት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ባለፈ በዋናነት የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ላይ ታስቦ በመሆኑ ተጨማሪ የባሕር መዳረሻ በር የዚያኑ ያህል የሚያስፈልገን ይሆናል:: ወደሀገር ውስጥ የምናስገባቸውም ሆነ ከሀገር የምናስወጣቸው ሸቀጦች የምጣኔ ሀብት እድገታቸን በጨመረ ቁጥር እነሱም በመጨመራቸው አንድ በንግድ ሕግ ስምምነት ላይ ተመስርተን የምንጠቀመው የጅቡቲ ወደብ ብቻውን ተሸክሞ ያዛልቀናል ብሎ ማሰቡ ጨርሶ የማይሆን ነው::

የዓለማችን ያደጉ ሀገራት አንዴም ከዐይናቸው እንዲርቅ በማይፈልጉት በዚሁ የጅቡቲ ወደብ ላይ ለአካባቢው ጂኦ ፖለቲካል ጥቅም ሲባል የጦር ካምፕ መሥርተው የተቀመጡበትን ወደብ እኛ ገና በእድገት ጉዞ ላይ ያለን ሕዝቦች የሆነ ኮሽታ ቢፈጠር እንኳን ጉሮሯችን እንደታነቀ ልንቆጥር ይገባል:: ነዳጁ፣ ማዳበሪያው፣ መድኃኒቱ፣ መለዋወጫ እቃው … በየት አልፎ ይግባ? የእኛስ ቡናው፣ ቆዳው፣ ቅመማ ቅመሙ፣ የግብርና ውጤቱ፣ … በየት በኩል ይውጣ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ‹‹እኛን የሚያስደነግጠን ምንድነው? አንድ ወደብ ነው ያለን:: የጅቡቲ ሕዝብና መንግሥት ወንድማችን ነው:: ግን ትላልቆቹ ቢጣሉ ጅቡቲ ላይ ካምፕ ስላላቸው ድንገት ቢታኮሱ የኛ ቦቴዎች ነዳጅ ሊያስገቡ አይችሉም:: የጅቡቲ መንግሥት እየፈቀደ እኛም ፍላጎት እያለን በሌሎች ግጭት ምክንያት ለአንድ ሳምንት ነዳጅ ባይኖር አስቡት? ማዳበሪያ ካልገባ አስቡት? …›› ብለዋል::

ጉዳዩን ማሰብ ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ ማናችንንም ሳይመርጥና ሳይለይ የእያንዳዳችንን ቤት በማንኳኳት መላ ሕይወታችንን በማመሰቃቀል የሳምንታት እድሜ እንኳን እንዳይኖረን ከማድረግም አልፎ ወደ ሌላም ሊያመራ ስለሚችል ጉዳዩ የሁላችንንም ትብብር እና ድጋፍ የሚጠይቅ፤ በጋራ እና በአንድነት መቆምን የሚሻ የህልውና እና የሰላም ጉዳይ ነው::

አማራጭ የባሕር በር ባናገኝ ምን ሊፈጠር ይችላል?

የኛ ሕዝብ ቁጥርና የኢኮኖሚ እድገታችን ከገቢ ወጪ ንግዳችን ጋር ተያይዞ ወጥቶ የትየለሌ በሆነበት በዚህ ጊዜ በአንድ መተንፈሻ ብቻ የ120 ሚሊዮንን ሕዝብ ጉሮሮ ሞልቶ ማሳደሩ የመክበዱን ያህል የ 160 ቢሊዮን ዶላር የምጣኔ ግስጋሴንም እንዳለ ማስቀጠሉ እየከበደ ይሄዳል:: ይህ ራሱን ለዘመናት እየኖረ ካለበት ድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ከህልም ባለፈ ሌት ከቀን እየተጋ ለሚገኝ ሕዝብ ምን ማለት ሊሆን ይችላል?

እንደ መውጫ

የሀገራችን የአማራጭ የወደብ ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት ካለው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አንጻር በአግባቡ ሊጤን የሚገባ ጉዳይ ነው። ሰጥቶ በመቀበል የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ተግባራዊ መሆን ከቻለ ለአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት አንድ ትልቅ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

ግዛቸው ገ/ማሪያም

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You