የስብሰባችን ውሎ ኢንቬንቶሪ

ውሎ ሲያድር ባህል ሆኖብን ይሆን?

ይህ ጸሐፊ ከ2000 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ ለአሥር ዓመታት ያህል የተካፈላቸውን ስብሰባዎችና ሴሚናሮች፣ ምክክሮችና አውደ ጥናቶች በአጭር በአጭሩ በዐውደ ዕለቱ መመዝገቢያ ማስታወሻው ላይ የዜና መዋዕሉን ማስፈርን “ልማዱ” ለማድረግ ሞክሮ ነበር፡፡ ከዚሁ ልማዱ ጎን ለጎንም በተካፈላቸው “መድረኮች” ላይ የተሰጡትን የማንነት መገለጫ የስም ባጆች ከነማንጠልጠያቸው፣ እኛ ተሰብሳቢዎች የተንቆጠቆጥንባቸውን የአንገት ልብሶችንና (ስካርፎች) ባህላዊ አልባሳትን በሙሉ በግሉ “አርካይቭ” በአግባቡ ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡

ከሚሊኒየም ክብረ በዓላት፣ እስከ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር፣ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ እስከ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተሳትፎው፣ ከደራሲያን ማኅበር ዝግጅቶች እስከ መንግሥታዊ ጥሪዎች፣ ከብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓላት እስከ የማኅበራት የይገኙልን ጥሪ፣ ከፖለቲከኞች ሸንጎ ተጋባዥነት እስከ የቲንክ ታንክ ቡድኖች አስተባባሪነትና ተሳታፊነት፣ ከመጻሕፍት ምረቃ ሥነ ሥርዓቶች እስከ ደረጃቸው “ከፍ ያሉ ስም አይጠሬ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ” ጉባዔዎች ወዘተ. ለመገኘት ዕድል አጋጥሞታል፡፡ የስብሰባውና የጥሪው ዓይነት ተዘርዝሮም ይሁን ተቆጥሮ በቀላሉ የሚዘለቅ ስላይደለ እዚሁ ላይ መግታቱ ይበጃል፡፡

ከዝርዝሮቹ በማስከተል ለሙግት መቅረብ ያለበት መሠረታዊ ጥያቄ የተጠቃቀሱት ስብሰባዎችም ሆኑ ዐውደ ጥናቶች፣ ምክክሮችም ሆኑ ግብዣዎች ለአዘጋጆቹ ተቋማት፣ ለተጋባዦቹና ለታዳሚዎቹ ከፍ ስናደርገውም ለሀገር ለውጥና መሻሻል ያስገኙት ትሩፋትና ጠቀሜታ ምን ነበር?” የሚል ሊሆን ይገባል፡፡ እርግጥ ነው ያኛውና ይሄኛው ብለን ባንዘረዝርም የተወሰኑት መርሃ ግብሮች በዛሬ ዐይን ሲፈተሹ ጥቂቶቹ ፍሬያቸው በግልጽ የሚታይ፣ ውጤታቸውም ጎምርቶ እንዳማረበት መመስከሩ አግባብ ነው ማለት ብቻ ሳይሆን እውነቱን ባንመሰክር “ኅሊና ራሱ” በትዝብት ልምጭ ይቀጣን ይመስለናል።

ችግሩ ልክ እንደ ቅዱስ መጽሐፉ ታሪክ ሆኖ ከሆነ ነው፡፡ ምሳሌውን እናስታውስ “እነሆ አንድ ገበሬ ዘር ሊዘራ ወጣ፡፡ እርሱም ሲዘራ አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀ፤ ወፎችም መጥተው ለቅመው በሉት። አንዳንዱም ዘር አፈሩ ስስ በሆነ ድንጋያማ መሬት ላይ ወደቀ፤ የዳበረ አፈር ስላልነበርም ወዲያው በቀለ፤ ፀሐይ በወጣ ጊዜ ጠወለገ፤ ሥርም ስላልነበረው ደረቀ። አንዳንዱም ዘር በእሾህ መካከል ወደቀ፤ እሾሁም ቡቃያውን አንቆ አደረቀው፡፡ ሌላው ዘር በመልካምና ታርሶ በለሰለሰ መሬት ላይ ወደቀ፤ ፍሬም አፈራ፤ አንዱ መቶ፣ አንዱ ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ፣ ፍሬ አፈራ፡፡ የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” (ማቴ. 13፡3 -9)፡፡

በመላው የሀገሪቱ ግዛት በቀበሌም ይሁን በወረዳ፣ በዞንም ይሁን በክልል፣ በድንኳን ውስጥም ይሁን በዳስ ውስጥ፣ በዛፍ ጥላ ሥርም ይሁን በመስክ፣ ደረጃቸውን በጠበቁ አዳራሽ ውስጥም ይሁን በተንደላቀቁና በከዋክብት ብዛት በተሰየሙ ሆቴሎች ውስጥ፣ በዘብ በሚጠበቁ የጉባዔ መሰብሰቢያዎች ውስጥም ይሆን በተመረጡ ቦታዎች እስከ ዛሬ የተሰየሙትና ምክክር ወይንም ትምህርት፣ ሪፖርት ወይንም መመሪያ የተላለፈባቸው ስብሰባዎች ያስገኙት ሀገራዊ ውጤት ምን ነበር? ደፍረን ልንጠያየቅ፣ ጨክነን ልንተራረም ጊዜውም ወቅቱም ግድ የሚል ይመስለናል፡፡

ስለ ሰላም የተሰበኩትና የተዘመሩት የጉባዔ ድምጾቻችን ምን ውጤት አስገኙልን? ስለ አብሮነት የተመካከርንባቸውና ቃል የገባንባቸው የአቋም መግለጫዎችስ የት ደረሱ? ለኢትዮጵያ ሁለተንተናዊ እድገትና ልማት ተስፋ ይሆናሉ ያልናቸውና በኪዳን ጭምር የተማማልንባቸው ተስፋዎች ፍሬያቸው ስለምን ደምቆ ሊወጣ አልቻለም? የስብሰባዎቻችንንና የዐውደ ጥናቶቻችንን ኢንቬንቶሪ እንደ ሀገር ወደ ኋላ መለስ ብለን መገምገሙና መፈተሹ ብልህነት ብቻ ሳይሆን ወደ ብሔራዊ ችግሮቻችን መፍትሔም ሊያቀርበን የሚችል ይመስለናል፡፡

“ይህን ያህል ይሆናል” የሚል ቁጥር ለመጥቀስ ለምንቸገርባቸውና ለልኬትም ከሚያዳግቱ ስብሰባዎች፣ ሴሚናሮች፣ ዐውደ ጥናቶች፣ ምክክሮችና ውሎዎች የተገኙት ሀገራዊ ትሩፋቶችና ፍሬዎች በርግጡ ለየትኞቹ ችግሮቻችን መፍትሔ ሆነው ታደጉን?” ከሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ጎን ለጎን እና ዛሬም ተጋግለውና ተነባብረው መሰብሰቢያ አዳራሽ እስኪጠፋ ድረስ በገፍ እየተተገበሩ ላሉት ሀገራዊ ስብሰባዎችና ጉባዔዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደ ጅረት ፈስሶ ነበር? ወይንም እየፈሰሰ ነው? ያ ለስብሰባ ይወጣ የነበረው ረብጣ ሀብት ለሌላ ልማት ቢውል ምን ያህል ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና የግብርና ትራክተሮች ይገዛ ነበር? በጉባዔ ማጠቃለያዎቹ ልዩ መርሃ ግብሮች ላይ በልዩ ሁኔታ ለሚደገሰው የ“ዋንጫ ኖር!” ፌሽታ (toast ‹raising glass› when drink­ing እንዲሉ ባህር ማዶኞች)፤ ምን ያህል ነዋይ እንደ ምግብ መጠጡ በገፍ ፈሰሰ? ለትልቁም ለትንሹም የስብሰባና የጉባዔ ማድመቂያ እየተባሉ ታዳሚዎች አንገት ላይ የሚሸመለሉት የአንገት ልብሶች፣ የባህል አልባሳት፣ ኮፍያዎች፣ ቦርሳዎች፣ የማስታወሻ ደብተሮችና የጽሕፈት መሣሪያዎች ዋጋቸው ቢተመን በስንት ሚሊዮን ብር ሊገመት ይችል ይሆን? በሆድ ይፈጀው! ቁጭት ብናልፈው ይበጃል፡፡

ሥልጡን ሀገራትና ተቋማት የስብሰባቸውን የፍሬያማነት ውሎ (Meeting Effectiveness Inventory – MEI) የሚገመግሙበት የራሳቸው ስልትና አተገባበር አላቸው፡፡ አጫጭር መርሃ ግብሮች እንደተጠናቀቁ ወዲያው “እጅ በእጅ” ግምገማ ለማድረግ ብቻም ሳይሆን በቀዳሚ ጊዜያት የተከናወኑ ስብሰባዎችና ዐውደ ጥናቶች ወይንም የምምክር ጉባዔዎችም የሚፈተሹት ታስቦባቸውና ምን ትርፍ፣ ምን ኪሳራ እንዳስከተሉ በተገቢ የጥናት ወንጠፍት እየተበጠሩና እየተጠኑ ነው፡፡ ያለበለዚያ ያለፈው ሳይፈተሽ ሌላ ጉባዔ ላይካሄድም ይችላል፡፡

ገንዘብ ጊዜ እውቀት የሚፈስባቸው የሀገራችን ዘርፈ ብዙ ስብሰባዎችና ጉባዔዎችስ በአግባቡ ይገመገሙ ይሆን? ለስብሰባዎችና ለውሎ አበል የሚከፈሉ ወጭዎችሽ በህሊና ዳኝነትና በተዘረጋው የየተቋማቱ የፋይናንስ ማጣሪያ ውስጥ በአግባቡ እየተጣሩ ያልፉ ይሆን? “ተው ቻለው ሆዴ!” አለ የሀገሬ አንጎራጓሪ!

“የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ” በሚል “የአጋኖ ድምጸት” ተደምድሞ ወደ ተጠቀሰው የላይኛው የቅዱስ መጽሐፍ ምሳሌ ዳግም መለስ ብለን ጥቂት ማነጻጸሪያ እናክልበት፡፡ በዚህ ጸሐፊ እምነት የአብዛኞቹ የሀገራችን ስብሰባዎችና ጉባዔዎች ተገቢውን ፍሬ ሊያፈራ ያልቻሉበት ምክንያቱ አንድም፡- “በጭንጫ ድንጋይ ላይ ተዘርተው እንደሆንስ?”፣ “አንድም ለም ባልሆነ መሬት ላይ ተዘርተውስ ከሆነ?”፣ “አንድም በመንገድ ላይ ተዘርተው ወፎች ለቅመዋቸው ቢሆንስ?”፣ “አንድም በሾህ ታንቀው እንደሆንስ?” አንድምታችንን ከዚህ በላይ ዘርዘር አድርጎ ማስፋቱ ተገቢነት አይኖረውም፡፡ “ስለምን?” ተብሎ ቢጠየቅ ምሳሌው የተደመደመው “ጆሮ ያለው ይስማ!” በሚል አማራጭ ስለሆነ መቀበል ያለመቀበል የአንባቢውና የሰሚው ድርሻ ነው፡፡

የብዙ ሀገራት ድርጅቶችና መንግሥታዊ ተቋማት “መደበኛ” የሚሰኙ የስብሰባ ባህሎቻቸውን ቴክኖሎጂው አግዟቸው ወደ ዘመናዊነት ካሸጋገሩ ሰንበት ብሏል፡፡ ይሄው የቴክኖሎጂ አተገባበር የሚገለጸው እንደሚከተለው ነው፡፡ “A virtual meeting is a form of communication that enables people in different physical locations to use their mobile or internet connected de­vices to meet in the same virtual room.”

ከላይ በተጠቀሰው ዘመን ወለድ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ስብሰባዎችም ሆኑ ጉባዔዎች የሚካሄዱት የቦታ ርቀትና ቅርበት ሳይገድባቸው እያንዳንዱ ታዳሚ በዚያው ባለበት ሆኖ ስለሚወያይ የጋራ መሰብሰቢያ አዳራሽና መድረክ የማያስፈልግበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ይገኛል፡፡

ይህ ማለት ግን ስብሰባዎች በሙሉ መካሄድ ያለባቸው በዚህ ቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ቢባልስ ማን ሊቀበለን!? እንዳስፈላጊነቱ በአካል እየተገናኙ መሰብሰብ ጭራሹኑ አስፈላጊ አይደለም ተብሎ “ውጉዝ ከመ አርዮስ” የሚል አንድምታም ሊሰጠው እንደማይገባም አበክረን እናሳስባለን፡፡

ከላይ ስለ ተጠቀሰው የቴክኖሎጂ ጥበብ ብዕረ መንገዳችንን አንዳንድ ጉዳዮችን ጠቅሰን ብናልፍ ይጠቅም ይመስለናል፡፡ ቨርችዋሉ የርቀት መገናኛ ዘዴ የሚያገልግለው ለበርካታ ማሕበራዊ ጉዳዮች ጭምር ነው፡፡ እንደ ቀደምት ዘመናቱ ልምምድ አንድ የተመሰገነ የዩኒቨርሲቲና የአንድ ሀገር ታዋቂ የኮሌጅ ፕሮፌሰር በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ ተማሪዎች ትምህርታዊ ገለጻ ለመስጠት የግድ የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጦ ወይንም ረዥም ርቀት ነድቶም ሆነ ተጓጉዞ ተማሪዎቹ ባሉበት ኮሌጅ ውስጥ እንዲገኝ ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ እዚያው ባለበት ሀገርና ቦታ ሆኖ በቴሌ ኮንፍረንስ ትምህርታዊ ገለጻውን ለተማሪዎቹ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ማስተማር ብቻ ሳይሆን ተማሪዎቹ ትምህርቱ ገብቷቸው እንደሆንም ይጠይቃል፣ እርሱም በተማሪዎቹ ጥያቄ ይቀርቡለታል፤ ፈተናም ይፈትናቸዋል፡፡

በርቀት ያሉ ሕሙማንና ለመጓጓዝ አቅም የሌላቸው ታካሚዎችም በተለያዩ ሀገራት በሚገኙ ዶክተሮች አማካይነት በዚሁ ዘመናዊ የቪዲዮ ኮንፍራንስ ሕክምና ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ ታላላቅ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችም እንዲሁ በቨርቹዋል ዘዴ ሲካሄዱ እየተመለከትን ነው፡፡

“ልማድ ውሎ ሲያድር ባህል ይሆናል” ሆኖብን እኛ ግን ዛሬም ድረስ እንደ ሀገር “ከአፍቅሮተ ስብሰባ” ሱሳችን ነፃ መሆን ተስኖናል፡፡ ስብሰባ ከሌለ ብርድ ብርድ እያለ የሚያንዘረዝረው፣ “ለምን ስብሰባ አይጠራም?” እያለ የሚያቁነጠንጠው የሀገሬ “የስብሰባ ቁራኛና” ልክፍተኛ ብዛቱና አበዛዙ ይህ ልኩ የሚባል ዓይነት እንዳይደለ ለመመስከር አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙትን መንግሥታዊ ተቋማት ብቻ መፈተሹ በቂና ከበቂ በላይ የሆነ ማስረጃ ይሆነናል፡፡

ጎበዝ! እንዴት ነው መላው? ይህ እንደ ዘጠና ደቂቃ የእግር ኳስ ጨዋታ የባከነ ጊዜ ሊሰጠው የማይችለው ሕይወታችን እንኳንስ “በስብሰባ ታጅሎ” ይቅርና ያቺው መደበኛ የሥራ ጊዜ እንኳን ምርታማና ትርፋማ እንዳትሆን መጨቆን ምን ይሉት አባዜ ነው፡፡ “እንኳንስ ዘንቦብሽ…” እንዲል ሀገራዊ ብሂል፤ የስብሰባ ሱሳችን ገና ሳይሰክን “በቡሃ ላይ ቆረቆር” እንዲሉ አብዛኛው ሠራተኛ “በሶሻል ሚዲያ” ላይ ተጠምዶ ሥራውን ቸል ባለበት ዘመን ሀገር እንዴት “ሀገር” ሆና ልትቀትል ትችላለች?

በሥልጡን ሀገራት ባህል እንደሆነው ሁሉ በእኛ ሀገርም የሥራ ጠባያቸው ከእጃቸው ላይ ስልክ እንዳይለይ ከሚፈቅዳላቸው የሥራ መሪዎች በስተቀር ለምን እያንዳንዱ ሠራተኛ የእጅ ስልኩን አስቀምጦ ወደ ሥራው እንዲሠማራ አይደረግም? በሥራ ሰዓት ተገልጋዮችን እያስለቀሱ በእጅ ስልካቸው ላይ ቲክ ቶክ፣ ዩ ቲዩብና ፌስ ቡክን የሙጥኝ በማለት በእንጀራቸውና በመብታችን ላይ በሚሳለቁት ላይስ ስለ ምን ርምጃ አይወሰድም? ርምጃ መውሰድ ሲገባቸው ርምጃ በማይወስዱትስ ላይ ርምጃ የሚወሰደው መቼ ይሆን?

ሀገሬን የውጥር እንደ ያዟት ፈተናዎች አባዛዝ ቢሆን ዛሬ ዛሬ ብዙው የህልውናችን ምሶሶ ተናግቶ “በነበር” በተዘከርን ነበር፡፡ መቼም ድህነቱና መከራው የሕይወታችን አንዱ ክፍል እንዲሆን የፈቀድንለት የስብሰባችን ባህል በቀዳሚነት ይጠቀስ እንጂ እጅግ በርካታ ከሆኑ ትብታቦች ገና ነፃ ለመውጣት ብርታት አላገኘንም፡፡

“ሰው መናገር ከሚችለው በላይ ነገሮች ሁሉ አድካሚ ናቸው፡፡…የነበረው ነገር እንደ ገና ይሆናል፣ የተደረገውም ተመልሶ ይደረጋል” (መክብብ 1፡8 – 11) እንዳለው ጠቢብ፤ ብዙው የእኛ ነገር “ውሃ ቅዳ፤ ውሃ መልስ” ብጤ ሆኖብን እነሆ ግራ ቀኝ እንደተላጋን ከሌት እስከ ንጋት፣ ከእሁድ እስከ ሰኞ፣ ከመስከረም እስከ ጳጉሜ፣ እንዲሁ ብቻ በከንቱ እየተብከነከንን “በቆይ ብቻ ፉከራ” እህህታችንን ቀለብ አድርገን መኖርን ተለማምደናል፡፡ “እህህ እስከ መቼ!?” አለች ድምጻዊቷ ዜመኛ፡፡ ሰላም ለሕዝባችን ለዜጎችም በጎ ፈቃድ፡፡

ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኀሣሥ 1 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You